Sunday, October 8, 2017

✍✝ “ተዝካር ምዋርት ነው!”-------ብጹእነታቸው✝✍




፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ላይክ ላይክ ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
  facebook.com/melkamubeyeneB  
ላይክ ላይክ ላይክ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
===================================================
ቤተክርስቲያናችን ለታመሙት ምሥጢረ ቀንዲልን እንደ አንድ ምሥጢር ይዛ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድ ብላ ትጠቀምበታለች ትጠቀምበታለችም፡፡ ሆኖም ግን ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከሞት እንዲሉ ሞተ ሥጋ ለሁሉም ፍጥረታት እኩል የተሰጠ ነውና ሰው ይሞታል፡፡ አፈር ነህና ወደ አፈርነት ትመለሳለህ እንዲል መጽሐፉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሞተ ሰው ጸሎተ ፍትሐት ታደርሳለች በክብርም የእረፍት ቦታ በቅጽሯ ትሰጣለች፡፡ ከዚህ የሥጋ ከነፍስ መለየት ቀን ጀምሮ በሚቆጠሩ ቀናት ወራት እና ዓመታት መታሰቢያ ታደርጋለች፡፡ መታሰቢያው የሚከናወነው ለጦም አዳሪዎች ምግብ በመመገብ ምጽዋት በመስጠት ነው፡፡ ይህ መታሰቢያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት ተገቢ ነው፡፡


ተዝካር ወይም መታሰቢያ በሦስት ቀን በሰባት፣ በዐሥራ ሁለት፣ በሠላሳ፣ በዐርባ፣ በመንፈቅ፣ በዓመት እየተባለ ይዘከራል፡፡ በዚህ ሁሉ በቅዳሴው የሞቱትን ነፍሳት ስማቸው ይጠራል፡፡ ከቅዳሴው ውጭም ዳዊት ይደገምላቸዋል ጸሎት ይደረስላቸዋል፡፡ ስለ ተዝካር አስፈላጊነት እና መጽሐፍ ቅዱሳዊነት በያላችሁበት ሊቃውንቱን እንድትጠይቁ መጻሕፍትንም እንድታነብቡ እያሳሰብሁ የአባታችንን ተዝካር ላይ ያላቸውን አመለካከት ግን ከዚህ ቪዲዮ ተመልከቱት፡፡

ተዝካር ምዋርት የሚሆንበት መቼ ነው እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ አባታችን ቢመልሱልን መልካም ነበር፡፡ ተዝካር ስታደርጉ አላስፈላጊ ወጭ አታውጡ በሌላችሁ ነገር ላይ እየተጨናነቃችሁ እንዲህ አታድርጉ፡፡ በሬ ካላረድን ጠጅ ካልጣልን እያላችሁ አትጨነቁ ቀለል አድርጋችሁ ፈጽሙ ብሎ ማስተማር ተገቢ ነው ልክም ነው፡፡ ተዝካር ለሞቱት መታሰቢያ ማድረጊያ እንጅ አለልክ አብልተን እና አጠጥተን የምናሰክርበት እና ሰውን ከሰው ጋር የምናጋጭበት መሆን የለበትም የሚለው ያስማማኛል፡፡ ግን የእኛ አባቶችስ ያል እህል ውኃ ዳዊት ይደግማሉ ወይ ብለን ስንጠይቅ ብዙ ነገር አለው ወደዚያ መግባት አልፈልግም፡፡ አባታችን ግን “በቁሙ ሰው ያልሆነ ሰው ከሞተ በኋላ ተዝካር ስላደረግነት ሰው ይሆናል ወይ ይህ እኮ ምዋርት ነው” ሲሉ አንደኛ ተዝካርን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም እያሉን ነው፡፡ ሁለተኛም ተዝካር ቢደረግም ፍትሐት ቢደረግም ሰው ከሞተ በኋላ ምንም ለውጥ አያመጣም የሚል መልእክት ነው፡፡

እውነቱ ሲገለጥ አባታችን ይህንን ያሉት በሬ ከምትገዙ ጠጅ ከምትጥሉ እህል ውኃ እያላችሁ ደካሞችን ከምታበሉ ይልቅ የዚያን ማዘጋጃ በጥሬ ገንዘብ ገቢ አድርጉ ለማለት ፈልገው ነው፡፡ ይህንንም በስብሰባ ጊዜ ደጀን ከተማ ተናግረውታል፡፡ የሚገርመው ነገር ደጀን ከተማ ላይ አንድ መምህሬ አሉ ዓይነሥውር ናቸው፡፡ እርሳቸውን ተዝካር በእህል ውኃ መሆኑ ይቅርና በጥሬ ገንዘብ ገቢ ይደረግ ብላችሁ ፈርሙ እንደተባሉ አጫውተውኛ፡፡ ጥሬ ብሩ የት እና እንዴት ለማን ገቢ ይደረጋል ሲባል ያው ዘረፋው ነው ሌላ ምን አለው፡፡ ቤተክርስቲያን እኮ የራሷ ሥርዓት አላት፡፡ አፍኒን እና ፊንሐስ ምን ነበር ያደረጉ ታስታውሳላች፡፡ እነዚህ የዔሊ ልጆች ግን ሦስት ዐበይት ኃጣውእ ሠሩ፡፡
፩ኛ. ሙሴና አሮን በሠሩት ሥርዓት መሠረት በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርቶ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት ይጠፋ የነበረውን ፋና ከባዶ ቤት ሲበራ ቢያድር ምን ይጠቅማል? ብለው አስቀሩ፣
፪ኛ. እስራኤላውያን መሥዋዕት በሚሠዉ ጊዜ ገና ስቡ ሳይጤስ የወደዱትን ሥጋ እየነጠቁ ይበሉ ነበር፣
፫ኛ. ሴቶችን በቤተመቅደስ ውስጥ ያስነውሩ ነበር፡፡ ሙሴና አሮን በሠሩት ሥርዓት መሠረት

የመጀመሪያውን ኃጢአታቸውን ልብ በሉ በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርቶ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት ይጠፋ የነበረውን ፋና ከባዶ ቤት ሲበራ ቢያድር ምን ይጠቅማል? ብለው አስቀሩ የሚለው ለቤተ መቅደሱ አስበው ነውን አይደለም ለራሳቸው ነው፡፡ ይሁዳስ ማርያም ባለሽቷዋ የጌታን እግር በእንባዋ እያራሰች ሽቱ እያርከፈከፈች ይቅር በለኝ ስትለው ምን ነበር ያለው፡፡ ይህ ሽቱ እንዲህ ከሚደፋ ተሸጦ ለድሆች ቢሰጥ አይሻልም ነበርን አለ እርሱ ግን ለድሆች አስቦ አልነበረም ለራሱ  ስለቀረበት እንጅ፡፡ የብጹእ አባታችን የአቡነ ማርቆስም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው፡፡ ተዝካር ምዋርት ነው አይባልም አወ አይባልም ክህደት ነውና!!!

ቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ እነኝህን አባት ነው እንግዲህ እንድንቀበል ሊያግባቡን የሚሹት!
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝
© መልካሙ በየነ
መስከረም ፳፰ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት
#comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝

No comments:

Post a Comment