፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
የዘንድሮው ቅዱስ ሲኖዶስ እንደ መጀመሪያው የመክፈቻው ቀን ቢሆን ኖሮ ቤተክርስቲያንን በታሪክ የሚያስወቅሳት
ጉዳይ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን የሐዋርያት
ጉባዔ በተከፋፈለ ሃሳብ ሲሰነጣጥቁት እና አንድ ልብ አንድ ሃሳብ መሆን ሲሳናቸው ሁላችንም አዝነን ነበር፡፡
ሆኖም ግን ከሁለተኛው
ቀን ጀምሮ የተከፋፈለው ሃሳብ ሁሉ ተዘጋ እና አንድ ሃሳብ ላይ መድረስ ተቻለ፡፡ በዚህም መሠረት ምንም እንኳ ብዙ የምንጠብቀው
ነገር ቢኖርም የተወሰኑ ውሳኔዎች ግን በጣም ጥሩዎች እንደነበሩ አልዘነጋነውም፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን ሥርጭት ያለእኛ ፈቃድ
በፓትርያርኩ ተጽእኖ ብቻ አይዘጋም ተብሎ ተወስኗል፡፡ የበጋሻው ደሳለኝ መወገዝ የአባ መዓዛ ስልጣነ ክህነት መያዝ የዘማሪት ምርትነሽ
በይቅርታ መመለስ የቅባት ኑፋቄ ያነገበው “ወልደ አብ” የተባለው መጽሐፍ መወገዝ በቅባት ካህን የተጠመቁ ምእመናን ወደ ተዋሕዶ
ሃይማኖታችን ሲመለሱ መጠመቅ አለባቸው የሚሉት ፍሬያማ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ የአቡነ ሙሴን ጉዳይ ግን አጀንዳ መሆኑም ወደ መንበራቸው
እንዳይሄዱ መታገዳቸውም ከጅምሩም አልገባኝም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ጥሩ ጥሩ ውሳኔዎች እንደተወሰኑ ግን መረዳት አለብን፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ ወደ ሊቃውንት ጉባዔ ሊመሩት ነው
ሲባል ብዙ ጊዜ ፈጀ ያም ሆኖ ግን እስካሁን ድረስ ለሊቃውንት ጉባዔ ያ የሰበሰብነው ፊርማ አልደረሰም በዚህ በጣም እናዝናለን፡፡
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ጉዳዩን እንደ አዲስ በማንሣት ብጹእ አቡነ ዘካርያስ መጽሐፉን አውግዘው ለአቡነ ማርቆስም ግልጽ ደብዳቤ
ጽፈው መጽሐፉ እንዲመረመር ለቋሚ ሲኖዶስ አቤት ብለው ለሊቃውንት ጉባዔ ያደረሱት፡፡ በዚህም መሠረት የሊቃውንት ጉባዔ ጉዳዩን ዓይተው
መጽሐፉን ገጽ በገጽ ቃል በቃል ተመልክተው ባለ አምስት ገጽ ውሳኔ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያደረሱ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የሊቃውንቱን ጉባዔ
የውሳኔ ሃሳብ መነሻ አድርጎ ዓርብ ጥቅምት ፲፯ ከሰዓት በፊት በነበረው ጉባዔ መጽሐፉን አውግዞ ለይቶታል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ
የተነሡ ጉዳዮችም መላ ተበጅቶላቸዋል፡፡
·
መጽሐፉ ከሚሠራጭባቸው ቦታዎች ሁሉ እየተሰበሰበ
እንዲቃጠል፡፡
·
መጽሐፉ በታተመበት አካባቢ ለካህናት እና
ለምእመናን የእቅበተ እምነት ሥራ መሥራት ሥልጠናዎችን መስጠት፡፡
·
ወልድ ፍጡር ብሎ በሚያምን በቅባት ካህን
የተጠመቀ ሰው የልጅነት ጥምቀት መጠመቅ እንዳለበት፡፡ ጥምቀቱም ዳግም አይባልም፡፡
·
ሀገረ ስብከቱ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ቋሚ
ኮሚቴ እንዲዋቀር፡፡
·
“ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ”
የሚለው ሁለተኛው የኑፋቄ መጽሐፍም በሊቃውንቱ ጉባዔ እንዲመረመር
የሚሉ ትእዛዛት አብረው ተላልፈዋል፡፡
ሆኖም ግን እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ለመሥራት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከቦታው መነሣት እንዳለባቸው ደፍረው
አልተናገሩም፡፡ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በፌስ ቡክ ላይ ቅባትን እናስተምራለን የሚሉ አንዳንድ ልጆች አሁንም ከድርጊታቸው ባለመታቀብ
የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ሲቃወሙ ታይተዋል፡፡ እነዚህን ልጆች ያስተማሩትን ትምህርት በወረቀት ላይ በማተም ሙሉ አድራሻቸውን በመያዝ
ለቅዱስ ሲኖዶሱ እምነታቸውን እንዲገልጡ በማድረግ ካልተመለሱ እንዲወገዙ መደረግ አለበት፡፡ “ወልደ አብ” የተወገዘው እኛን ለማስደሰት
ቅባቶችንም ለማበሳጨት ሳይሆን መጽሐፉ አርዮሳዊ ስለሆነ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ መጽሐፍ ክህደት ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ብዙ
መጻሕፍት አሉ አልተወገዙም ምክንያቱም በቤተክርስቲያናችን ስም ስላልታተሙ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ግን በድፍረት ጥንታዊቷን ገዳም ነው
አሳታሚ ብሎ በፊት ገጹ ላይ ያስቀመጣት፡፡ ከመጽሐፎቹ ጋር በተያያዘ “ሚሥጢረ ሃይማኖት ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የሚለው በቀጣይ
እንደሚወገዝ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አሁን ላይ እየፈለግነው ያለው “መሠረተ ሃይማኖት” የሚለው “ሀ” ብለው ኑፋቄ የጀመሩበትን
መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ያላችሁ ወንድሞቼ እህቶቼ አድርሱን፡፡ በቤተክርስቲያናችን ስም ኑፋቄ አይተላለፍ ነው የምንለው እንጅ
ሰው የፈለገውን ማመን ይችላል መብቱ ነው ያውም ከፈጣሪ የተቸረው፡፡ በእኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ ግን የእኛ ያልሆነን ነገር ማስተማር
አይቻልም ያስቀጣል፡፡
ነገ በሚውለው የቅዱስ ሲኖዶስ ስበሰባ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጉዳይ ዳግም እንደሚነሣ እና የምእመናንን
እንባ የሚያብስ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይርዳን!
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፲፱
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment