Tuesday, October 31, 2017

"ምእመናን አልከሰሱኝም” ብጹእነታቸው አቡነ ማርቆስ




፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
#የምሥራቅ_ጎጃም_ሀገረ_ስብከት_ጉዳይ_ጉዳየ_ነው_በሚል_ለብጹአን_አባቶቻችን_የስልክ_መልእክት_እያደረሳችሁ_እና_ስልክ_እየደወላችሁ_ያላችሁ_ወንድሞች_እህቶች_አባቶች_እናቶች_ጉዳዩ_ስለታየልን_ስልክ_መደወሉን_እና_መልእክት_መላኩን_እንድታቆሙ_እናሳስባለን፡፡ #ብጹአን_አባቶቻችን_ሥራ_መሥራት_አልቻልንም_መልእክት_በዛብን_ስላሉ_አሁን_ጀምሮ_ቢቆም_መልካም_ነው፡፡ ላደረጋችሁት ትብብር ግን ከልብ እናመሰግናለን፡፡
************************




የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ማርቆስ ይህን ሀገረ ስብከት ከተረከቡበት ሕዳር ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ እስካሁኑ ድረስ የምእመናን ተቃውሞ አልበረደላቸውም፡፡ ምእመናን ከዚህ በፊት የቀደሙ አባቶቻችን ያሳዩን ያስተማሩን ነገር ሁሉ በእርስዎ እየተጣሰብን ነው ስለዚህ ከዚህ ድርጊትዎ ታቅበው እንደአባትነትዎ ይባርኩን ይመርቁን በማለት ምእመናን ብጹእነታቸውን ሁሌም ይጠይቃሉ፡፡ የመጀመሪያው ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሣባቸው ከቆራቢ ውጭ ማንም ሊጠጣው እንኳ ያልተፈቀደውን የቅዳሴ ጸበል እያወጡ እንደ ጥምቀት ጸበል ምእመናንን በረጩ ጊዜ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ “ብጹእ አባታችን ይህ የቅዳሴ ጸበል እኮ ነው እንዴት እንዲህ ይረጫል?” በማለት ምእመናን ወዲያውኑ የጠየቁ ሲሆን ብጹእነታቸውም ሲመልሱ “የጳጳስ ወጉ ጸበል መርጨት ነው እንጅ አረቄ ልረጭህ ነው” በማለት ምእመናንን ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመቅደሱን መጋረጃ በመክፈት ማንም ሊመለከተው የማይገባውን ምሥጢር ለማንም እንዲታይ ማድረጋቸው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ መጋረጃዎች ተከፍተው ካህናት የሚያደርጓቸውን ከቅዳሴው ጋር የተያያዙትን እያንዳንዱን እንቅስቃሴዎች ምእመናን እንዲመለከቱ በማድረጋቸው ተቃውሞ ተነሥቶባቸዋል፡፡

በዚህ መልኩ የጀመረው የምእመናን አቤቱታ ከእርሳቸው አልፎ ለጠቅላይ ቤተክህነት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲደርስ መእመናን በመደራጀት አቤታቱቸውን አሳውቀዋል፡፡ እርሳቸው ግን እየባሰባቸው እንጅ እያስተካከሉ ሲሄዱ አልታዩም፡፡ እንዲያውም በአሸናፊነት መንፈስ ነው አዳዲስ የስህተት ትምህርቶችን እና አስተዳደራዊ በደሎችን ሲፈጽሙ የነበረው፡፡ ባለፈው የግንቦቱ ሲኖዶስ አቤቱታውን ያቀረበው የምሥራቅ ጎጃም ምእመን ጉዳያችሁ የሚታየው በጥቅምቱ ሲኖዶስ ነው ዛሬ ላይ አጀንዳ አንቀርጽም በሚል ጥቅምት እስኪደርስ ድረስ ዓመት ሆኖ ታይቶት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ጥቅምት ደረሰ ጥቅምት ሲደርስ ይህ የመጨረሻችን ይሆናል ተብሎ ለሰባተኛ ጊዜ በሰባት አውቶቡስ #ከሞጣ #ከቢቸና #ከቁይ #ከሸበል #ከአምበር #ከሉማሜ #ከደጀን #ከደብረ_ማርቆስ #ከየጁቤ የተውጣጣ የምእመናን ተወካይ በቅዱስ ሲኖዶሱ የጸሎት መክፈቻ መርኃ ግብር ላይ በመገኘት አቡነ ማርቆስ አድርሰውታል የተባለው ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ በደሎች ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበት በጽሑፍ ተነቦ ማስረጃዎችም በፍላሽ ተደርገው ለብጹእ ጸሐፊው ለአቡነ ሳዊሮስ የተሰጠ ሲሆን አቡነ ማትያስም “ችግሩን እናየዋለን” በማለት ቃል ገብተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በቃሉ የሚገኝ ሰው የጠፋበት ጊዜ እና ዘመን ላይ ደረስን መሰለኝ ብጹእነታቸው አቡነ ሳዊሮስ እንደ አንድ አጀንዳ የያዙትን የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጉዳይ በፓትርያክ አቡነ ማትያስ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ጭቅጭቅ እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ ብጹአን አባቶች የምሥራቅ ጎጃም ጉዳይ እንዲታይ በብርቱ የታገሉ ቢሆንም የጉባዔውን ሰላም ለመጠበቅ ሲሉ በቅዱስነታቸው ሃሳብ ተስማምተው “ወልደ አብ” በሚታይበት አጀንዳ ላይ የአቡነ ማርቆስን ጉዳይ እናነሳለን በሚል ራሳቸውን አሳምነው ተቀመጡ፡፡ እንደተባለውም “ወልደ አብ” የተባለው የክህደት መጽሐፍ በታየበት አጀንዳ ላይ የአቡነ ማርቆስ ጉዳይም በመጠኑ ለመታየት ሞክሯል፡፡ በተለይ በዚህን ጊዜ አሳይተውታል የተባለው አባታዊ ያልሆኑ ንግግሮች በዲሲፕሊን ጉዳይ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ብጹእነታቸው “ይቅርታ” በማለት ምልአተ ጉባዔው በይቅርታ እንዲያልፋቸው ተማጽነዋል፡፡ አቡነ ማርቆስ ለሁሉም ነገራቸው “ማኅበረ ቅዱሳን ነው ይህን የሚያደርግ” በሚል እርሳቸው በሚጠሉት መጠን ሌሎች ብጹአን አባቶችም የሚጠሉት እየመሰላቸው ማኅበሩን በመክሰስ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ “ማኅበረ ቅዱሳን ዳግም ያጠምቃል” በሚል ማኅበሩ ይወገዝልኝ እስከማለት የደረሱት ብጹእነታቸው ከምልአተ ጉባዔው ያገኙት መልስ ግን እንደጠበቁት አልነበረም፡፡ “የሚያጠምቅ ቄስ ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳን ድርሻው ማስተማር ነው፡፡ ደግሞም ከጳውሎስ ሳምሳጢ ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ይጠመቅ ይልብዎታል” በማለት ሊቃውንት ጳጳሳት በቅባት ካህን የተጠመቀ ሰው ወደ ተዋሕዶ እምነት ሲመጣ መጠመቅ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ አንዳንድ የቅባት እምነት ተከታዮች በአቡነ ማርቆስ አስቸኳይ የድረሱልኝ ጥሪ ተሰባስበው አቡነ ማርቆስ አይነሱብን፤ “ወልደ አብ” አይወገዝብን ብለው ለጠቅላይ ቤተክህነት አቤቱታ ባቀረቡ ጊዜ ያዘጋጁት አንዱ ባነር “ዳግም ጥምቀት” የሚል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በፊትም አሁንም ወደፊትም ዳግም ጥምቀት የለም በቃ የለም፡፡ በቅባት ካህን የተጠመቀ ሰው ግን ወደ ተዋሕዶ ሲመለስ ይጠመቃል አራት ነጥብ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዱስ ሲኖዶስ የምሥራቅ ጎጃምን ጉዳይ በአጀንዳነት አለመያዙ ሲታወቅ እሁድ ጥቅምት ፲፱/ ፳፻፲ ዓ.ም የምእመናን ተወካዮች ከዚህ በፊት የተሰጡትን ማስረጃዎች በመያዝ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቤቱታቸውን ለማቅረብ እንዲሄዱ ተወሰነ፡፡ በዚህም መሠረት ሌሊቱን ሲጓዙ አድረው ጠዋት ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ አካባቢ በመሆን ብዙ እንግልት እና ድካም በመቋቋም ደጅ ሲጠኑ ውለዋል፡፡ በወቅቱ ማንም እንዳይገባ ማንም እንዳይወጣ የሚል ትእዛዝ ተላልፎ ስለነበር የምሥራቅ ጎጃም ተወካዮችም ይኸው ትእዛዝ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ሲሆን ወደ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ቦታ በመሄድ በግል ሊቃነ ጳጳሳትን አወያይተዋል፡፡ በተለይ ብጹእ አቡነ ሳዊሮስ መልካም አቀባበል በማድረግ ሌሎችን ሊቃነ ጳጳሳትንም በማገናኘት ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው አድርገዋል ተብሏል፡፡ እነዚህ የምእመናን ተወካዮች የመንግሥት አካላትንም በማግኘት ደስ የሚል ውይይት እንዳደረጉ ነው የተነገረው፡፡
ይህን አቤቱታ ምክንያት በማድረግ ብጹእ አቡነ ሳዊሮስ የምሥራቅ ጎጃም ጉዳይ መታየት አለበት ብለው ባመጡት ሃሳብ መሠረት ምልዓተ ጉባዔው ውሳኔ ላይ ለመድረስ የቻለ ቢሆንም ብጹእነታቸው አቡነ ማርቆስ ዛሬም እንደ ልማዳቸው “የእኔ ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን ነው” በማለት ተቃውመዋል፡፡ ብጹእ አቡነ ሳዊሮስም “እርስዎን የከሰሰ ማኅበረ ቅዱሳን አይደለም ምእመናን ናቸው እንጅ” በማለት ጉዳዩን ከዳር ለማድረስ ሞክረዋል፡፡ በዚህ ስበሰባ ቀን አቡነ ዘካርያስ ያልተገኙ በመሆኑ ጉዳዩ ይበልጥ ባይታይም ምልዓተ ጉባዔው ግን ውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ በጠቅላይ ቤተክህነቱ የሚመረጡ አጣሪ ኮሚቴዎች ወደ ቦታው በመሄድ እንዲያጣሩ ተወስኗል፡፡ ሙሉ የማጣራት ሂደቱም በቪዲዮ ተቀርጾ እንዲቀርብ ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት የሚመረጠው አጣሪ ኮሚቴ ጉዳዩን በጥልቀት የሚረዳ አስተዳደራዊውንም ሃይማኖታዊውንም ጉዳይ በጥልቀት ሊመረምር የሚችል አካል እንዲሆን እንመኛለን፡፡ ይህ ኃላፊነት የብጹእ ሥራ አስኪጁ የአቡነ ዲዮስቆሮስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በተለይ “የእኔ ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን ነው” የሚለው የብጹእነታቸው አቤቱታ በአጣሪ ኮሚቴው የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡ ይህ አጣሪ ኮሚቴ አሁኑኑ በፍጥነት ወደ ቦታው ካልመጣ ብጹእነታቸው ካህናትን በመሰብሰብ የንስሐ ልጆቻችሁን አሳምኑ በማለት እንደሚያነጋግሩ የታወቀ ነው፡፡ በዚህም ሃሳባቸው የማኅበረ ቅዱሳን ጠላት የሆኑ ግለሰቦችን ድጋፍ ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ለአቤቱታ ለሰባት ጊዜ በበረሃ የተንገላታውን ምእመን በመናቅ “የእኔ ከሳሽ ማኅበሩ ነው” ማለታቸው ከአንድ አባት የማይጠበቅ ንግግር እንደሆነ ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ሃሳብ የሰጠው ከቦታው ለማንሣት በቂ መረጃ አጥቶ አጣሪ ኮሚቴው በሚለው ሃሳብ ለመወሰን አይመስለኝም፡፡ መረጃ ከበቂ በላይ በብዙ ቅጅዎች ተባዝቶ ተሰጥቷል ነገር ግን አሁን ባለበት ሁኔታ አቡነ ማርቆስን ከምሥራቅ ጎጃም አንሥተው የት ያሰቀምጧቸዋል? ትልቁ ፈተናቸው ይህ ብቻ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቀጣይ በዚህ ሀገረ ስብከት መንበር ላይ ማን ይቀመጥ የሚለው ጥያቄ በራሱ የራስ ምታት ነው፡፡ አቡነ ቶማስ ከአዊ ወደዚህ ቢዛወሩ የበለጠ ችግር እንደሚፈጥሩ ሲያስቡት አቡነ ማርቆስን በዚሁ ማቆየት መፍትሔ መስሎ ስለታያቸው ይመስለኛል፡፡ ግን እንጅ የአንድ ሀገረ ስብከት መንበር የቤተክርስቲያኒቱ ነው ወይስ የዚያ አካባቢ ብቻ ነው? የትም ይወለድ የት የቤተክርስቲያናችን የሆነ አባት ያለምንም የዘር ቆጠራ ያለምንም የብሔር ሁኔታ ቢመደብ ችግር የለውም ባይ ነኝ፡፡ ይህን ሀገረ ስብከት ለመታደግ ካስፈለገ ቅዱስ ሲኖዶስ መፍትሔ ማድረግ ያለበት በትውልዱ በዚህ አካባቢ ያልሆነ አባት ቢሆን መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም እዚሁ አካባቢ ተወልደው ያደጉ አባቶች ዘመደ ብዙዎች ናቸው ሰው ደግሞ ይፈተናል ቅድሚያ ለዘመዴ ማለት ይጀምራል ያ ደግሞ እንቅፋት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ቅድሚያ ለምእመናን ድኅነት ነው መሥራት ያለባት ባይ ነኝ፡፡ እስኪ ለማንኛውም አምላከ ቅዱሳን ዕድሜ ሰጥቶ የሚሆነውን ነገር ያሳየን፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፳፩ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment