Wednesday, October 11, 2017

✍✝ ተስፋ አትቁረጥ!!!✝✍




፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ተስፋ መቁረጥ የተሸናፊነትና የደካማነት ስሜት ማሳያ ነው፡፡ ሰው ተስፋ የሚያደርገው ነገር ከሌለው ህይወቱ በፈተናና በመከራ የታጠረ ይሆናል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው ነገን ሳይሆን ዛሬን ብቻ ያስባል ለዚህም በኃጢአት ላይ ኃጢአት በበደል ላይ በደል ሲሰራ ይኖራል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው ግዴለሽና ራሱን የሚጥል ይሆናል፡፡ ቀናት የሚተካኩ እርሱን ለመጉዳት ይመስለዋል፡፡ አንተ ግን ከዚህ ተስፋ መቁረጥ ስሜት መውጣት ያስፈልግሃል፡፡ በምንም ዓይነት ፈተና ውስጥ ብትወድቅ ኢዮብን ሁልጊዜ እያስታወስክ ተስፋህን ማለምለም አለብህ፡፡
ተስፋህን የሚያጨልምብህ ጠላት ብቻ ነው እርሱ ደግሞ በዚህ ምድር ያለህን ቆይታ እስክትፈጽም ድረስ ተስፋህን አጨልሞ ለዘለዓለም ለራሱ ብቻ አድርጎ መኖር የሚሻ የማይራራ ክፉ ጠላት ነው፡፡ ስለዚህ ተስፋ የምታደርገው ነገር መኖር አለበት፡፡ ለነገ ተስፋ የሌለው ሰው የዛሬን መምሸት አብዝቶ ይቃወማል፡፡ ስለዚህ አንተ ከዚህ የተስፋ ቢስነትና የተስፋ ቆራጭነት ስሜት መውጣት ያስፈልግሃል፡፡ ራስህንም በቀናው መንፈስ  ማደስ ያስፈልግሃል፡፡ አንተ ተስፋ የምታደርጋት ርስት መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ለአንተ ከዚህ የበለጠ ተስፋ ካለህ ተስፋ እንደሌለህ፤ ተስፋ እንደቆረጥህ በዚህ ተረዳ፡፡ ተስፋህ ሃብት ንብረት ማፍራት፣ ቤት መሥራት፣ ቤተሰብ መመሥረት ብቻ ከሆነ እነዚህ ሲሟሉልህ አምላክህን መርሳትህ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ተስፋ የመቁረጥ ስሜትህን ማራቅ አለብህ፡፡
በቤቱ ለዘለዓለም ለመጽናት ተስፋ አለመቁረጥ እንደሚገባ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህም አባታችን አዳምንና እናታችን ሄዋንን መመልከት እንችላለን፡፡ አዳምና ሄዋን ተስፋ ቢቆርጡ ኖሮ ገነት መንግሥተ ሰማያት ባልተከፈተችላቸው እና ባልገቡባትም ነበር፡፡ ነገር ግን ተስፋ አልቆረጡምና ፈጣሪያቸውን በመማጸናቸው ተስፋቸውን አለመለሙ፡፡
ዳዊትንም ስንመለከተው እንደዚሁ ተስፋ ባለመቁረጥ በቤቱ እንደጸና እናስታውሳለን፡፡ ዳዊት የማይገባ ሥራ በመሥራቱ ነቢዩ ናታን ከእግዚአብሔር ተልኮ ሲመክረው ነቢዩን አልተተናኮለውም ነበር፡፡ ተስፋውንም ይበልጥ አለመለመ እንጅ አላቀጨጨውም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ያን የመሠለውን ድንቅ ምስጋና ለማመስገን የደረሰው፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው እንደዚያ ያለውን ምስጋና ከወዴት ያገኘዋል? 
ሐዋርያው ጴጥሮስንም ስንመለከተው ለተወሰነ ጊዜ ተስፋ የቆረጠ መስሎ ነበር፡፡ ለዚያም ነው “የምትሉትን ሰው በፍጹም አላውቀውም” ብሎ ፈጣሪውን እስከመካድ የደረሰው፡፡ ነገር ግን ተስፋ መቁረጡ እና አምላኩን መካዱ በአፉ እንጅ በልቡ አልነበረምና ዶሮ ሲጮኽ መራራ እንባን በማንባት የተቆረጠ ተስፋውን ቀጥሎታል፡፡ በተስፋ መቁረጥ ስሜት የወደቀው ይሁዳ ግን ክህደቱ በአፉ ብቻ ሳይሆን በልቡ ጭምር ነበርና እንደ ወንድሙ ጴጥሮስ በንስሐ አልተመለሰም፡፡ ተስፋ መቁረጡ እስከሞት ድረስ አደረሰው እንጅ፡፡
ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ወገንን ብቻ ሳይሆን ራስንም ያስጠላል፡፡ ለዚህ ነው በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ያሉ ሰዎች በብዛት ራሳቸውን ሲያጠፉ የምንመለከተው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ተስፋችንን እንዲቀጥልልን እና እንዲያለመልምልን ሁልጊዜ በጸሎት መማጸን ተገቢ ነው፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው በቤቱ ሊጸና አይችልምና በቤቱ ጸንተን ርስት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ተስፋ መቁረጥን ልናስወግድ እንደሚገባን ማዎቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ተስፋ ያለመቁረጥ ስሜት ለማዳበር ደግሞ የቅዱሳኑን ተጋድሎ ማሰብ ያስፈልገናል፡፡ ነገሮችን ሁሉ ለበጎ እንደተደረጉ አድርገን ማሰብም ተስፋችንን የማለምለም ስሜት ይኖረዋል፡፡ በሆነ ባልሆነው ራሳችንን ለጭንቀት አለማጋለጥም ለተስፋ መለምለም አስፈላጊ ነው፡፡
(አቤቱ ለምን ርቀህ ቆምህ? ከሚለው ያልታተመ መጽሐፍ የተወሰደ)
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፩ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment