Wednesday, October 25, 2017

✍✝ከፓትርያርኩ በላይ የለም እያላችሁ ካቶሊክ እንዳታደርጉን ተጠንቀቁ!✝✍




፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
በገዛ፡ ደሙ፡ የዋጃትን፡ የእግዚአብሔርን፡ ቤተ፡ ክርስቲያን፡ ትጠብቋት፡ ዘንድ፡ መንፈስ፡ ቅዱስ፡ እናንተን፡ ጳጳሳት፡ አድርጎ፡ ለሾመባት፡ ለመንጋው፡ ዅሉና፡ ለራሳችኹ፡ ተጠንቀቁ። ግብ.ሐዋ ፳፥፳፰


፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ካልተጠበቀ ሳንወድ በግድ ካቶሊካውያን መሆናችን ነው። ፓትርያርክ አይሳሳትም እርሱ ካለው ማለፍ ማትረፍ አይቻልም የሚለው ብሒል ካቶሊካዊነት ነው። መንበረ ፕትርክናውን እናከብረዋለን ፓትርያርኩን እንወድዋለን ሲኖዶሱ ከእኔ በታች ይሁን ያለን ፓትርያርክ ግን እንገስጻለን። ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በታሪክ ተወቃሾች እንዳትሆኑ ዝምታችሁን ስበሩት። እግዚአብሔር እናንተን ጳጳሳት ያደረገበት ዓላማ አለው ያንን ዓላማ መፈጸም ካልቻላችሁ ግን ታሪክ ይፋረዳችኋል። መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ታግለው እና ተከራክረው ከራሳችን ልጆች ሊቀ ጳጳስ መሾም አለብን ብለው የተሟገቱት ለእምነቱ የሚሞትን ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ለመሾም እንጅ በዝምታ በተኩላ የሚያስነጥኩትን ለመሾም አልነበረም።
ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሆይ! እኔ አዝንላችኋለሁ አለቅስላችሑማለሁ የተቀበላችሁት አደራ ቀላል አይደለም ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊም ነው። ቤተክርስቲያን የምትለማው በእናንተ ነው። ፓትርያርኩ የበላይ ወሳኝ አካል ናቸው ብላችሁ ዝም ካላችሁ ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ ያወገዙት ውግዘት በላያችሁ ላይ እንደሆነ ልብ በሉ። አንድ ካህን አንድን ጳጳስ ሲያወግዝ ያየን በአለቃ አያሌው ታምሩ ነው። አለቃ አያሌው ያወገዙትን ውግዘት ማንም አልፈታውም። ዛሬም የሲኖዶሱን ልዕልና ካላስከበራችሁ የእናንተ መሰባሰብ ምንም ትርጉም የለውም። ምእመናን በመናፍቃን ተወስደው አለቁ የሚለውን አሳዛኝ እና አስቂኝ ከአንድ ፓትርያርክ የማይጠበቅ ንግግር ልትሰሙ ከሆነ የተሰባሰባችሁት ስብስቡ ጉባዔ ከለባት ሊሆንባችሁ እንደሚችል ገምቱ። ከምንም ጊዜ በላይ በሕይወቴ እያዘንኩ ያለሁበት ቀን ቢኖር አሁን ነው።
ሳናውቅ ካቶሊካውያን እንዳታደርጉን ፓትርያርኩን ገስጻችሁ የሲኖዶሱን ልዕልና አስከብሩ። ያን ካላደረጋችሁ ግን አቡነ የሚላችሁ አታገኙም በእውነት ያለ ሐሰት።

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፲፬ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment