Monday, October 23, 2017

✍✝የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን የደርሶ መልስ ዘገባ✝✍



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አጫጭር መረጃዎች!
·        አባ ማርቆስ ባስተላለፉት አስቸኳይ የድጋፍ ጥሪ መሠረት ከእነማይ ከደጀን እና ከደብረ ማርቆስ የተውጣጣ የሥራ አስኪጆች የጸሐፊዎች እና የአድባራት እና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ስብስብ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ላይ ነው፡፡
·        አባ ማርቆስን ደግፈው ከብቸና ታርጋ ቁጥሩ 15835 ከደጀን ታርጋ ቁጥሩ 13552 በሆኑ መኪናዎች እየሄዱ እንደሆነ መረጃው ደርሶኛል፡፡
·        ይህንን ጉዞ በዋናነት ያስተባበሩትም የእነማይ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ አባ ፍቅረ ሥላሴ እና ጸሐፊያቸው ሊቀ ጠበብት አብርሃም ካሳ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
·        ዛሬ አዲስ አበባ ካልገባችሁ ከሥራ ትታገዳላችሁ ደመወዝም አይከፈላችሁም ተብለው እንደተነገሩ ከተጓዦች መካል አንዱን ዋቢ አድርጎ “መጽሔተ ተዋሕዶ” መዘገቧንም ዓይተናል፡፡



·        የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን ጉዟቸውን በሰላም ፈጽመው ወደ መካነ ግብራቸው ተመልሰዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስን ይህን ሀገረ ስብከት ከተረከቡበት ከሕዳር ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ እንዲነሡላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ቅዳሜ ጥቅምት ፲፩/፳፻፲ ዓ.ም በሰባት አውቶቡስ ለአቤቱታ የሄዱት ምእመናን ይህ ሰባተኛ ጊዜያቸው እንደሆነ በአቤቱታቸው ላይ አውስተዋል፡፡ በ፳፻፭ ዓ.ም ካቀረቡት አቤቱታ በተጨማሪ የጸሎት መጻሕፍት ላይ በተለይም ሰኔ ጎልጎታ ላይ ያላቸው አመለካከት፤ የገዳማት ገንዘብ ላይ የቼክ ፈራሚ መሆናቸው፤ ሹም ሽሩ በቁጥር ተገልጾ ተባብሶ እንደቀጠለ፤ ለቅዱሳን ያላቸውን አመለካት በተመለከተ፤ የክህደት መጻሕፍት ሲታተሙ ዝም ማለታቸው ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡ በበ፳፻፭ ዓ.ም የቀረበው አቤቱታ ይህን የሚመስል ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም የተወሰኑ ጭማሬዎች አሉበት፡፡ በመጨረሻም ይህ አቤቱታ ለሰባተኛ ጊዜ የሆነ ስለሆነ የመጨረሻችን እንዲሆን አቡነ ማርቆስን እንድታነሡልን እንማጸናለን ተብሎ ተጠቃሏል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቀን፡- ኅዳር30/2005 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ 
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
ከሁሉም በፊት የሀገረ ስብከቱን ምእመናን አቤቱታ ለመስማት በመፍቀዳችሁ በእግዚአብሔር ስም እያመሰገንን እኛ በሀገረ ስብከቱ በተለይም በደብረ ማርቆስ ከተማና አካባቢው የምንኖር የቤተክርስቲያን ልጆች በሀገረ ስብከቱ የተከሰቱትንና እየተከሰቱ ያሉትን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ለመፍታት ከብፁዕነታቸው ጋር የመንግስት ከፍተኛ የአመራር አካላትንም በመጨመር ተደጋጋሚ ውይይት ለማድረግ የሞከርን ቢሆንም ብፁዕነታቸው በሚያሳዩት አባታዊ ያልሆኑ ንግግሮች ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ እኛም የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ተሰባስበን በመወያየት የቤተክርስቲያኒቱን እሴት የሚያንኳስሱ ክንዋኔዎች፤አሠራሮችና ሁኔታዎች ከዕለት ዕለት እየበዙ በመምጣታቸው ጉዳዩን ለቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ለቅዱስ ሲኖድስ ሰላማዊና ተቋማዊ መዋቅሩን በጠበቀ መልኩ ይኸው ዛሬ ለማቅረብ ተገደናል፡፡
ምክንያቱም፡-

í) በሀገረ ስብከታችን እየተከሰቱ ያሉ አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ችግሮችን ከምንጩ ለማስረዳት፤
î) አሁን የተከሰቱትና እየተከሰቱ ያሉት ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ምንም መፍትሔ ሳይበጅላቸው በዚህ አካሄድ ከቀጠሉ ለሀገረ ስብከታችን እና ለመላ ቤተክርስቲያናችን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ከወዲሁ መፍትሔ እንዲፈለግበት፤
ï) ሀገረ ስብከታችን ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው “ከቅባት” ጋር የተገናኙ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችንና መላ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ልዩ ትኩረት እንዲሠጡት ለማስገንዘብ ሲሆን ብፁዕነታቸው አቡነ ማርቆስም በተደጋጋሚ ራሳቸውን ከሁሉም የተለዩ ፣የማይገኙ ፣ የማይተኩ ፣ እሳቸው ያሉትን የማይቀበል ያልዳነና ያልገባው መሆኑን በመግለጽ ካህናቱን በመሳደብ፣ ምእመኑን ወንጌል ያልገባው በደብተራ የተተበተበ እና ሌሎች የንቀት፣ የስድብ እና የእርግማን ንግግሮችን በመናገር የበደሉን በመሆኑ ለችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ እንጂ አቤቱታችን ከጭፍን ጥላቻና ነቀፌታ የነፃ ፍጹም ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ መፍትሄን በመሻት ነው፡፡
   

        íኛ. አስተዳደራዊ ችግሮች
ብፁዕነታቸው አቡነ ማርቆስ ወደ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት እንደመጡ ብዙ ጉዳዮችን በትችት ሕዝቡንም በንቀት የተመለከቱ ሲሆን በመጡ በ3ኛ ወራቸው ጀምረው፡-
í)  ከ41 በላይ ሹም ሽርና እገዳ ያካሄዱ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሹም ሽሮችና እገዳዎች ሕገ ቤተክርስቲያንን /ቃለ አዋዲውን/ ያልተከተሉ፤ተቋማዊ መዋቅሩን የጣሱ ይገኙባቸዋል፡፡
î) ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በቃለ ዓዋዲው መሠረት የተቋቋሙትን ሰ/ት/ቤቶችን “ወንበዴዎች፤ሌቦችና አሸባሪዎች” በማለት በሕዝብ ፊት ተሳድበው ለሰዳቢ ሠጥተዋል፡፡
ï በንጹሐን ምእመናን ላይ ሰብአዊ ክብርንና ነፃነትን የሚጋፋ የስድብ፤ንቀትና እርግማን አካሄደዋል፡፡
ð ) ብፁዕነታቸው ከሦስት በላይ መኖሪያ ቤቶች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል ተወልደው ባደጉበት፣ በተማሩበትና ባስተማሩበት ጉንደወይን ከተማ /በ2004 ዓ.ም የተገዛ/ እና አዲስ አበባ / በ2000 ዓ.ም የተገዛ/ ያላቸው ሲሆን ከአዲስ አበባው መኖሪያ ቤት የግንባታ ውል ክፍያ ጋር በተያያዘ በብፁዕነታቸው በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ላይ የተፈጸመው ክስና እስራት በሀገረ ስብከታችን ያሉትን ምእመናንን አንገት ሰብሯል፤ አዋርዷል፡፡ በዚህም ወቅት በሀገረ ስብከታችን አስተዳደር ውስጥ በሂሳብ ሹም፣ ገንዘብ ያዥና መዝገብ ቤት መካከል  ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአንድ ቀን የተደረጉ ለውጦችና ሰዎቹ ለብፁዕነታቸው ካላቸው ዝምድናና አካሄድ አንጻር ነገሩን ለሀገረ ስብከቱ ምእመናን ከጥቂት ዓመታት በፊት በብፁዕነታቸው አቡነ ዘካርያስ ከተፈጸመብን በደል አንጻር እንቅስቃሴውን እንቆቅልሽ  አድርጎብናል፡፡

                
îኛ. ሃይማኖታዊ ችግሮች
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ወደ ሀገረ ስብከታችን ከመጡበት ከኅዳር 2004 ዓ.ም ጀምሮ በካህናት፤በዲያቆናትና በሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን ዘንድ ያልተለመዱ፤እንግዳ ክንዋኔዎች እየተስተዋሉ ሲሆን ክንዋኔዎቹና አሠራሮቹም ምእመናንን ግራ ያጋቡ፤ለመናፍቃንም በር የከፈቱና የሚከፍቱ ናቸው፡፡

ከእነዚህም መካከል ፡-

1 ) ብፁዕነታቸው አቡነ ማርቆስ ከመጡ ከሁለት ወራት በኋላ ጀምሮ የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ቅዱሳን አበው ለመናፍቃን መልስ የሰጡበትና ለአማኞች ያስተማሩበት ሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ‹‹እኔ ልማታዊ ነኝ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም አለብን›› በሚል ተገቢ ያልሆነ ምክንያት ከቅዳሴ በኋላ እንዳይነበብ ተደርጓል፡፡



)2 በአንዳንድ አድባራትና ገዳማት በውል በታወቀ ምክንያት የቅዳሴ ጸሎት ሰዓቱ ቢቀየርም በፍትሐ ነገስት አንቀጽ 12 ላይ ‹‹ሕዝቡ ሳይሰበሰቡ የቅዳሴውን ጸሎት አይጀምሩ›› የሚለውን በመተው በሀገረ ስብከታችን ለብዙ ዘመናት ምቹ ከሆነው ንጋት የ12፡00 ሰዓት የቅዳሴው ጸሎት ያለ ምንም ተጨባጭ ምክንያት ‹‹ሰዓቱን ለወንጌል መጠቀም አለብን›› በሚል ምክንያት ወደ 11፡00 ሰዓት እንዲሆን ተደርጓል፡፡በዚህም እናቶች፤እህቶች፤ሕጻናትና አረጋዊያን ሌሊት 10፡00 ሰዓት ከቤታቸው እንዲወጡ በመገደዳቸው መቸገራቸውን፤መማረራቸውንና በቅዳሴ ሰዓትም የምእመኑ ቁጥር መቀነሱን እንገልጻለን፡፡
 3)  በክብር ለቡራኬ በእጃችን በማድረግ እንቀበለው የነበረውን የቅዳሴ ጸበል ያለ ምንም ምክንያትና ጥቅም ብፁዕነታቸው በጆግ በማደረግ በጅምላ ምዕመናንን መርጨት በማዘውተራቸው ምእመናንም ሲጠይቋቸው ‹‹እንግዲያውስ አረቄና ጠላ ልርጫችሁ?›› በማለት የተዘባበቱና የመለሱ ሲሆን ነገና ከነገ ወዲያ ይህ አካሄድ ወደ ቅዱስ ቁርባኑ የማይሄድበት ምንም ተጨባጭ ምክንያት እንደማይኖር እንገልጻለን፡፡
 4) በቅዳሴ ጸሎት ጊዜ ታቦተ መንበሩን ለምእመናን ግልጥ ሆኖ እንዲታይ በማስገደድ (ካህናቱ ሥጋውና ደሙን ሲፈትቱ እንዲታይ በማድረግ) በአካባቢው ሽማግሌዎች አበባል ‹‹የኢትዮጵያ ሙሽራ ዛሬ ተገለጠ ክፉ ቀን መጣ›› እስኪባል ድረስ ብዙ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም በቤተክርስቲያናችን ያልተለመደ የጸሎተ ቅዳሴ ሥርዓት እንድንከተል እየተገደድን እንገኛለን፡፡
 
5) በቅድስት ቤተክርስቲያናችን የሥርዓት መጽሐፍት በሆነው በፍትሐ ነገስት መሠረት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጾሙን ወራት በሚታሰብበት በጾመ ኢየሱስ ወይም ዐቢይ ጾም በአርምሞ፤በጾምና በጸሎት፤በንስሐና ቅዱስ ቁርባን፤በሱባኤ የጌታን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ማዘን፤ማልቀስ የሚገባ በመሆኑ ከበሮ የማይመታ የማይጨበጨብ ቢሆንም ብፁዕነታቸው ይህንን ሥርዓት በመተው ምእመናን “አልለመድንም ከበሮ አንመታም አናጨበጭብም” ቢሉም ‹‹እኔ ሊቀ ጳጳሱ ተቀምጬ፤እኔ ፊታችሁ እያለሁ›› በማለት በደ/ማርቆስ ከተማ በሚገኘው ጽርሐ ጽዮን አብማ ማርያም ቤተክርስቲያን በተደረገ ጉባኤ ምእመኑ ሳይፈልግ በማስገደድ ከበሮ አስመትተዋል፤ አስጨብጭበዋል፡፡
  )6 ካህናት ምእመናንን በተለይም የንስሐ ልጆቻቸውን በቅርብ መከታተል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መሰረት ካህናቱ በየንስሐ ልጆቻቸው ቤት በመዘዋወር ቡራኬ ይሰጣሉ፡፡ ብፁዕነታቸው ግን የሀገረ ስብከቱን ካህናት ክብርን በሚነካ መልኩና በጸበሉ ፈዋሽነት አለማመንን በሚያሳይ አነጋገር ‹‹ውኃ ግድግዳ ላይ ከመርጨት በቀር ወንጌል የማያውቁ›› በማለት ተሳድበዋል፡፡ ጸበል ውኃ ብቻ ነውን? ካህናቱስ አይባርኩትምን? እርሱስ መጻጉዕ የተፈወሰበት ወንጌል አይሆንም? ካህናቱስ ሌላ አያውቁምን?
)7 በፍትሐ ነገስት አንቀጽ 14 ላይ በተገለጸው መሠረት ሴት በወር አበባ(በወርኃ ጽጌ) ወቅትና አራስ ስትሆን ቤተክርስቲያን መግባትን የሚከለከል እንደሆነ ቢታወቅም ብፁዕነታቸው መግባት እንደሚችሉ የፈቀዱ ሲሆን እርሳቸው በተገኙባቸው ጉባኤያት ላይ ‹‹እኔ አባታችሁ እያዘዝሁ፣እኔ ፈቅጄ፣ እኔ የቤተክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያው እያለሁ›› በማለት እንዲገቡ በማስገደዳቸው የተወሰኑት እናቶችና እህቶች ትዛዛቸውን አክብረው ሲገቡ ቀሪዎቹ ለቤተክርስቲያን ክብር ሲሉ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ማየት የተለመደ ትርኢት ሆኗል፡፡
 )8 ብፁዕነታቸው ከላይ በተራ ቁጥር ሁለት ከተጠቀሰው የቅዳሴ ጸሎት  ሰዓቱን እንዲሻሻል ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ መውጣት እንጂ መግባት ይቻላል በማለት አባቶቻችንና ወላጆቻችን ያላስተማሩንን የማናውቀውን ሥርዓት እንድንከተል እየተገደድን መሆናችንን እንገልጻለን፡፡
9)  ብፁዕነታቸው ነገረ ቅዱሳንን በተመለከተ ግራ የሚያጋባ አቋም ያላቸው ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ሰባኪያነ ወንጌልን በመንበረ ጵጵስና ሰብስበው ‹‹ክርስቶስን ስበኩ እንጂ አቡሀይ እሙሀይ አትበሉ›› በማለት ስለ ቅዱሳን ያላቸውን አመለካከት ተናግረዋል፡፡
     
 በአጠቃላይ በሀገረ ስብከታችን ብፅዕነታቸው ያደረሱብን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደል እኝህ ብቻ ሳይሆኑ የተጠቀሱት ማስረጃ ማቅረብ የሚቻልባቸው ሲሆኑ በዚህ ጹሑፍ ቢቀርቡ የቤተክርስቲያንና የአባቶቻችንን ክብር የሚያስደፈሩ በመሆናቸው ያላቀረብናቸው ሲሆን እኛ በምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የምንገኝ የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች ከጥቂት ዓመታት በፊት በብፁዕነታቸው አቡነ ዘካርያስ የደረሰብን በደል ከልባችን ሳይሽር ከኃሊናችን ሳይወጣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለችግራችን መፍትሄ ለመፈለግና ምእመናንን ለመካስ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው በብፁዕነታቸው መቀጠል ሲገባውና የደረሰብንን በደል መካስ ሲገባቸው ድጋሜ ዘርፈ ብዙና መሰረታዊ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች በመከሰታቸው ምክንያት ይህን ችግር ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችንና ለመላ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ጉዳዩን ለመግለጽ የተገደድን ሲሆን አስፈላጊውን ተቋማዊ መዋቅር ተከትለን ችግሩን ለመፍታት ጥረት ብናደርግም ባለመሳካቱና ምላሽ ባለማግኘታችን መሆኑን እየገለጽን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችን ይህን ጉዳይ በጥልቀትና በስፋት ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡን ከዚህ ሸኝ ደብዳቤ ጋር ባያያዝነው 116 ገጽ የድጋፍ ፊርማ እየገለጽን እኛ የሀገረ ስብከቱ ምእመናን በቅዱስ እግዚአብሔርና  በቅዱሳኑ ስም እንጠይቃለን፡፡
   
“ቡራኬያችሁና ጸሎታችሁ አይለየን”
      
የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ምእመናን ተወካዮች

ግልባጭ
  •  ለብፁዕ አቡነ ናትናኤል አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
  •  ለመንበረ ፓትሪያሪክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት
  •  ለፓትሪያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት
  •  ለምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት
  •  ለምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ዘርፍ ጽ/ቤት
ይህ የአቤቱታ ደብዳቤ ሲነበብ አቡነ ማርቆስ እና ሥራ አስኪያጁ አባ እንባቆም ጫኔ ቆመው ያዳመጡት ሲሆን ፊት ለፊታቸው በምእመናን የተያዙትን ባነሮች እየተመለከቱ ፊታቸው ሲለዋወጥ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ አቡነ ማርቆስ አቡነ ማትያስን እየጠቆሙ አስቁሙልኝ ሲሉ እንደነበርና አቡነ ማትያስም አቁሙ ይበቃል ሲሉ ምእመናን በመጮኽ “ይጨርስ ይጨርስ ይጨርስ” በማለት እንባ እያወጣ ተማጽኗል፡፡ በዚህም መሠረት ሳይወዱም ቢሆን በግዳቸው ቆመው ሰምተውታል፡፡ ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ይህንን ጉዳይ ሲነጋገርበት እንዳደረም ተነግሯል፡፡ እዚያው መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም አጥር ላይ እንደጉድ የሚቸበቸቡት የቅባት መጻሕፍት “ወልደ አብ” እና “ምሥጢረ ሃይማኖት” የተሰኙት መጻሕፍት ዋና አጀንዳዎችም እንደሆኑ ተሰምቷል፡፡

ዛሬ የሚጀምረው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የምሥራቅ ጎጃምን ጉዳይ አንድ አጀንዳ ማድረጉን ብጹእ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ የገለጹልን ሲሆን የቅባት መጽሐፍ የሆነው “ወልደ አብም” በሊቃውንቱ ታይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ ይቀርባል ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት የውሳኔ ሃሳብ እንደሚሰጥበት ተጠቁሟል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ጉዳይ እንደሚሳስባቸው የገለጹት ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ምእመናን በርቱ አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን ብለው እንዳበረታቱ ተነግሯል፡፡ ከዚህ አቤቱታ ከተጻፈበት ደብዳቤ ጋራ ተያይዞ የገባውን ቪዲዮ እንድትመለከቱ ከዚህ በታች  አያይዠላችኋለሁ፡፡ ይህን ቪዲዮ በማውረድ ለአበው ሊቃነ ጳጳሳት በቻላችሁት መጠን እንድታሳዩ የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን ይማጸናሉ፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=PE5ZQqZFiDE&feature=youtu.be
 
በጣም የሚገርመው ለአቡነ ዲዮስቆሮስ የተሰጠው ድጋፍ ነበር፡፡ በግቢው የፈሰሰው ምእመና በሙሉ ነበር በጭብጨባ እና በእልልታ “አባታችን ይኑሩልን” በማለት አቀባበል ያደረገላቸው፡፡ ሌላው እንባ የሚቀድማቸው አቡነ ቀውስጦስ አቤቱታን ስናቀርብ እንባቸውን አፍሰዋል፡፡ “ወልደ አብ” የተባለውን የክህደት መጽሐፍ ገጽ በገጽ ቃል በቃል አንብበው ምልክት ያደረጉበት ታላቁ ሊቅ የሊቃውንቱ ጉባዔ የበላይ ኃላፊ አቡነ እንድርያስም በመገረም ነበር ሲያዳምጡ የነበረው፡፡ በዚህ ጉባዔ አቤቱታችን በትክክል እንደሚፈታ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ምስጋና!
ለብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት በሙሉ
ለየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል አካባቢ ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር
ለደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ፤ ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምእመናን ይሁንልን፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፲፫ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment