፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አጫጭር መረጃዎች!
·
“ቅባት የሚባል ነገር የለም ዳግም ጥምቀትም
የለም” በሚል በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የሚገኙ የወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪጆች የየአጥቢያዎችን ካህናት ሰብስበው እያወያዩ
ነው፡፡
·
አቡነ ማርቆስን በመደገፍ አዲስ አበባ የሄዱ
ሥራ አስኪጆች ጸሐፊዎች እና ካህናት የውሎ አበላቸውን ከቤተክርስቲያኒቱ ሊወስዱ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የግንቦቱ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ መናፍቁን አሰግድ ሣሕሉን አውግዞ መለየቱ ይታወቃል፡፡
መንፈስ ቅዱስ የሚመራው ይህ ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው ዓመት የተጀመረው የጥቅምቱ ስብሰባ ደግሞ እስካሁን ድረስ በማን አለብኝነት
አባቶችን ሲሰድብ ቤተክርስቲያናችንንም ሲያናንቅ የነበረውን መናፍቅ በጋሻው ደሳለኝን አውግዞ የለየው በትናንትናው የቀትር በኋላ
ስብሰባው ነው፡፡ ለቤተክርቲያናችን የማይመጥን፤ ቤተክርስቲያናችን ከምታስተምረው የተለየ ትምህርት ይዞ የተገኘን ሁሉ ያለምንም የማዕርግ
ልዩነት መክራ አስተምራ አልመለስ ያለውን በማውገዝ ስትለይ ኖራለች እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን፡፡ በዚህ መሠረት ወደፊትም በቅዱስ
ሲኖዶሱ ማጣራት እየተደረገ ኑፋቄ ይዞ የተገኘን ሁሉ በማውገዝ ቤተክርስቲያናችንን ከመናፍቃን እጅ ነጻ እንደምትሆን እንረዳለን፡፡
ቀጣዩ ውግዘት የሚያርፈው “ወልደ አብ” የተባለውን የኑፋቄ መጽሐፍ በጻፈው “መምህር ገብረ መድኅን እንዳለው”
ላይ ይሆናል፡፡ “ወልደ አብ” ብጹእነታቸው አቡነ ዘካርያስ አውግዘው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ እንዳልሆነ እውቅና ከመስጠት ባለፈም
ለሊቃውንት ጉባዔ አሳውቀው መጽሐፉ ገጽ በገጽ ቃል በቃል በሊቃውንት ጉባዔ ታይቶ ሙሉ ክህደት የተሞላ መሆኑን በመግለጽ ለቅዱስ
ሲኖዶስ የውሳኔ ሃሳባቸውን በማሳወቅ ተልእኳቸውን ፈጽመዋል፡፡ ቀጣዩ ሥራ የሚሆነው የዚህን መጽሐፍ አዘጋጅ “መምህር ገብረ መድኅን
እንዳለውን” በጉባዔው ፊት አስቀርቦ መልስ እንዲሰጥበት በማድረገስ ተጸጽቶ የሚመለስ ከሆነ ቀኖና ሊሰጠው የማይጸጸት እና የማይመለስ
ከሆነ ግን ተወግዞ ሊለይ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን እኔ እንደሰማሁት ከሆነ የዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ በሥጋ እንደሌለ ነው፡፡
ንስሐ ሳይገባ ቀኖና ሳይቀበል እንደሞተ በቅርብ እናውቀዋለን ያሉት መረጃ ሰጥተውኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን “ወልደ አብ” የተባለው
የቅባቶች መጽሐፍ ተወግዞ የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ እንዳልሆነ ለተዋሕዶ አማኞች እውቅና ይፈጠራል ተብሏል፡፡ በዚሁ ጉዳይም መጽሐፉ
የታተመበት የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጉባዔው እንደሚጠየቁ እና መልስ እንደሚሰጡበት ተጠቁሟል፡፡
ብጹእ አቡነ ዘካርያስ “ወልደ አብ” የተባለውን መጽሐፍ ለሊቃውንት ጉባዔ ካሳወቁ በኋላ “ሚሥጢረ ሃይማኖት
ወትንቢተ ዘዝክሪ ወጳውሊ” የተባለውን መጽሐፍ ገጽ በገጽ እየተመለከቱ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ብጹእነታቸው ይህንን ሥራ እንደጨረሱ
ለሊቃውንት ጉባዔ አስቀርበው “ወልደ አብ” የሚገጥመውን ዕጣ ለዚህኛውም መጽሐፍ እንደሚያሰጡት ይጠበቃል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ጉዳይ
በጉባዔው ንቁ ተሳታፊ ሆነው እስከመሰደብ እና ስማቸው እስኪጠፋ ድረስ እየታገሉ ያሉት ብቸኛ አባት አቡነ ዘካርያስ እንደሆኑም ነው
የተነገረው፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ የቅባት እምነት ተከታዮች አቡነ ዘካርያስን ለማሸማቀቅ እና ከዚህ ትግላቸው እንዲሸሹ ለማድረግ
ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከትን ይመሩ በነበሩበት ጊዜ ስለጠፋው ገንዘብ አብዝተው ይናገራሉ፡፡
ብጹነታቸው አቡነ ዘካርያስ ጠፋብኝ
ያሉትን ገንዘብ ያልካዱ ቃል በገቡት መሠረትም ከልጆቻቸውን ለምነው ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ያስረከቡ ናቸው፡፡
አንድ ነጥብ ስድስት
ሚሊዮን ብር ጠፋባቸው የተባሉት ብጹእነታቸው ያንን ብር አሁን ላሉት ሊቀ ጳጳስ በጉባዔ መካከል ማስረከባቸው ተዘግቧል፡፡ ነገር
ግን አሁን ያ ገንዘብ የት እንደገባ ምን እንደተሠራበት የተነገረ ነገር ስለሌለ በዚህ ጉዳይ መወቀስ የሚገባቸው አቡነ ዘካርያስ
ሳይሆኑ አቡነ ማርቆስ ናቸው፡፡ ብጹእ አቡነ ዘካርያስ የምሥራቅ ጎጃምን ህዝብ እንባ ለማበስ በንቃት እየታገሉ እንደሆነ መረጃው
ደርሶኛል፡፡ በፊት የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እያሉ አቡነ ዘካርያስ ከምሥራቅ ጎጃም እንዲነሡ በምእመናን አቤቱታ
ቀርቦባቸው እንደነበር የታወቀ ነው፡፡
ዛሬ ግን ያንን ለመካስ እየሠሩ ያሉ አባት ሆነዋል ተብሏል፡፡ ዛሬ የምንሰማው ሌላም ደስታ
እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ ለተዋሕዶ ልጆች ብቻ ማለቴ ነው፡፡
እዚህ ላይ አስተያየት ሊሰጡ የሚቋምጡ የቅባት እምነት ተከታዮች
አቡነ ዘካርያስን ምን ብለው እንደሚገልጿቸው ተመልከቱ፡፡ አቡነ ማርቆስስ የገዳመ አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገዳም ገንዘቡን
ህጋዊ ሆነው ሊበሉት ይህንን ከታች አብሮ የተያያዘውን ደብዳቤ ሲጽፉ ምን አላችሁ ቃለ ዓዋዲው ስላዘዘ ነው ትሉ ይሆን በፍጹም!
አስተያየታችሁን ሚዛናዊ ለማድረግ ሞክሩ ያ ካልሆነ ግን #BLOCK ስላለ ዳግም አንተያይም፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፲፮
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment