Friday, October 13, 2017

ስለእያንዳንዳችን የልጅነት ድርሻ ብንነጋገርስ




፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ግንቦት ፲፯/ ፳፻፲ ዓ.ም ለቤተክርስቲያናችን ዘበኞች ራሳችን እንሁን! በሚል ርእስ ቤተክርስቲያናችንን ከመናፍቃን ለመታደግ በርካታ የዘብነት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባን ገልጨ ጽፌ ነበር፡፡ ይህንንም ሙሉውን ይህንን ሊንክ ተጭናችሁ እንድትመለከቱ እጠይቃለሁ፡፡ https://melkamubeyene.blogspot.com/2017/05/blog-post_25.html በዚህ ጽሑፍ በዋናነት ያነሣኋቸው ነገር ግን በእናንተም የሚጨመርባቸው እና የሚጠናከሩ ነጥቦች የሚከተሉት ነበሩ፡፡ ዘብነት በሚል ያስቀመጥኋቸው የልጅነት ድርሻችንን ነው፡፡ እኛ እንደ አንድ የቤተክርስቲያን ልጅነት መወጣት የሚገባን ምንድን ነው?
#ዘብነት_፩. ሁሉም ሰው የአብነት ትምህርትን በሚችለው አጋጣሚ ሁሉ መማር አለበት፡፡ የሚችል ሰው ጉባዔ ቤት ገብቶ ሁሉንም የቤተክርስቲያናችን እውቀት ማወቅ አለበት፡፡ ያልቻለ ሰው ደግሞ ዘመናችን ቴክኖሎጅው የተራቀቀበት ዘመን ስለሆነ ሁሉንም የአብነት ትምህርቶችን በድምጽም ሆነ በምስል እየቀረጸ ከቤቱ ቁጭ ብሎ ጊዜ ሰጥቶ ማጥናት እና መማር ይችላል፡፡ ያጠናውን ነገር በአግባቡ መያዙን ለማረጋገጥ ከአብነት መምህራን ጋር ተገናኝቶ ስህተቱን በማረም ሙሉ መሆን ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማኅበረ ቅዱሳን በሚያቀርባቸው የአብነት ትምህርቶች ውስጥ በመሳተፍ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም መማር ይቻላል፡፡ አሁን ድራማ ፊልም ጨዋታ ምናምን የሚባል አሸንክታብ ጥለህ መገኘት አለብህ፡፡
#ዘብነት_፪. በነጻ ማገልገል፡፡ ይህኛው ዘብነት ከዘብነት ፩ በኋላ የሚመጣ ጸጋ ነው፡፡ የአብነት ትምህርቶችን ከተማርክ በኋላ ክህነት ማምጣት ከቻልህ ክህነት ታመጣለህ ማምጣት የማትችል ከሆነ ግን ትምህርትህን ብቻ ይዘህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ትገባለህ፡፡ ታዲያ አገልግሎትህ ፍቅረ ንዋይ የሌለበት ለነፍስህ ብቻ ብለህ ይሁን፡፡ በቃ በነጻ አገልግል፡፡ በነጻ ማገልገል ስትጀምር ለ ”ቢዝነስ” ብሎ ቆቡን ያጠለቀው መሸሽ ይጀምራል፡፡ የምንኩስናው ቦታ ከተማ እንዳልሆነ መረዳት ይጀምራል፡፡ የምንኩስናው ቦታ በጾም በጸሎት የሚታገሉበት በረኃ ነው፡፡ እዚያ የአራዊቱን ድምጽ ፈርቶ የአጋንንቱን ፈተና ሸሽቶ ከተማ ለከተማ ቀሚሱን እያዝረከረከ የሚዞረውን አስመሳይ መነኮስ ሁሉ ቀልብ ያስገዛልሃል፡፡ በቃ አገልግሎት በነጻ ይሁን፡፡ ጳጳስም በለው የመምሪያ ኃላፊም በለው ሥራ አስኪያጅም በለው ቀዳሽም በለው ምንም በለው ምን በነጻ ያለገንዘብ አገልግል ተብሎ የነጻ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ ያን ጊዜ ቆቡን እየጣለ አዲስ “ቢዝነስ” ይጀምራል፡፡ ቤተክርስቲያናችንን ለቅቆ ይሄድልናል፡፡ ለአገልግሎት ሳይሆን ለፊርማ ብሎ ሰዓታት እና ማኅሌት የሚቆመው፣ ኪዳን የሚያደርሰው ቅዳሴ የሚቀድሰው ሁሉ በነጻ አገልግል ሲባል በሉ ደህና ሁኑ ብሎ ከቤታችን መውጣት ይጀምራል፡፡ 
#ዘብነት_፫. የያገባኛልነት ስሜትን መላበስ፡፡ ሁሉም ሰው ለቤተክርስቲያኑ ክብር ያገባዋል ይመለከተዋልም፡፡ ስለዚህ ቃጭል እያቃጨለ ስለ ጊዮርጊስ ስለ ማርያም እያለ የስእላትን ክብር ዝቅ በማድረግ በየመንገዱ በስእላት የሚነግደውን ነጋዴ ሁሉ እያነቁ ለፖሊስ ማስረከብ አለብን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ማሰሪያ ተዘከሩን እያለ ተሰርተው በተመረቁ አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀር ለልመና መናኸሪያ ለመናኸሪያ የሚዞረውን ነጋዴ ሁሉ እያነቁ መያዝ ነው፡፡ ስእላችን ክብር ይኑረው፣ ስማችን ክብር ይኑረው፣ ለማኞች ናቸው አንባል፡፡ ይህ ይቆጨን፡፡ ባለቤት የሌላት እስከምትመስል ድረስ ሁሉም ተነሥቶ የሚነግድባት ቤተክርስቲያናችን ታሳስበን እንጅ፡፡ ሁላችንም ያገባናል ሁላችንም ይመለከተናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የሚባል ደንቀራ መወገድ አለበት ይመለከተናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸነፈ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስህተት ሰራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወራጅ ቀጠና ገባ ወዘተ እየተባለ ሲነገር እንዴት አይሰቀጥጠንም፡፡ ስእላትን አስፋልት ላይ አንጥፈው የሚሸጡ፣ ከደብረ ሊባኖስ ከግሸን ተባርኮ የመጣ መስቀል እያሉ በሞንታርዶ የሚጮኹብንን እያነቅን ለፖሊስ እንስጣቸው፡፡ የራሷ የቤተክርስቲያናችንን ሱቅ እንከፍትላታለን፡፡
#ዘብነት_፬. የቶማስን እምነት መያዝ፡፡  ዘንድሮ መጠርጠር ጥሩ ነው፡፡ ቶማስ ኢየሱስ ክርስቶስን የተወጋ ጎንህን ካልዳሰስሁ አላምንም ብሎታል፡፡ በቃ! ይህ ለዘንድሮ ሰዎች ለእኛ ጥሩ ትምህርት ነው፡፡ ቀሚሱን ስለለበሰ አስኬዋውን ስለደፋ ብቻ መነኩሴ ነው ብለህ አትታለል፡፡ ውስጡን ማንነቱን ዳሰው ካልዳሰስኸው አትመን፡፡ እርሳቸው ጳጳስ ናቸው አይሳሳቱም አትበል ንስጥሮስ ፓትርያርክ እንደነበረ አትዘንጋ፡፡ እኛ ከሰበክንላችሁ ወንጌል ውጭ የሰማይ መልአክም ቢሰብክላችሁ አትቀበሉ ብሎናል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ በቃ መልአክ መስሎ ከሰማይ ቢወርድም አንሰማም!!!
#ዘብነት_፭. ከቤተክርስቲያን አለመራቅ፡፡ ብዙዎቻችን እኔን ጨምሮ ከቤተክርስቲያን ርቀናል፡፡ መቅደሳችን ውስጥ ገብተው ሲቀድሱ ላለማየት ሸሽተኛል፡፡ ይህ ግን መፍትሔ አይደለም፡፡ ሕጓን ሥርዓቷን እንማር ሁላችንም ሰንበት ትምህርት ቤት እንግባ፡፡ ልጆቻችንን እየያዝን እንማማር፡፡ ታሪካችንን እምነታችንን እናጥና፡፡ ሥርዓቷን ሕጓን እንማር፡፡ ከዚህ የወጣ ካየን ግን እንታገል፡፡
አሁን ሁላችንም ከእነዚህ ዋና ዋና ብየ ካነሣኋቸው ዘብነቶች በተጨማሪ እናንተም መጨመር እና ማጠናከር ትችላላችሁ፡፡ ይህንን የምንለው እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኒቱ አያስብላትም ብለን አይደለም፡፡ እርሱ ያስብላታል ነገር ግን የእኛ በረከት ማግኛችን መንገዶች እነዚህ ናቸውና ነው፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት ዘብነቶች በተጨማሪም ዛሬ ላይ የምጨምራቸው የዘብነት ሥራዎች ይኖራሉ፡፡
#ዘብነት_፮. ንስሐ መግባት፡፡ ሁሉም ሰው ተዘጋጅቶ መኖር ያስፈልገዋል፡፡ የት፣ መቼ፣ እንዴት፣ ማን ላይ ንስሐ እገባለሁ የሚለው የየራሳችን ምርጫ እና ፍላጎት ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ንስሐ የግድ እንደሆነ ማወቅ ከቻልን ከዚህ በኋላ ስላለው ዝርዝር አፈጻጸም የራሳችን ድርሻ ነው የሚሆነው፡፡ ንስሐ ገብተን ነጽተን በሥጋ ወደሙ ተወስነን እንኑር፡፡ አሁን ላይ ተሐድሶ እንዲፈነጭብን ዕድሉን የፈጠርንለት ራሳችን ነን፡፡ የመድረክ ላይ ስብከቶችን እንሰማለን ግን ለውጥ አምጥተን አናውቅም ለምን ቢባል ሰባኪውን ስለምናይ ነው፡፡ የምንናገረውን እና የምንጽፈውን ነገር ሆነን መገኘት ከቻልን በቃ እኛ ለተሐድሶ እሳቶች መሆን እንችላለን፡፡ ነውር ነቀፋ እንዳይገኝብን ራሳችንን ከሁሉ ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ በንስሐ እንኑር በሥጋ ወደሙ እንወሰን፡፡
#ዘብነት_፯. ጾም እና ጸሎት፡፡ እስኪ ሃያ ዐራት ሰዓት መብላት እና መተኛት እናቁም፡፡ መናፍቃን  ሃያ ዐራት ሰዓት ለጥፋት ሲሰሩ እኛ ግን የሚመች ፍራሽ እየቀያየርን ሃያ ዐራት ሰዓት ሙሉ አልጋችን ላይ ነን ቆይ ግን አይቆጫችሁም፡፡ አሁን እኛ ሰዎች ነን፡፡ ሥራ በጣም ስለሚበዛብኝ ስለሚደክመኝ አልቻልኩም ወዘተ ብለን ለምን ተልካሻ ምክንያት እንደረድራለን፡፡ በእውነት እንደምናወራው እና እንደምንጽፈው ያለን ሰዎች ከሆንን እኮ ሌሊቱ ሙሉ የእኛ ነው፡፡ እስኪ ለዚሁ ብለን ጸሎት እንጀምር ጾም እናውጅ፡፡ እሽ ማን ብላ ብሎ አስገድዶህ ነው ጾም የምትሽረው እሽ ማን አትጸልይ ብሎህ ነው ሌሊቱን ሙሉ ተኝተህ የምታድረው፡፡ ይህን የምላችሁ እኔ ስለማደርገው አይደለም እኔንም ራሴንም ነው እየወቀስኩ ያለሁት፡፡ እኔማ እንዲያውም ቢሮ ውስጥም ሳንቀላፋ የምውል እልም ያልሁ እንቅልፋም ነኝ፡፡ ግን መሻሻል እንዳለብኝ አውቃለሁ መጸለይ አለብኝ መጾም አለብኝ፡፡ ይህ እኮ ለራሳችንም የበረከት ምንጭ ነው፡፡
#ዘብነት_፰. ለገዳማውያኑ ማሳሰብ፡፡ እስኪ መጸለይ ደከመን መጾም አልችል አልን ጸልዩልን ብሎ ገዳማውያኑንንስ መማጸን መባዕ መስጠት አንችልም፡፡ የተነሣብን ወረራ ቀላል አይደለም የዚህ ታሪክ አባል መሆናችን ደግሞ ለበጎ ነው፡፡ ከሠራን የምንመሰገንበት ለትውልድ የሚተላለፍ ሐውልት የምንተክልበት ካልሠራን ደግሞ ስም አጠራራችን የማይታወስበት ዘመን ነው፡፡ አባታችን ዲዎስቆሮስን ዛሬ ድረስ የምንዘክረው እኮ ለተዋሕዶ እምነቱ ጥርሱን እስኪያወልቁት ድረስ ስለታገሰ ጽሕሙ እስኪነጭ ድረስ ስለታገሰ ነው፡፡ አርዮስን በክፉ የምናነሳውስ ስለምንድን ነው ወልድ ፍጡር ስላለ ስለካደ እኮ ነው፡፡ የእኛም እጣ ፈንታ እንደዚሁ ያለ ነው፡፡ በእውነት አንተ እያለህ አንቺ እያለሽ ተዋሕዶ ስትደፈር ድንበሯ ሲፈርስ ቆመህ ትመለከት ቆመሽ ትመለከች፡፡ በቃ አንተ ካልቻልህ የሚችሉትን ገዳማውያኑን ቅዱሳን አባቶችን አሳስብ መባዕ ውሰድ፡፡
#ዘብነት_፱. ማኅበራትን ማጠናከር፡፡ አሁን በርካታ ማኅበራት አሉ እነዚህ ማኅበራት በጋራ ሆነው ለአንድ ዓላማ ወደፊት መገስገስ አለባቸው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የጽዋ ማኅበራት፣ ዕድሮች፣ግቢ ጉባዔያት፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወዘተ ሁሉም ለአንድ ዓላማ ኅብረታቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡ መርዝ የሚረጩትን አካላት ለይቶ ለህግ እስከማቅረብ ድረስ መጠናከር አለብን፡፡ በጋራ እየተረዳዳን እውነተኛ ስብከቶችን ያሬዳዊ መዝሙር ካሴቶችን ልዩ ልዩ መጽሐፎችን እና መጽሔቶችን በራሪ ወረቀቶችን ሳይቀር በማዘጋጀት ለህብረተሰቡ ማዳረስ ይኖርብናል፡፡ እውነቱን እውነት ሀሰቱን ሀሰት የሚል መልካም ራእይ ያለው ትውልድ መገንባት ያስፈልገናል፡፡ ይህን ማድረግ ስንችል መናፍቃኑን ከራሳችን ትክሻ ላይ አውርደን በባዶ እግራቸው መንዳት እንችላለን፡፡

በነገራችን ላይ ሌሎችንም በርካታ ነገሮችን መጨመር ትችላላችሁ እኔ ግን ለዛሬ ያለኝን ሃሳብ እዚህ ላይ ልቋጨው ተገደደሁ፡፡
#ውይይቱ_ጠንካራ_ሃሳቦችን_ማፍለቅ_አለበት_እስኪ_እንነጋገር_ዝም_አትበሉ_አስተያየት_ስጡ_እንወያይበት_ወደፊት_እንዴት_እንቀጥል? በረከት ማግኘት የምንችልበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ ከዚህ በረከት መሳተፍ ካልቻልን አለቀልን መቼ በረከቱን ጸጋውን ልናገኝ እንችላለን ታዲያ፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፫ / ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍

No comments:

Post a Comment