፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠


ቅዱስነታቸው አቡነ ማትያስ “ሥልጣን እለቃለሁ” አሉ ሲባል የተረዳሁት ነገር አለ፡፡ እውነት ይህን ተናግረውት
ከሆነ ስለሚከተሉት ነገሮች ይህን እንደተናገሩ ተረድቻለሁ፡፡
፩. በሙስና እና በልዩ ልዩ የምግባር እና የእምነት ችግሮች ውስጥ የተዘፈቁትን የአንዳንድ ሥራ አስኪያጆችን
እና አስተዳዳሪዎችን ሙሉ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ነው፡፡
፪. የራሳቸውን ጉዳይ ለማስፈጸም ሲሉ የእርሳቸውን በፓትርያርክነት መቀጠል የሚፈልጉትን የአንዳንድ ሊቃነ
ጳጳሳት ድጋፍ ለማግኘት ነው፡፡
፫. ፕትርክናው አቡነ ማትያስ ተወልደው ካደጉበት ብሔር እንዳይወጣ በእግዚአብሔር አሠራር ላይ ገብተው የሚፈተፍቱትን
የብሔርተኞችን ድጋፍ ለማግኘት ነው፡፡
፬. በመጨረሻም እርሳቸው እንዲቀጥሉ የሚፈልግ ከሆነ የመንግሥትን ድጋፍ ለማግኘት ነው፡፡

በነገራችን ላይ “ፕትርክና” እለቀዋለሁ እያሉ የሚያንገራግሩበት ሥልጣን ሳይሆን አደራ ነው፡፡ በርግጥ “ይደልዎ!
ይደልዎ! ይደልዎ!” ሳይባል ዕጣ ሳይጣጣል የተሰጠን አደራ ከሥጣን እኩል ቆጥረውት “ሥላጣኔን እለቃለሁ” ቢሉ አይገርመንም፡፡ ይህ
አደራ እስከሞት ድረስ ስለእውነት የሚሠሩበት እንጅ “አልቀዋለሁ” እያሉ የሚያንገራግሩበት እና የሚያስፈራሩበት እንዳልሆነ ነው እኔ
የሚገባኝ፡፡ “ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁ ፓትርያርክ” መባልን ሽተው ከሆነ እናዝናለን፡፡ “አደራቸውን
የተወጡት ፓትርያርክ” መባል በተሻለ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከራሷ ልጆች መሾም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ የተሾሙት ሁለቱ ፓትርያርኮች
አቡነ ባስልዮስ እና አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው በህጉ እና በሥርዓቱ መሠረት የተሾሙት ከዚያ በኋላ ያለው ግን የህግ እና የሥርዓ ጥሰት
የተፈጸመበት ነው፡፡ ደጉ መናኝ መነኩሴ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሦስተኛ ፓትርያርክ ሆነው ሲሾሙ እኮ አቡነ ቴዎፍሎስ እስር ቤት ነበሩ፡፡
“ፓትርያርክ ሳይሞት ሌላ ፓትርያርክ አይተካ” የሚለው ህግ የተጣሰ ያንጊዜ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የፕትርክናቸውን ተልእኮ
እና አደራ በአግባቡ የተወጡ ቅዱስ አባት ቢሆኑም በወቅቱ በነበረው አገዛዝ ተጽእኖ ህጉን ሽረው ነው ወደ ፕትርክናው ያመጧቸው፡፡
ዐራተኛ የተሾሙት አቡነ መርቆርዮስ እስካሁን ድረስ በሕይወት እያሉ በአገራችን ሁለት ፓትርያርኮች ተሸመዋል (አቡነ ጳውሎስ እና
አቡነ ማትያስ)፡፡ አንድ ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ ሲሾም እየተመለከትን ባለንበት በዚህ ከባድ ዘመን “ሥልጣኔን
እለቃለሁ” ብሎ ሌላ አዲስ ነገር በሀገራችን ላይ ማምጣቱ ለእኔ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ እሁድ በጸሎት የሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ
ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ዓይቶ የራሱን ውሳኔ እንደሚያሳርፍ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ “ሥልጣኔን እለቃለሁ” ብለው ለቅዱስ ሲኖዶስ ካቀረቡ
እንኳ በሥርዓቱ መሠረት ተወግዘው ተለይተው ሌላ አባት “ይደልዎ፣ ይደልዎ፣ ይደልዎ” ብለው በመንበሩ ላይ ይተካሉ፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው
ለቤተክርስቲያኒቱ እንጅ ለግለሰቦች ምቾት አይደለም፡፡ እውነታቸውን ሆኖ “እለቃለሁ” በሚለው ሃሳባቸው ከጸኑ ግን ለቤተክርስቲያናችን
ደህንነት ሲባል ቢለቁ በእኔ በኩል ደስታየ ወሰን የለውም፡፡
የዘንድሮው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከባድ ውሳኔዎችን እንደሚያሳርፍ ይጠበቃል፡፡ አሁን ላይ በቤተክርስቲያኒቱ
ላይ እየተፈጸመ ስላለው ጉዳይ በጥልቀት ይመረምራል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፲
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
No comments:
Post a Comment