Friday, October 6, 2017

✍✝ “እያደር የሚቀጭጭ እምነት” ✝✍



፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ላይክ ላይክ ላይክ
facebook.com/beyenemelkamuA
facebook.com/melkamubeyeneB
ላይክ ላይክ ላይክ
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
እምነት በተስፋ የሚረዷት፣ ያለጥርጥር የሚቀበሏት፣ ከኅሊና በላይ የሆነች ምጡቅ፣ የማትመረመር ረቂቅ፣ የማይታየውን ስውር ነገር አጉልታ የምታሳይ መስታወት፣ ከፈጣሪ ጋር ቃል ለቃል የምታነጋገር ድንቅ መስመር፣ የሚመጣውን የምታውቅባት የትንቢት መነጽር፣ በመዳሰስ የማትረጋገጥ በሳይንስ እውቀት የማትለካ የማትመዘን፣ በቤተ ሙከራ ከመፈተሽ የራቀች፣ ቁስ አካላዊ ያልሆነች፣ የራቀው የሚቀርብባት የረቀቀው የሚጎላባት ድንቅ መሣሪያ ናት እምነት፡፡ እምነት ተስፋ ለሚያደርጓት የተረዳች ናት፡፡ ተስፋ ለማያደርጋት ግን እምነት ትርጉም አልባ ናት፡፡ በእምነት ውስጥ ተስፋ ይኖርሃል ተስፋ ሲኖርህም እምነትህ ይጠነክራል፡፡
ጌታችን በወንጌሉ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ ሂድ ብትሉት ይደረግላችኋል ብሎናል፡፡ እምነት እንደዚህ ያለ ተአምራዊ እና ድንቅ የሆነን ሥራ ያሠራል፡፡ ፍጹም እምነት ካለን ተራራ ማፍለስ፣ ድውይ መፈወስ፣ሙት ማንሣት፣ ሽባ መተርተር፣ ጎባጣን ማቅናት፣ ለምጻሙን ማንጻት፣ ባሕር መክፈል፣ ከእሳት ማምለጥ ወዘተ እንችላለን፡፡ ይህ ሁሉ ግን ፍጹም እምነት ላለው እንጅ ለሁሉም የታደለ አይደለም፡፡ ፍጹም እምነት ብዙ ድንቅ ሥራን ያሠራል፡፡ ይህንንም ያረጋገጡልን እንደ ዮናስ፣ እንደ ዳንኤል፣ እንደ ሠለስቱ ደቂቅ፣ እንደ ሙሴ፣ እንደ ጴጥሮስ፣ እንደ ጳውሎስ፣ እንደ ዮሐንስ ወዘተ ያሉ ደጋግ ቅዱሳን አባቶችን መጥቀስ እንችላለን፡፡
ቅዱሳን በመከራ ሲፈተኑ እምነታቸው እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ ደማቸውን የሚያፈስ ዓላዊ ሲነሣ እነርሱ እምነታቸውን አጠንክረው አንገታቸውን ለስለት ደረታቸውን ለጦር ግንባራቸውን ለጠጠር አሳልፈው ይሰጡ ነበር፡፡ ዓላውያን ነገሥታት ዕለት ዕለት እልፍ ይገድላሉ ዕለት ዕለት ከእልፍ በላይ የሆኑ አዲስ ክርስቲያኖች ይነሡ ነበር፡፡ ገድለው መጨረስ እስኪሳናቸውና በሥራቸውም እስኪጸጸቱ ድረስ ቅዱሳን በሞታቸው ዓላውያኑን ይፈትኗቸው ነበር፡፡ እምነት ከሞት በኋላ ደስ ታሰኛለችና!
የእኛ እምነት ግን እያደር እያደር ሲቀንስ ሲቀንስ ሲቀጭጭ ሲቀጭጭ ጭራሽ ከእምነት መስመር ወርደን ክህደት መስመር ውስጥ እንገኛለን፡፡ በእምነት መስመር ጉዞ ጀምረን ስንነቃ ክህደት መስመር ውስጥ ቆመን እንገኛለን፡፡ እምነታችን እያደር ይቀንሳል ይቀጭጫልም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን በውኃ ዘንድ እንደ የብስ እንድራመድ እዘዘኝ አለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ና አለው፡፡ ጴጥሮስ ውኃውን እንደየብስ እየረገጠ መጓዝ ጀመረ ነገር ግን እሰጥም ይሆን የሚል ጥርጥር በውስጡ መጣበት፡፡ ያኔ በዚያ ጥርጥሩ ምክንያት እንደየብስ ይጓዝበት የነበረው ውኃ የብስነቱን ትቶ የቀደመ የማስጠም ግብሩን ጀመረ፡፡ ያን ጊዜም ቅዱስ ጴጥሮስ በጥቂት በጥቂቱ እየሰጠመ አንገቱ ላይ ደረሰ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታ ሆይ አድነኝ አለ፡፡ አሁን እምነታችን ለምን ቀነሰብን ለምን ቀጨጨብን ብለን ራሳችንን መውቀስ የለብንም፡፡ ነገር ግን እንደቅዱስ ጴጥሮስ የእምነታችንን መቀነስ ማረጋገጥ እና ጌታ ሆይ አድነኝ ብለን ፈጣሪያችንን መጣራት ያስፈልገናል፡፡ እምነት ከአምላክ ስትሰጥ ትጸናለችና!
የእምነት መቀጨጭን ሀገራችንን ቀጥ አድርጎ የያዛትን የደመራ ጊዜ “ሸረኛን ያጥፋ ሟርተኛን ያጥፋ አራሽ ገበሬን እንዲህ ያቅና” ብለው የሚያወድሱትን አራሽ ገበሬ እንመልከተው፡፡ እኔ መቸም ሥራየ መታዘብ ብቻ ነው የሆነባችሁ አይደል፡፡ አይደለም እኔ በሁሉም አቅጣጫ እመለከተዋለሁ ደግነት ከክፉነት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ደግነት ባለበት ከፋት አይታጣም፡፡ ስለዚህ ፊቱን ስትመለከቱ ጀርባውንም መመልከት ግድ ይላችኋል፡፡ እኔም በጀርባው በኩል ስላለው የአባቶቻችን የአርሶ አደር ገበሬዎች ሥራ ከእምነት መቀጨጭ ጋራ አዛምደው ዘንድ ኅሊናየ አወጣብኝ አወረደብኝም እናም ይኸው ጻፍሁት፡፡
ገበሬ በመጀመሪያ ያለውን እምነቱን ይዞ እህሉ ጎተራ እስኪገባ ድረስ አይቆይም፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የግል ምልከታየ ስለሆነ ማንንም ለመናቅ ወይም ለማንቋሸሽ አልጻፍሁትም ለመማሪያ ይሆን ዘንድ እንጅ፡፡ ደግሞ እያንዳንዱ የአርሶ አደር ተግባር ወቅታዊ እና ትክክለኛ ተግባር እንደሆነ እረዳለሁ ነገር ግን ለጽሑፉ የግል ምልከታየን አሰፍራለሁ፡፡ ገበሬው አምላኩን ተማምኖ በእምነቱ ጸንቶ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ በነፋስ አሳድጎ ይመግበኛል ብሎ እህሉን ከጎተራ እያወጣ በባዶ ሜዳ ላይ ሲዘራው መመልከት እምነቱ ትልቅ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው፡፡ እህሉን ከጎተራ ዝቆ አውጥቶ ሜዳ ላይ ሲዘራው ፈጣሪውን በመተማመን ነው፡፡ ፈጣሪውም በዝናብ ያበቅልለታል በነፋስ ያሳድግለታል፡፡ ገበሬውም ያርማል ይኮተኩታል ብዙ ይደክምበታል ይጥርበታል ይግርበታል፡፡ እግዚአብሔርም የገበሬውን ድካም ተመልክቶ በፀሐይ ያበስልለታል አንዷን ቅንጣት መቶ ያደርግለታል፡፡ ገበሬውም የእህሉን ማፍራት ለመታጨድም መድረሱን አረጋግጦ ማጨድ ይጀምራል፡፡ አጭዶ ግን ዝም ብሎ ነስንሶ አይተወውም ምክንያቱም ነፋስ ይበትንበታል እንስሳት ይመገቡበታል፡፡ የእምነት መቀጨጭ ቁጥር አንድ እዚህ ጋር ይጀምራል፡፡ በእምነት የዘራውን እህል አሁን በመጠራጠር ይሰበስበዋል ወደ አንድ ቦታም ይከምረዋል፡፡ እስከዚህ ድረስ በእምነቱ ከመቀጨጭ ውጭ አንድኛውን እምነት አልባ አልሆነም፡፡ እስካሁን ድረስ ፈጣሪየ ይጠብቀው ብሎ ሁሉን ነገር ለፈጣሪ ሰጥቶአልና እህሉ በሜዳ ነው የሚገኘው፡፡ ከዚህ በኋላ እህሉ ወደ መውቂያ ቦታው ይሰበሰባል ከዚያም ፍሬውን ከገለባው ይለዩታል፡፡ ፍሬውን ከገለባው የሚለዩበት ነፋስ የፈጣሪ ነው እስካሁን በአምላኩ መተማመኑን አልዘነጋም፡፡ ፍሬውን ከገለባው ከለየ በኋላ ፍሬውን ወደ ጎተራው ያስገባል፡፡ ምክንያቱም ፍሬ ነውና በዚያ ላይ ደግሞ ብዙ ደክሞበታልና ጎተራ ውስጥ ያስቀምጠዋል፡፡ ፍሬውን አንድ ቀን እንኳ ከውጭ አያሳድረውም ምክንያቱም ሌባ ይወስድበታላ፡፡ የእምነት መቀጨጭ ቁጥር ሁለት ይኼኛው ነው እዚህ ደረጃ ላይ ጭራሽ እምነት የሚጠፋበት ጊዜ ነው፡፡ በእምነት ከጎተራው አውጥቶ ሜዳ ላይ የበተነው ገበሬ ገለባውን ከፍሬው ከለየ በኋላ ፍሬውን አንድ ቀንም ቢሆን ከውጭ አያሳድረውም ቢያሳድረው እንኳ እንቅልፍ በማጣት ሲጠብቅ የሚያድር ከሆነ ብቻ ነው፡፡ እምነት እንዲህ ነው እየመነመነ እየቀጨጨ የሚሄደው፡፡
በእምነትህ ለመጠቀም እምነትህን እያጠነከርህ ልትሄድ ይገባል፡፡ ክህደትን ከልቡናህ አውጥተህ ጣለው የእውነትም ጥላው፡፡ እምነትህን ግን በልቡናህ ውስጥ አጠንክረው፡፡ በእምነት የዘራኸውን በእምነት እጨደው፡፡ በእምነት የዘራኸውን በጥርጥር ለማጨድ አትሞክር፡፡ እምነትህ ዕለት ዕለት ይጠንክር በጾም በጸሎት ደግፈው፡፡ ፈጣሪህም እምነትህን እንዲያጸናልህ ተማጸነው፡፡ እምነትህ አንዲት ናት፡፡ ከፈጣሪህ ጋራ የምትገናኝባት እምነት አንዲት ብቻ ናት አዎ አንዲት ብቻ እርሷም አባቶቻችን ያስረከቡን ርትዕት ሃይማኖታችን ናት፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፡፡ ከመንገዷ አትውጣ ከመስመሯም አትለፍ ድንበሯንም አታፍርስ በእርሷ የዘላለም ሕይወትን ታገኛለህና፡፡
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

© መልካሙ በየነ
መስከረም ፳፬/ ፳፻፲ ዓ.ም
መርጡለ ማርያም፣ ኢትዮጵያ
✝✝✝✝✝
አንብባችሁ ከጨረሳችሁ አስተያየት #comment ስጡ
#share አድርጉ፡፡
✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝✝
— with Tesfaye Tadese, Alem Gebray, Mekdes Shuemet and 26 others.

No comments:

Post a Comment