Monday, June 29, 2015

መሞት ብርቅ አይደለም (ክፍል አራት)

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ስለ ሞት አይነቶች በተከታታይ ክፍሎች ተመልክተናል በዚህ ክፍል ደግሞ መሞት ብርቅ እንዳልሆነ እናያለን።

ብዙዎቻችን ኑሮ አልሰምርልን ሲል፣ ገንዘብ ሲጠፋብን፣ የምንወደው ሰው ሲከዳን፣ የምንወደው ሰው ሲሞትብን፣ የፈተና ውጤት አልመጣ ሲለን፣ ከስራ ስንባረር፣ ከሰው ስንጣላ ወዘተ ተስፋ እንቆርጣለን። ተስፋ መቁረጥም ብቻ አይደለም ለመሞት እንመኛለን። ሰይጣን ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ ራሳችንን በምን ልናጠፋ እንደምንችል የሞት መንገዶችን ያማርጠናል። ራስህን በመርዝ አጥፋ የሚል መንፈስ ሹክ ይልሃል። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ለምን ታንቀህ አትሞትም ይልሃል። ትምሽ ቆይቶ ደግሞ ለምን ኤሌክትሪክ ገመድ ጨብጠህ አንዴ አትገላገልም ይልሃል። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ሌላ መንፈስ ለምን ራስህን ወደ ገደል ወርውረህ አትገላገልም ይልሃል። ሌላው መንፈስ ደግሞ ይመጣል ለምን ራስህን ውኃ ውስጥ አጥልቀህ አትገድልም ይልሃል። ብቻ ተስፋ መቁረጥህን ያየ መንፈስ ሁሉ የምትሞትበትን ምርጫ በገፍ ያቀርብልሃል። ብልጥ መሆንን የሚጠይቀው ያን ጊዜ ነው። ሞኞች የሚሞቱት ሞት መነሻው ይህ ተስፋ የመቁረጥ ተስፋ የማጣት ሂደት ነው። ሰይጣን መንግሥተ ሰማያት ስትገባ ማየት አይወድም። ለዚህም ነው የሞት አማራጭ የሚያቀርብልህ። ተስፋ በማስቆረጥ በቁምህ እንድትሞት ካግባባህ በኋላ ራስህን እንድታጠፋ ይጋብዝሃል። ጫቱን በገፍ፣ሲጋራውን በገፍ፣ ዝሙቱን በገፍ ያቀርብልሃል። አንተ እጅህን ወደዚያ ከጨመርህ ያንጊዜ ወደ ሞት መስመር መግባትህን ልትዘነጋ አይገባውም። ሰይጣን የሞት አማራጭ ሲያቀርብልህ መሞት ብርቅ አይደለም መርዝ አልጠጣም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ራሴን አላንቅም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ራሴን ወደ ገደል አልወረውርም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ኤሌክትሪክ አልጨብጥም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ጫት አልቅምም፣ ሲጋራ አላጨስም፣ ዝሙት አልፈጽምም በለው፡፡ መሞት ብርቅ አይደለም ራሴን ውኃ ውስጥ አልገድልም በለው፡፡ ለእኔ ብርቄ መሞት አይደለም ለኔ ብርቄ በህይወት መኖር ነው በለው። ሞት ብርቅ አይደለም እኔ የምፈልገው ብርቅ የሆነውን እንጅ የረከሰውን አይደለም በለው። ወንድሜ ሆይ መሞት ብርቅ አይደለም። ዛሬ ራስህን ልትገድል እድሉ አለህ ነገር ግን ብርቅ አይደለም። ብርቁ ነገር ንስሐ መግባት ነው። ብርቁ ነገር ሥጋ ወደሙን መቀበል ነው። ብርቁ ነገር ከኃጢአት መራቅ ነው። ብርቁ ነገር በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ መሄድ ነው። ብርቁ ነገር ራስን መግደል ሳይሆን ራስን ማዳን ነው። ስለዚህ ሰይጣንን መሞት ብርቅ አይደለምና ለአንተ አንገዛም እንበለው። በቤተ ክርስቲያን ፊት ቆመን እንካደው። ርኩስ መንፈስ ሲገፋፋህ ቆም ብለን አስብ። 

Sunday, June 28, 2015

መሞት ብርቅ አይደለም (ክፍል ሦስት)

©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
በክፍል ሁለት ሁሉን አቀፍ ሞት እና የሞኞች ሞት በሚል ማብራሪያ መስጠታችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የሞኞች ሞት በራሱ በሁለት የሚከፈል በመሆኑ በዚህ ክፍል እነዚህን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡
          ሀ.የቁም ሞት
ሰው ነፍስና ሥጋው ሳይለይ የሚሞተው ሞት ነው፡፡ አንድ ሰው ከእግዚአብሔርተለይቶ የኃጢአትን መንገድ ተከትሎ የሚጓዝ ከሆነ በቁሙ ሞቷል ይባላል፡፡“እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” 1ኛ ቆሮ10፥12 እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሕይወት ያለው የሚመስለው ሁሉ ሕይወት ያለውአይምሰለው፡፡ መንቀሳቀስ ብቻውን በሕይት የመኖር መገለጫ አይደለም፡፡ ተንቀሳቃሽ የሆነ ነገር ግን በሥራ የሞተ ብዙ ነው፡፡ የቁም ሞትንየሞተ ሰው በሥጋ ከሞተ ሰው የሚለየው መንቀሳቀሱ፣ መናገሩ፣ መማር የሚችል በንስሓ ሊመለስ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ተለይቶ በረከሰ ሥራ በኃጢአት ተዘፍቆ ለሰይጣን ተገዝቶ መብላት፣ መጠጣት፣ መስከር፣ መደነስ፣ መዳራት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ መዋሸት ወዘተ… የዕለት ከዕለት ተግባሩ ያደረገ ሰው የሞተ ነው፡፡ ማስቀደስ ያቆመ ሰው፣ መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ፣ መመጽወት፣ የረሳ ሰው የሞተ ነው፡፡ንስሓ መግባት፣ መቁረብ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የተወ ሰው የሞተ ነው፡፡ አባትና እናቱን የማያከብር፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የማይጠብቅ፣ አምላክነቱንም የሚጠራጠር፣ቅዱሳንን አማላጆቼ ብሎ የማይቀበል፣ ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብሎ የማያምን ሰው የሞተ ነው፡፡ የልጅነት ጥምቀት ያልተጠመቀ፣ በአህዛባዊ ግብር የሚኖር በምንፍቅና ዕድሜ የሚቆጥር፣ በክህደት የሚኖር ሰው ሁሉ የሞተ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በንሥሓ በመመለስ እግዚአብሔርን አምነን በጽድቅ መመላለስ ከቻልን የሞኞችን ሞት ሳንሞት መኖር እንችላለን፡፡ ሞኞች ሲጋራ በማጤስ፣ ጫት በመቃም፣ ቡና በመጨለጥ ወዘተ… ሞተዋል፡፡እነዚህን በመተው ደግሞ ሕይወት የሚኖሩ አሉ፡፡ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ለሰው ልጆች ያለአድልዎ እኩልየሆነ ነገር ተሰጥቶናል፡፡ ይህን የተሰጠንን ነገር በአግባቡ የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ነው የሞኞችን ሞት የፈጠረው፡፡ ስለዚህ ብልጥ በመሆን ማለትም ኃጢአትን ባለመሥራት፣ በእግዚአብሔር ትእዛዛት በመመራት፣ በአባቶቻችን ሥርዓት በመጽናት፣ ንስሓ በመግባት፣ ሥጋን ለነፍስ በማስገዛት የቁምን ሞት ማምለጥ ይቻላል፡፡ ሞኝ ሆነህ ነፍስህን ረስተህ ለሥጋህ ብቻ የምትኖር ከሆነ ግን ሁሉም የሞት አይነቶች በተራ ማስተናገድህ አይቀርም፡፡
ለ. የነፍስ ሞት

አስፈሪው የሞት አይነት ይህ ነው፡፡ለሞኞች ይህ ሦስተኛ ሞት ነው፡፡ ይህ ሞት የዘላለም ሞት ነው፡፡ ሥጋ ወደ መቃብር ነፍስ ወደ ሲኦል በትንሣኤ ጊዜ ደግሞ ሥጋ ከመቃብር ተነሥቶ ነፍስ ከሲኦል መጥታ ከሥጋ ጋር ተዋሕዳ ወደ ገሐነም የሚገቡበት ለዘላለም ከዲያብሎስ ጋር የሚኖሩት ኑሮ የዘላለም ሞት /የነፍስ ሞት/ ይባላል፡፡የቁም ሞት የሞተ ሰው በንስሓ ካልተመለሰ የነፍስ ሞት ያገኘዋል፡፡ በዳግም ምጽአት ጊዜ በእንባ ብንታጠብ ንስሓ ብንገባ ማንም የሚቀበለን የለም፡፡“እናንተ ርጉማንለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ፡፡” ማቴ 25፥41የሚለው ዘላለማዊ ፍርድ ከተፈረደብን የትም ማምለጥ አንችልም፡፡ ወገኖቼ ይህን ሞት ፍሩ፡፡ የሥጋ ሞትማ ለሁሉም ነው፡፡ ደግሞም ከምድር የስቃይ ኑሮ የምንገላገልበት ትልቅ እረፍት ነው፡፡እረፍት የሚሆነው ግን እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለተጓዘ ነው፡፡የነፍስ ሞት ቆሻሻቸውን ላላስወገዱ ሞኞች የተሰራ ነው፡፡ በእድፍ /በኃጢአት/ እንደ ተጨማለቁ መንግሥተ ሰማያት መግባት አይቻልም፡፡ ስለሆነም የገሐነም ፍርድ ይፈረድበታል፡፡ በአጠቃላይ በቁሙ የሞተ ሰው ንስሓ እስካልገባ ድረስ የነፍስ ሞት አይቀርለትም፡፡ ሞኞች ሦስት ጊዜ ይሞታሉ ብልጦች ግን አንድ ጊዜ ብቻ፡፡ ስለዚህ በሞኝነት ከምንሞታቸው ሁለት ሞቶች ልንቆጠብ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የቁም ሞትና የነፍስ ሞት ራሳችን በራሳችን ላይ የምንወስናቸው ሞቶች ናቸው፡፡ የሥጋ ሞት ግን ሁሉን አቀፍ ሁሉን የሚጎበኝ ስለሆነ ፈቀድንም አልፈቀድንምአይቀርልንም፡፡ እኛ ልንቆጠብ የሚያስፈልገው ፈቅደን ከምናመጣቸው ሞቶች ነው፡፡

Saturday, June 27, 2015

መሞት ብርቅ አይደለም (ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ስለሞት ትርጉም አይተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ስለ ሞት አይነቶች ዝርዝር ማብራሪያ እንሰጣለን፡፡ መልካም ንባብ
1.    ሁሉን አቀፍ ሞት
ይህ የሞት አይነት ለፍጡራን ሁሉ እኩል የተሰጠ ነው፡፡ እንስሳት፣ ዕፅዋት፣ ሁሉም ይሞታሉ፡፡ የሰው ልጅም እንዲሁ ይሞታል፡፡ ይህን ሞት የሥጋ ሞት ብለን የምንጠራው ነው፡፡የነፍስ ከሥጋ መለየት ማለት ነው፡፡ ውሎ ውሎ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከሞት የሚባልለት ይህ ነው፡፡ ማንኛውም ፍጡር የሆነ ሁሉ የሚጎነጨው ጽዋእ ነው፡፡ እንኳን ፍጡራን አምላካችን ክርስቶስም ስለኃጢአታችንና በደላችን ለሞት ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡1ኛ ቆሮ15፥4አምላክ የሞተውን ሞት ሁሉም ፍጡር ይቀምሰው ዘንድ ግዴታ አለበት፡፡ አሁን በብሔረ ሕያዋን የሚኖሩ ቅዱሳን እነ ሄኖክ፣ እነ ዕዝራ፣ እነ ኤልያስወዘተ… በዓለም ፍጻሜ ስለክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትመስክረው በሰማዕትነት ያርፋሉ እንጅ ሞትን ሳይቀምሷት አይቀሩም፡፡ይህን ሞት ልንፈራውና ልንሸሸው አይገባም፡፡“ ሥጋንየሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ” ማቴ 10፥28እንዲል የሥጋን ሞት መፍራት አይገባም፡፡ ብንፈራውስ ብንሸሸውስ አይቀርልን ነገሩ ነው እንጅ፡፡ ደግሞም እኮ አላስተውል ብለን እንጅ ሁልጊዜ በትክሻችን ይዘነው የምንዞረው እርሱን ነው፡፡ ሰው ሥጋው ከነፍሱተለየ ማለት በስብሶ አፈር ትቢያ ሆኖ ይቀራል ማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ “ዋይ” እያለ ወደ ዓለም እንደመጣ “ዋይ” እያሉ ያሸኙታል፡፡ እንደገል ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው የገዙ ነገሥታት እንዲሁም በወርቅና በዕንቊ ያሸበረቁት ከመጋረጃ ወጥተው ታይተው የማይታወቁ ንግሥታት በአሸበረቀና በተዋበ በዕንቊበተጌጠ ባማረ ቤት ይኖሩ የነበሩት ባለጠጋዎች ዛሬ ከመቃብር በታች ሥጋቸው ፈርሶ አጥንታቸው በስብሶ ትንሣኤን ይጠባበቃል፡፡ሞት ሲመጣ አሜን ብሎ ተቀብሎ እንሂድ ሲል አብሮ መሔድ ነው ቀጠሮ የለውም ተዘጋጅቶ መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ሞት ሊያስጨንቀን የሚገባ አይደለም የሚያስጨንቀንና የሚያስፈራንስ ሞት የነፍስ ሞት ነው፡፡“ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሐነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፡፡” ማቴ10፥28ማለቱ ለዚህ ነው፡፡
2.   የሞኞች ሞት

ይህኛው የሞት አይነት ሁሉን የሚያቅፍ /ሁሉን አቀፍ/ አይደለም፡፡ ሞኞች ብቻ የሚሞቱት የሞት አይነት ነው፡፡ በውስጡ የቁም ሞትንና የነፍስ ሞትን ይይዛል፡፡ ዝርዝር መረጃውን በክፍል ሦስት ይጠብቁን፡፡
©መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

Friday, June 26, 2015

መሞት ብርቅ አይደለም (ክፍል አንድ)

© መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

የዚህን ትምህርት ዋና መልእክት የምንጀምረው በድርሳነ ሚካኤል ዘመስከረም ከቁጥር 23-27 ያለውን ስለሞት የተጻፈ መልእክት በማስቀደም ይሆናል፡፡ ጽሑፉ እንዲህ ይላል፡-“እንግዲህ በስንፍና ነፍሱን ያጠፋ ወዮለት ወዮታ አለበት፡፡ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ሣለ ይቅርታ ካላደረገ በጎ ሥራ ካልሠራ ምን ይጠቅመዋል? ምን ይረባዋል?የሚሞትበትን ቀን አያውቅም፡፡ገንዘቡም ከእርሱ ጋር አብሮት አይሔድም ነፍሱም ድንገት ተመንጥቃ ትለየውና መላእክት በሐፀ እሳት እየነደፉ በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በሰማያዊው ንጉሥ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሳ ራቁቷን ትቆማለች፡፡ ይህች ምድራዊት ዓለም ሳታዋርደን ሳታስንቀን በፊት እኛ እናዋርዳት እናሳጣት ከእርሷ ተፈጥረን ሁላችንም ወደ እርሷ ተመልሰን እንሔዳለንና አላፊ ጠፊ ስለሆነች የተናቀች ሰነፍ ናት፡፡ እንደ ተውሶ ልብስም ፈጥና ታረጃለች፡፡እንደ ጥላም ታልፋለች፡፡ በዚህ ዓለም የተደሰታችሁበት ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ቋሚነት የለውም፡፡ መግቢያችንና ማደሪያችን በዚያ ነውና እስከዘላለሙ ድረስ፡፡ ወንድሞቼ ሆይ ያች የመከራ ቀን ከመድረሷ አስቀድሞ ስለራሳችሁ አልቅሱ፡፡ ወዳጆቼ ሆያ እስኪ ልብ አድርጋችሁ አስተውሉ፡፡ የቀደሙ አባቶቻችን ነገሥታቱ መኳንንቱ መሳፍንቱ የተከበሩት ሽማግሌዎች ሕጻናትና ዋጋው ብዙ የሆነ ነጭ ሐር የለበሱ በወርቅና በብር ጌጥ የተሸቆጠቆጡ የሴት ወይዘሮዎች ሁሉ ወዴት አሉ?እናንተም እንደ እነርሱ ትሞታላችሁ የዚህን ዓለም ሀብትና ንብረት ትታችሁ ትሔዳላችሁ፡፡ ወዳጆቼ ሆይ አላፊ ጠፊ የሚሆን የዚህን ዓለም ሃብት ከመውደዳችሁ በስተቀር እስከዛሬ አላስተዋላችሁምና፡፡ ወንድሞቼ ሆይ እናንተስ ገሐነማዊ ፍርድ ያለበትን ሰማያዊ ሞት ፍሩ እንጅ የዚህን ዓለም ሞት አትፍሩ፡፡”ከዚህ እንደምንረዳው ሞት ንጉሥ አይል ሎሌ፣ ካሕን አይል ምእመን፣ መምህር አይል ተማሪ፣ አዋቂ አይል ሕጻን፣ ሃብታም አይል ድሃ፣ ሴት አይል ወንድ ለሁሉም እንደየተራውጊዜውን ጠብቆዕጣው ይወጣል፡፡ ሞትን ማን አመጣው ቢሉ የሰው ልጅ ነው፡፡ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፡፡” ሮሜ5፥12እንዳለ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ይህስ እንዴት ነው ቢሉ አዳም በገነት ላይ አዛዥ እና ገዥ ሆኖ በተፈጠረ ጊዜ ሦስት ዕፅዋት ነበሩ፡፡ እንዲበላው የታዘዘ፣ እንዳይበላው የታዘዘ እና እንዲበላውም እንዳይበላውም ያልታዘዘው ማለት ነው፡፡“ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህቀን የሞት ሞትን ትሞታለህ” ዘፍ2፥17እንዳለ፡፡ ይህችን አትብሉ የተባሏትን ዛፍ ሳይበሉቢጠብቋት ኖሮ ከሺህ ዘመን በኋላ ብላም አትብላም ተብሎ ያልታዘዘውን ዕፀ ሕይወት በልተው ታድሰው መንግሥተ ሰማያት ይገቡ ነበር፡፡ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ በሉ ሞትንም ወደ ዓለም አመጡ፡፡ዘፍ3፥6ለዚህም ነው ሞትን የሰው ልጅ አመጣው የምንል፡፡ ሞት በተለያየ መልኩ ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ እነዚህም፡-
1. ሁሉን አቀፍ ሞት
2. የሞኞች ሞት በማለት መክፈል ይቻላል፡፡
ለእያንዳንዳቸው የሞት አይነቶች ዝርዝር ማብራሪያ በክፍል ሁለት ይጠብቁን፡

Thursday, June 25, 2015

ቸርነቱን ለኃጢአት አትጠቀምበት

ወንድሜ ሆይ ኮልታፋ በሆነው አንደበቴ ላይ የአሮንን አንደበት ተክቼ ልመክርህ ነው፡፡ በእርግጥ ልመክርህ አይደለም ልንመካከር ልንማማር ነው እንጅ፡፡ አምላክ ለምን ፈጠረኝ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? አምላክ ሥነ ፍጥረትን በየወገኑ ሲፈጥር ምክንያት አለው፡፡ እንድንማርባቸው የተፈጠሩ አሉ፣ እንድንመገባቸው የተፈጠሩ አሉ፣ እንድንገለገልባቸው የተፈጠሩ አሉ፣ ፈጣሪን እንድናውቅበትም የተፈጠሩ አሉ፡፡ የምድር ጠቢባን ምንም ያህል ቢራቀቁ ካለው ነገር ነው እንጅ ከራሳቸው አንቅተው የሚፈጥሩት ነገር የለም፡፡ አምላክ ግን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ሥነ ፍጥረትን ፈጥሯል፡፡ ሰውን ግን አልቆ ፈጠረው ለምን ፈጠረው? እግዚአብሔር አንድነቱ ሶስትነቱን ሳይጠቀልለው፣ ሦስትነቱም አንድነቱን ሳይከፋፍለው የገዛ ባሕርይው ባሕርይውን እያመሰገነ ክብሩ በራሱ እንደቀረ ባየ ጊዜ ክብሩን የሚወርስ ስሙን የሚቀድስ ሰውና መላእክትን ፈጠረ፡፡ ፍጠረን ሳንለው ስለፈጠረንም ቸርነቱን አብዝቶልን በምሕረቱ ሁሌም ይጠብቀናል፡፡ እንደውም ለኃጢአታችን ከሳ ሆኖ በመስቀል ሞት ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ፍቅር ማለት እንዲህ ጠላትን አብዝቶ መውደድ ነው ብሎ ፍቅርን በተግባር ተረጎመልን፡፡ በደሙ ፈሳሽነትም 5 ሺ ከ 5 መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችውን ገነት ከፍቶ ነፍሳትን ከባርነት ቀንበር አሳርፎ በዚያ አኖራቸው፡፡ የአምላክ ትእግስት እና ቸርነት መጠን የለውም ስንበድለው ይክሰናል፣ ኃጢአት ስንሰራ ወዲያውኑ አይቀጣንም ነጻ ፈቃዳችንን ሊሽርብን አይሻም፡፡
የእኛ ችግር ምንድን ነው? ቸርነቱን ሲያበዛልን ጻድቅ የሆንን ይመስለናል፡፡ ትልቁ ውድቀታችን ያን ጊዜ ይጀምራል፡፡ ዛሬን በሰላም ውለህ ነገን በተስፋ የምትጠብቀው ቸርነቱ ስለጠበቀህ ነው፡፡ በልተህ የምትጠግብ፣ ጠጥተህ የምትረካ፣ ለብሰህ የምትደምቅ የአምላክ ቸርነቱ ስለጠበቀህ ነው፡፡ እንደ ዮሴፍ በስደት ሳለህ ሞገስ የሚሰጥህ ቸርነቱ ስለጠበቀህ ነው፡፡ ጸሎት የምታደርሰው እስከ ምሽት የምትጾመው ቸርነቱ ስላበረታህ ነው፡፡ እስከምትደክም የምትሰግደው፣ ያለህን ሁሉ የምትመጸውተው ቸርነቱ ስላበረታህ ነው፡፡ ያዘኑትን የምታረጋጋው፣ የደከሙትን የምታበረታው፣ የተጣሉትን የምታስታርቀው ቸርነቱ ስለበዛልህ ነው፡፡ የሰራኸው የሚባረክልህ ቸርነቱ ስለበዛልህ ነው፡፡ በኃጢአትህ ብዛት ዛሬ ያላጠፋህ ቸርነቱ ስለሚከለክለው ነው፡፡
ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል፡፡ እውነቱን ነው ሰነፍ የአምላኩን ቸርነት አይረዳም፡፡ እንዲያውም ትላልቅ ኃጢአትን እየሰራ አምላኩ ሲታገሰው “እውነት ፈጣሪ ካለ ለምን እኔን አላጠፋኝም?” ይላል፡፡ የአምላክ ትእግስትና ቸርነት እንደ ሰው ትእግስትና ቸርነት የሚመስለው ሰው አለ፡፡ ያ ሰው ኃጢአት በየጊዜው እየሰራ በሰላም ሲኖር እግዚአብሔር እንደሌለ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ እግዚአብሔርን እንደ ሰው ቆጥረነው ካልሆነ በቀር ስንበድለው ዝም ቢለን ትእግስቱንና ቸርነቱን እያደነቅን ልናመሰግነው እንጅ እንደሌለ ልንቆጥረው አይገባም፡፡ የትእግስቱ ብዛትማ ሲሰቅሉት ምንም አላላቸውም እኮ እንደውም ጎኑን የወጋው ለንጊኖስ አንድ ዓይና ነበርና ደሙ ነጥቦ ቢነካው ዓይኑ በርቶለታል፡፡ በእውነት በጦር የሚወጉትን ዓይን ማብራት እንዴት ያለ ቸርነት ነው ብለን ማድነቅ ሲገባን እግዚአብሔር ስለሌለ ነው ልንል አይገባም፡፡ የጠፋውን ዓይን ማን አበራለት ልንል ነው ታዲያ?

እግዚአብሔር እንዲህ በቸርነት ጥላው ከልሎ ዘመናትን ሲያሻግረን ልናመሰግነው ይገባል እንጅ ቸርነቱን ለኃጢአት ሥራ ልንጠቀምበት አይገባም፡፡ ትናንት ንስሐ ካልገባን ዛሬ ንስሐ እንድንገባ ነው ቸርነቱ የሚጠብቀን፡፡ ነገር ግን አምላክ የሰጠንን ቸርነት በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ፍዳው ለራሳችን ነው፡፡ ስለዚህ ቸርነቱን ለኃጢአት ሥራ ልናውለው አይገባንም፡፡ አምላካችን ቸርነቱን ዛሬም ይላክልን፡፡

Wednesday, June 24, 2015

የመጨረሻው ዘመን መጀመሪያ /ክፍል አራት/

በተከታታይ ሶስት ክፍሎች ስለመጨረሻው ዘመን የማቴወስ ወንጌል ምእራፍ 24 ን ከአንድምታ ትርጉሙ ጋር ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ በተከታታይ ያየናቸውን እናጠቃልላቸዋለን፡፡ ሰው ሁሉ ዛሬ እየተጨነቀ ያለበት በርካታ ጉዳይ አለ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ከዘመኑ መጨረሻነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ሥር ተሰግስገው ወተቷን የጠቧትን እናታቸውን ጡቷን የሚነክሱ ተሃድሶ መናፍቃን የዘመኑ መጨረሻነትን አርጅዎች ናቸው፡፡ ዛሬ በየ መንገዱ ኢየሱስን ተቀበሉ እያሉ ህዝቡን መከራ የሚያበሉ መናፍቃን መኖራቸው ዘመኑን ለመጨረሳችን አርጅዎች ናቸው፡፡ ዛሬ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ኢየሱስ ነኝ እያሉ የተነሡት በእኛም ሃገር ሳይቀር ድንግል ማርያም ነኝ ብላ የተነሣችው ዘመኑ ማለቁን አስረጅዎች ናቸው፡፡ ዛሬ እኮ ማታ በሰላም እደር ብለህ የሸኘኸውን ጓደኛ ነገ ሞተ ተብለህ እየገረመህ ልትቀብር የምትሄድበት ጊዜ ነው፡፡ መንግሥት በመንግሥት ላይ ህዝብም በሕዝብ ላይ ይነሣል የተባለውስ ቢሆን ስንቱ አገር ነው ዛሬ ድረስ የሰላም እንቅልፍ ያጣው? የአንዲት አገር መንግሥትም እንዲሁ በሌላው አገር መንግሥት ላይ እየተነሣ ያለበት ዘመን ነው፡፡ የሰው ልጅ ሞቱ እጅግ የበዛበት ነው፡፡ ድሮ ሕመም ብቻ ይገድለው የነበረው ሰው ዛሬ ባልታወቀ ነገር ሁሉ ሞቶ ይገኛል ሬሳው ወድቆ የአራዊት መጫዎቻ ይሆናል፡፡ ግፍ መከራ ስደት እንግልት ሆኗል፡፡ ዘመኑ ቀርቧልና ንስሐ ግቡ የሚለው የእውነት አዋጅ ዛሬ ላይ ሊታወጅ የሚገባው ነው፡፡ በእርግጥ ሁሌም ቢሆን ቤተክርስቲያናችን ይህንን ስታውጅ ኖራለች ዛሬም ታውጃለች ወደፊትም ዘመኑ እስከተፈጸመ ድረስ ታውጃለች፡፡ የአሁኑ ችግር የእኛው ነው፡፡ መስማት መስማት አሁንም መእማት በመስማት ብቻ ጆሯችን ሰባ ሥራ ግን ያው ባዶ፡፡ ቅዱስ ዳዊት አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ ማለቱ የድሮውን ልቤን አስወግደህ አዲስ ልብ እንደገና ፍጠርልኝ ማለቱ አይደለም ልቤን አስተዋይ ጥበበኛ ብልህ አዋቂ አድርግልኝ ሲል ነው፡፡ ስለዚህ ዘመኑ ቀርቧልና ንስሐ ልንገባ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ግን በሰው ልብ ዘንድ ሽብር  እና ጭንቀትን መፍጠር ማለት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን ግድ ነው ብሏል እኮ ታዲያ የቃሉ ባለቤት ይዋሸናል? በፍጹም ውሸት የለበትም አምላክ የተናገረውን አያስቀርም ሁሉም ጊዜውን ጠብቆ ይደርሳል፡፡ በርካታ መከራ ወደፊትም ይመጣል የግድም ይሆናል ያንን መከራ ግን እንዳንሰቀቅ እንዳንፈራ አምላካችን ብርታቱን እንዲሰጠን መለመን አለብን፡፡ ፎቅ በፎቅ ላይ ስንቆልል፣ ሃብት በሃብት ላይ ስንደርብ ባልታወቀ ሰዓት ባልተጠበቀ ቀን ሞት መጥቶ እንዳይጠራን እንጸልይ፡፡ አቤቱ በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ ብለህ ፈጣሪያችንን እንማጸነው፡፡ የዘመን እኩሌታ ማለት ንስሐ ሳንገባ ፍሬ ሳናፈራ ኃጢአት ስንሰራ ባለንበት ወቅት አትውሰደኝ ማለት ነው፡፡ ዕድሜ የሚሰጠን ለንስሐ ነው እድሜ ብቻ ስንቆጥር የምንውል ከሆነ ግን ችግር አለብን፡፡ እኔ ዛሬ የተወለድኩበትን ቀን ሰኔ 17 ን ለ27 ዓመት ያህል አከበርኩ በዚህ 27 ዓመት እድሜዬ ላይ እልፍ አእላፋት ጊዜ አምላኬን በድያለሁ ነገር ግን የእድሜዬን ያህል እንኳ 27 ጊዜ ማለት ነው ንስሐ አልገባሁም ታዲያ እድሜዬ ምን ፈየደልኝ፡፡ በዓለም ብዙ ዓመት የኖረ ሰው ተብዬ ሪከርድ አላስመዘግብ ነገር ማቱሳላ 969 ዓመት ኖሮ ሪከርዱን ይዞታል፡፡ ታዲያ ዛሬ ብሞት ነገ ብሞት ንስሐ ካልገባሁ ምኑ ያስፈራኛል? አመጣጣችን እዚህ መሬት ላይ ብዙ ዘመን ለመኖር ሳይሆን ባለን ዘመን ሁሉ የሚጠቅም የጽድቅ ሥራ እንድንሠራ ነው፡፡ ስለዚህ መከራውን ታግሰን ልንኖር ያስፈልጋል ዋጋችን የሚበዛው እሱን ማድረግ ስንችል ብቻ ነውና፡


Tuesday, June 23, 2015

የመጨረሻው ዘመን መጀመሪያ /ክፍል ሦስት/

በተከታታይ ሁለት ክፍሎች ውስጥ የዓለምን ፍጻሜ አስመልክተን በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24 ባለው መነሻነት የዓለም ፍጻሜ የምጥ መጀመሪያ ምልክቶችንና እነዚያን ምልክቶች ስንመለከት ምን አይነት ጥንቃቄ ልንወስድ ይገባናል የሚሉትን ዓበይት ነጥቦት ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ፍጻሜው ሊደርስ ጥቂት ሲቀረው ምን ይከሰታል የሚለውን እንመለከታለን፡፡
1ኛ. “ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል በዚያም ጊዜ መጨረሻው ይመጣል” ጌትነቱን የምትናገር ወንጌል በአራቱ ማእዘን ትነገራለች በእስላም ቤት ሳትቀር፡፡ ይህ የሚሆንበት ታሪክ አለው በአገራችን ቴዎድሮስ በአገራቸው ዮሐንስ የሚባል ይነግሣል የእኛም ሄዶ የእነርሱም መጥቶ በእስክንድርያ ሦስት ቀን ይዋጋሉ አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት የክርስቲያን ደም ለምን ይፈሳል፤ መሥዋእት ሰውተን በመሥዋእቱ ምልክት በታየለት ሃይማኖት ይጽና ይሏቸዋል ሁሉም በያሉበት መሥዋእት ያቀርባሉ፡፡ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በሰዋው “እኔ ክርስቶስ ነኝ” ብሎ በርግብ አምሳል ወርዶ ይመሰክራል ከዚህ በኋላ በሃይማኖት አንድ ይሆናሉ በግቢ ይገናናሉ፡፡ ገድለ ፊቅጦርና ራእየ ሲኖዳ እንደሚለው፡፡
2ኛ. “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ያልሆነ እንገዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል” በክፍል አንድ ከተመለከትናቸው መከራዎች ሁሉ የሚከፋው መከራ መቼም መቼ  ሊሆን የማይችል ከባድ መከራ ይሆናል፡፡ ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ የሌለ ወደፊትም የማይኖር ጸዋትወ መከራ አለ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቀኖች ክፉ እንደመሆናቸው ስለተመረጡት ሲባል ያጠሩ ባይሆኑ ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፡፡ ስለተመረጡት ሲል እግዚአብሔር ከቀኑ አራት ከሌሊቱ አራት በድምሩ ስምንት ሰዓታትን ያነሣለትና አንድ ሙሉ ቀን የሚባለው 16 ሰዓታት ብቻ ይሆናሉ፡፡

3ኛ. “መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምእራብ እንደሚታይ የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ይሆናልና” በበረሃ አለ ቢሏችሁ አትመኑ፣ በዚህ አለ በዚያ የለም ቢሏችሁ አትመኑ፣ ወዲህ ይመጣል ወዲያ ይሄዳል ቢሏችሁ አትመኑ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ መእራብ እንደሚታይ ሁሉ የእግዚአብሔርም አመጣጡ እንዲሁ ነው፡፡ ለአንዱ የሚታይ ለአንዱ የማይታይ ሆኖ ሳይሆን ለሁሉም የሚታይ ሆኖ ነውና ተጠበቁ ሀሰተኞችን አትመኑ፡፡

4ኛ. “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም ክዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ” ይህ ሁሉ መከራ ከተደረገ በኋላ ፀሐይ ያልፋል ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም ክዋክብትም ያልፋሉ ይወድቃሉ አድማስ ድንዑን ይለቃል፡፡ በዕለተ አርብ በሠሩት ኃጢአት እንደተፈረደባቸው ለማጠየቅ በእለተ አርብ የተደረገው ይደረጋል፡፡
5ኛ. “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል”  የተወጋ ጎኑ፣ የተቸነከረ እጁን ሳያጠፋ ለሁሉ እያሳየ ይመጣል፡፡ አባ ጳኩሚስ ሲሰግድ ወዙ ወርዶ መሬቱን ጭቃ አደረገው ወዲያውም ጌታ ተገለጠለት አንተን አገኝ ብየ እንዲህ እደክማለሁ አለው፡፡ ጌታም በዕለተ አርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ጎኑን እንደተወጋ ደሙን እንዳፈሰሰ ሆኖ ታይቶታል እንደዚሁም በመጨረሻው ዘመን እንዲህ ሆኖ በክብሩ ይታያል፡፡
6ኛ. “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ይህ ሁሉ መከራ ቢሆንም ቅሉ ቤተ አይሁድ አታልፍም እንደማታልፍ እነግራችኋለሁ፡፡
7ኛ. “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” እኔ እለፍ ያልሁት ያልፋል እኔ አትለፍ ያልሁት አያልፍም አንድም ህጌን የጠበቀ አያልፍም ህጌን ያልጠበቀ ግን ያልፋል

8ኛ. “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ፈጽሞ ይህን ሁሉ መከራ እና ስቃይ ታግሶ በሃይማኖትና በምግባር የተገኘ እርሱ ከሞት፣ ከፍዳ፣ ከመከራ ነፍስ ይድናል፡፡ እሰከ እለተ ሞቱ ድረስ መከራውን ታግሶ የጸና መከራውን ሳይሰቀቅ የተቀበለ ከፍዳ የሚድን እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናት ያስፈልጋል መከራ ሊያሰቅቀን አይገባም፡፡ 

Monday, June 22, 2015

የመጨረሻው ዘመን መጀመሪያ /ክፍል ሁለት/

የዓለምን ፍጻሜ ምልክቶች በክፍል አንድ ውስጥ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የምንመለከተው ዓለም ከማለፏ በፊት ልንወስደው የሚገባውን ጥንቃቄ ይሆናል፡፡ ማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24 ላይ ነን ዛሬም፡፡
1ኛ. “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል  የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል”  በቅዱስ ቦታ የሚቆም ማለት ለቤተመቅደስ አንባቢነት የሚሾም ያስተውል የተነገረውን ቤተመቅደስ በሚፈርስበት ጊዜ የሚሆን የጥጦስን ጣኦቱን ያያችሁ እንደሆነ ያንጊዜ ፍጻሜው ይመጣል ማለት የአይሁድ ጥፋት ይሆናል፡፡
2ኛ. “በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ” በሃይማኖት ያሉ ረድኤተ እግዚአብሔርን ጥግ ያድርጉ
3ኛ. “በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ” ነፍስ ያለውም ወደ ትህትና አይወርድም ሥጋዊ ሥራን ይሠራ ዘንድ
4ኛ. “በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ”የመነነም ዓለማዊ ሥራን ይሠራ ዘንድ ወደ ዓለም አይመለስ
5ኛ. “በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው” ይህ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ኃጢአትን በሐልዮ ፀንሰው በነቢብ ወልደው በገቢር ለሚያሳድጉ ሰዎች ወዮላቸው የሚል ማስጠንቀቂያ መከራ አለባቸውና፡፡ አንድም  ምእመናንን በትምህርት ጸንሰው በትምህርት ወልደው በትምህርት የሚያሳድጉ መምህራን ወዮላቸው መከራ ሥጋ አለባቸውና፡፡
6ኛ. “ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” ክረምት ላዩ ውኃ ታቹ ውኃ ነው አያሻግርም፤ ሰንበትም  እለተ እረፍት ነው መንገድ የሚያሳይ አይገኝም አንድም ሦስት ወር ክረምት ለማረፍ ዘጠኝ ወር በጋ የሚሰራ አለ አንድ ቀን ሰንበትንም ለማረፍ ስድስት ቀን የሚደክም አለ፡፡ አርፍባታለሁ ባለበት ስደት ሲመጣ ያሰቅቃል ተስፋ ያስቆርጣልና ነው፡፡ አንድም በሃይማኖት ብቻ ሳላችሁ ምግባር ሳትሠሩ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ ለምኑ፡፡  ክረምት ወርኃ ልምላሜ ነው ፍሬ የለውም ሰንበትም እለተ ጽርአት (እረፍት) ናትና በጽርአት  ሳላችሁ፡ በእረፍት ሥራ በማትሠሩበት ምግባር በማትፈጽሙበት ሲል ነው፡፡
7ኛ. “በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ ቢላችሁ አትመኑ” ክርስቶስ ከወዲህ አለ ከወዲያ የለም ከወዲህ ወዲያ ይሄዳል ወዲህ ይመጣል ቢሏችሁ አትመኑ እንዲህ አይሆንምና፡፡ በበረሃ ነው ቢሏችሁም በእልፍኝ ነው ቢሏችሁም አትመኑ፡፡
8ኛ. “ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠሏም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ እወቁ”  የጥጦስን በቅጠል፣ የሐሳዊ መሲሕን በአበባ፤ የምጽአትን በፍሬ መሰለው፡፡ አንድም እንደ ቅጠሉ ሐሳዊ መሲሕ ነግሦላቸው ቤተ አይሁድ ደስ ብሏቸዋልና፡፡ እንደ አበባው የምእመናን መከራቸው እንደ ፍሬው ሞታቸው፡፡ አንድም እንደ ፍሬው ሞታቸው እንደ አበባ ክብራቸው ፡፡ አንድም ቅጠል አይለወጥም እንደ አበባው የአይሁድ መከራቸው እንደ ፍሬው ሞታቸው፡፡ አንድም እንደ አበባው ሞታቸው እንደ ፍሬው ፍዳቸው፡፡
9ኛ.  “እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ” ከደጅ የቆመ ፈጥኖ እንዲገባ እንዲሁ የዓለም መፈጸምም ፈጥኖ እንዲሆን እወቁ

10ኛ. “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” በኖኅ ዘመን ጊዜ ዓለም  በጥፋት ውኃ ለመጥፋት 120 ዘመን ተሰጣቸው፡፡ እነርሱም አገቡ ተጋቡ፤ ወለዱ ተዋለዱ፤ በሉ ጠጡ ፤ጠገቡ ረኩ፤ ጨፈሩ ደለቁ ዳንኪራ ረገጡ፤ የእግዚአብሔር ፍርድ ቀን ቀድማ መጣች ዓለምም በንፍር ውኃ ጠፋች፡፡ አንድም የሚመጣበት ቀን ያለማሳወቁ ምስጢር ይህ ነው፡፡ ሰብአ ትካት 120 ዘመን ቢሰጣቸው መቶውን ጨፍረን 20ውን ንስሐ እንገባበታለን ብለው በድለዋልና፡፡  የጥፋት ውኃ መጥቶም ውኃው እስከ አንገታቸው ደርሶ ይዘፍኑ እንደነበር ሊጠፉ መሆናቸውን አላወቁም፡፡ ጌታ ግን የሚመጣበትን ቀን ሰወረ፡፡ ስለዚህም ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ ብሎ አስተማረን፡፡ ንስሐ ገብታችሁ፣ በንጽሕና ሆናችሁ፣ ሥጋና ደሙን ተቀብላችሁ፣ በፍቅር በትህትና ሆናችሁ ጠብቁ፡፡ ሌባ መቼ እንደሚመጣባችሁ እንደማታውቁ ሁሉ የእኔም አመጣጥ እንዲሁ ነው፡፡ ሌባ መቼ እንደሚመጣ ብታውቁ ያንን ሰዓት ነቅታችሁ ትጠብቁ ነበር ነገር ግን የሌባው መምጫ ስለማይታወቅ ሁል ጊዜ ነቅታችሁ ጠብቁ፡፡ አመጣጡ መምጣቱን በማታስቡበት ሰዓት ነውና፡፡

Friday, June 19, 2015

የመጨረሻው ዘመን መጀመሪያ /ክፍል አንድ/

ሴኮንድ አድጋ ደቂቃ ስታክል ደቂቃም ታድግና ሰዓትን ታክላለች፡፡ የሰዓትም እድገት እንዲሁ ይገዝፍና ቀንን መፍጠር ይጀምራል፡፡ ቀንም ብርሃንንና ጨለማን እያፈራረቀ ወራትን ይመሰርታል፤ ወራትም እንዲሁ ዓመታትን፤ ዓመታትም ዓመታትን እየፈጠሩ የማያልቅ የሚመስለን ዘመን ይቆጠራል፡፡ ዘመኑም ዘመኑን እየተካ ያልፋል፡፡እስኪ ዛሬ ላይ ቆመን ዓለም የተፈጠረችበትን ዘመን ወደ ኋላ ዞር ብለን እናስብ እዩትላችሁ ድፍን 7507 ዓመት ኖራለች፡፡ ዓመተዓለም ማለት እርሱ ነው እንግዲህ እኛ የምንፈራው ስምንት ሽህ ስንት ዓመት ቀረው ይሆን?
በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24 ላይ እንደምናነበው ሐዋርያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድን ነው? አሉት፡፡ ይህ ጥያቄ ዓለም የምትጠፋበት የመጨረሻው ዘመን መቼ እንደሆነ ለማዎቅ የሚረዳ ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የመለሰላቸው መልስ በትክክል ዓለም በዚህን ቀን፣ በዚህን ወር በዚህን ዓመት ትጠፋለች የሚል አይደለም የዓለምን መጨረሻ የመጀመሪያ ምእራፎች ነበር የነገራቸው፡፡ የዓለም መጨረሻ የመጀመሪያ ምእራፎች ምንድን ናቸው ብለን ስንመለከት የሚከተለውን መልስ እናገኛለን፡፡ “1ኛ. እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ 2ኛ. ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ 3ኛ. ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ 4ኛ. ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል 5ኛ. ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል ይገድሏችሁማል 6ኛ. ስለስሜ በአህዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ 7ኛ. እርስበእርሳቸው አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ 8ኛ. ብዙ ሃሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ 9ኛ. የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡
ከላይ የተመለከትናቸው 9 ዋና ዋና ነገሮች የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸው ተብለዋል፡፡ ይህም ማለት ዋናው ምጥ ከመምጣቱ አስቀድመው የምጡን መድረስ የሚያሳዩ ነገሮች ናቸው ማለት ነው፡፡ ምጡ የዓለም ፍጻሜ ሲሆን የዓለም ፍጻሜ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን እነዚህ ዘጠኝ ዓበይት ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ ይህም ሊሆን ግድ ነው ይለናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በመፈጸም ላይ ያሉ ወይም ደግሞ ወደፊት ሊፈጸሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሳይፈጸሙ ግን ዓለም አትጠፋም ምክንያቱም የዓለም ፍጻሜ መጀመሪያዎች እነዚህ ናቸውና፡፡ እነዚህ ምልክቶች እኮ በቃ ተፈጽመው አልፈዋል ወይም እየተፈጸሙ ናቸው ታዲያ ዓለም መቼ ትጠፋለች የሚለውን ቁርጥ ያለ ጊዜ ንገረን እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ ምክንያቱም ሐዋርያት ራሳቸው በደብረ ዘይት ተራራ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብለው ጠይቀውት ነበር ነገር ግን  መልስ አላገኙበትም፡፡ መልሱ ይህ ነው “ከበለስ ተማሩ ጫፍዋ ሲለመልም ቅጠሏም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታወቃላችሁ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ” ታዲያ አሁን ዓለም መቼ ትጠፋለች የሚል ጥያቄ ብትጠየቁ  በራሳችሁ መልስ ልትሰጡ የምትችሉት ነገር ቢኖር አሁን በደጅ ቀርቧል የሚል ብቻ ነው፡፡ ለምን? ካልን ደግሞ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ብሎናልና አምላካችን፡፡ ያች ቀን ያች ሰዓት የተባለችው የዓለም መጨረሻ የምትሆንባት ቀንና ሰዓት ናት፡፡ ያች ቀን ደግሞ ሥጋ ለባሽ ከሆነ ሁሉ የተሰወረች ናት፤ ከሥጋ ለባሽም ብቻ ሳይሆን ከሰማይ መላእክትም እንዲሁ ናት፡፡ በአምላክ ልብ ብቻ ታስባ ያለች ናት እንጅ፡፡ ሊቃውንቱ የዓለም መጨረሻ ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ፣ ወሩ ወርኀ መጋቢት፣ እለቱ እለተ ሰንበት (እሁድ)፣ ሰዓቱ መንፈቀ ሌሊት (ሌሊት ስድስት ሰዓት) ነው ቢሉም የትኛው ዘመነ ዮሐንስ፣ የትኛው መጋቢት ወር፣ ከመጋቢት ውስጥም የትኛዋ ሰንበት የትኛዋ መንፈቀ ሌሊት እንደሆነች ማንም አያውቃትም ከአምላክ በቀር፡፡

ለምን ቀኒቱንና ሰዓቲቱን ሰወረብን? እግዚአብሔር አምላክ የዓለምን ፍጻሜ ምጦች እንጅ ቀንና ሰዓቱን አልተናገረም፡፡ ምክንያቱም 1ኛ. ሰው በባህርዩ የሚኖረው ነገን ተስፋ አድርጎ ነው፡፡ ሞት እንዳለበት ያውቃል ነገር ግን የሚሞትበትን ቀን ስለማያውቅ በተስፋ ነገን እያቀደ ይኖራል፡፡ የዛሬን ፀሐይ እየሞቀ የነገን ፀሐይ ለመሞቅ ተስፋ ያደርጋል፡፡ የሞትህ ቀን ተነግራህ ቢሆን ኖሮ ነገን ተስፋ ማድረግ እንዴት ይቻልህ ነበር? አምላክ ለእኛ ምን ያህል እንደሚያስብልን አስተውሉ! ከሰዓታት በኋላ ልንሞት እንችላለን ነገር ግን እግዚአብሔር እንጅ እኛ አናውቅም፡፡ የዓለምም መጨረሻ እንዲሁ ቢነገረን ኖሮ ይህን ያህል ዓመት ቀረን እያልን ስናዝን እንውል እናድር ነበር፡፡ አዲስ ዘመን መለጫን አስቡት እንዴት እንደምንጓጓለት! ወር ቀረው፣ ሳምንት ቀረው 3 ቀን ቀረው እያልን የምንጠባበቀው መስከረም 1 ዘመን ስለሚለወጥ ነው፡፡ ይህ ቀን ደግሞ ለማንም ግልፅ ቀን ነው፡፡ ያንን ቀን የምንሞትበት ቀን እንደሆነ አድርጋችሁ ቁጠሩት ይህን ያህል ቀን ቀረችብኝ እያልን ሥራ ፈቶች ሆነን አልነበረም? ታዲያ አምላክ ውስጣችንን እያወቀ ዓለም በዚህን ወር፣ ቀን ፣ ዓመት ታልፋለች ብሎ እንዴት ይንገረን?

Tuesday, June 16, 2015

ንስሓ

ንስሓ ማለት መጸጸት፣ መቆርቆር፣ ኃጢአትን ስለሠሩ ማዘን፣ ማልቀስ፣ መቆጨት ነው፡፡ የበጎ ሥራ ጠላት ዲያብሎስ የሰው ልጅ መንግሥተ ሰማያትን እንዳይወርስ ክፉ መርዙን እየረጨ ከንስሓ መንገድ ያርቀናል፡፡ ኃጢአትን በኃጢአት ላይ ደርቦ ደራርቦ ያሠራህና ራስህን እንደ ሰው መቁጠር እስኪያቅትህ ድረስ ያስጨንቅሃል፡፡ ንስሓ ለመግባት ስትፈልግ “ይህን ያህል ኃጢአት እንዴት ነው ለንስሓ አባትህ የምትነግራቸው? የሚያሳፍር ኃጢአትም ሠርተሃል፡፡ ስለዚህ አሁን ተወውና ስታረጅ አንድ ጊዜ ትገላገላለህ” ይልሃል፡፡ የዕድሜ ዘመንህንም ረዘም አድርጎ ያሳይሃል፡፡ አንተም ትታለላለህ “ኃጢአቴን በሙሉ አንድ ጊዜ በሙሉ ልገላገለው” እያልህ ኃጢአትን ማጠራቀም ትጀምራለህ፡፡ እግዚአብሔር በሞት የሚጠራህ መቼ እንደሆነ ታውቃለህ? በፍጹም አታውቅም ጠላት ግን ሽህ ዘመን የምትኖር አስመስሎ ያሳይሃል፡፡ጠላት አሁንም ይቀርብና “የሠራኸው ኃጢአት በጣም ከባድ ነው፡፡ ለንስሓ አባትህ ከነገራካቸው በኋላ ለሌላ ሰው ቢነግሩብህሳ” ይልሃል፡፡ አንተ ግን አትስማው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው የማሰርና የመፍታት ስልጣን ለንስሓ አባቴም ተሰጥቷቸዋል በለው፡፡ /ማቴ 17፥19/ ዲያብሎስ ግን አሁንም ሌላ ወሬ ይጀምራል፡፡ “ንስሓ አባት ምናምን እያልክ ለምን ጊዜ ትፈጃለህ? ዝም ብለህ ወደ አምላክህ ቀርበህ ይቅር በለኝ ብትለው ይቅር ይልህ የለምን?” ይልሃል፡፡ አንተ ግን ምክሩን አትቀበል በኃጢአት ማሰሪያ እንደታሰርክ ወደ ክርስቶስ ብትቀርብ “ራስህን ለካህን አሳይ” ይልሃል እንጅ አይቀበልህም፡፡ “ክርስቶስ ወደ አንዲት መንደር ሲገባ በሩቁ የቆሙ አሥር ለምጻሞች ተገናኙት እነርሱም እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉ፡፡ አይቶም ሂዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው”፡፡ /ሉቃ17፥12-14/ ስለዚህ የንስሓ አባት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ልትረዳ ያስፈልጋል፡፡ ንስሓ ሳትገባ መንግሥተ ሰማያት መግባት አትችልም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” እያለ ይሰብክ የነበረው ለዚህ ነው፡፡ /ማቴ3፥1-2/ በንስሓ መመለስ ኃጢአትን ሁሉ እንዳይታስብ (እንዲሰረይ) ግዱፍ እነዲሆን ያደርጋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይላል “ሕመምተኞች እንጅ ባለጤናዎች ባለመድኃኒት አያስፈልጋቸውም ነገር ግን ሄዳችሁ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ተማሩ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ እንጅ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና” /ማቴ 9፥12-13/ ስለዚህ ንስሓ መግባት ተገቢ ነው ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ወደ ምድር የወረደ ኃጥአንን በንስሓ ለመጥራት እንጅ ለጻድቃን አይደለምና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የለበሰ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ አይደለም ኃጢአትን ላደረጉ ኃጥአን ነው እንጅ፡፡ ንስሓ ኃጢአተኛን ንጹሕና ጻድቅ የሚያደርግ ልዩ ምስጢር ነው፡፡ “በደላቸውን እምራቸዋለሁና ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ /ኤር31፥34/ ጠላት ያንተን ይቅር መባል አይወድምና ከዚህ ምሥጢር እንድትርቅለት በርካታ መሰናክሎችን ያስቀምጥብሃል፡፡ ኃጢአት ስትሠራ እነደ ማር ይጥምሃል፡፡ በኃጢአት ላይ ኃጢአት በበደል ላይ በደል ትደራርባለህ፡፡ የኃጢአት ካባ ሙቀት ይሆንሃል፤ የጽድቅ ሥራ ይቀዘቅዝሃል፡፡ ከዚህም የተነሣ ኃጢአት ባሪያው ያደርግሃል አንተም ትሆንለታለህ፡፡ የታሰርክበትን ሰንሰለት ለመፍታት ስታስብ እንቅልፍህ ይመጣል፡፡ ዕድሜህ እንደዋዛ በከንቱ ትሮጣለች፡፡ እንደ ኖኅ ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔር ቁጣ ሳታስበው መጥቶ ንፍር ውኃ ቢዘንብብህ የት ትገባለህ? /ዘፍ6 እና ዘፍ 7 በሙሉ ተመልከት/ የሞትህ ቀን መቼ እንደሆነ አታውቅምና ንስሓ ገብተህ ተዘጋጅተህ መኖር ተገቢ ነው፡፡ ሙሽራው ሲመጣ ዘይት ፍለጋ ልትሄድ አይገባም ዘይትህን ከመብራት ጋር ይዘህ መጠበቅ እንጅ፡፡/ማቴ25፥1-ፍጻ/ የጠላትን ምክር አትቀበል እርሱ ጥሩ ምክር አይመክርህምና፡፡ እናታችን ሔዋን የጠላትን ምክር በመቀበሏ ስትጎዳ እንጅ ስትጠቀም አላየናትም፡፡ ስለዚህ ለጠላት ጆሮ ሰጥተህ አትስማው፡፡ንስሓ አትግባ እያለ የሚያስጨንቅህ ወደ ዘላለም ቅጣት ሊጥልህ እንጅ የዘላለም ሕይወትን እንድታገኝ አይደለም፡፡ የቀደመው እባብ አሁንም ንስሓ አይጠቅምም እያለ የሚጨቀጭቅህ ከሆነ የጥጦስን (ፈያታዊ ዘየማን) ታሪክ ዘርዝረህ ንገረው፡፡ ጥጦስ ቀማኛ ሽፍታ ወንበዴ ነበር፡፡ በዕለተ አርብ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ በኩል ተሰቀለ፡፡ ሰባቱን ተአምራት በዓይኑ ተመለከተ፡፡ የተሰቀለው ክርስቶስ አምላክ እንደሆነም አመነና “ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” የሚል ታላቅ ልመና ለመነ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በንስሓ ተቀበለውና “እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ” አለው፡፡ ይህ ወንበዴም አዳምን ተቀድሞ በክርስቶስ ደመ ማኅተም ለ5500 ዘመናት ያህል ተዘግታ የነበረችን ገነት ከፍቶ ገባ፡፡ /ሉቃ 23፥39-43/ ስለዚህ ንስሓ ቆሻሻን ሁሉ እንዲህ የሚያጠራ ሳሙና ነው እታጠብበታለሁ በለው፡፡ የኅሊናን ሸክም የሚያራግፍ ኃጢአትን ሁሉ የሚደመስስ ልዩ መድኃኒት ነውና በየሰዓቱ ውሰደው ንስሓን፡፡

Saturday, June 13, 2015

የሞተውን ለመቅበር ያልሞተውን መግደል

አንድ ቀን ሂድ ሂድ የሚል መንፈስ ያዘኝና መጓዝ በለመደው እግሬ እከንፍ ጀመር፡፡ በእርግጥ ክንፍ እንደሌለኝ አምናለሁ ነገር ግን በላይ በሰማይ ከሚበርሩት አእዋፋት እኩል የምበር ይመስለኛል፡፡ ዳሩ ግን አርሱ ፈጣሪ ቢያውቀው እንጅ ማን ሊያውቅ ይችላል? እኔም በመንፈሴ አይደለሁምና፡፡ ነገር ግን ከሰውነቴ አልወጣሁም፡፡ ለዚያም ነው አንድ ሽማግሌ በምሬት ሲናገሩት የነበረውን ምርር የሚል ንግግር የሰማሁ፡፡ ምሬቱ ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለእኔም ነበር፡፡
ሽማግሌው ሌሊት የሰሙት የእድር ጥሩንባ የቀሰቀሳቸው ይመስላሉ፡፡ “እንቅልፍ አጣን እኮ እናንተ! ቀን ከሌሊት ጥሩንባ ብቻ፡፡ የእድር ጥሩንባ ነፊዎች እገሌ ሞተ ለማለት ጥሩንባ፣የቀበሌ ልማት ቡድኖች  እርከን ሥራ ውጡ ለማለት ጥሩንባ፤ ቀበሌ ስብሰባ አለ ለማለት ጥሩንባ፤ ምርጫ ለመምረጥ ጥሩንባ፤ ሰላማዊ ሰልፍ ውጡ ለማለት ጥሩንባ፣ መኪናዎች መንገድ ልቀቁልኝ ለማለት ጥሩንባ፣አምቡላንሶች  በሽተኛ ይዣለሁ ለማለት ጥሩንባ፣ ጋዜጠኞች ልማቱን ለማብሠር ጥሩንባ ብቻ ሁሉም ጥሩንባ ሆነብን እኮ፡፡ አረ መቼ ነው ከዚህ ድምጽ ጆሮዬ ነጻ የሚሆነው? እስከመቼ ድረስ ነው እንድንሰማቸው ብቻ የሚፈልጉትን ሁሉ የምንሰማቸው?” አሉ፡፡ ሽማግሌው  በሁሉ ነገር በጣም የተበሳጩ ይመስላሉ፡፡ እሳቸው ሲናገሩ ስሰማ እኔም  ውስጤ ትንሽ ተሰማው፡፡ እርግጥ ነው መናገረን ይናገሩ ግን ግድ ስሙኝ የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ አይገባም አልኩ በውስጤ፡፡ እሳቸው ግን በነጩ እንደያዘው የሃምሌ ዝናብ በቀላሉ ከምሬታቸው የሚያባሩ አይመስሉም፡፡ ቀጠሉ “የትናንትናን ታሪክ ደፍጣጭ ምኑ ይደመጣል? የበሬ ወለደን ንግግር ማን ይሰማል? ዜና እና የጉዞ ማስታወሻ የተቀላቀለበትን ጋዜጠኛ ማን ይሰማል? አሉባልታ አይሉት ምክር፣ ማስጠንቀቂያ አይሉት ማስፈራሪያ፣ መግለጫ አይሉት ማላገጫ የመሰለውን ትርኪምርኪ ማን ያዳምጣል? ያለፈውን ታሪክ ለመቅበር የዛሬውን ታሪክ የሚገለውን ማን ይከተላል? በሽተኛውን ለማዳን ሲል ያልታመመውን የሚያሳምም ሃኪምን ማን ይቀርበዋል? ዘንዶ የሚወጣበትን ጉድጓድ ዓሣ ይኖርበታል ብሎ ማን እጁን ይሰዳል?” አሉ ሽማግሌው፡፡ ውስጤ ነደደ ተንቦገቦገ፡፡ ግን የትኛው እስር ቤት ሊገቡ ፈልገው ነው እንዲህ ዘራፍ የሚሉት? ስል አሰብኩ፡፡ እስር ቤቶች እንደ አሸን በዝተው እንደተራበ አንበሳ አፋቸውን ከፍተው ሊውጡ በተዘጋጁበት ወቅት እንዲህ አይነት ንግግር  የምሬታቸው ደረጃ ራሳቸውን እንዳሳታቸው ማሳያ መሰለኝ፡፡

ሽማግሌው በዚህ አላበቁም “በዚያ በቀደምለት ማናቸው አያ! እኒያ ትልቁ ባለሥልጣን የሞቱ ጊዜ ትልልቅ የተባሉት የጦር መሪዎች አስከሬናቸውን ይዘው ወደ መቃብር ሊያውርዷቸው ሲሉ የአገራችን ሰው በሕይወት ሳሉ በቴሌቪዥን እንጅ በአካል አይተዋቸው ስለማያውቁ ቢያንስ ሬሳቸው ያለበትን ሳጥን እንመልከት ብለው ሲጠጉ በፖሊሶች ዱላ እንደ እባብ ራስ ራሳቸውን ተቀጠቀጡ፡፡ በሕይወት ሳሉስ ጠባቂ የተመደበላቸው ለህዝብ ቅን ስለማያስቡ ሰው ይገለኛል ብለው ፈርተው ወይም ሰግተው ሊሆን ይችላል፡፡ ለህዝብ የሚያስቡ ከሆነ ማንን ፈርተው ነው ታዲያ ጠባቂ የሚያቆሙት? እሽ እሱስ ይቅር ከሞቱ በኋላ ሬሳቸውን የሚሰርቅ ሰው አለ እንዴ ያን ያህል በግድ ሃዘን እንዲወጣ የተቀሰቀሰውን ሰው በዱላ የሚቀጠቅጡት? የሞተውን ለመቅበር ያልሞቱትን መግደል ምን አይነት ግፍ ነው? የሞተው እኮ ከዚህ በኋላ አገሪቱን ላይመራ አንዴ የተሰናበተ ነው? ሊቀብሩ የመጡት ግን እድል አላቸው እድሉን ማን ይሰጣቸዋል እንጅ? ታዲያ በቁሙ ባናየው ቢያንስ ከሞተ በኋላ አስከሬኑን እንመልከት ያለውን ህዝብ በዱላ! የሞተውን ማን ይገለዋልና ነው ግን እንዲህ የተደረገው?” አሉ፡፡  እኔ አሁን ዋና መልእክታቸው ገባኝ እውነታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ገንዘብ ሞልቶት ሁሉ ኖሮት የዓለም ቁጥር አንድ ባለሃብት ለመባል ሲል የስንቱን ምስኪን ኪስ ይዳስሳል መሰላችሁ፡፡ ሰው የሚበላው ሞልቶት ሁሉ ተርፎት የዳቦ ሽራፊ የቀረችውን ደሃ ተካፍሎ ሊበላበት ሲጠጋ አይገርምም ትላላችሁ? የድሮ ታሪክን ለማጥፋት ሲባል ስንት የዛሬ ታሪክ ተጨፈለቀ መሰላችሁ? በሽተኛውን ለማዳን ሲሉ ስንቱን ጤነኞች በሽተኞች አደረጉ መሰላችሁ? የምትለውን ሳይሆን የሚሉትን ብቻ እንድትሰማቸው በየቀኑ ስብሰባ የሚጠሩህ ስንት ናቸው? አረ ተውት ስንቱ ስንቱ ስንቱ ጉድ ይነገራል?????? ናርምም አለ ሊቁ ነገሩ ቢረቅበት፡፡

Thursday, June 4, 2015

የማታውቀውን አትንካ

ሊቃውንቱ የሰውን ልጅ በዐራት ወገን ይከፍሉታል፡፡ ማወቁን የሚያውቅ፣ ማውቁን የማያውቅ፣ አለማወቁን የሚያውቅ፣ አለማወቁም የማያውቅ በማለት፡፡ በእነዚህ ዐራት ሰዎች ዙሪያ ጥቂት ነገር እንነጋገር፡፡
ማወቁን የሚያውቅ፡- እንደዚህ ዓይነቱ ሰው አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ ከመሆኑም ባለፈ አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ መሆኑን በሚገባ የሚያውቅ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ሰው መሥራትን ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚሰራ፣ ለምን እንደሚሰራ፣ መቼ እንደሚሰራ፣ ለማን እንደሚሰራ በሚገባ ያውቃል፡፡ ሁሉን ከማወቁ የተነሣም ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና የሚኖር ዓይነት ነው፡፡ የሚገጥመውን ፈተና ለማለፍ ብዙ አይቸገርም፣ የሚመጣበትን መከራ አይሰቀቅም፣ የሚደርስበትን ችግር ሁሉ ከችግር አይቆጥርም ምክንያቱም ማወቁን ስለሚያውቅ፡፡ እውቀቱ ዋጋ እንዳለው ከራሱ የሕይወት ውጣ ውረድ ጋርም እንዴት ማዛመድ እንደሚችል በሚገባ ያውቃል፡፡ አዲስ የስልጣኔ ማዕበል አያናጋውም፤ አዲስ አስተሳሰብ አይነጥቀውም፣ አዲስ ትምህርት አያታልለውም፣ አዲስ አለባበስ አያስደነግጠውም፣ አዲስ ርዕዮተ ዓለም አይደንቀውም፣ አዲስ ነገር አያሳስበውም፣ በሚነፍስበት አይነፍስም፣ ሌላው በሚነዳበት ሁሉ አይነዳም፣ ሌላው ስላደረገ ብቻ አያደርግም ምክንያቱም ማወቁን ስለሚያውቅ፡፡ ከሥራ በፊት ለምን? የሚለውን ይመልሳል፤ ከመስራቱ በፊት ከሥራው ምን እንደሚጠብቅ ውጤቱን ቀድሞ ይተነብያል፡፡ ይህ ዓይነቱን ሰው ብንቀርበው ያስተምረናል፤ መጽሓፋችን ይሆናል፤ ጉድፋችንንም የምንመለከትበት መስታወት ይሆነናል፡፡
ማወቁን የማያውቅ፡- እንደዚህ ዓይነቱ ሰው አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ ይሁን እንጅ እንደዚህ መሆኑን አያውቅም፡፡ በመሆኑም ከእርሱ ማወቅ ይልቅ የሌሎች እውቀት ይገዛዋል፤ እንሂድ ባሉት መንገድ ሁሉ ይሄዳል፤ በነፈሰበት ሁሉ ይነፍሳል፤ ሌሎች በተጓዙበት ተከትሎ ይጓዛል፤ ሌሎች በፈሰሱበት ይፈስሳል፡፡ ሥራን የመሥራት ችሎታ አለው ነገር ግን ለምን እንደሚሰራ፣ የሥራው ውጤትም ምን ሊሆን እንደሚችል አያውቅም፡፡ እንደዚህ አይነቱን ሰው ብትቀርበው የእውቀቱን ፍሬ ልትመገብ አትችልም ምክንያቱም ማወቁን ስለማያውቅ ለአንተ ለማሳወቅ የሚችልበትን ጥበብ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ይህንን ሰው መቅረብ ጊዜን ከማባከን ውጭ ምንም ሊጠቅመን የሚችል አይደለም፡፡ ከእርሱ ለመማር ከምትቀርብ ይልቅ ማወቁን ብትነግረው ይበልጥ ተጠቃሚ ታደርገዋለህ፡፡ ይህ ሰው የሚጎድለው እውቀት ሳይሆን እውቀቱን እንዴት በተግባር መቀየር መቻል ብቻ ነው፡፡ አንተ ከጀመርክለት ፈሩን ካስያዝከው እርሱ በሚደንቅና በሚገርም ጥበብ ይፈጽመዋል፡፡ ስለዚህ በምክር እውቀቱን እንዲጠቀምበት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
አለማወቁን የሚያውቅ፡- እንደዚህ አይነቱ ሰው አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ አይደለም፡፡ አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ አለመሆኑን በሚገባ የተረዳ ነው፡፡ ሥራ መሥራት ይፈልጋል ነገር ግን እንደማያውቅ ስለሚያውቅ አይሰራም፡፡ ምክንያቱም ቢሰራም የስራው ውጤት ጥሩ እንደማይሆን በሚገባ የሚያውቅ ነው፡፡ ይህ ሰው ስራ ከመስራቱ በፊት ሌሎችን ያማክራል ምክንያቱም አለማወቁን ስለሚያውቅ፡፡ ይህ ሰው ተመራማሪ ነው እንደመጀመሪያው ያለ ሰው ነው ልዩነቱ እውቀት ብቻ ነው፡፡ ሌሎች በነፈሱበት አይነፍስም፣ ሌሎች በተጓዙበት አይጓዝም ምክያቱም አለማወቁን ስለሚያውቅ ከብዙ ሰዎች ጋር መመካከርን ይመርጣል፡፡ የተቀበለውን በርካታ ምክር አመዛዝኖ የራሱን ውሳኔ መስጠት የሚችልበት ችሎታ አለው፡፡ ይህ ሰው ለሌሎች መትረፍ የሚችል እውቀት አይኑረው እንጅ ራሱን የሚጥል አይነት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አለማወቁን ስለሚያውቅ አለማወቁን ተጠቅመው ሊጥሉት የሚመጡትን ሁሉ ከሌሎች ጋር በመመካከር ይፈታልና፡፡ ይህ ሰው ሌሎችን ሳያማክር የሚነካው ነገር አይኖርም፡፡ ይህ ሰው ቅንነት፣ ትህትና አለው ስለዚህ በማስተማር አዋቂ ማድረግ የሚቻል ነው፡፡
አለማወቁን የማያውቅ፡-እንደዚህ አይነቱ ሰው አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ አይደለም፡፡ አዋቂ፣ ብልህ፣ አስተዋይ፣ ጠቢብ አለመሆኑንም አያውቅም፡፡ ይህ ሰው ለራሱም ሆነ ለሌላ ሰው በሚተርፍ ችግር ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ያየውን ሁሉ ማድረግ ይፈልጋል ነገር ግን ካደረገው በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት አያውቅም፡፡ ሰው ሲሮጥ ካየ ይሮጣል ለምን እንደሚሮጥ ግን አያውቅም፤ ሰው ሲዘል ካየ ይዘላል ለምን እንደሚዘል ግን አያውቅም፤ ሰው ሲሄድ ካየ ይሔዳል የት ሊደርስ እንደሚችል ግን አያውቅም፡፡ እንደዚህ አይነቱ ሰው ድክመቱን በምላሱ መሸፈን ይፈልጋል፤ እንደዚህ አይነቱ ሰው ግብዝነቱ ይጎላል፤ እንደዚህ አይነቱ ሰው ለሌሎች መሰናክል የሚሆን ነው፡፡ ይህንን ሰው ብትከተሉት መጨረሻቹህ ገደል መግባት ነው፡፡ ምክንያቱም ገደሉንም ሆነ ገደሉን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል የሚያውቅ ስላልሆነ፡፡ ስለዚህ አትከተለው፡፡
አሁን አሁን በ FACEBOOK አጠቃቀም ላይ የአንዳንድ ሰዎች ሥራ የዚህ የሁለተኛው ሰው አይነት ነው፡፡ ታግ (TAG) ማድረግ ያውቃሉ ምን ታግ እንዳደረጉ፣ በማን ታግ እንዳደረጉ፣ ለምን ታግ እንዳደረጉ፣ መቼ ታግ እንዳደረጉ ግን አያውቁም፡፡ ሼር (SHARE) ማድረግ ይችላሉ (ያውቃሉ) ነገር ግን ምን፣ ለማን፣ መቼ፣ እንዴት ሼር እንዳደረጉ ግን አያውቁም፡፡ ለዚህ ነው የዝሙት ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን በሌሎች PROFILE ላይ ሲፈልጉ ሼር ሲፈልጉ ደግሞ ታግ የሚያደርጉት፡፡ ሼር እና ታግ ማድረግ ብቻውን ማዎቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ለማን ሼር ማድረግ እንዳለብን፣ ለማን ምን ሼር ማድረግ እንዳለብን፣ ለምን ሼር ማድረግ እንዳስፈለገም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የግድ ሼር ማድረግ አለብኝ ያለ ሰው ግን አዋቂ የሚባለው ለራሱ ብቻ ሼር ማድረግ ከቻለ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ማወቁን የማያውቅ ሰው ነው እንዲህ አይነቱን ተግባር የሚፈጽመው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ግን በእኔ PRIFILE ላይ ሼር የሚደረጉ የዝሙት ፎቶዎችና ቪዲዮዎች የእኔ እንዳልሆኑ እያሳወቅሁ ሼር የተደረጉብኝን ነገሮች ግን ወዲያውኑ የማጠፋቸው መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ተግባር ላይ የተሰማራችሁ ግለሰቦች ግን ከዚህ ተግባራችሁ ተቆጠቡ፡፡ በብዛት ሼር ያደረጋችሁብኝ ልጆች ለምን እንዳደረጋችሁ፣ መቼ እንዳደረጋችሁ፣ ለማን እንዳደረጋችሁ እንዳደረጋችሁ ራሱ የማታውቁ እንደሆነ በግል ተረድቼያለሁ፡፡ ስለዚህም የመጨረሻ መልእክቴ “የማታውቀውን አትነካካ” የሚል ነው፡፡


Wednesday, June 3, 2015

ይከራያል

በትንሽ ከተማ በኪራይ ቤት የሚኖር አንድ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው የተከራየው ትልቅ መኖሪያ ቤት ነው፡፡ በዚህ ቤት ባለቤቱን፣ ልጆቹን፣ ከብቶቹን ይዞ ነበር የሚኖረው፡፡ ሰው ግን እጅግ አብዝቶ ያስመርረዋል፡፡ ሰውየው ማንበብና መጻፍ አይችልም፡፡ ማንበብ እና መጻፍ አለመቻሉ ነው ለዚህ ሁሉ ስቃይ የዳረገው፡፡ ኪራይ የሚፈልግ ሰው ሁሉ የተከራየውን ቤት እያንኳኳ “ስንት ነው የሚከራየው” ይለዋል፡፡ ሰውየው ይህንን ጥያቄ እጅግ በጣም ሰልችቶታል፡፡ ነጋ ጠባ ሰው ሁሉ እያንኳኳ “ስንት ነው ኪራዩ” ይለዋል፡፡ እርሱም በጣም ሰለቸና አንድ ቀን “እንዴ ሰው ሁሉ ምን ነካው? እኔ  ተከራይቼ እያያችሁ እንዴት አይነት ጥያቄ ነው የምትጠይቁኝ? ቤቱ እኮ የእኔ አይደለም የተከራየሁት እንጅ፡፡ ቆዩ ግን ለምንድን ነው እንዲህ በላየ ላይ ኪራይ ምናምን የምትሉት? ሰው እንደው ትንሽ ይሉኝታ የሚባል ነገር የለውም ልበል ሆ ወይ ጉድ ነገር፡፡ ግሩም እኮ ነው የእናንተ ደግሞ! እሽ ግን ይከራያል ብላችሁ ልትደረቡብኝ ነው እንዴ?” አለ በቁጣ ገንፍሎ፡፡ ሰውየው ቤቱን ሲከራይ አብሮ የተከራየውን ጽሑፍ አላወቀም፡፡ አላፊ አግዳሚው ግን ያንን ጽሑፍ እየተመለከተ ነበር “ኪራይ ስንት ነው?” የሚለው፡፡ከቤት በር ላይ የቤቱ ባለቤት ቤቱ ከመከራየቱ በፊት “ይከራያል” ብሎ በቆርቆሮ ቀለም በጉልህ ጽፎበት ነበር፡፡ ሰውየው ይህንን ቤት ሲከራይ ይህንን ጽሑፍ አላነበበውም ምክንያቱም ማንበብ ስለማይችል፤ የቤቱ ባለቤትም ቤቱ ከተከራየ በኋላ የተጻፈውን አላጠፋውም፡፡ ለዚህ ነው ሰው ሁሉ ቤቱን እያንኳኳ “ስንት ነው ኪራይ” በማለት ሰውየውን ልቡን ያወለቀው፡፡ ቤቱን ከነጽሑፉ ስለተከራየው ይህ ሰው በጣም ተቸገረ፡፡

ዛሬ ዛሬ ከዚህ ሰው በከፋ ችግር ውስጥ ያለን በርካታ ሰዎች አለን፡፡ ከግለሰብ እስከ ቡድን፣ ከነጠላ እስከ  ማኅበራት፣ከተማሪ እሰከ አስተማሪ፣  ከቀበሌ እስከ ፌዴራል፣ ከክልል እስከ አገር ድረስ ሳናውቅ በምንከራያቸው ነገሮች በጣም ስቃይ ጸንቶብናል፡፡ አንድ ሰው ባለማዎቅ ከልብሱ ጋር በሚገዛው ጽሑፍ ይሸማቀቃል፡፡ አንዲት እርጉዝ ሴት “I AM VIRGIN” የሚል ልብስ ለብሳ ስትሄድ ሰው ቢስቅባት ሳቁን ከማስተናገድ ውጭ የለበሰችው ልብስ ላይ የተጻፈውን ነገር አትረዳውም፡፡ አንዱ ደግሞ ያገኘው ሰው ሁሉ ባገኘው ነገር ይመታዋል፡፡ ለምን እንደሚመቱት ግን አያውቅም፡፡ ለካስ “KICK ME” የሚል ጽሑፍ ከልብሱ ላይ ተጽፏል፡፡ ሳናውቅ በምንሰራቸው ሥራ፤ ሳንረዳ በምንገለብጠው ነገር ሁሉ ተጠቂዎች ራሳችን ነን፡፡ ቆዩ እንጅ ግን የማናውቀውን የምንሠራ እና የምንገለብጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን እንዴ? ሰው የማያውቀውን እያደረገ በመከራ ይኖራል፤ መንግሥት የማያውቀውን ሕግ እየገለበጠ አገዛዝ ያከፋብናል፡፡ ተማሪው መልስ መሆን አለመሆኑን ሳይረዳ ከጓደኛው ይኮርጃል (ይሰርቃል)፤ አረ አንዳንዱስ ከነ ስሙም የሚኮርጅ አለ አሉ፡፡ የማናውቀውን ስንሠራ ትንሽ ኃፍረት የማይሰማን ግን ለምንድን ነው? አገርን ያህል ነገር በተቀዳ ፖሊሲ፣ በተኮረጀ እቅድ፣ ይጥቀም አይጥቀም በማይታወቅ አስተሳሰብ ስናስተዳድር ትንሽ አይሰቀጥጠንም፡፡ አይጥና ዝንጀሮ ለላብራቶሪ ምርመራ እንደሚጠቀሙባቸው ሁሉ እኛን ኢትዮጵያውያንንም የፖሊሲ፣ የስታራቴጅ፣ የአመለካከት፣ የአስተሳሰብ መፈተኛ ቤተሙከራዎች ያደረጉን በርካቶች ናቸው፡፡ ለማንኛውም ቢያንስ በራሳችን መፍታት የምንችላቸውን ቀላል ነገሮች መፍታት የተሻለ ስለሆነ ሥራን ከመስራታችን በፊት ጥቅሙን፣ ለምን እንደምንሰራው፣ መቼ እንደምንሠራው፣ እንዴት እንደምንሠራው ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

Saturday, May 30, 2015

ባል ማነው?

እባካችሁ ሼር በማድረግ ወገኖቻችንን እንታደግ!!!!

ሁለት “ፍቅረኛሞች” ነበሩ፤ አብዝተው “ይዋደዳሉ”፡፡ ዘመኑ ዛሬ አልነበረም እጅግ ብዙ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ “ታሪክ ራሱን ይደግማል” አለ አሉ አንድ ፈላስፋ፡፡ ማለቴ ዛሬም ያ ከብዙ ዘመን በፊት የነበረው ዘመን ዛሬ ዘመን ሆኖ እየዘመነ ነው ማለቴ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ “ፍቅረኛሞችንም” ከዛሬው ዘመን ጋር አብረን እናዘምናቸው እና ዘመኑን አብረውን ይዘምኑ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- እነዚያ ሁለቱ “ፍቅረኛሞች” ፍቅራቸውን ወደ ትዳር ደረጃ ከፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ጋብቻቸውን ልዩ በሆነ ሁኔታ ማስረግ ጉጉታቸውና ምኞታቸው ነው፡፡ የመኪና ዘር የሚባል አልቀራቸውም፣ አርቲስት የሚባል ከዘፋኝ እስከ ኮሜዲያን ድረስ ሁሉም ተጠርተዋል፤ የካሜራ ባለሙያ በሙሉ  የስዕል ባለሙያዎችም ሳይቀሩ ተጋብዘዋል፤ የአካባቢው ሰው በሙሉ አደራ ልጆቻችንን እንድተመርቋቸው ተብለዋል፤ የሚታረዱት  ፍሪዳዎች  ከመድለባቸው የተነሣ ጫንቃና ሻኛቸው የማይታወቅ ለቁጥር የሚያስቸግሩ እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ የሚጠጣው መጠጥ ለባላገሩ ጠጅ፣ ጠላ፣ አረቄ ለከተሜውም ቢራው፣ ለስላሳው ተዘጋቷል፡፡ የሙሽሮቹ ልብስ ታዋቂ በሆኑ “ዲዛይነሮች” የተሠራ በርካታ ጥበብ የፈሰሰበት ነው፡፡ በወርቅ እና በዕንቁ የተጌጠ ካባ ሊደርቡ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡
እናም ይህንን ሁሉ አድርገው የጋብቻቸውን ቀን ቆረጡ፤ ሁሉም በጉጉት ጠበቀ፡፡ ከሙሽሮቹ ይበልጥ የተጠራው ሰው ቋመጠ፡፡ “ሙሽራን ሊሞቀው ሰርገኛን ልብ ወደቀው” የሚባለው አባባል ባይኖር ኖሮ እነዚህን ሰዎች ሊገልጥ የሚችል አቻ ቃል ባልተገኘ ነበር፡፡ የሆነው ሆነና መቼም ቀኑ መሄዱን ውኃም መፍሰሱን አያቆምምና የሰርጉ ቀን ደረሰ፡፡ ሙሽሮቹ የናፈቁት፣ የተጠሩ ሰዎች በጉጉት የጠበቁት ልዩ ትእይንት የሚታይበት ቀን ደረሰ፡፡ እልል ተባለ፣ ተጨበጨበ፣ ሰርገኛንም ልብ ወደቀው፤ ሙሽራንም ሞቀው፣ ዘለለ ሁሉም በየፊናው የየራሱን ደስታ ገለጸ፡፡ ሁሉም በየቋንቋው ደስታውን ገለጸ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚባለውን “ለሙሽሮች ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እያሉ እንደ ሚዳቋ ይዘሉ ገቡ፡፡
እየተጨበጨበ፣ እየተዘለለ፣ ሆ ቀን ወጥቶላት ሁሉም እያላት  ጉዞ ወደ ማዘጋጃቤት፡፡ መዘጋጃ ቤቱ እንዲህ አይነት ሰርግ ሲያስተናግድ የመጀመሪያው አይደለም ለካ፡፡ እኔ በጣም ተገርሜያሁ፤ ከመገረሜም የተነሣ እጄን አፌ ላይ ጭኜ ለብዙ ሰዓታት ራሴን ብቻ እያነጋገርሁ ነበር፡፡ ሙሽሮቹ ወደ መዘጋጃ ቤት ኃላፊው በሚዜዎቻቸው ታጅበው ሄዱ፤ ከባለጉዳዮች መቀመጫ ላይ ተቀምጠውም ቃለ መጠይቁን በሚገባ አድርገው መለሱ፡፡
ኃላፊው ፡ “ሥም” አለ
ሙሽሮቹ፡ “እገሌ እና እገሌ”
ኃላፊው፡  “ዕድሜ”
ሙሽሮቹ “25 እና 27 ዓመት”
ኃላፊው “ጾታ”
ሙሽሮቹ፡ “ወንድ”
ኃላፊው፡ “ባል ማነው?”
ሙሽሮቹ፡ “እኔ ባል፤ እርሱ  ደግሞ ሚስት”
ኃላፊው “መጠይቁን ጨርሻለሁ፤ የጋብቻ የምሥክር ወረቀታችሁን እስከማዘጋጅላችሁ ድረስ ትንሽ ጠብቁኝ” አላቸውና የምሥክር ወረቀታቸውን አዘጋጅቶ ሲሰጣቸው ርችቱ ተተኮሰ፣ መኪኖች ሁሉ አክላሉ፣ ሰው ሁሉ አጨበጨበ፣ በእልልታ አቀለጠው፡፡

ዘመናችን ለካ ዘመነ ሰዶም ነው፡፡ ዛሬ ገና ገባኝ ዓለም ዳግም በንፍር ውኃ እንደማትጠፋ ለኖኅ ቃል ኪዳን የተገባለት ቢሆንም እንኳ ነገ በሌላ መቅሰፍት ምድራችን ሙት ባሕር ልትሆን እንደምትችል  ዛሬ ተረዳሁ፡፡ ዓለም ልትጠፋ ትንሽ የቀራት የመሰለኝ ሁለት ወንዶች ሊጋቡ ሄደው ባል ማነው? ሁለት ሴቶችም ሊጋቡ ሄደው ሚስት ማናት? ተብሎ ከሚጠየቅበት ዘመን መድረሴን ሳስታውስ ነው፡፡ ሴት እና ሴት፤ ወንድና ወንድ ሊጋባ ሄዶ ባል ማነው? ሚስት ማናት? መባል እንዴት ያለ ውርደት ነው? 

Monday, May 25, 2015

“ትናንት አልባው ዛሬ”

አንድ ውሻ ነበር አሉ፡፡ ይህ ውሻ እንደማንኛውም ውሻ ያው ውሻ ነው፤ እርሱን ከሌላው ልዩ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ እናም ይህ ውሻ ጠገብኩ በቃኝን ሳይሆን ራበኝ አብሉኝን ከዚያ ውጭ ግን እበላችኋለሁ በማለት የሚያስፈራራ ነው፡፡ የሰጡትን ሁሉ በቃኝ ሳይል ንጹሁን ከቆሻሻ ሳይለይ የሚያግበሰብስ በቃኝ የሚለው ቃል የተዘነጋው ነው፡፡ ሲፈልግ ጌታውን አስፈቅዶ ሲፈልግ የጌታውን ጓዳ በርብሮ ያግበሰብሳል፡፡ አንድ ቀን ጌታው ተገረመ እና “አንተ ግን ለምን በቃኝ አትልም” አለው፡፡ ውሻም መለሰ “እንዴ ጌታዬ ከማን የተማርኩትን” ብሎ አረፈው፡፡ ጌታውም እርሱን የሰደበው ስለመሰለው በጣም ተበሳጨና “ውሻ መቼም ውሻ ነው ከማን ተማርኩት ልትል ነው ደግሞ!” አለው፡፡ “ከአባቴ፣ ከአያቴ፣ ከቅድመ አያቴ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልዩ ስጦታዬ ነው” በማለት የዘሩ እንደሆነ ገለጸ፡፡ ጌታም “እኔ እኮ ከአንተ ነው የተማርኩት ልትለኝ መስሎኝ በጣም ተናድጄብህ ነበር” አለው፡፡ “እርስዎንስ አይደለም” ብሎ መለሰ፡፡ “በነገራችን ላይ ግን  እምብርት የሚባል ነገር አልፈጠረብህም እንዴ” አለው ጌታው፡፡ “ጌታዬ እርስዎ እኮ የእኔን ልዩ ባህሪ አልተረዱም ማለት ነው” አለ ውሻ፡፡ “ምን አይነት ባህሪ አለህ መቼም ያው ማግበስበስ ብቻ!” አለው፡፡ “እርስዎ የሚመለከቱ ማግበስበሴን እንጅ የት እንደማጠራቅመው አያውቁም፡፡ በእናንተ በሰዎች ዘንድስ ይህ አይነት ነገር አለ አይደለም እንዴ? የአገር ሃብትን በቃኝ ሳይሉ የሚያግበሰብሱ ሙሰኞች ሞልተው የለም እንዴ? እነዚህ ሰዎች እኮ ከእኔ አባቶችና አያቶች በሚገባ የተማሩ የሰው ውሾች ናቸው፡፡ እነዚህ እኮ ሲያግበሰብሱ እንጅ በቃኝ ሲሉ፣ ሲያጠራቅሙ አይታዩም፡፡ ዛሬ ያገኙትን ሁሉ ያግበሰብሳሉ፤ ትናንት ምን እንዳግበሰበሱ እንኳ አያውቁም ምክንያቱም የሚያግበሰብሱት እጅግ በጣም ብዙ ስለሆነ፡፡ እኔ ያገኘሁትን ሁሉ እበላለሁ በቃኝን አላውቅም ሆዴ በጣም ሲሞላ እኔ ብቻ ከማውቃት ቦታ ሄጄ አስወጣዋለሁ(እመልሰዋለሁ)፡፡ ነገ ሌላ የምመገበው ካላገኘው ያንን ትናንት የመለስኩትን እመገባለሁ፡፡ እነዚህ የናንተ ሰዎች ግን ትናንት ያጠራቀሙትን ነገር ዛሬ አይጠቀሙበትም ምክንያቱም በየቀኑ የሚበሉት አያጡማ፡፡ የሚበሉትን ማግኘት እኮ ለእኛ የሚከብደንን ያህል ለእነርሱ እጅግ በጣም ሲበዛ ቀላል ነው፡፡ ሥራ አጡን ሥራ ላስይዝህ ይሉና ይበላሉ፣ አገር ለቆ መሰደድ የሚፈልገውን ከደላላ ላገናኝህ ይሉና ይበላሉ፣ መታወቂያ ፈላጊውን ቶሎ እንድሰጥህ ክፈል ይሉና ይበላሉ፣ ባለመኖሪያ ቤቱን ቤትህ እንዳይፈርስ ይሉና ይበላሉ፣ ተማሪውን ውጤት እንድሰጥህ ይሉና ይበላሉ፣ ገበሬውን ማዳበሪያ እንድሰጥህ ይሉና ይበላሉ፣ ነጋዴውን ግብር እንድቀንስልህ ይሉና ይበላሉ አረ ስንቱ!!! የሚበሉበት መንገድ እንደ ትልቅ ከተማ ባጃጅ እጅግ በጣም የበዛ ነው፡፡ እነርሱ ግን እንደእኔ ሲያስመልሳቸው አይታዩም፡፡ እምብርት አልባ የሚባሉት እንደነዚያ ያሉት ናቸው፡፡ ስልጣናቸውን መከታ አድርገው ደሃን የሚበድሉ ፍርድ የሚያጓድሉ ያገኙትን የሚውጡ የሰው ዘንዶዎች ናቸው እኮ ጌታዬ፡፡ እርስዎስ ግብር በዝቶብዎ የፍትህ ያለህ እያሉ ሲንከራተቱ አልነበረም እንዴ? ፍትህ ማግኘት አልችል ብለው አይደል እንዴ ያን ያህል ገንዘብ ለበላተኛ የሰጡት፡፡ አሁን አርስዎ ይህንን ረስተውት ነው?” አለ ውሻው፡፡ ጌታውም ገረመው፤ የበላተኞች ሲሳይ የሆነባቸውን አጋጣሚዎችም ዞር ብሎ አስታወሳቸው፡፡ በተለይ ግብር ለማስቀነስ ብሎ ከግብሩ በላይ እቀንስልሃለሁ ላለው ሁሉ የዘራውን ገንዘብ አስታወሰ፡፡ “እሽ ሌላስ ምን አለሀ?” አለ ጌታው ውሻውን እያሻሸ፡፡ ውሻውም ቀጠለ “ጌታዬ የሰው ውሻ እኮ ይከብዳል ምክንያቱም ከሰው ጋር እንደሰው ከውሻ ጋርም እንደ ውሻ ነውና፡፡ እንዴ አኔ እኮ ውሻነቴን ጠንቅቄ አውቃለሁ ውሻ ብቻ ነኝ እነርሱ ግን የውሻና የሰው ባህሪ የተደባለቀባቸው ናቸው፡፡ እነርሱ ዛሬን እንጅ ትናንትን የማያውቁ ናቸው፡፡ እነርሱ ዛሬ መጥገባቸውን እንጅ ትናንት መራባቸውን፣ ዛሬ መበደላቸውን( በ ይላላል) እንጅ ትናንት መበደላቸውን (በ ይጠብቃል) ፣ ዛሬ መንደላቀቃቸውን እንጅ ትናንት መኮሳመናቸውን አያውቁም፡፡ ባጠቃላይ ትናንት አልባዎች ናቸው፡፡ ዛሬን እንጅ ትናንትን ዞር ብለው ማሰብ የማይፈልጉ ናቸው፡፡ አገር ወዳድ ሲባል የትናንቱን ቴዎድሮስ ሳይሆን የዛሬውን መሪ ነው የሚያስቀድሙ፡፡ የአገሩን ድንበር ያስከበረ ሲባል የትናንቱን ሚኒሊክን ሳይሆን የዛሬውን ቆርሶ ሰጥ ነው የሚያሞግሱ፡፡ አገሩን ከጠላት የጠበቀ ሲባል የሚኒልክን ጦር ጣልያንን ያሳፈረውን ሳይሆን የአገሩ ክፍል የነበረችውን ኤርትራን ተዋግቶ የተሸነፈውን የዛሬውን ወታደር ነው  የሚያደንቁ፡፡ ከኃይለ ሥላሴ ይልቅ የሞሶሎኒን ሐውልት ማቆም ነው የሚቀናቸው ፡፡ ብቻ ትናንትን ሳይሆን ዛሬን ብቻ ነው የሚያሞግሱ፡፡ ስልጣኔ የጀመረ ዛሬ እንጅ ትናንት በአክሱም ዘመነ መንግስት አይመስላቸውም፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የተጀመረ ዛሬ እንጅ በኃይለሥላሴ ዘመን አይመስላቸውም፡፡ ታዲያ እነዚህ እኮ ታሪክ የማያውቁ ሆነው ሳይሆን የትናንትን ታሪክ መደፍጠጥ ስለሚቀናቸው ነው፡፡ አረ እኔው እውነተኛው ውሻ እሻላለሁ፡፡ ወቼው ጉድ፡፡ በሰው ባህሪ ገብቼ እዘባርቃለሁ እንዴ? እኔ እኮ ማግበስበስንም ከአባቴ፣ ከአያቴ፣ ከቅድመአያቴ የወረስኩት ነው ብያለሁ፡፡ የትናንት ማንነቴን አልዘነጋሁትም እናንተ ሰዎች ግን የትመጣችሁን ዘንግታችኋል፡፡ ማግበስበስ ቢያመሳስለንም ታሪክ ጥበቃ ግን ያለያየናል፡፡ ዛሬን ያለትናንት የሚተርከው እኮ የሰው ልጅ ነው፡፡ መቼ እንደተማሩ፣ መቼ እንደተወለዱ፣ እንዴት እንዳደጉ እኮ የዘነጉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ትናንትን ዞር ብለው ማሰብ ስለማይሹ አለቀ!!!” ሰውዬውም ማንነቱን ወደኋላ ለማዬት የሞከረው ዛሬ ከውሻው ምክር በኋላ ነበር፡፡ አስተዳደጉ ትዝ አለው፡፡ ዛሬን ትቶ ትናንትን አስታወሰ ልዩ ክስተቶችንም አስታወሰ፡፡ “እውነትም የሰው ልጅ ትናንት አልባ ዛሬን ነው ሲላዝን የሚውለው” በማለት ራሱን መከረ፡፡

Wednesday, May 20, 2015

አማርኛችን ወዴት እየሔደ ነው?

ቋንቋ መግባቢያ ነው፡፡ ከመግባቢያነቱ ባለፈ  ቋንቋ የራሱ የሆነ  የአነጋገርና የአጻጻፍ ሥርዓት አለው፡፡ አንድ ቋንቋ በራሱ ለተናጋሪው ምሉዕ (የተሟላ) እንዲሆን ዘመኑን የሚዋጁ (ዘመኑ የሚወልዳቸው) ቃላት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እኔ ምንም እንኳ የቋንቋ ተመራማሪ ባልሆንም አንድ ቋንቋ ምን ማሟላት እንዳለበት ግን እረዳለሁ፡፡ የሰው ልጅ በበርካታ ነገሮች ሊግባባ ይችላል፡፡ የሚግባባበት ሁሉ ግን ቋንቋ አይደለም፡፡ ወፎችም፣ እንስሳትም ሁሉም ይግባባሉ (የራሳቸው የሆነ መግባቢያ አላቸው) ነገር ግን ቋንቋ የላቸውም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ሥልጣኔ ውስጥ አብራ የሰለጠነች በዘመናት መካከልም አብራ የዘመነች እንደሆነች በርካታ ማስረጃዎችን ማንሣት እንችላለን፡፡ አክሱም ሐውልትን የመሰለ ልዩ ምህንድስና ያለበት፣ ላሊበላን የመሰለ ልዩ ጥበብ የፈለቀበት፣ ልዩ የሆነውን 13 ወራት የሚይዘው የቀን አቆጣጠር ሃብታችን፣ የራሳችን የሆነው የፊደል ገበታችን ስልጣኔያችን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር በቂ ማሳያዎቻችን ናቸው፡፡ በርካታ አገራት ፊደላትን ከሌሎች እየተዋሱ ሲጠቀሙ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያ ይህንን የመሰለውን የራሷ የሆነውን ብርቅየ ቋንቋ ከነፊደሉ ማዘጋጀቷ ትልቅ እና የጥበብ መፍለቂያ አገር እንደነበረች ያስረዳናል፡፡
የግዕዝ ፊደላት አማርኛ ቋንቋ ውስጥ የምንጠቀምባቸው ብቸኛ ፊደላት ናቸው፡፡ ቃላት እንደዘመናት መፈራረቅ ሁሉ ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይሞታሉ፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ የቃላት ዑደት በማንኛውም ቋንቋ ዘንድ እንደሚኖር አልጠራጠርም፤ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ግን አለ፡፡ አሁን አሁን ግን እየተወለዱ ያሉት ቃላት አማርኛ አማርኛ የማይሸቱ እየሆኑ በመምጣታቸው ለአማርኛ ቋንቋችን ከፍተኛ ተጽእኖን እያሳደሩ ናቸው፡፡ በቋንቋችን አፍረን ለሌላ ቋንቋ ልባችንን ከፍተን የማንነታችን መታወቂያ የሆነውን ቋንቋ በርዘነዋል፡፡ የተወሰነውን የቋንቋ ባህሪ ለሌላው በማውረስ ቃላትን የምንፈጥር አለን፡፡ ለምሳሌ እንመልከት፡- ኮምፒዩተር የሚለው ቃል እንግሊዝኛ ነው እኛ እንደአማርኛ ኮምፒዩተሮች እያልን አናረባዋለን፡፡ አበበ የኮምፒዩተርኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር ብለንም ማስታወቂያ እንሰራለን፡፡ የእንግሊዝኛ ቃላትን ከአማርኛ ቃላት ጋር በማጣመርም ቃል የፈጠርን የሚመስላቸው ሞኞች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡ መስከረም ባርሬስቶራንትፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሳይንስቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ፣ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ሬጅስትራር ጽ/ቤት፣ አርቲስት እገሌ፣ ኢንጅነር እገሌ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የፋይናንስ አስተዳደር፣ የኮምፒዩተርኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር  አረ ስንቱ፡፡ በአማርኛ ፊደል  መጻፉ ብቻ አማርኛ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ይኼ ደግሞ በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ባህሪ የጎደለው ግድየለሽነት ነው፡፡ በዚህ የምንቀጥል ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ፊደላችን ብቻ ሊቀር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እንግሊዝኛን ከአማርኛ ጋር ቀላቅሎ  መናገር ትልቅነት የሚመስላቸው በርካታዎች ናቸው፡፡ እንግሊዝኛ ማለት አማርኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ጣልያንኛ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ቋንቋዎች፣ መግባቢያዎች ስለሆኑ፡፡ አለቀ፡፡ ማግባባት ከቻለ የእኛው አማርኛ ምኑ ላይ ነው ድክመት ያለበት? የተለያዩ ቋንቋዎችን መቻል በጣም ጥሩ ነው ደስም ይላል፡፡ ምክንያቱም ብዙ እውቀት ልናገኝበት የምንችልበትን እድል ስለሚከፍቱ፡፡ ነገር ግን አንዱን ከአንዱ ጋር እየቀላቀሉ መናገርም ሆነ መጻፍ አላዋቂነት ነው፡፡
በተለያዩ ቦታዎች የተጻፉ ማስታወቂያዎችን ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? አንድ ከተማ ውስጥ ግቡ እና ማስታወቂያዎችን ተመልከቱ ሙሉ አማርኛ አታገኙም፡፡ እኔ ባለሁበት አካባቢ ጥቂቶችን ልግለጽላችሁ፡፡ ጎዛምን ሆቴልኤፍ. ኤም ኢንተርናሽናል ሆቴልስታር ቢዝነስ ግሩፕፎቶ ስታርፓራዳይዝ ሕንጻ፣ አበበ የኮምፒዩተርኤሌክትሮኒክስ መሸጫ መደብር፣ማርታ ጁስ መሸጫ ወዘተ ዘርዝሬ መግለጽ አልችልም በእርግጥ፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም የዚህ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ፋይናንስና ግዥ አስተዳደር፣  የታክስኦዲት ባለስልጣን፣ የፌዴራል ኦዲተር፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትዳይሬክተርዲፓርትመንት ሄድ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የገንዘብና  ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ወዘተ … እነዚህ ሁሉ በአማርኛ የተጻፉ በአማርኛ የቃላት እርባታ እንደአስፈላጊነቱ እየረቡ ያሉ ናቸው፡፡ ለነገው ትውልድ ምንድን ነው የምናወርሰው? ይህን የተበረዘ አማርኛችንን ነው? የመንግስት ተቋማትስ ምን እየሰሩ ነው? የአማርኛ ትምህርት ክፍልስ ምን አይነት መምህራንና ተማሪዎችን እያፈራ ነው? መቼ ይሆን በራሳችን ፊደል የራሳችንን ቋንቋ ብቻ የምንጽፍበት? ሁኔታው አሳሳቢ ነው፡፡ አንድ ደብዳቤ ምን ያህል የእንግሊዝኛ ቃላትን በአማርኛ ፊደላት እንደተጠቀመ በየአጋጣሚው  የሚጻፉ ደብዳቤዎችን ተመልከቱ፡፡ በውኑ የአማርኛ ቋንቋ መግለጽ የማይችለው ነገር አለን? ካለስ የአማርኛ ምሁራን ሰብሰብ ብለው ለዚያ ነገር አዲስ የአማርኛ ቃልን መውለድ (መፍጠር) እንዴት ተሳናቸው? በዚህ ችግር እስከመቼ እንቆይ ይሆን?
ታዲያ መፍትሔው ምን ሊሆን ይችላል? በመጀመሪያ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ተናጋሪው በራሱ ትክክለኛውን አማርኛ መናገር አለበት፡፡ ሁለተኛም የአማርኛ ምሁራን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በመጨረሻ መንግሥትም ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል፡፡ ከራሱ መሥሪያ ቤቶች ስያሜ በመጀመር፡፡ የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን የወሰነ መንግስት የመገናኛ ብዙኃኑን (EBC) ማለቱ በጣም የሚያናድድና የሚያበሳጭ ነው፡፡ ኢብኮ- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ‹‹ብሮድካስቲንግ - ኮርፖሬሽን›› የትኛው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ ነው እነዚህ ቃላት የሚገኙት? ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ትልቁን ድርሻ ሊወስድ ይገባዋል፡፡ ማደግ የምንችለው በራሳችን ሃብት መጠቀም ስንችል ብቻ ነው፡፡  ቋንቋችን ደግሞ ትልቁ ሃብታችን ነው፡፡ ቻይና ለማደጓ ምሥጢሩ የራሷን ቋንቋ መጠቀሟ ነው፡፡ እኛም ማደግ የምንችለው በራሳችን ቋንቋ መጠቀም ስንችል ብቻ ነው፡፡


Monday, May 18, 2015

የማስመሰል አባዜ

ማስመሰል ማለት መሆን ማለት እንዳይደለ ሁሉም ይስማማበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ልዩ ስጦታ ያለው ሰው የተለያዩ እንስሳትን ድምጽ ያስመስላል ነገር ግን እነዚያን እንስሳት ሊሆን አይችልም፡፡ እንዴት ሆኖ አረ በፍጹም!!! ሰው የእንስሳ ድምጽን ከማስመሰል አልፎ እንስሳቱን ራሳቸውን ሊሆን የሚችልበት ተሰጥኦ የለውም፡፡ አንዳንዶች የሰውን ልጅ የማስመሰል ጥበብ የተረዱ አይመስለኝም፡፡ በርካታ የሚባሉ ወጣቶች በማስመሰል ጥበብ ውስጥ እጅግ የተካኑ ባለሙያዎች እየሆኑ መምጣታቸው የማይካድ እውነታ ነው፡፡ አንድ ወጣት አንዲትን ወጣት በዝሙት ለመጣል ከፈለገ የማስመሰል ጥበቡን ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ የማስመሰል ጥበብ የሚጀመረው ዝም ብሎ ከምድር ተነሥቶ አይደለም፡፡ ማስመሰል ከመጀመሩ በፊት በማስመሰል ስለሚጥሉት ሰው ወይም አገር ልዩ ባህሪ ማዎቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ወጣት በዝሙት ሊጥላት በልቡ ኃጢአትን ከጸነሰ በኋላ ያች ወጣት ምን ትወዳለች? ምንስ ትጠላለች? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይጠበቅበታል፡፡ የምትወደውንና የምትጠላውን ከተረዳ በኋላ ወደማስመሰል ጥበቡ ይጓዛል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ያች ወጣት ጥሩ መንፈሳዊ የቤተክርስቲያን ልጅ ከጾምና ጸሎት ውጭ ሌላ የማታውቅ ሆና ካገኛት እርሱም እንደዚያ ይመስላል፡፡ ጥሩ መንፈሳዊ ይመስላል፡፡ ነጠላውን መስቀለኛ ለብሶ ትልቅ የጸሎት መጽሐፍ ይዞ ያች ወጣት በምትገባበትና በምትወጣበት ሰዓት እየጠበቀ መታየትን ምርጫው ያደርጋል፡፡ ቀስ በቀስም ሰላምታ መለዋወጥን፣ መተዋወቅን፣ በአፉም ሰው ከሚመለከተው ማንነቱ ባለፈ እጅግ የበዙ ሥራዎችን እንደሠራ መንገር ይጀምራል፡፡ በዚህ የማስመሰል ጥበብ ውስጥ ትክክለኛውን ነገር የማትገነዘበው ወጣት በፍጹም መንፈሳዊ ፍቅር በወንድምነት እስከመኖሪያ ቤቱ ድረስ የምትሄድበትን እድል ሲያመቻችላት ትከተለዋለች፡፡ በስተመጨረሻም እርሱ ያን የማስመሰል ሰይጣናዊ ጥበቡን ተጠቅሞ የወደደውን ያደርጋል፡፡ ሴት እህቶቻችን እዚህ ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ልትወስዱ ያስፈልጋል፡፡ ነጠላ ለባሽ ሁሉ መንፈሳዊ፣ ቀዳሹ ሁሉ ዲያቆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሁሉ ሰባኪ፣ ድምጽ ማጉያውን የያዘው ሁሉ ዘማሪ፣ የጸሎት መጽሐፍ ያነገበው ሁሉ ጸሎተኛ አይደለም፡፡ የሰው ማንነቱ ከውስጡ የተደበቀ እንጅ ከላይ የምንመለከተው አይደለም፡፡
ማስመሰል ለምን ያገለግላል?
ሰዎች ማስመሰልን ለበርካታ ነገሮች ይጠቀሙበታል፡፡ ለተቀደሰ ዓላማ ማስመሰልን የተጠቀመው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ያላመኑትን ለማሳመን፣ ያልተጠመቁትን ለማስጠመቅ፣ ያልተማሩትን ለማስተማር ቅዱስ ጳውሎስ ሳይታመም የታመመ መስሎ ከታመሙት ጋር አብሮ ተኝቶ ብዙ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት መልሷል፡፡ አብዛኞቻችን ግን ማስመሰልን የምንጠቀመው ለኃጢአት ሥራ ብቻ ነው፡፡ ከላይ ከአገሪቱ መሪ እስከታች ተራው ሰው ድረስ ማስመሰልን የምንጠቀመው የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ብቻ ነው፡፡ በቅርበት የማያዩን ሰዎች እውነት እንደሆነ እንዲረዱን ስንሻ ማስመሰልን አማራጭ እናደርጋለን፡፡ ልማትን በማስመሰል፣ ምርጫን በማስመሰል፣ መንገድን በማስመሰል፣ ባቡርን በማስመሰል፣ ግድብን በማስመሰል፣ ትምህርትን በማስመሰል፣ ጤናን በማስመሰል አረ  ስንቱን ብቻ ሁሉንም በማስመሰል የውጭ ብድር እና እርዳታ ማግኘትን የሚሻ መንግሥት አለ፡፡ ለምን ማስመሰልን መፍትሄው አደረገ? ካልን መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ለታይታ በማስመሰል የውጭ መንግስታትን ድጋፍ ለማግኘት ስለሚፈልግ ነው፡፡ እነዚያ ረጅ ድርጅቶች የሚመለከቱት በወረቀት የሰፈረውን እንጅ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ እውነታ አይደለም፡፡ ጸሎት ምን እንደሆነ የማያውቅ የኔቢጤ የሚፈልገውን ለማግኘት ሲል በማስመሰል ለምድ ተደብቆ ትልቁን የጸሎት መጽሐፍ ይዞ ቤተክርስቲያን ይሄዳል፡፡ የሚፈልገውን በዚህ መልኩ ማግኘት የለመደ ሰው ሁሌም ሲያስመስል እንጅ ሲሆን አናየውም፡፡ በለምድ ውስጥ ተደብቆ የራሱን የተደበቀ ሥራ ብቻ የሚሠራ ሰው ሁሌም አስመሳይ ነው፡፡
ሌላው ማስመሰልን ተከታይ ወይም ደጋፊ ለማፍራት የሚጠቀሙበትም አሉ፡፡ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ማስመሰልን ለዚህ ዓላማ የሚጠቀሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ተሐድሶ መናፍቃን የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይሆኑ እንደሆኑ አስመስለው የእግር ኳስ ደጋፊ የሚመስል “ክርስቲያን” ያፈራሉ፡፡ ሳይማሩ በማእረግ ስሞች ውስጥ ተደብቀው “ዲያቆን፣ መምህር፣ መጋቢ ሐዲስ …” በሚለው የማጭበርበሪያ ስልት ተጠቅመው ወገኖቻችንን ለመናፍቃን አዳራሽ ያዘጋጁ በርካታዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ነቅተን ራሳችንን፣ አገራችንን፣ ቤተክርስቲያናችንን፣ ወገናችንን ልንጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ በማስመሰል ሥራ የተሰማራን ካለንም ከዚህ ድርጊታችን ልንቆጠብ ይገባናል፡፡
                                                                                                  መልካሙ በየነ (ወልደ ማርያም)

Friday, May 15, 2015

“ለካ ጊዜው ኖሯል”

አንድ ስሙን ለጊዜው የማላስታውሰው ሰው እንዲህ የሚል አባባል አለው “ALL COLOURS WILL AGREE IN THE DARK”. ይህን አባባሉን ሳነበው ትልቅ መልእክት እንዳለሁ ልቤ ተረዳ፡፡ የተረዳው ልቤም መላ አካላቴን አነቃቃው እና አጆቼን ወደ መጻፊያ ሰሌዳው ወሰዳቸው፡፡ በዚያም የሚንኳኳውን የመጻፊያ ሰሌዳ በእኛው በአገራችን በለመድነው ቋንቋ እንዲጽፍ የመጻፊያ ስልቱን ቃኘሁት (ቀየርኩት)፡፡ ከዚያም ይህንን ቁም ነገር በኢትዮጵያዊ ለዛው ተናዘዝሁ፡፡
“ፀሐይኒ አእመረ ምዕራቢሁ፣ ታመጽእ ጽልመተ ወይከውን ሌሊተ” መዝ 103÷20 እንዳለው ነቢዩ  ቅዱስ ዳዊት፡፡ “ፀሐይም መግቢያውን አወቀ፣ ጨለማን ታመጣለህ ሌሊትም ይሆናል” በሚለው ግርድፍ አማርኛ እንቀይረውና በምንግባባበት መጠን እንግባባ፡፡ ለማንኛውም ግእዙን በቀጥታ የመፍታት አቅሜ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ የምትረዱት እንደሆነ ባውቅም ከዋናው የቅዱስ ዳዊት ሃሳብ ግን እምብዛም የራቅሁ አይመስለኝም፡፡ ይህንን ጥቅስ የመረጥኩት ሌሊት የሚባለው የጊዜ ቀመር ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ነው፡፡ ነገርን ነገር ያመጣዋልና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 3 ቀናት እና 3 ሌሊት በከርሰ መቃብር ማደሩን የምንቆጥረው አንዱ በዚህ አቆጣጠር ዘዴ ነው፡፡ አርብ ከቀኑ 11 ሰዓት ወደ መቃብር ወረደ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሌሊት 6 ሰዓት ተነሣ በጠቅላላው 31 ሰዓታት ማለት ነው፡፡ ይህን ነገር በምንም አይነት ቀመር 3 ቀን እና 3 ሌሊት ማለት አይቻልም፡፡ 1 ቀን እኩል ይሆናል 24 ሰዓት ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ 3 ቀናት 36 ሰዓታት 3 ሌሊት 36 ሰዓታት በጠቅላላው  72 ሰአታትን በከርሰ መቃብር ማደር ነበረበት፡፡ ነገር ግን ቀመሩ እንዲህ አይደለም፡፡ አቆጣጠሩ ፀሐይ ስትኖር ቀን፤ ስትጠልቅ ደግሞ ሌሊት በሚል ቀመር ነው፡፡ አርብ ከተያዘበት እስከተሰቀለበት 6 ሰዓት ድረስ( 1ኛቀን)፣ ከ 6- 9 ሰዓት ጨለማ ሆነ (1ኛሌሊት)፣ ከ9-11 ሰዓት ብርሃን ሆነ(2ኛቀን)፣ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ(2ኛ ሌሊት)፣ ቅዳሜ ሙሉ ቀን(3ኛ ቀን)፣ ቅዳሜ ለእሁድ እስከተነሣበት ድረስ(3ኛ ሌሊት)፡፡ በእርግጥ ሌላ አቆጣጠርም አለው ነገር ግን ከዚህ ሃሳብ ጋር የሚመሳሰለው ይኼኛው አቆጣጠር ስለሆነ ብቻ በዚህ እናብቃ፡፡ በአጠቃላይ ሌሊት ማለት ጨለማ የሚሆንበት  ወይም ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ ማለት ነው፡፡
ሌሊት ምን እንደሆነ ከተረዳን ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ የዚያ የማላውቀው ሰውዬ አባባል ከሞላ ጎደል በግርድፉ እኔ በተረዳሁበት አገላለጽ  እንዲህ አልኩት ፡- “በጨለማ ሁሉም ቀለሞች ይስማማሉ”፡፡ ቀይ ቀይ የሚሆነው ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ አረንጓዴም አረንጓዴ የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ቢጫም ቢጫ የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ሰማያዊም ሰማያዊ  የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ነጭም ነጭ የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ  ቀለም ቀለም  የሚሆነው  ፀሐይ ካለች ብቻ ነው፡፡ ለካ ቀይ የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ አረንጓዴም  የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ ለካ ቢጫም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ ሰማያዊም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ለካ ነጭም የምንለው በፀሐይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለካ የቀለም አይነቶችን የምንዘረዝረው  በፀሐይ ነው፡፡ ቀለምን ቀለም የሚያሰኘው ለካ ጊዜው ኖሯል፡፡ ለካ ቀለሞች ያልተስማሙት አንድ ያልሆኑት ፀሐይ ስላለች ነው፡፡
አሁን ምልከታዬ ሰፋ እያለ መጣ፡፡ ለካ ሃብታም ሃብታም የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ደሃም ደሃ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ለካ ባለሥልጣንም  ባለሥልጣን  የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ አልቃሽም አልቃሻ  የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የራበውም ረሃብተኛ  የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ካገሩ የወጣም ስደተኛ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የተቸገረ ሰውም ችግረኛ የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ የታመመ ሰውም በሽተኛ  የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ያልተማረ ሰውም ማይም የሚባለው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለካ ጊዜ የማይለውጠው ዘመን የማይሽረው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ለካ ሁሉም በጊዜ ይለወጣል፣ በዘመንም ይሻራል፡፡
እኔ ደሃ ነኝ አንድ ቀን ግን ከሃብታሙ ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ ረሃብተኛ ነኝ አንድ ቀን ግን ከጠገቡት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ አልቃሻ ነኝ አንድ ቀን ግን ከሚስቁት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡  እኔ ችግረኛ  ነኝ አንድ ቀን ግን ካልተቸገሩት  ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ በሽተኛ ነኝ አንድ ቀን ግን ከጤነኞች ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ እኔ ያልተማረኩ ማይም ነኝ አንድ ቀን ግን ከተማሩት ጋር አንድ እሆናለሁ፡፡ ይህ አንድ የሚያደርገኝ  ቀን ሩቅ አይደለም ቅርብ ነው፡፡ ቀለሞችን ሁሉ አንድ ያደረጋቸው ጨለማ እኔ ጋርም አለ፡፡ እርሱ አንድ ቀን ከሌሎች ጋር አንድ ያደርገኛል፡፡ ትልልቅ መሪዎች፣ አስፈሪ ወታደሮች፣ የተከበሩ ምሑራን፣ ሁሉ የሞላቸው ባለጠጎች፣ ሕዝብን በግፍ ያንገላቱ ጨካኞች፣ ፀሐይ ስትወጣላቸው የምንፈራቸው፣ በሥልጣን ኮርቻ ሲቀመጡ የበደሉን ሁሉ ነገ አንድ እንሆናለን፡፡ ቀይ፣ አረንጓዴ ፣ቢጫ፣ ሰማያዊ፣ ነጭ በጨለማ ሁሉም ተስማምተው ጥቁር እንደሚሆኑ ሁሉ እኛም እነደዚሁ  የማንረታው፣ ጥበባችን የማያርቀው፣ መቼ እንደሚመጣ የማናውቀው ፣ ባለሥልጣን፣ ሃብታም፣ ደሃ የማይለየው ለሁሉም እኩል የሚፈርደው ሞት ሲመጣ ያኔ እኩል እንሆናለን፡፡ የተበደለው ከበደለው ጋር፣ የተገደለው ከገደለው ጋር፣ ያለቀሰው ካስለቀሰው ጋር፣ በግፍ የተንገላታው ከአንገላታው ጋር፣ የተንቋሸሸው ከአንቋሸሸው ጋር፣ የተደበደበው ከደበደበው ጋር፣ የተሰደደው ከአሳደደው ጋር፣ የተገረፈው ከገረፈው ጋር፣ የተሰረቀው ከሰረቀው ጋር፣ የተደፈረው ከደፈረው ጋር፣ የተሸማቀቀው ካሸማቀቀው ጋር፣ የተመራው ከመሪው ጋር፣ የተቀለደበት ከቀለደበት ጋር… ፩ ቀን ፩ እንሆናለን፡፡ ሕይወት አላስማማን ቢልም  ቅሉ ፩ ቀን ግን ሞት ያስማማናልና በዚህ እንጽናናለን፡፡ ለካ አላስማማን ያለ ጊዜው ነው፡፡ የፀሐይ መኖር አላስማማቸው ያሉ ቀለሞች በጨለማ ሁሉም ጥቁር ሆነው እንደሚስማሙ ሁሉ ጊዜው ሲደርስ በሕይወት አልስማማ ያልን ሁሉ በሞታችን እንስማማለን፡፡

Tuesday, April 28, 2015

በጣም አልበዛም ግን?

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ችግሮች ይገጥሟታል፡፡ አንዱ ችግር ሌላውን ተከትሎ ስለሚመጣ አንዱን አዝነን ሳንጨርሰው ሌላው አሳዛኝ ችግር ይተካል፡፡ የአንዱ ችግር ተከትሎ መምጣትም ያለፈውን ያስረሳናል፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ጉዳይ ይህ ነው፡፡ በአገሪቱ አለመረጋጋት ሳቢያ በየመን ይኖሩ የነበሩ ወገኖቻችን እጅግ አስጨናቂ መከራ ላይ መውደቃቸውን እያሰብን ሳለን ከወደ ደቡብ አፍሪካ የሰማነው ጉዳይ እነርሱን እንድንዘነጋቸው አደረገን፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወገኖቻችን በእሳት ተቃጠሉ በአደባባይ በስለት ተቆረጡ እጅግ አለቀስን፡፡ ለነጻነታቸው ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራት አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ያንን ነጻነታቸውን ከተጎናጸፉ በኋላ ግን ይህንን ክፉ ሥራ ፈጸሙብን፡፡ ስለ እነርሱ ስናለቅስ ስናነባ 30 ወንድሞቻችን በሊብያ በረሃ ደማቸው ከውኃ ጋር  ጎረፈ፡፡ አሰቃቂ ዘግናኝ የተባለውን መከራ ተቀበልን፡፡ አብዝተን በምሬት አለቀስን እንባችንን አፈሰስን በአደባባይም በሰላማዊ ሰልፍ ሀዘናችንን ገለጽን ሆኖም ግን ሀዘናችን ሃዘናቸው ያልሆኑ ፖሊሶች በአገራችንን በዱላ ቀጠቀጡን፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አምላክን ከመለመን ውጭ ምንም ማለት ስለማንችል “አንመካም በጉልበታችን፣ እግዚአብሔር ነው የእኛ ኃይላችን” እያልን ዘመርን፡፡ ያም ሆኖ በዚያ አለፈ፡፡ ሲኖዶሱ በ 7 ቀናት ጸሎተ ፍትሐት ረሳቸው፣ መንግሥትም በ 3 ቀናት ብሄራዊ ሀዘን ዘነጋቸው እኛ ቤተሰቦቻቸው ግን እስከመቼም ድረስ አንዘነጋቸውም አንረሳቸውም፡፡
በጣም የሚሳዝነውና የሚገርመው ጉዳይ ግን እስከዛሬ ድረስ በመገናኛ ብዙኃኑ የሚነገረው ዜና መሰል ትርኪ ምርኪ ንግግር ነው፡፡ “እስልምናን አይወክልም” ከሚለው በሻገር እኛ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ከእስላም ለብዙ ዘመናት በፍቅር አብረን የኖርን ነን፤ እንዲያውም መስጊድ ሲሰራ ክርስቲያኑ፤ ቤተ ክርስቲያን ሲሰራም እስላሙ ማህበረሰብ ይደጋገፋሉ ተባለ፡፡ ትክክል ነው ለብዙ ዘመናት አብሮነታችን ዘልቋል፡፡ አንድ በጣም የበዛው ጉዳይ ግን “በጋብቻም ተሳስረናል” ተብሎ የሚገለጸው የመገናኛ ብዙኃኑ ግዴለሻዊ ዘገባ ነው፡፡ ፍቅራችን ምን ወደር ባይኖረው፣ እጅግ ብንረዳዳ፣ በለቅሶ በደስታ ብንጠያየቅ፣ አብረን በጉርብትና ብንኖር በጋብቻ ግን ልንተሳሰር እንዴት እንችላለን? ፖለቲካው ምን ያህል ጫና እየፈጠረብን እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል፡፡ የሃይማኖት መሪዎች በአንድ ወንበር ተቀምጠው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ፎቶ ቢነሱ፣ ቪዲዮ ቢቀረጹ ከፊት የነበራቸውን ፍቅር የሚያሳይ ነው እንጅ ሌላ መልእክት ያለው አይመስለኝም፡፡ አሁን አሁን  ግን ድሮ ከነበራቸው አንድነት የተለየ ሌላ አንድነት የፈጠሩ ይመስል ለታይታ በአደባባይ እጅ ለእጅ መያያዝን የፍቅር መገለጫ አድርገውታል፡፡ ቤተክርስቲያን እንዲገቡም ሳይፈቀድላቸው አልቀረም፡፡ በጣም በዛ “ፍቅራችን” ከልኩ አለፈ ሥርዓት እየተጣሰ እንዲህ ያለ ነገር መሠራቱ አስፈላጊ መስሎ አይታየኝም፡፡ እስላሙ ያረደውን ክርስቲያኑ፤ ክርስቲያኑ ያረደውን ሙስሊሙ አለመመገብን እንደልዩነት የሚመለከተው መንግሥት አንዱ ያረደውን ሌላው እንዲመገብ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ በጋብቻ ተሳስረናል ላለ አካል ይህን ማድረግ እጅግ ቀላል ነዋ!!!

ስደት ለምን?

ኢትዮጵያውያን ለምን ይሰደዳሉ? የሚለውን ከባድ ጥያቄ መጠየቅ ግድ ከሚልበት ሰዓት ላይ እንደደረስን የተረዳሁት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያኑ አገር ለቅቆ በባእድ አገር መበተን ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? በውኑ ይችን ቅድስት አገር ጠልተው ይሆን የተሰደዱት? እስኪ የገባኝን የተረዳሁትን ትንሽ ነገር ልበላችሁ፡፡ ብዙዎች በችግር ወድቀው መድረሻ ባጡበት በዚህ ጊዜ ወደ ሊብያ፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ወደ የመን ወደ ሌሎችም አገራት  ለመጓዝ (ለመሰደድ) የሞከሩ እንዳሉ በመገናኛ ብዙኃን ሲነገር ሰምተናል፡፡ እርሱማ አበውስ “ከረሃብ ጦር ይሻላል” ብለው የለም እንዴ? ትክክል ነው መከራ ያስጨንቃል፣ ረሃብ ክፉ ነው ለስደት ይዳርጋል፣ ነገ ተስፋ የምናደርገውን እንጅ ስንጓዝ የሚደርስብንን መከራ ከምንም አንቆጥረውም ምክንያቱም እዚህ ብንቀመጥም በአእምሮ ከመቁሰል፣ በረሃብ አለንጋ ከመገረፍ የዘለለ ምንም ነገር ላናተርፍ እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያውያን የማይገኙበት ቦታ አንታርክቲካ ብቻ ነው፡፡ በሌላው የዓለም ክፍል ነፋስ እንደበተነው እህል እንደዚያው ተበትነዋል፡፡ ወገኖቻችን ለእኛ ሲሉ፣ ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ፣ ለአገራቸው ሲሉ ተበትነዋል፡፡
ስደት የቅድስና መንገድ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ እነ ቅዱስ አትናቴዎስን፣ እነ ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅን ለአብነት ያህል መጥቀስ እንችላለን፡፡ ዓላውያን ነገሥታት በተነሡባቸው ወቅት ከተከበረው መንበራቸው ወርደው ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ለምን ተሰደዱ? የሚለውን ጥያቄ ስንመለከት እንጀራ ፍለጋ  ወይም የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለመቀየር ነው ብለን አንመልስም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ እጅግ አብዝቶ የሚወዳቸው  የተቀደሱ የዓለም ብርሃን የነበሩ ጳጳሳት ናቸውና፡፡ ወንጌል “የሚያሳድዷችሁን መርቁ” ስለሚል ያንን የወንጌል ቃል ይፈጽሙ ዘንድ ተሰደዱ፡፡ ዓለም አልተገባቻቸውምና በምድረ በዳ ተንከራተቱ፣ ተራቡ፣ ተጠሙ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስደትም እንዲሁ ለቅድስና ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ እንጀራ ፍለጋም ይሁን ለፖለቲካ ነጻነት አገርን ለቅቆ መሰደድ የወንጌልን ቃል መፈጸም ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሰላሙን ለማግኘት ነጻነቱን ለማስከበር ብቸኛው መንገድ ስደት ሆኖ ያገኘው ሰው ቢሰደድ ኃጢአት የለበትም፡፡ ከተማረ ሰው ይልቅ ለአበባ ምርት ቅድሚያ በምትሰጥ አገር ውስጥ መኖር ከመረረው ያ ሰው ብቸኛው ምርጫው ስደት ነው፡፡ በአገሩ ላይ ከሁለተኛ ዜጋ በሚያንስ ክብር እየኖረ ያለ ሰው ቢሰደድ ፍርዱ በተሰደደው ሕዝብ ሳይሆን ባሰደደው ወገን ላይ ነው፡፡ ለስኳር መሰለፍ፣ ለውኃ መሰለፍ፣ ለዱቄት መሰለፍ፣ ለመብራት መሰለፍ፣ ለታክሲ መሰለፍ፣ ለዘይት መሰለፍ ወዘተ ክንዱን ያዛለው ህዝብ ቢሰደድ ማነው ሊጠየቅ የሚገባው ህዝቡ ወይስ አስተዳዳሪው? ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ ዲፕሎማውን፣ ዲግሪውን፣ ማስተርሱን፣ ዶክትሬቱን ወዘተ ያጠናቀቀ ሰው የሥራ እድል ለማግኘት ሲሞክር ቀድመው በሥራው ላይ በተቀመጡ 8ኛ ክፍልን እንኳ ባግባቡ ባላጠናቀቁ ሰዎች ሲሰደብ ሲንቋሸሽ ሲሸማቀቅ መሰደድ ሲያንሰው ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ሥም ለውጭ ኢንቨስተር ከ100,000 ሄክታር መሬት በላይ በነጻ በሚሰጥባት አገር ውስጥ እኛ ዜጎቿ 1 .ሜ  ከ 1000 ብር ባላነሰ ዋጋ በምንገዛበት ሁኔታ መኖር ሲያቅተን ብንሰደድ ማነው ተወቃሹ? የፖለቲካ መሪዎቹ እስከውጭ ድረስ እየሄዱ በሚማሩበት፣ በሚታከሙበት እና በሚዝናኑበት ገንዘብ ላይ ማዘዝ የማይችለው ሕዝብ በረሃብ አለንጋ ሲገረፍ፣ ነጻነቱ ሲገፈፍ፣ ቴክኒክ ለመማር እንኳ ክፍያ ሲጠየቅ፣ ሙያውን በአግባቡ ባልተማረ ሃኪም በማይገባ መድኃኒት በበሽታው ላይ ሌላ በሽታ ሲጨምር መታገስ ያልቻለ ህዝብ ቢሰደድ ነውሩ ምኑ ጋር ነው? የወገኖቻችን ሞት አብዝቶ አሳዝኖናል እና በአደባባይ ማልቀስ አለብን ብሎ የወጣ ሰላማዊ ህዝብ ላይ ዱላ የሚሰነዝር፣ አስለቃሽ ጋዝ የሚረጭ  ፖሊስ በተሰማራባት አገር ውስጥ መኖር ሲሰለቸው ሰው ቢሰደድ ማው የሚጠየቀው? በሃይማኖቱ ያበረቱኛል ያላቸው አባቶች የፖለቲካ መሪዎች ሲሆኑበት ህዝቡ ቢሰደድ ምን በደል አለበት?
ኢትዮጵያውያን በእውነት ቅዱስ ነን፡፡ ስለራሳችን ቅድስና መመስከር የተገባ ባይሆንም እኔ ግን እመሰክራለሁ፡፡ እኔ ቅዱስ አይደለሁም ህዝቡ ግን ሲበዛ ቅዱስ ነው፡፡ ለምን? በአገሩ ሰርቶ በአገሩ መኖርን የሚጠላ ለዚያውም ኢትዮጵያዊ ሰው ይገኛል ብየ አላምንም፡፡ ነገር ግን በአገሩ የሚያሰራው ሲያጣ እንዳይሰራ ያደረገውን አካል ከመቃወም፣ ረብሻ ከመፍጠር ይልቅ ስደትን ይመርጣል፡፡ ክፉን በክፉ የሚቃወም ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ማሳያው ይኸው ነው፡፡ ከግብጽ የጀመረው አብዮት ወደ ሊብያ ብሎም ወደ የመንና ሶሪያ ሲዘልቅ ተረኛ አገር ትሆናለች ተብላ ብዙዎች ይጠብቋት የነበረ ኢትዮጵያን ነው፡፡ ነገር ግን የህዝቡ ጨዋነት፣ ቅዱስነት እዚህ ላይ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃውሞ ያልተነሣው ህዝቡ ፈሪ ስለሆነ፣ የተደራጀ ፖሊስ ስላለ፣ ህዝቡ 1 ለ 5 ስለተደራጀ፣ ችግር ስላልገጠመው፣ በሰላም ስለሚኖር፣ መንግሥት እንደሚለው 11 በመቶ ስለተመነደግን፣ መሰረተ ልማት ስለተሟላልን፣ ሥራ አጥ ስለቀነሰ ወዘተ አይደለም ህዝቡ ጨዋና ቅዱስ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ በአገሩ መኖር የቸገረው ሰው ይሰደዳል፡፡ ቢሮ ክራሲ ያዛለው ሰው ይሰደዳል፡፡ ህጋዊ ሆኖ ለመሄድ ዓመት ደጅ መጥናት የሰለቸው ሰው በኮንቴነር ታፍኖ በበረሃ በጥምና በረሃብ እየተገረፈ ይሰደዳል፡፡ በቃ ምርጫ የለውማ! እዚህም ሞት እዚያም ሞት ብሎ ወስኗላ!  ለሌላው የሚያስብ ህዝብ ማለት ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው፡፡ አገሬን አልለቅም በአገሬ መብቴን አስከብራለሁ፣ ነጻነቴን እጎናጸፋለሁ የሚል ሰው የግብጹን ተቃውሞ ኢትዮጵያ ውስጥም መፍጠር አይሳነውም ነበር፡፡ ነገር ግን ርኅራኄ በማይሰማው ፖሊስ የሚገደለውን  የወገኑን ሞት፣ እልቂት  ያስባል፣ የሚወድመውን ሃብትና ንብረት፣ ቅርስ እና ታሪክ ከግምት ውስጥ ያስገባል ስለዚህ ብቸኛው አማራጭ ራሱን ይዞ መሰደድ ብቻ ነው፡፡ ለሌላው መጨነቅ፣ ክፉን በክፉ አለመመለስ (አለመቃወም) ማለት ይህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች የተባለውም ለዚህ ነው እኮ፡፡ ህዝበ ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን እንጅ መሪውን ፈርቶ አያውቅም፡፡ በዚህ ልንተማመን ይገባል፡፡ ስንቱ ገንዘብ የሞላው፣ ሁሉ የተረፈው ባለሃብት አገሩን ለቅቆ ወጥቷል? ስንቱ የተማረው የተመራመረው ከከርሰ ምድር እስከ ጠፈር አበጥሮ የሚያውቀው ምሁር ነው የተሰደደው? ታዲያ ኢትዮጵያ የተሰደዱት ለእንጀራ ፍለጋ ብቻ ነው ማለትን እንዴት እንደፍራለን፡፡ መንግሥት ራሱን መፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ኢትዮጵያኑ ለምን ተሰደዱ የሚለውን ጉዳይ ነው፡፡ ህዝቡ ሁሉ ተሰድዶ አልቆ ዛፍና ውኃውን ገደል ተራራውን ሸለቆ ኮረብታውን የሚወስዳቸው ያጡ እንስሳትን ብቻ የሚመራ ብቸኛው መንግሥት ተብሎ እንዳይነገር እፈራለሁ፡፡ ህዝቡ ያልፈለገው ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ስለዲሞክራሲ ሲል ሲለቅ እንጅ የሙጥኝ ብሎ ሲቀመጥ ያየሁት የእኛውን ልማታዊ መንግሥት ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ከውጭ በሚያገኘው ምንዛሬ ቤቱን የሚገነባ የፖለቲካ መሪ ስላለን በዚህ ላንገረም እንችል ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ ለወገኖቻችን ስደት ዋናው ተጠያቂው በመምራት ላይ ያለው መንግሥት ብቻ ነው፡፡ አየነው እኮ የሆነውን ሁሉ ዛሬ እንደድሮው ሊደልለን የሚችልበት   ምንም ወኔ የለውም፡፡ ይችን የመሰለች ቅድስት አገር ትቶ በባእድ አገር መንገላታት ያ ክፉ ስደት ግን ለምን?  አኔን የሚናፍቀኝ ያ እውቀቱ ለዓለም መብራት የሆነው የተማረው ወገናችን ሁሉ ተመልሶ በእውቀቱ አገሩን ገንብቶ ድሮ የነበራትን ኃያልነት የሚመልስበት ቀን ብቻ ነው፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃት፡፡
ታናሽ ወንድማችሁ የምሆን መልካሙ ነኝ፡፡

Monday, April 27, 2015

የ ISIS ዳግም ግድያ በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች የተባለላት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም  የአስራት የበኩራት አገር ናት፡፡ ታዲያ ይች አገር በተለያዩ ዘመናት ክርስትናን የሚቃወሙ አረመኔዎች እጅግ በርካታ ፈተናዎችን ሲያደርሱባት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ አረመኔው ግራኝ መሀመድ ጨካኟ ዮዲት ጉዲት እንዲሁም በቅርቡ ፋሽስት ኢጣሊያ ከዚያም በኋላ በኢትዮጵያ የተመሠረተው የደርግ መንግሥት በቤተክርስቲያናችን ላይ ጦራቸውን ሲያዘምቱ ምእመናንን ለሞት ሲዳርጉ ክርስትናዊ የሆኑ ትውፊቶችን ሲያጠፉ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲበርዙ መቆየታቸው የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ እነዚህ አረመኔዎች በተነሡባቸው ጊዜያት ሁሉ በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ምእመናን  እና ካሕናት ጳጳሳት ሳይቀሩ ለሞት ተዳርገዋል፡፡ እነዚያ ለሞት የተዳረጉት ወገኖቻችን በተቀደሰው የሰማዕትነት (የምስክርነት) ሥራቸው ስናወሳቸው ነበር ወደፊትም እናወሳቸዋለን እንማርባቸዋለን፡፡ ማንም ቢሆን ስለእምነቱ የመጣበትን ጠላት በትእግሥት ሊያሸንፍ ይገባዋል፡፡ የጥላቻ ማጥፊያ ብቸኛው መሳሪያ ፍቅር ነውና፡፡ ለዚያም ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በፍቅር መኖራችን ለዓለም ሁሉ ተምሳሌት ሆነን እንድንዘልቅ የረዳን፡፡
በቅርብ ቀናት ክርስትናን ለማጥፋት (ለዚያውም ጠላቴ ናት ያላትን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን) የሚንቀሳቀሰው ጨካኙ ሃይማኖታዊ ቡድን ራሱን  ISIS ብሎ የሚጠራው እስላማዊ መንግሥት በ 30 ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ተግባር አይተናል ተመልክተናል አዝነናል አልቅሰናልም፡፡ ከሃዘኑ ባሻገር ምን ተደረገ ለሚለው ግን ጥያቄው ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ የሚቀጥል ለመሆኑ እየተመለከትን ነው፡፡ እጅግ እስኪሰለቸን የምንሰማው የመገናኛ ብዙኃኑ የጋዜጠኞች ንግግር የሚያስረዳን ግን የሞቱት ኢትዮጵያውያን ህገ ወጥ ስደተኞች ናቸው በሚል ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለይ ብቻ የተመሠረተ ነው፡፡ እሽ ሕገወጥ  ስደተኞች ናቸው እንበል ISIS የሚገድለው  ሕገወጥ ስደተኛ ማነው ብሎ ነው እንዴ ከሆነ ጥሩ፡፡ እንደዚህ ከሆነ ከዚህ የምገነዘበው ነገር አለ እርሱም ISISን ያደራጀው የኢትዮጵያ መንግሥት  እንደሆነ፡፡ ለምን አደራጀው ስንል ሕገወጥ ስደተኞችን ከሕጋዊ ስደተኞች እንዲለይለት፡፡ በቃ፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኞችም ሆኑ የመንግሥት አካላት የሐይማኖት መሪዎችም ሆኑ ተራው ምእመን ሕገወጥ እና ህጋዊ ስደት የሚለውን ከአእምሯችን ፍቀን ልናወጣው ይገባል፡፡የኢትዮጵያኑ ሞት ከስደት ጋር የተያያዘ ነገር ስላልሆነ፡፡ ስንቱ ሰው ነው ዛሬ በስደት የሚኖረው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ከአንታርክቲካ በስተቀር ሰው በሚኖርባቸው አረገራት ሁሉ ተበትኖ የሚኖር ነው፡፡ ታዲያ ያ ሁሉ ሰው ተገደለ እንዴ፡፡ አልተገደለም፡፡ ለእነዚህ ሞት ዋናው ምክንያት ክርስትናቸው መስቀላቸው ብቻ ነው፡፡ አለቀ፡፡ በዚህ ልንወናበድ አይገባም፡፡ ሰማዕትነታቸውን አጉልተን ልናወጣው ይገባል እንጅ ስደታቸውን ልናጎላው የፖለቲካ ፍጆታ ልናደርገው አይገባም፡፡
ሌላው ከሃይማኖት አባቶች የሰማነው መግለጫ መሰል ንግግር ዳግም ግድያን ለመፈጸማቸው ማስረጃ ነው፡፡ ISIS ን እናወግዛለን የሚል መፈክር ይዞ መዞር ብቻውን ISISን ያጠፋል ማለት ከሆነ አምላክ ይፋረደናል፡፡ ከሃይማኖት መሪ ነን ባዮች ይልቅ የተሻሉ መምህራንን የተመለከትነው በሊብያ በረሃ ከዚያ ከውኃማው አካባቢ ነው፡፡ ስለእውነት መራራ ሞትን የታገሱት እነዚህ ቅዱሳን ሰማእታት ስለክርስትናቸው ታረዱ በጥይት ተደበደቡ ጳጳሱን ተቀድመውት መንግሥተ ሰማያትን ወረሱ፡፡ እኛ እዚህ ስለክርስትናችን ባልተፈተንበት ቦታ ሳለን የምንቀልድበትን ክርስትና እነርሱ እስከሞት ድረስ ታምነው በደማቸው ኢትዮጵያን ቀደሷት፡፡ ሲኖዶሱ ምን አለ ምን መግለጫ ሰጠ፡፡ ሊባል ይገባው የነበረው ነገር ተባለ ወይ ስንለ አልተባለም ነው መልሱ፡፡ ክርስትና ሰይፍ ለሚያነሱባችሁ ሰይፍ አንሱ አይልም እንዲያውም ቀኝ ፊትህን ለሚመታህ ግራ ፊትህን ደገሞ ስጠው ይላል፡፡ በአጠቃላይ ክርስትና ስለእምነታችሁ ስለመንግሥተ ሰማያት ተሰደዱ ሙቱ ይላል እንጅ አሳድዱ ግደሉ አይልም፡፡ ለዚህም ነው ከነማተባቸው አንገታቸውን ለስለት የሰጡት፡፡ ይህን የተቀደሰውን ሰማዕትነት ከምንም ባለመቁጠር መንግሥት ከሚዘበዝበን ፖለቲካ የበለጠ ፖለቲካዊ ዝብዘባ ከሃይማኖት መሪዎች አንፈልግም፡፡ የትኛው የሃይማኖት መሪ ነው በሊብያ የተሠዉት ኢትዮጵያውያን ስለሃይማኖታቸው ፍቅር ነው እና ሰማዕታት ናቸው ብሎ ባለማፈር የተናገረው፡፡ ይህን ብል እንዲህ እደረጋለሁ በሚል ፍርሃት ተሸብበን ወገናችን እስከመቼ አገሩን ትቶ ሲኮበልል ይኖራል፡፡ እኛ ለማንም መሬታችንን እየሰጠን በሃገራችን መኖር እንደ እሳት እየፈጀን  እስከመቼ እንቀጥላለን፡፡ አባቶች መስቀሉን ከፍ አድርገው የሚመሩትን ሕዝብ ሃዘን ካልተረዱ በጣም አሰቃቂ ግድያ ማለት እርሱ ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስን ዛሬ ላይ ምነው ባገኘናቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለፋሽስት ኢጣሊያ እንድትገዛ ከፋሽስቱ የመጣላቸውን የመኪና፣ የቤት፣ የገንዘብ እና የተለያዩ የማግባቢያ ሽልማቶች ከምንም ባለመቁጠር ኢትዮጵያ ለፋሽስቱ እንዳትገዛ በተቀደሰ መስቀላቸው በተከበረው ስልጣናቸው መላ ኢትዮጵያን አወገዙ፡፡ ይህንን ውግዘት የሰማው ፋሽስትም በጥይት ደብድቦ ገደላቸው፡፡ አያችሁ የአገር ፍቅር ማለት፡፡ በአፍ ከመናገር ባለፈ በተግባር የተረጋገጠ የአቡነ ጴጥሮስ የአገር ፍቅር፡፡ ታዲያ ዛሬ ምነው ይሄ የአገር ፍቅር ጠፋ፡፡ ምእመናን በሚከፍሉት ገንዘብ የምንተዳደር አባቶች ትንሽ ቆም ብለን  የምናስብበት ወቀት ላይ ነን፡፡
እጅግ የሰለቸኝ ሌላው ነገር ISIS የማንንም እምነት አይወክልም የሚለው የቂልነት ንግግር ነው፡፡ እስላማዊ ነኝ እያለ፣ ቁራንን ካልተቀበላችሁ ብሎ እያስገደደ፣ የሸሪአ ሕግን ተቀበሉ ብሎ እያስፈራራ የማንንም እምነት አይወክልም የሚለው አባባል ጅልነትን የሚያሳይ ነው፡፡ “ሃይማኖት አንዲት ናት የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሉ” ስንባል በዝምታ አለፍነው፡፡ አወ አሉ ብለን በራሳችን ላይ ፈረድን፡፡ የመጽሐፉን ቃል ዘንግተን መንግሥት የሚቀባጥረውን ፖለቲካ አብረን ተናገርነው፡፡ በክርስትናችን ላይ አፈርን፡፡ ቃሉ መጽሐፍ ውስጥ መኖሩንም ተጠራጠርን፡፡ ያ የመጽሐፍ  ውዱስ ቃል እንደ አንድ ተራ መፈክር ተቆጥሮ “መፈክር አንግበው” ስንባል ይህንን ለማስረዳት የሞከረ ማነው አረ ማንም፡፡ ያ የያዝነው የመጽሐፍ ቃል ሰው አልገደለም እኮ ነገር ግን ክርስቲያኖች እንዲህ አደረጉ ተባልንበት፡፡ ዛሬ 30 ንጹሃንን የገደለው እስላም የማንንም እምነት አይወክልም ማለት ምን ማለት ነው? ሙስሊሙ ማህበረሰብስ ይበል መንግስትም ይበል ሲኖዶሱ እንዴት እንዲህ ይላል፡፡ ግጭት ይቀሰቅሳል ተብሎ ታስቦ ከሆነ እኛ ክርስቲያኖች በማረድ ደም በማፍሰስ ላይ አልተመሰረትንምና አናደርገውም፡፡ እኛ ብንሆን ኖሮ እኮ አስተምረን እንመልሳቸዋለን ብለዋል ተብለን ነበር እኮ፡፡ እስላም ነን ባዮች ናቸው ያረዱን ታዲያ እነዚህ እስልምናን የማይወክሉ ከሆነ ሙስሊሙ ማህበረሰብ አስተምሮ ሊመልሳቸው ይገባል፡፡ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ  የዐረቡ ክፍል ባሳደዳቸው ጊዜ እስልምና እምነትን የሚከተሉ ሰዎችን ከነእምነታቸው ተቀብላ ያስተናገደች እንጀራዋን ቆርሳ ያበላች ብቸኛ አገር እንደሆነች ማንም የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡ ክርስቲያኑ ከእስላሙ ጋር በፍቅር እና በመተባበር በመረዳዳት እና በመተዛዘን እንኖራለን፡፡ በዚህ መዋደዳችንም ብዙ ዘመናትን አስቆጥረናል ወደፊትም እንደዚሁ እንዘልቃለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ እስላሞች ይህንን አረመኔያዊ ተግባር ላይፈጽሙት ይችላሉ ISIS የተባሉት እስላሞች ግን አድርገውታል፡፡ አባቶቻችን ደፍረው ያልተናገሩት ጉዳይ ይኼ ነው፡፡ እስላም የሆኑት ISIS ክርስቲያን የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ገድለዋል፡፡ እኛ ግን እነርሱን ለመግደል አናስብም ምክንያቱም ክርስቲያኖች ስለሆንን ማለት ነበረባቸው አላሉንምና እናዝናለን፡፡የ ISIS ዳግም ግድያ በኢትዮጵያ ተፈጽሟል የሚያሰኘን ቅሉ ይኸው ነው፡፡ ከዐረፉት ወንድሞቻችን ረድኤት በረከቱን አምላካችን ይክፈለን፡፡ አሜን፡፡

Wednesday, April 22, 2015

ሰማዕታተ ሊቢያ


ሰማዕታተ ሊቢያ
 “ሰማዕት” የሚለው ቃል ከግዕዝ ቋንቋ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ምስክርነት ማለት ነው፡፡ እምነት አንለውጥም፣ ማተብ አንበጥስም፣ ከእግዘዚአብሔር ሌላ አምላክ የለም ብለው ስለሚያመልኩት አምላክ ታምነው አንገታቸውን ለስለት ደረታቸውን ለጦር የሰጡ ሰዎች ሁሉ ሰማዕታት ይባላሉ፡፡ እነዚህ ሰማዕታት ከራሳቸው ክብር ይልቅ የእግዚአብሔርን ክብር አብልጠው በቃል የሰሙትን በተግባር የቀየሩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በንባብ ብቻ ሳይሆን በተግባር የተረጎሙ ናቸው፡፡ ከሥጋ ሞት ይልቅ የነፍስን ሞት አብልጠው የሚፈሩ ለመሆናቸው ማረጋገጫው ይህ ቅዱስ ሰማዕትነት ነው፡፡ ዓለምን እየተፈታተናት ያለው በግፍ የሰውን ልጅ እንደ እንስሳት የማረድ (ለእንስሳት ከሚሰጥ ክብር በታች)፣ በጥይት የመደብደብ አስነዋሪ እና አስቀያሚ ተግባር ላይ የተሠማሩ የሰውን ልጅ ከመጤፍ የሚቆጥሩ “ሰው መሰል ሰው በላ” ፍጡራን ናቸው (አሸባሪ የሚለው ቃል የሚገልጻቸው ስላልመሰለኝ ነው)፡፡ እነዚህ “ሰው መሰል ሰው በላ” ፍጡራን በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስሞችን ለራሳቸው እየሰጡ ዘግናኝ ተግባራትን ሲፈጽሙ ተስተውለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተወሰኑ አገራት ብቻ ተወስነው ሲፈጽሙት የነበረውን አሰቃቂ ድርጊት አሁን ላይ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ በተለያዩ የዓለም አገራት ላይ ይህን ከሰብአዊ ፍጡር የማይጠበቀውን ክፉ ሥራ እንደ ተቀደሰ ሥራ አድርገው መፈጸማቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እያየነው እና እየሰማነው ያለው ነገር እጅግ የከፋ እየሆነ መምጣቱን ነው፡፡ የአገር መከላከያ ሰራዊቱን ልብስ የመሰለ ለብሰው ሰላም አስከባሪ መስለው በመንገድ የሚጓዘውን ሁሉ ክርስቲያን መሆን አለመሆኑን እያጣሩ ክርስቲያን ከሆነ ወደ አዘጋጁት “ኮንቴነር” አፍነው በማስገባት ወደ እንግልት ቦታቸው ይወስዷቸዋል፡፡ በዚያም የእንግልት ቦታ እምነታቸውን እንዲለውጡ፣ ማተባቸውን እንዲበጥሱ በብዙ ስቃይ ያንገላቷቸዋል፡፡ ይህን ስቃይ ሳይሰቀቁ እምነታቸውን እንደማክዱ፣ ማተባቸውን እንደማይበጥሱ ካሳወቁ ወደሚቀጥለው እጅግ ዘግናኝ ወደሆነው ጉዞ ይቀጥላሉ፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ርኅራኄ በሌለበት ግፍ በስለት መቆራረጥ አልያም በጥይት በተደጋጋሚ መደብደብ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መከራ የሚደርስባቸው ስለእግዚአብሔር መንግስት፣ ስለመስቀል ክብር ስለክርስትና ነው፡፡ ክርስትና በተግባር ሲፈተሽ እንዲህ አይነት ስቃይ ውስጥ መግባትንም የሚጠይቅ መሆኑን ያረጋገጡልን ሁሉ ሰማዕታት ይባላሉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በሀሙስ ውዳሴ ማርያም እንዲህ ሲል ተናገረ፡-- “ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለእግዚአብሔር አፈሰሱ መራራ ሞትንም ታገሡ” የሰማዕትነት ሥራ ይህ ነው፡፡ 1. የዚችን ዓለም ከንቱነት መረዳትና መናቅ 2. ደምን ስለእግዚአብሔር ሲሉ ማፍሰስ (መታመን) 3. መራራ ሞትን መታገስ ሰማዕታት እነዚህ ታላላቅ ሀብታት አሏቸው፡፡ እኛ ዓለምን ለመናቅ የምንችልበት ደረጃ እና ቅድስና ላይ አልደረስንም ሰማዕታት ግን ደርሰውበታል ከዚያም በላይ አልፈውታል፡፡ እኛ ስለ እግዚአብሔር ብለን ስለእግዚአብሔር ምስክርነት አንገታችንን ለስለት ደረታችንን ለጦር አልሰጠንም፣ በእሳት አልተቃጠልንም፣ በፈላ ውኃ አልተቀቀልንም ሰማዕታት ግን የህንን ሁሉ በተግባር አረጋግጠውልናል፡፡ እኛ ሞትን እንጠላልን፡፡ ቤተሰቤን ማቄን ንብረቴን ለማን ሰጥቼ እያልን የሥጋን ሞት እንፈራለን፡፡ መከራ ለሚያጸኑብንም ከነፍስ ይልቅ የሥጋን ሞት ስለምንፈራ በመከራው እንሰቀቃለን፡፡ ሰማዕታት ግን “ሥጋን የሚገድሉትን አትፍሩ ይልቅስ ነፍስን የሚገድሉትን ፍሩ” የሚለውን የወንጌል ቃል በተግባር መራራ የሆነውን ሞት ታግሰው አሳይተውናል፡፡ ሰማዕትነት በብዙ መንገድ ሊፈጸም ይችላል፡፡ የሰማዕትነት መሠረት ግን አንድ ብቻ ነው እርሱም “አምላኬን አልክድም እምነቴን አልለውጥም ማለት ነው” ይህንን ስንል ድርጊት ፈጻሚዎች በስለት፣ በእሳት፣ በጦር፣ በውኃ፣ በተለያዩ ዘግናኝ ተግባራት ግድያ ሊፈጽሙብን ይችላሉ፡፡ እነዚህ የሚፈጸሙብን አስነዋሪ ተግባራት የተናገርነውን ቃል በተግባር የመግለጣችን፣ ለቃሉ መታመናችንን የምናሳይበት ማረጋገጫ ነው፡፡ ሰማዕትነት ድሮ በእነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በእነ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ በእነ ቅዱስ ቂርቆስ… ብቻ የቀረ አይደለም ዛሬ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ሰማዕትነት እየተፈጸመ ያለ ቅደስና ነው፡፡ ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ በተለያዩ አገራት እየተገደሉ ያሉ ወገኖቻችን ሰማዕታት ናቸው፡፡ ይህን የሰማዕትነት ክብር የተጎናጸፉ በርካታ የዓለም አገራት ዜጎች አሉ፡፡ በቅርቡ ሚያዝያ 11 /2007 ዓ.ም ደግሞ ይህ የሰማዕትነት ክብር ለቅድስቲቱ አገር ለኢትዮጵያ ደረሳት፡፡ በአፍሪካዊቱ አገር በሊቢያ ይኖሩ የነበሩ 30 ኢትዮጵያውያን ራሱን “እስላማዊ መንግሥት” በእንግሊዝኛ አጠራሩ “ISLAMIC STATE (IS)” ብሎ የሚጠራው የ “ሰው መሰል ሰው በላ” ስብስብ ሰብአዊነት በጎደለው ጭካኔ በስለት አርዶ በጥይት ደብድቦ በግፍ ገደላቸው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን በሃይማኖታቸው ላይ ለሚመጣ ነገር ድርድር የሌላቸው ናቸው፡፡ መራራ የሆነ ሞትን ለመታገስ የበቁት ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ የመጣ ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህ ሰማዕታት እምነታቸውን ቢለውጡ፣ ማተባቸውን ቢበጥሱ ኖሮ ለዚህ የሰማዕትነት ክብር ባልበቁ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ በንባብ የምንሰማውን የወንጌል ቃል እነርሱ እንዲህ ነው ብለው በተግባር ገለጡልን ለእኛም አሳዩን እኛም አየነው፡፡ ሰማዕትነትን እኛም ዛሬ አየነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ገድል ሲነበብ “እንዴት ያን ያህል መከራ የሰው ልጅ ሊሸከም ይችላል” እያልን ልባችንን ለኑፋቄ ስንከፍት የነበርን ሰዎች እዩት እንግዲህ እንዲህ አይነቱን አሰቃቂ ተግባር ግፍ እና መከራ የእኛው ልጆች፣ የእኛው ወንድሞች በሚገባን ኢትዮጵያዊ ቋንቋ እና ለዛ ሲያስረዱን፡፡ እነዚህን ሰማዕታት የወለዱ እናቶች የተባረኩ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ባለማዎቅ እነዚህን ሰማዕታት “ነፍስ ይማር” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ነፍስ ይማር የምንል እኮ ክርስተናቸውን በተግባር ስለእግዚአብሔር ምስክር ሆነው ስለሞቱ ሰማዕታት አይደለም፡፡ እርሱ የራሱ የሆነ ቦታ አለው እነዚህ ጋር ግር ቦታ የለውም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዐረፈ ጊዜ “ነፍስ ይማር” ያሉ ሰዎች ከነበሩ ተሳስተዋል፡፡ ከሰማዕታቱ ረድኤትና በረከት አምላካችን እግዚአብሔር ያካፍለን አሜን፡፡

Wednesday, April 1, 2015

የተዋሱትን ማበላሸት

ሰላም ጤና ይስጥልኝ እንደምን ከረማችሁ ውድ ጓደኞቼ፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር በያላችሁበት ይጠብቃችሁ፡፡ ከጠፋንበት ፈልጎ በቸርነቱ ጥላ ሥር ለሚያሳርፈን፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በነበረ ዓለምንም አሳልፎ በሚኖር አምላክ ረድኤት ተከልለን ለምንኖር ለእኛ ነገን በቸርነቱ ይጠብቀን ዘንድ ለእርሱ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ የሰውን ልጅ ከፍጥረት ሁሉ አክብሮ እና አልቆ መፍጠሩን ሁልጊዜም ቢሆን ልንዘነጋው የሚገባ አይደለም፡፡ እኛ ከመላእክትም በላይ እጅግ የምንዋብበት ትልቅ ጸጋን አልብሶናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ባመሰገነበት ድርሳኑ እንዲህ አለ “አንች ከመላእክት ትበልጫለሽ…” እንግዲህ ልብ እናድርግ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ትባላለህ፡፡ እግዚአብሔር እጅህን ሲሰጥህ አንድ ብቻ ማድረግ ሲቻለው ሁለት አደረገልህ፡፡ ለምን ሁለት እጅ ሁት እግር፣ ሁለት ዓይን… ኖረኝ ብለህ አትጨነቅ አትመራመር ይሆናል፡፡ እርሱ ግን አንተ ላንተ ከምታስበው በላይ ስላን ስለሚያስብልህ ሁለት ሁለት አድርጎ ፈጠረልህ፡፡ ምክንያቱም አንዱ ቢዝል ሁለተኛው እንዲያበረታው ነው፡፡ አንዱ በሆነ ጉዳት ሥራውን ቢያቆም ሌላኛው ተክቶ እንዲሰራልህ ነው፡፡ አንተ ግን ይህን ሁሉ ላታስተውለው ትችላለህ፡፡ እግዚአብሔር የሰጠህን ነገር ታበላሸዋለህ፡፡ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ሀብት በነጻ ሲሰጥህ ሠርተህ እንድትከብርበት አመስግነህ እንድትጸድቅበት ነው፡፡ ወደ ኃጢአት ስትጓዝ እግር ባይኖረኝ ኖሮ ይህ ኃጢአት ማድረግ እችል ነበርን? ብለህ ራስህን ጠይቅ፡፡ አይተህ ስትመኝ በልብህም ስታመነዝር ዓይን ባይኖረኝ ኖሮ ይህን ኃጢአት እሰራ ነበርን? ብለህ ራስህን ጠይቅ፡፡ ሰውን የሚስቀይም ንግግር ስትናገር ወይም አሉባልታ እና ሃሜት ስታበዛ ምላስ ወይም አፍ ባይኖረኝ ኖሮ ይህን ኃጢአት እሰራ ነበርን? ብለህ ራስህን ጠይቅ፡፡ ፊት አይተህ ስታደላ ይህን የስልጣን ወንበር አምላክ ባይሰጠኝ ኖሮ ይህን ኃጢአት እሰራ ነበርን? ብለህ ራስህን ጠይቅ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ መልስ መስጠት ከቻልክ አንተ ከኃጢአት ትርቃለህ ማለት ነው፡፡ በዓለምሰው ናት፡፡ ነገር ግን መላእክት ሳይቀሩ ይሰግዱላትና እጅግ ያከብሯት ይፈሯትም ነበር፡፡ ለምን ብንል አምላክን ለመውለድ በቅታ ተገኝታለችና ነው፡፡ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ በመፈጠሯ እኛን ትመስላለች፡፡ ስለዚህ ሰው በመሆኗ እንመካባታለን፡፡ ሌላው ግን አምላክ አክብሮ የፈጠረን ለመሆናችን ማሳያው “ሰውን በአርአያችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” ማለቱ ነው፡፡ የእግዚአብሔር የማይመረመር አርአያ እና አምሳል እኛ ነን፡፡ ምሳሌውን እና አርአያውን አስመስሎ የፈጠረው ፍጡር ሰው ለመሆኑ ብዙ ምስክሮችን ልንሰጥ እንችላለን ነገር ግን ለመግቢያነት ያህል ይህንን ካነሳን ይበቃናል፡፡ እንግዲህ የሰው ልጅ የከበረ ፍጥረት እንደሆነ ከተረዳን እግዚአብሔር እኛን ያከበረበት በርካታ ስጦታ ሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን ስጦታውን ልቀማችሁ መልሱልኝ ስላላለን ራሳችን የፈጠርነው ያህል እንቀልድበታለን( እናበላሸዋለን)፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠንን ነገር እንደተዋስነው አድርገን እናስብ፡፡ እግር፣ እጅ፣ ዓይን፣ ጆሮ፣ ምላስ፣ አፍንጫ፣ ጸጉር፣ ልብ፣ ኩላሊት ወዘተ… ይቅርታ ዘርዝረን ልንጨርሰው ስለማንችል ነው፡፡ በምድር ላይ ያሉትን ሁሉ ንዱ ግዙ ስለተባልን የምድር ንጉሧ እኛ ነን፡፡ ይህም ማለት በምድር ያሉ ሀብታት ሁሉ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠን ሀብታችን ናቸው ማለት ነው፡፡ መሬት፣ ጸሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት፣ አየር፣ ውኃ፣ ነፋስ፣ ዕጽዋት ወዘተ… ስለማያልቁ እነዚህን ብቻ ጠቀስኩ እንጅ ምኑ ተዘርዝሮ የፈጣሪ ውለታ፡፡ የሰው ልጅ ትልቅ ሲሆን እጅግ ትንሽ፣ ክቡር ሲሆን እጅግ ወራዳ፣ ሃብታም ሲሆን እጅግ ምስኪን ለመሆኑ ምክንያት እግዚአብሔር ነፍጎት ሳይሆን ከእግዚአብሔር የተበረከተለትን ስጦታ (የተዋሰውን ነገር) በአግባቡ ባለመጠቀሙ ነው፡፡ እግዚአብሔር ወደ ቤቱ እንድትሄድበት እግር ሰጠህ አንተም ተቀበልህ ነገር ግን ይህን ትልቅ ስጦታ ዘንግተህ ወደ ጠንቅ ዋይ፣ መተተኛ፣ ስርቆት… ብትሄድበት አንተ የተዋስከውን በአግባቡ መጠቀም ያቃተህ ሰነፍ ስትኖር ከሌሎች ፍጡራን ጋርም በሰላም መኖር አለብህ ምክንያቱም አምላክ የሰጠህ እንድትጠቀምባቸው እንጅ ኃጢአት እንድትሠራባቸው አይደለምና፡፡ አብዝተህ ስትጨፍር፣ ስትዘል ፣ ስትዘፍን፣ ስትሰክር … የተሸከመችህን ምድር ልብ ልትላት ይገባሃል፡፡ አብዝተህ ስትዘልባት ምድር እንደ እንቁላል “ጥርቁስ” ብትል እና ተከፍታ ብትውጥህስ፡፡ ስለዚህ ሁሉ ነገር በልክ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ወንድሜ ሆይ!! አምላክ የሰጠህን ስጦታ (መክሊት) በአግባቡ ልትጠቀምበት ይገባል፡፡ ባለህ ነገር ጥሩ ሥራ ልትሠራ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ያለን ሃብት ሁሉ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት በቅጽበት ሊጠፋ የሚችል ነው፡፡ ስንት ወገኖቻችን በመኪና አደጋ፤ በመብራት፣ በእሳት እና በመሳሰሉት አደጋዎች ድሮ የነበራቸውን ውበት አጥተው ዓይናቸው ፈርጦ እግራቸው ተቆርጦ ቀርተዋል፡፡ ይህንን ልብ ልንለው ይገባናል፡፡ እግር፣ እጅ፣ ዓይን፣ ጆሮ፣ ምላስ፣ አፍንጫ፣ ጸጉር፣ ልብ፣ ኩላሊት ወዘተ… የተሰጡን ትልቅ ስጦታዎች ናቸውና በእነዚህ ስጦታዎች በአግባቡ ልንጠቀም ይገባናል፡፡ የተዋስነውን ይህን ሃብት ልናበላሸው አይገባም፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡