====================
የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ
ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፳፮።
******
ዘከመ ጸለየ ኢየሱስ በጌቴሴማን።
፴፮፡ ወእምዝ ሖረ እግዚእ ኢየሱስ ምስሌሆሙ ውስተ ዓፀደ ወይን
ዘስሙ ጌቴሴማን።
፴፮፡ ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ ጌቴሴማን ከሚባለው
ወይን ቦታ ሄደ።
ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ንበሩ ዝየ እስከ ሶበ አሐውር ከሀ ወእጼሊ።
ደቀ መዛሙርቱን ከዚያ ሄጄ አስክጸልይ ድረስ ከዚህ ቆዩ አላቸው፡፡
አንድም እጼሊ ይላል እጸልይ ዘንድ፡፡
******
፴፯፡ ወነሥኦሙ ምስሌሁ ለጴጥሮስ ወለ፪ሆሙ ደቂቀ ዘብዴዎስ
******
፴፯፡ ሦስቱን ባለሟሎቹን አስከትሎ ሄዶ ስምንቱን በጌቴሴማኒ
ትቶ፡፡
ወአኀዘ ይተክዝ ወይኅዝን፡፡
******
፴፰፡ ወእምዝ ይቤሎሙ ተከዘት ነፍስየ እስከ ለሞት፡፡
******
፴፰፡ ከዚህ በኋላ ለደቀመዛሙርቱ ነፍሴ እስከ መለየት ደርሳ
አዘነች አላቸው፡፡
ወንበሩ ዝየ
ከዚህ ቆዩ፡፡
ወትግሁ ምስሌየ
ከእኔ ጋር ለመኖር እንደ እኔ ተግታችሁ አመልክቱ፡፡
******
፴፱፡ ወተአተተ ሕቀ እምህየ ወሰገደ በገጹ።
******
፴፱፡ ከዚያ ጥቂት እልፍ ብሎ ግንባሩን ምድር አስነክቶ ሰገደ።
በሉቃስ መጠነ ሙጋረ ዕብን ይላል ደንጊያ ወርውሮ እስከሚደርስበት፡፡
ወጸለየ
አመለከተ፡፡
ወይቤ ኦ አቡየ እመሰ ይትከሃል ይኅልፍ እምኔየ ዝንቱ ጽዋዕ፡፡
ያለኔ ሞት የዓለሙ ድኅነት ያለኔ ሐሣር የዓለሙ ክብር አይቻልም
እንጂ የሚቻልስ ከሆነ ይህ ጽዋዓ ሞት ይለፍልኝ
ወባሕቱ ፈቃደ ዚአከ ይኩን ወአኮ ፈቃደ ዚአየ።
ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይደረግ እላለሁ እንጂ የኔ ፈቃድ ይደረግ
አልልም፡፡
አንድም በኔ ሞት የዓለም ድኅነት በኔ ኃሣር የዓለም ክብር የሚቻልስ
ከሆነ እኔ ከሞትሁላቸው ከኔ ሞት የተነሣ ይህ ጽዋዓ ሞት ይቅርላቸው፡፡
አንድም ከኔ ለምዕመናን ይለፍላቸው እኔን አብነት አድርገው ይሙቱ።
ወባሕቱ ፈቃደ ዚአከ ይኩን ወአኮ ፈቃደ ዚአየ።
ነገር ግን የኔ ፈቃድ ከአንተ ፈቃድ ልዩ ሁኖ የኔ ፈቃድ ይሁን
አልልም። የኔ ፈቃድ ከአንተ ፈቃድ ጋራ አንድ ነውና ያንተ ፈቃድ ይሁን አላለሁ እንጂ፡፡
******
፵፡ ወሖረ ኀበ አርዳኢሁ፡፡
******
፵፡ ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄደ፡፡
ወረከቦሙ እንዘ ይነውሙ፡፡
ተኝተው አገኛቸው፡፡
ወይቤሎ ለጴጥሮስ ከመዝኑ ስአንክሙ ተጊሃ አሐተ ሰዓተ ምስሌየ።
ጴጥሮስን ከኔ ጋራ ለመኖር እንደ እኔ አንድ ሰዓት መትጋት ተሳናችሁ
አለው፡፡
******
፵፩፡ ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፡፡
******
፵፩፡ ወደ ኃጢአት ወደ ክህደት ወደ መከራ ወደ ገሃነም እንዳትገቡ
ተግታችሁ ለምኑ።
እስመ መንፈስ ይፈቅድ።
ነፍስ ሥራ ልትሠራ ትወዳለችና ትግሁ።
ወሥጋ ይደክም።
ሥጋ ግን ደካማ ነውና ኢትባኡ ላለው።
******
፵፪፡ ወካዕበ ሖረ ወጸለየ።
******
፵፪፡ ሁለተኛ ሂዶ አመለከተ፡፡
ወይቤ እመ ይትከሃል ይኅልፍ እምኔየ ዝንቱ ጽዋዕ እንበለ እስተዮ
ይኩን ፈቃድከ። እንዳለፈው በል።
******
፵፫፡ ወገብአ ካዕበ ኀበ አርዳኢሁ።
******
፵፫፡ ሁለተኛ ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄደ፡፡
ወረከቦሙ እንዘ ይነውሙ።
ተኝተው አገኛቸው፡፡
እስመ ከብዳ አዕይንቲሆሙ በድቃስ።
እንቅልፍ ጸንቶባቸዋልና በልተው ጠጥተዋልና።
******
፵፬፡ ወኀደጎሙ ወሖረ ካዕበ በሣልስት ወጸለየ ኪያሁ ከመ ቃለ
እንዘ ይብል።
******
፵፬፡ ሦስተኛ ሂዶ ያነኑ ጸለየ ለቀረበው ካዕበ ለመጀመሪያው
ሣልሰ አለ፡፡ ሦስት ጊዜ መሆኑ የሦስትነት። ቃሉ አለመለወጡ የአንድነት ምሳሌ።
******
፵፭፡ ወእምዝ ገብአ ካዕበ ኀበ አርዳኢሁ።
******
፵፭፡
ከዚህ በኋላ ሁለተኛ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደ።
ወይቤሎሙ ኑሙ እንከ ወአእርፉ።
ከእንግዲህስ ወዲህ ዕረፉ አላቸው፣ ጊዜው ነውና ንሣእ ሀካይ
ሥጋየ መክፈልተከ እንዲል፡፡
አንድም እኔ ካስሁላችሁ ዕረፍተ ነፍስ ዕረፉ።
አንድም ይሁዳ አራት ቤት ጭፍራ ይዞ የሚመጣ ነውና አያሳርፋችሁም
እንጂ ካሳረፋችሁስ ዕረፉ ለማለት።
ናሁ በጽሐ ጊዜሁ ወያገብዕዎ ለወልደ እጓለ እመሕያው ውስተ አደ
ኃጥአን።
እነሆ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ በኃጥአን እጅ የሚያዝበት
ጊዜ ደርሷል አላቸው።
******
፵፮፡ ተንሥኡ ንሑር ናሁ በጽሐ ዘያገብአኒ።
******
፵፮፡ የሚያሲዘኝ ይሁዳ እነሆ መጥቷል ተነሡ እንሂድ አላቸው፡፡
******
ዘከመ አግብኦ ይሁዳ ለክርስቶስ ወዘከመ ተእኅዘ
፵፯፡ ወእንዘ ዘንተ ይትናገር ናሁ በጽሐ ይሁዳ ዘያገብዖ እም፲ቱ
ወ፪ቱ ፩ዱ፡፡ ማር ፲፬፥፵፫፡፡ ሉቃ ፲፪፥፵፯፡፡ ዮሐ ፲፰፥፫፡፡
******
፵፯፡ ይህን ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ ሊያሲዘው መጣ፡፡
ወመጽኡ ምስሌሁ ብዙኃን ሰብእ በመጣብሕ ወበአብትር እምኀቤሆሙ
ለሊቃነ ካህናት ወለሊቃናተ ሕዝብ፡፡
ሾተል ጎመድ የያዙ ብዙ ሰዎች ከሊቃነ ካህናት ዘንድ ከእሱ ጋራ
መጡ፡፡
(ሐተታ) አምስት ገበያ ሰው ይከተለዋል አግባ መልስ ብሎ ቢጣላንሳ
ብለው እሳቸው ከጲላጦስ ዘንድ ይዘው ይመጣሉ እሱ ከእነሱ ተቀብሎ ይዞ መጥቷልና፡፡
******
፵፰፡ ወዘያገብዖ። ወሀቦሙ ትእምርተ እንዘ ይብል ዘሰዓምኩ ውእቱ
ኪያሁ አኃዙ።
******
፵፰፡ የሚያሲዘው ይሁዳ የምስመው እሱ ነው እሱን ያዙ ብሎ ምልክት
ሰጣቸው፡፡
አንድም የሚያሲዝበትን ምልክት ነገራቸው።
******
፵፱፡ ወቀርበ ይእተ ጊዜ ኀበ እግዚእ ኢየሱስ ወሰዓሞ ወይቤሎ
በሀ ረቢ።
******
፵፱፡ ወደ ጌታ ቀርቦ መምህር ቢሰኛህን ጥለኛህን አያውለው አያሳድረው
ብሎ እጅ ነሳው፡፡
(ሐተታ) ከሱን ሌላ ቢሰኛ ጠበኛ አለው አያውለኝ አያሳድረኝ
ሲያሰኘው ነው፡፡
******
፶፡ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ በእንተ ዝንቱኑ መጻእከ አርክየ።
******
፶፡ ወዳጄ ትእምርተ ፍቅሩን ትእምርተ ጸብእ አድርገኸው መጣህን
አለው።
ወእምዝ ቀርቡ ወአንሥኡ እደዊሆሙ ወአሐዝዎ ለእግዚእ ኢየሱስ።
እጃቸውን አንስተው ማለት ጌታን አጽንተው ያዙት።
******
፶፩፡ ወናሁ ተንሥአ እምእለ ምስሌሁ ለእግዚእ ኢየሱስ ሰፍሐ እዴሁ ወመልሐ መጥባሕቶ ወዘበጦ ለገብረ ሊቀ ካህናት።
******
፶፩፡ ከጌታ ጋራ ካሉት አንዱ ተነሥቶ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን
ባሪያ መታው።
ወመተሮ ዕዝኖ ዘየማን፣
ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው ትፈቅድኑ ንዝብጦሙ ብለውታል በሉቃስ፡፡
አብሮ መብላት አብሮ ለመሞት እንጂ ነው እንበላቸው እንበላቸው ተባብለዋል። እሱ ፈጣን ነውና መታው ቀኝ ጀሮውን ቈረጠው። ከመታው
አንገቱን አይለውም ቢሉ የካህን እጅ አያቀናምና ለአንገቱ ያለው ለጆሮው ሆነ።
አንድም አንገቱን ብሎት ቢሆን በሞተ ነበር። የጌታም ሞት ርትዕ
በተባለ ነበርና። ጆሮውንሳ ቢሉ በተአምራት ቀጥሎለታል፡፡ ጆሮ የቀጠለ አንገት መቀጠል ይሳነዋልን ብሎ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም፣
ትንቢት ለትትቀረጽ ይእቲ ዕዝን እንተ ኢትሰምዖ ለውእቱ ነቢይ ተብሎ ተነግሯል። ምሳሌም ወለእመ አጥረይከ ገብረ ዕብራዌ ቅንዮ ስድስተ ዓመተ ወበሳብዕ ዓም አግዕዞ በከንቱ።
ዕብራዊ ባሪያ ቢኖርህ በደመወዝ ገዝተህ በሰባተኛው ዓመት ገንዘብ
ሳትሰጥ ነጻ አውጣው ትላለች ኦሪት፡፡ እሱ ግን የጌታዬ ባሕርዩ ተስማምቶኛል። የእመቤቴ እንጀራዋ ወጧ ጣፍጦኛል ነጻ መውጣቱ ይቅርብኝ
ያለ እንደሆነ ከቤተ እግዚአብሔር ወስደህ ከመድረኩ አስተኝተህ ጆሮውን ተርትረህ አፍንጫውን ሰቊረህ እስከ ዕለተ ሞቱ ግዛው ትላለች
ኦሪት። እንደዚህም ሁሉ በሰባተኛው ሽህ ለዲያብሎስ ከመገዛት ላወጣችሁ መጥቼ ነበር አናምን ካላችሁ በሥጋችሁ ቄሣር በነፍሳችሁ ዲያብሎስ
ይሠልጥንባችሁ ለማለት። ያውስ ቢሆን ግራዪቱ አለመሆኑዋ ቀኝቱ መሆኑዋ ስለምን ቢሉ ከነገደ ይሁዳ የተወለዱ ቀኝ ቀኝ አካላቸውን
እየተቀቡ መንግሥት ከነገደ ሌዊ የተወለዱ ቀኝ ቀኝ አካላቸውን እየተቀቡ ክህነትን ገንዘብ ያደርጉ ነበር ክህነትንም መንግሥትንም
እንዳሳለፈባቸው ለማጠየቅ በቀኝ ጆሮው ምትረትን አዘዘበት።
******
፶፪፡ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ አግብእ ለመጥባሕትከ ውስተ ቤታ።
ዘፍጥ ፱፥፮፡፡ ራዕ ፲፫፥፲፡፡
******
፶፪፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን ሾተልህን ወደ
አፎት ቊጣህን ወደ ትዕግሥት መልስ አለው።
እስመ ኵሎሙ እለ መጥባሕተ ያነሥኡ በመጥባሕት ይመውቱ
በሾተል የገደሉ ሁሉ በሾተል ይሞታሉና።
******
፶፫፡ ይመስለክሙኑ ዘኢይክል አስተብቊዖቶ ለአቡየ ከመ ይፈኑ
ሊተ ዘይበዝኁ እም፲ቱ ወ፪ቱ ሠራዊተ መላእክት።
፶፫፡ ከአሥራ ሁለቱ ነገደ መላእክት የሚበዙትን ይልክልኝ ዘንድ
አባቴን መለመን መማለድ የማይቻለኝ ይመስላችኋልን
******
ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ
በየነ
ደብረ
ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
24/10/2011
ዓ.ም