Thursday, June 27, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 124


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ደናግል ጠባባት ወአብዳት፡፡
ምዕራፍ ፳፭።
                    ******        
፴፪፡ ወይትጋብዑ ኵሎሙ አሕዛብ ቅድሜሁ።
                    ******     
፴፪፡ ሙታን ሁሉ ከሱ ዘንድ ይሰበሰባሉ።
ወይፈልጦሙ ዘዘዚአሆሙ።
እየራስ እየራሳቸው ይለያቸዋል
ከመ እንተ ይፈልጥ ኖላዊ አባግዓ አምአጣሊ።
እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንዲለይ ጻድቃንን ከኃጥአን ይለያቸዋል።
                    ******     
፴፫፡ ወያቀውም አባግዓ በየማኑ።
                    ******     
፴፫፡ ጻድቃንን በቀኙ ያቆማቸዋል።
ወአጣሌ በጸጋሙ።
ኃጥአንንም በግራው ያቆማቸዋል።
(ሐተታ) ጻድቃንን አባግዕ አላቸው በግ ትሑት ነው ወደ ምድር እያየ ይሄዳል። ጻድቃንም ዕለተ ሞታቸውን እያሰቡ ይኖራሉና፡፡ ዓብድ ውእቱ ዘይሄሊ ዘእንበለ መቃብሩ ዘውእቱ ርስቱ እንዲል። በግ ኃፍረቷን በላቷ ትሰውራለች፣ ጻድቃንም የራሳቸውን ኃጢአት በንስሐ የወንድማቸውን ኃጢአት በትእግሥት ይሠውራሉና።
አንድም በግ ጭቃውን አይጸየፈውም ጻድቃንም መከራውን አይሰቀቁትምና።
አንድም በግ ከዋለበት አይታወቅም፤ ጻድቃንም ካሉበት አይታወቁምና፡፡
አንድም ከበግ አውሬ አንዱን የነጠቀለት እንደሆነ ይሸሻል ከሸሸም በኋላ አይመለስም በግ ከበረረ የሰው ልጅ ከተመረረ እንዲሉ። ጻድቃንም ከባልንጀራቸው አንዱ የሞተ እንደሆነ ይመንናሉ ከመነኑም በኋላ አይመለሱምና።
አንድም በግ ኑሮው በደጋ ነው ጻድቃንም ኑሯቸው በደጋ መንግሥተ ሰማይ ነውና። በቀኝ ያቆማቸዋል አለ የሚመጣው በክበበ ትስብእት ነውና።
አንድም ቀኝ ኃያል ነው ጻድቃንም ለበጎ ሥራ ኃያላን ናቸውና።
አንድም ቀኝ ፈጣን ነው ፈጣኖች ናቸውና ቅን ነው ቅኖች ናቸውና።
አንድም በክብርም ሲል ነው፡፡
ኃጥአንን አጣሊ አላቸው ፍየል ትዕቢተኛ ናት ሽቅብ ሽቅብ ትመለከታለች። ኃጥአንም ትዕቢተኞች ናቸውና፡፡
አንድም ፍየል ኃፍረቷን ባላቷ አትሠውርም ኃጥአንም የወንድማቸውን ኃጢአት በትእግሥት የራሳቸውን ኃጢአት በንስሐ አይሠውሩትምና፡፡
አንድም ፍየል ጭቃውን ይጸየፈዋል። ኃጥአንም መከራውን ይሰቀቁታልና።
አንድም ፍየል ከዋለበት ሁሉ ከእህል ከተክል እየገባ ሰው ሲያሳዝን ይውላል፣ ኃጥአንም ሰው ሲያሳዝኑ ይኖራሉና።
አንድም ፍየል አንዱን አውሬ የነጠቀበት እንደሆነ ለጊዜው ይሸሻል ኋላ ችፍ እያለ ይቀርባል እየነጠቀ ይፈጀዋል፡፡ ኃጥአንም ከወገናቸው አንድ የሞተ እንደሆነ መነንን ይላሉ ተመልሰው በርስቱ በጉልቱ በቤቱ በንብረቱ ሲጣሉ ይገኛሉና።
አንድም ፍየል ኑሮው ቈላ ነው ኃጥአንም ኑራቸው ቈላ ገሃነም ነውና። በግራው ያቆማቸዋል አለ የሚመጣ በክበበ ትስብእት ነውና፡፡
አንድም። ግራ ደካማ ነው ኃጥአንም በጎ ሥራ ለመሥራት ደካሞች ናቸውና። ግራ ኅዱዕ ነው በጎ ሥራ ከመሥራት ኅዱአን ናቸውና። ጠማማ ነው ጠማሞች ናቸውና፣ በኃሣርም ሲል ነው፡፡
                    ******     
፴፬፡ አሜሃ ይቤሎሙ ንጉሥ ለእለ በየማኑ ንዑ ኀቤየ ቡሩካኑ
ለአቡየ ትረሱ መንግሥተ ሰማያት ዘድልው ለክሙ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም።
                    ******     
፴፬፡ ያን ጊዜ ንጉሥ ክርስቶከ በቀኙ ያሉ ጻድቃንን በረከተ ገሪዛን ያደረባችሁ በረከተ ነፍስ ያላችሁ ዓለም ሳይፈጠር በጣዕም በመዓዛ በስን በብርሃን ያዘጋጀላችሁ መንግሥተ ሰማይን ትወርሱ ዘንድ ወደኔ ኑ ይላቸዋል። ወአስተዳሎኩ እምቅድመ ይኩን ዓለሞሙ ለእለ ይነብሩ ውስቴታ እንዲል የሚመጣ በክበበ ትስብእት ነውና ወደኔ ኑ አለ።
አንድም ትእምርተ ፍቅር ነው፡፡
                    ******     
፴፭፡ እስመ ርኅብኩ ወአብላእክሙኒ፡፡ ኢሳ ፶፰፥፯። ሕዝ ፲፰፥፯-፲፮።
                    ******     
፴፭፡ ብራብ አብልታችሁኛል።
ጸማዕኩ ወአስተይክሙኒ።
ብጠማ አጠጥታችሁኛልና።
ነግደ ኮንኩ ወተወከፍክሙኒ፤
እንግዳ ብሆን ተተብላችሁኛልና።
                    ******     
፴፮፡ ዓረቁ ወአልበስክሙኒ። መክ ፯፥፴፮።
                    ******     
፴፮፡ ብታረዝ አልብሳችሁኛልና።
ደወይኩ ወሐወፅክሙኒ።
ብታመም ጠይቃችሁኛልና።
ተሞቃሕኩ ወመጻእክሙ ኀቤየ ወነበብክሙኒ።
ብታሠር ወደኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና።
(ሐተታ) ካልጀመሩት አይሆንምና አብላዕክሙኒ አስተይክሙኒ ተወከፍክሙኒ አልበስክሙኒ ሐወፅክሙኒ ነበብክሙኒ አለ የመንግሥተ ሰማይ ዋጋ አይሆንምና። አጠገባችሁኝ አኖራችሁኝ አስጌጣችሁኝ አዳናችሁኝ አስፈታችሁኝ አላለም ይህም ሦስቱ የባለጠጎች ሦስቱ የነዳያን ነው። ርኅብኩ ዓረቁ ተሞቃሕኩ የባለጠጎች። ጸማዕኩ ነግደ ኮንኩ ደወይኩ የነዳያን። አልብከኑ ጽዋዓ ማይ ቈሪር ለአስትዮ ፅሙዕ አልብክኑ ጠሪፊሬር ለአኅድሮ ነግድ አልብከኑ እግር ለሐውፆ ድውይ እንዲል።
አንድም ለመምሕራን። በክህደት ምክንያት ብራብ ብጠማ አስተምራችሁኛልና። በክህደት እንግዳ ብሆን በትምህርት ተቀብላችሁኛልና።፡ በክሀደት ምክንያት ልጅነት ባይሰጠኝ በሃይማኖት እንዲሰጠኝ አድርጋችኋልና። በክህደት ብታመም በትምህርት ጠይቃችሁኛልና። በማዕሠረ ክህደት ብታሠር በትምህርት አስፈትታችሁኛልና።
አንድም ለቀሳውስት በኃጢአት ከሥጋው ከደሙ ብከለከል በንስሐ ሥጋውን ደሙን ሰጥታችሁኛልና። በኃጢአት እንግዳ ብሆን በንስሐ ተቀብላችሁኛልና። ልጅነት በኃጢአት ቢነሣኝ በንስሐ እንዲመለስልኝ አድርጋችሁኛልና። በማዕሠረ ኃጢአት ብታሠር በንስሐ አስፈትታችሁኛልና።
አንድም አንድ ወገን ለባሕታውያን ተባሕትዎ ብይዝ በተባሕትዎ መስላችሁኛልና።
                    ******     
፴፯፡ አሜሃ ያወሥኡ ጻድቃን እንዘ ይብሉ እግዚኦ ማዕዜኑ ርኢናከ ርኁበከ ወአብላዕናከ።
                    ******     
፴፯፡ ጻድቃንም ሰርተውት ያልሠሩት ይመስላቸዋል ከትሕትና ወደ ትሕትና ይሄዳሉና አቤቱ መቼ ተርበህ አይተንህ አብልተንህ።
                    ******     
፴፰፡ ወፅሙዓከ ወአስተይናከ።
                    ******     
፴፰፡ መቼ ተጠምተህ አይተንህ አጠጥተንህ።
ወማዕዜ ርኢናከ እንግዳከ ወተወከፍናከ።
ምን ጊዜ እንግዳ ሆነህ አይተንህ ተቀብለንህ።
ወዕሩቀከ ወአልበስናከ።
ምን ጊዜ ታርዘሕ አይተንህ አልብሰንህ።
                    ******     
፴፱፡ ወድውየከኒ ወሐወፅናከ።
                    ******     
፴፱፡ ምን ጊዜ ታመህ አይተንህ ጠይቀንህ።
ወሙቁሐከኒ ወመጻእነ ኀቤከ ወነበብናከ።
መቼ ታሥረህ አስፈታንህ ጠየቅንህ ይሉታል።
                    ******      
፵፡ ወይቤሉሙ አማን እብለክሙ ኵሎ ዘገበርክሙ ለ፩ዱ እምእሉ ንዑሳን አኃውየ እለ የአምኑ ብየ ሊተ ገበርክሙ።
                    ******     
፵፡ በእኔ ከአመኑ ምዕመናን ለአንዱ ያደረጋችሁ ለእኔ አደረጋችሁልኝ ለአንዱ ያደረጋችሁ ለኔ ማድረጋችሁ ነው ብሎ በእውነት ይመልስላቸዋል።
                    ******     
፵፩፡ ወእምዝ ይብሎሙ ለእለ በፀጋሙ ሑሩ እምኔየ ውስተ እሳት ዘለዓለም ዘድልው ለሰይጣን ወለመላእክቲሁ። መዝ ፮፥፰። ማቴ ፯፥፳፫። ሉቃ ፲፫፥፳፯፡፡
                    ******     
፵፩፡ ከዚህ በኋላ በግራው ያሉ ኃጥአንን መርገመ ጌባል ያደረባችሁ መርገመ ነፍስ ያለባችሁ ለሰይጣን ለሠራዊቱ ወደ ተዘጋጀ ማለት ተፈርዶ ወዳለ ወደማያልፍ ሥቃይ ሂዱ ይላቸዋል።
(ሐተታ) የሚመጣ በክበበ ትስብእት ነውና ሑሩ እምኔየ ይላል።
አንድም ትእምርተ ፀብ ነው።
                    ******     
፵፪፡ እስመ ርኅብኩ ወኢያብላእክሙኒ፡፡
                    ******     
፵፪፡ ብራብ አላበላችሁኝምና።
ፀማዕኩ ወኢያስተይክሙኒ።
ብጠማ አላጠጣችሁኝምና።
                    ******     
፵፫፡ ነግደ ኮንኩ ወኢተወከፍክሙኒ።
                    ******     
፵፫፡ እንግዳ ብሆን አልተቀበላችሁኝምና፡፡
ዓረቁ ወኢያልበስክሙኒ።
ብታረዝ አላለበሳችሁኝምና።
ደወይኩ ወኢሐወፅክሙኒ።
ብታመም አልጠየቃችሁኝምና
ተሞቃሕኩ ወኢመጻእክሙ ኀቤየ ወኢነበብክሙኒ።
ብታሠር መጥታችሁ አልጠየቃችሁኝምና።
                    ******     
፵፬፡ አሜሃ ያወሥኡ እለ በፀጋሙ።
                    ******     
፵፬፡ ያን ጊዜ በግራ ቆመው የነበሩ ኃጥአን ይመልሳሉ።
እንዘ ይብሉ እግዚኦ ማዕዜ ርኢናከ ርኁበከ ወኢያብላዕናከ፡፡
ከትዕቢት ወደ ትዕቢት መሄድ ልማዳቸው ነውና ምን ጊዜ ተርበህ አይተንህ አናበላህ ብለን።
ወማዕዜ ርኢናከ ጽሙዓከ ወኢያስተይናከ።
ምን ጊዜ ተጠምተህ አይተንህ አናጠጣህ ብለን።
ወእንግዳከ ወኢተወከፍናከ።
ምን ጊዜ እንግዳ ሁነህ አይተንህ አንቀበልህ ብለን።
ወዕሩቀከ ወኢያልበስናከ።
ምን ጊዜ ታርዘህ አይተንህ አናለብስህ ብለን።
ወድውየከኒ ወኢሐወፅናከ።
ምን ጊዜ ታመሕ አይተንህ አንጠይቅህ ብለን።
ወሙቁሐከኒ ወኢነበብናከ።
ምን ጊዜ ታሥረህ አይተንህ አንጠይቅህ ብለን ብለው ይመልሱለታል።
                    ******     
፵፭፡ ወእምዝ ያወሥኦሙ ንጉሥ ወይቤሎሙ አማን እብለክሙ ኵሎ ዘኢገበርክሙ ለ፩ዱ እምእሉ ንዑሳን አኃውየ ሊተ ኢገበርክሙ።
                    ******     
፵፭፡ በእኔ ከአመኑ ምዕመናን ለአንዱ አለማድረጋችሁ ለእኔ አለማድረጋችሁ ነው ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡
                    ******     
፵፮፡ ወየሐውሩ እሉሂ ውስተ ኵነኔ ዘለዓለም፡፡ ዮሐ ፭፥፳፱፡፡ ዳን ፲፪፥፪፡፡
                    ******     
፵፮፡ ኃጥአን ወደ ማያልፍ ሥቃይ ይሄዳሉ ሲወርዱ ይኖራሉ፡፡
ወጸድቃንሰ ውስተ ሕይወት ዘለዓለም።
ጻድቃን ግን ወደ ማያልፍ ክብር ይሄዳሉ። ሲወጡ ሲወጡ ይኖራሉ።
(ሐተታ) ይህ ሁሉ መነጋገር አለ ቢሉ አዎን ይላሉ፡፡ ይህማ እንዳይሆን ንቃሕ መዋቲ ባለ ጊዜ ጻድቃን ከፀሐይ ሰባት እጅ አብርተው ጌታቸውን ኢየሱስ ክርስቶስን መስለው ይነሣሉ። ኃጥአንም ከቁራ ሰባት እጅ ጸልመው አለቃቸውን ዲያብሎስን መስለው ይነሣሉ ጽድቁም ይህ ፍጻሜውም ይህ ነው። ፍርድ በፊት ወቀሳ ወደ ኋላ ይሆን የለም ቢሉ የለም የለም ነገሩ የሚያሰኝ ስለሆነ ለሰው በሚረዳ መናገር ነው እንጂ የለም፡፡
                    ******     
ምዕራፍ ፳፮።
፩፡ ወሶበ ፈጸመ እግዚእ ኢየሱስ ዘንተ ኵሎ ነገረ ይቤሎሙ ለአርዳኢሁ። ተአምሩ ከመ እምድኅረ ሠኑይ መዋዕል ይከውን ፋሲካ፡፡ ማር ፲፬፥፩፡፡ ሉቃ ፳፪፥፩።
፩፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አስተምሮ ከፈጸመ በኋላ እስከ ሁለት ቀን ድረስ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁን አላቸው፡፡
                    ******            
  ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
20/10/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment