Saturday, June 1, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 108

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ዘከመ ቦአ እግዚእ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም።
ምዕራፍ ፳፩።
                    ******     
፩፡ ወቀሪቦ ኢየሩሳሌም በጽሐ ቤተ ፋጌ እንተ ገቦ ደብረ ዘይት። ማር ፲፩፥፩። ሉቃ ፲፱፥፩-፱፡፡
                    ******   
፩፡ ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ የደብረ ዘይት አጠገብ ከምትሆን ቤተ ፋጌ ደረሰ። ገቦ ይላል ትግሬ አጠገብ ሲል ፋጌ ፎናና የተመሳቀለ ጐዳና ማለት ነው።
ወሶቤሃ ፈነወ እግዚእ ኢየሱስ ፪ተ እምአርዳኢሁ።
ያን ጊዜ ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከ።
                    ******     
፪፡ ወይቤሎሙ ሑሩ ሀገረ ዘቅድሜክሙ።
                    ******     
፪፡ በፊታችሁ ወዳለ ሀገር ሂዱ።
ወይእተ ጊዜ ትረክቡ ዕድግተ ዕሥርተ ምስለ ዕዋላ።
ያን ጊዜ አህያ ከውርንጭላዋ ጋራ ታስራ ታገኛላችሁ።
ፍትሕዎን ወአምጽእዎን ሊተ።፡
ፈታችሁ አምጡልኝ አላቸው፡፡
(ሐተታ) ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ።
                    ******     
፫፡ ወእመቦ ዘይቤለክሙ ምንተ ትገብሩ።
                    ******     
፫፡ ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖር።
በሉ እግዚኦሙ ይፈቅዶሙ፡፡
ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ በተፈጥሮ ጌታቸው ነውና እንዲህ አለ።
ወበጊዜሃ ይፌንዉክሙ።
ያን ጊዜ ያሰናብቷችኋል።
                    ******     
፬-፭፡ ወዝ ኵሉ ዘኮነ ከመ ይትፈጸም ዘተብህለ በነቢይ በልዋ ለወለተ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ ጻድቅ ወየዋህ ይመጽእ ኅቤኪ እንዘ ይፄዓን ዲበ ዕድግት ወዲበ ዕዋላ።
                    ******     
፬-፭፡ ይህ ሁሉ የተደረገ ጻድቅ የባሕርይ አምላክ የዋህ ኃዳጌ በቀል ንጉሥሽ በዕዋል በእድግት ተቀምጦ ይመጣል ብላችሁ ለጽዮን ልጅ ንገሯት ብሎ የተናገረው ቃል ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ነው።
(ሐተታ) ወለት እስራኤል ናቸው ጽዮን ኢየሩሳሌም ናት፡፡ በሀገሪቱ ሰዎቹን መናገር ነው ልጅ ያማራ ልጅ የጐጃም እንዲሉ፡፡
አንድም ወለት አይለወጥም ጽዮን ሕግ ናት እናት ልጆቹዋን ሠርታ ቀጥታ እንድታሳድግ ሕግም ሕዝቡን ሠርታ ቀጥታ ታኖራለችና። ቃለ ነቢያት ያለ እንደሆነ አያሳትትም በልዋ ለወለተ ጽዮን ያለ ኢሳይያስ ይመጽእ ንጉሥኪ ያለ ዘካርያስ ነውና። ቃለ ነቢይ ያለ እንደሆነ የሁሉ ስም ነውና። ቃለ ኢሳይያስ ይላል አብነት ኢሳይያስ እንደ አባት እንደ መምህር ዘካርያስ እንደ ልጅ እንደ ደቀ መዝሙር ናቸውና።
                    ******     
፮-፯፡ ወሐዊሮሙ አርዳኢሁ ገብሩ በከመ አዘዞሙ እግዚእ ኢየሱስ። ወአምጽኡ ሎቱ ዕድግተ ምስለ ዕዋላ።
                    ******     
፮-፯፡ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው እንደ አዘዛቸው አደረጉ። አህያ ከውርንጫዋ ጋራ አመጡለት፡፡
ወረኃኑ አልባሲሆሙ ላዕሌሆን
ልብሳቸውን ጐዘጐዙለት።
(ሐተታ) ኮርቻ ይቆረቊራል ልብስ አይቆረቊርምና የማትቆረቊር ሕግ ሠራሁላቸሁ ሲል።
አንድም ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሠውራል፡፡ አንተም ከባቴ አበሳ ነህ ሲሉ።
ወተፅዕነ እግዚእ ኢየሱስ ዲቤሆን።
በሁለቱም ጌታ በጥበብ ፩ ጊዜ ተቀመጠባቸው።
(ሐተታ) ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ ፲፮ ምዕራፍ ነው፡፡ ፲፬ ቱን በእግሩ ሄዶ ሁለቱን በእድግት ሄዷል በዕዋል ሁኖ ቤተ መቅደስን ፫ ጊዜ ዙሯል። የሦስትነት ምሳሌ፤ አሥራ አራቱን በእግሩ መሄዱ ፲ ቃላት ፬ቱ ኪዳናት፡፡ ኪዳነ ኖኅ፤ ክህነተ መልከ ጼዴቅ፤ ግዝረተ አብርሃም፤ ጥምቀተ ዮሐንስ ነው።
አንድም ፭ቱን ሽህ ከአምስት መቶ ዘመን በአራት በአራት መቶ ዘመን ቢቆጥሩት አሥራ አራት ሊሆን መቶ ይጐድለዋል፤ ይህ ሲፈጸም ሰው እንደሆነ ለማጠየቅ በአህያ መቀመጡ ስለምን ቢሉ። ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም።
ትንቢት አጠፍዕ ሠረገላ እምኤፍሬም ወአፍራሰ እምይሁዳ ተብሎ ተነግሯል፡፡
ምሳሌም ቀድሞ አባቶቹ ነቢያት ዘመነ ጸብዕ የሆነ እንደ ሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረሰ ሲል ትንቢቱን ባወቀ አናግሯል ምሳሌውንም እንጅ ባወቀ አስመስሏል ምሥጢሩ እንደምነው ቢሉ በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልሹኝ አልገኝም ከሹኝም አልታጣም ሲል።
አንድም እለ ከመ እንተ አድግ ነፍስቶሙ እንዲል  በንጹሐን መሐይምናን አድሬባቸው እኖራለሁ ሲል። ዕድግት የእስራኤል ምሳሌ የሠረገላ ቀንበር መሸከም የለመደች እንደሆነች እስራኤልም ሕግ መጠበቅ ለምደዋልና ዕዋል የአሕዛብ ቀንበር መሸከም ያለመደች እንደሆነች አሕዛብም ሕግ መጠበቅ ያለመዱ ናቸውና።
አንድም ዕድግት የኦሪት ዕዋል የወንጌል ምሳሌ፡፡ እድግት ቀንበር መሸከም የለመደች እንደሆነ ኦሪትም የተለመደች ሕግ ናትና ዕዋል ቀንበር መሸከም ያለመደች እንደሆነች ወንጌልም ያልተለመደች ሕግ ናትና።
                    ******     
፰፡ ወዘይበዝኁ ሕዝብ ነጸፉ አልባሲሆሙ ውስተ ፍኖት።
                    ******     
፰፡ የሚበዙት ሕዝብ ልብሳቸውን በጎዳና አነጠፉ።
(ሐተታ) ስንኳን ላንተ ለተቀመጥህባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ።
አንድም በኢዩ ልማድ ኤልሳዕ ከደቂቀ ነቢያት አንዱን ቀርነ ቅብዑን ይዘህ ሂደህ ኢዩን ቀብተህ አንግሠኸው ፈጥነህ ና ከሰው ጋራ አትጫወት ብሎ ላከው። ቢሄድ ኢዩን ከባልንጀሮቹ ጋራ ሲጫወት በአደባባይ ተቀምጦ አገኘው ብየ መልእክት አለው። እምኔነኑ እምኀበ መኑ አለው ከእኛን ነው ከሌላ ቢለው ኀቤከ መልአከ ከአንተ ተልኬ መጥቻለሁ አለው። ከእልፍኝ ይዞት ገባ ከመዝ ይቤ አምላከ እስራኤል ቀባዕኩከ ትንግሥ ላዕለ ሕዝብየ እራኤል ብሎ ቀብቶት ሩጦ ሄደ። ኋላ ኢዩ መጣ ምን አለህ ንገረን አሉት። ኢተአምሩኑ ከመ በከ ይዛዋዕ ዝ ብእሲ። ይህ ሰው ዋዛ ፈዛዛ እንዲናገር አታውቁምን አላቸው፡፡ ዕውነቱን ንገረንማ ካላችሁኝ ትነግሣለህ ብሎ ቀብቶኝ ሄደ አላቸው እኛስ ሌላ ምን እንሻለን ብለው እኵሌቶቹ አንጽፈዋል እኵሌቶቹ ጋርደዋልና በዚያ ልማድ፡፡
ወካልዓንሂ ይመትሩ አዕፁቀ እምውስተ ዕፀው ወይነጽፉ ውስተ ፍኖት።
ሌሎችም ቅጠል እየቆረጡ ከመንገድ ያነጥፉ ነበር።
(ሐተታ) ሰሌን ነው ያሉ እንደሆነ አብርሃም ይስሐቅን ይስሐቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፤ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፤ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ፣ ሰሌን ቆርጠው ይዘው አመስግነዋልና በዚያ ልማድ።
አንድም ሰሌን እሾኻም ነው ትእምርተ ኃይል ትእምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ። እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል፤ ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ፡፡ ተምር ነው ያሉ እንደሆነ ተምር ልዑል ነው፡፡ ልዑለ ባሕርይ ነህ ሲሉ ፍሬው አንድ ነው። ዋህደ ባሕርይ ነህ ሲሉ፡፡ ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ፡፡ ዘይት ነው ያሉ እንደሆነ ዘይት ጽኑዕ ነው ጽኑዓ ባሕርይ ነህ ሲሉ። ብሩህ ነው ብሩሃ ባሕርይ ነህ ሲሉ። መሥዋዕት ነው። መሥዋዕት ትሆናለህ ሲሉ።
                    ******     
፱፡ ወሕዝብሰ እለ ይመርሁ ወእለሂ ይተልዉ ይጸርኁ ወይብሉ ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት። መዝ ፻፲፯፥፳፮። ማር ፲፩፥፩፡፡ ሉቃ ፲፱፥፴፰፡፡
                    ******     
፱፡ በፊት በኋላ ያሉ ሕዝቡም ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል አሉ።
(ሐተታ) ይተልዉ አዕሩግ ይመርሑ ሕፃናት ይተልዉ ሕፃናት ይመርሑ አዕሩግ ይተልዉ ሐዋርያት ይመርሑ ነቢያት ዕልፍ ቅድሜሁ ዕልፍ ድኅሬሁ። ጻድቃን በየማኑ ተነሳሕያን በፀጋሙ እኒህ ሁሉ ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል እያሉ አመሥግነዋል።
ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር።
በእግዚአብሔር ስም ማለት እግዚአብሔር ነኝ ብሎ እግዚአብሔር ባወጣለት ስም በስምዓ እግዚአብሔር እግዚአብሔር መስክሮለት የመጣ እሱ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል ነው አሉ።
ሆሣዕና በአርያም።
በሰማይ ያለ መድኃኒት ነው፡፡
                    ******     
፲፡ ወበዊዖ ኢየሩሳሌም ተሀውከት ኵላ ሀገር እንዘ ትብል መኑ ውእቱ።
                    ******     
፲፡ በኢየሩሳሌም ከተማ በገባ ጊዜ ይህ ማነው ብላ ከተማዪቱ ተደረፀች የፊቱ ብርሃን ፀሐይን ሲበዘብዛት አይታ፤ የሕፃናትን ምስጋና ሰምታ።
                  ******     
፲፩፡ ወይቤሉ ሕዝብ ዝንቱ ውእቱ ኢየሱስ ዘእምናዝሬት ዘገሊላ። ማር ፲፩፥፲፭። ሉቃ ፲፱፥፵፭፡፡ ዮሐ ፪፥፲፬።                               ****** 

፲፩፡ ሕዝቡ የገሊላ ክፍል በምትሆን በናዝሬት ያደገ ኢየሱስ ነው አሉ።

                    ****** 

ዘከመ ሰደዶሙ ኢየሱስ ለእለ ያረኵሱ ቤተ መቅደስ።

፲፪፡ ወቦአ እግዚእ ኢየሱስ ውስተ ቤተ መቅደስ።

፲፪፡ ጌታ ከቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ።

                    ******        


  ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
24/09/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment