====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ደናግል ጠባባት ወአብዳት፡፡
ምዕራፍ ፳፭።
******
፩፡ አሜሃ ትመስል መንግሥተ ሰማያት አሥሮን ደናግለ እለ ነሥአ መኃትዊሆን ወወፅአ ውስተ ቀበላ መርዓዊ
******
፩፡ አብነት አሜሃ ይእተ አሚረ ይላል ያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ ሕገ ወንጌል። ሕገ ወንጌል ተስፋ፡፡ ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ፋና ይዘው አሥሩ ደናግል ሊቀበሉት የወጡ ሙሽራን ትመስላለች።
አንድም መንግሥተ ሰማይ ሕገ ወንጌል ትመስል መኃትወ ፤ መርዓዊን ሲቀበሉ ፲ ደናግል ይዘውት የወጡ ፋናን ትመስላለች።
አንድም መንግሥተ ሰማይ ምዕመናን ትመስል አሥሮን ደናግለ። ሙሽራውን ለመቀበል ፋና ይዘው የወጡ ደናግልን ትመስላለች፡፡
(ሐተታ) ደናግል አላቸው ምዕመናንን፤ ድንግል በአባት በእናቷ ቤት ሳለች ኋላ ከባሏ ጋራ አንድ የምትሆንበትን ሥራ ስትማር እንድታድግ ምዕመናንም በዚህ ዓለም ሳሉ ኋላ ከክርስቶስ ጋራ አንድ የሚሆኑበትን ሥራ ሲሠሩ ይኖራሉ።
አንድም በተፈጥሮ ደናግል ናቸውና።
አንድም ድንግልና ሥጋ አላቸውና ይሀህ ለሁሉ አይቻልም ብሎ ድንግልና ነፍስ አላቸውና።
******
፪፡ ወኃምስ እምኔሆን አብዳት እማንቱ።
******
፪፡ ከአሥሩ አምስቱ ሰነፎች ናቸው፡፡
ወኃምስ ጠባባት ።
አምስቱ ልባሞች ናቸው።
******
፫፡ ወዓብዳትሰ ነሢኦን መኃትዊሆን ኢነሥኣ ቅብዓ ምስሌሆን።
******
፫፡ ሰነፎች ፋና ይዘው በማሠሯቸው ዘይት አልያዙም።
******
፬፡ ወጠባባትሰ ነሥኣ ቅብዓ ምስለ መኃትዊሆን በገማዕዊሆን።
******
፬፡ ልባሞች ግን ከፋናቸው ጋራ በማሰሯቸው ዘይት ይዘዋል፡፡
(ሐተታ) ዓብዳት የሚላቸው ሃይማኖት ጾም ጸሎት ትሕትና ኃፊረ ገጽን ይዘው ፮ተኛ በልቡናቸው ፍቅርን ያልያዙ ናቸው። ኃፊረ ገጽና ትሕትናስ አንድ ወገን ናቸው ብሎ ሃይማኖት ጾም ጸሎት ትሕትና ኃፊረ ገጽ አንድ ወገን ንጽሕናን ይዘው ፮ተኛ በልቡናቸው ፍቅርን ያልያዙ ናቸው። ጠባባት የሚላቸው አምስቱን ይዘው ስድስተኛ በልቡናቸው ፍቅርን የያዙ ናቸው። ቅብዕ ኢይርኀቀ ቅብዕሰ ፍቅረ ደቂቀ እጓለ እመሕያው እንዲል። አምስቱን ይዛችሁ ስድስተኛ በልቡናችሁ ፍቅርን ከልያዛችሁ አይሆንም ይሏቸዋል ከነግህ ከሠለስት እንይዛለን ሲሉ ሞት ይመጣባቸዋል። እኒያ አለመጠቀማቸውን እነዚህ መጠቀማቸውን መናገር ነው።
******
፭፡ ወጐንድዮ መርዓዊ ደቀሳ ኵሎን ወኖማ።
******
፭፡ ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ዓብዳትም ጠባባትም ተኙ።
******
፮፡ ወከዊኖ መንፈቀ ሌሊት ውውዓ ኮነ ናሁ መርዓዊ መጽአ ፃዑ ተቀበሉ።
******
፮፡ መንፈቀ ሌሊት ሲሆን ሙሽራው መጥቷልና ወጥታችሁ ተቀበሉ ተብሎ ተነገረ።
(ሐተታ) በሀገራቸው ሙሽራ የሚመጣ በመንፈቀ ሌሊት ነውና፡፡
******
፯፡ ወእምዝ ነቅሓ እልኩ ደናግል ኵሎን ወአሠነያ መኃትዊሆን ወወፅኣ ውስተ ቀበላ መርዓዊ።
******
፯፡ ከዚህ በኋላ ልባሞች ተነሥተው ፋናቸውን አዘጋጅተው ሙሽራውን ሊቀበሉ ወጡ።
******
፰፡ ወእልኩ ዓብዳት ይቤላሆን ለጠባባት ሀባነ ቅብዓ አምቅብዕክን።
******
፰፡ ሰነፎች ልባሞችን ከዘይታችሁ ዘይት ስጡን አሏቸው።
እስመ መኀትዊነ ጠፍአነ።
ዘይት አልቆብናልና ።
******
፱፡ ወአውሥኣሆን ጠባባት አንዘ ይብላ አልቦ ዘየአክል ለነ ወለክን
******
፱፡ ልባሞች ለኛና ለእናንተ የሚበቃ ዘይት አልያዝንምና።
አላ ሑራ ወተሣየጣ ለክን እምኀበ እለ ይሠይጡ።
ሄዳችሁ ዘይት ከሚሸጡ ግዙ እንጂ አሏቸው።
******
፲፡ ወሐዊሮን ይሣየጣ በጽሐ መርዓዊ።
******
፲፡ ለጊዜው ሂደው ሳሉ ሙሽራው መጣ።
ወቦአ ምስሌሁ እልኩ እለ ድልዋት ውስተ ከብካብ።
የተዘጋጁ ከሱ ጋራ እንደ እሱ ወደ ሰርግ ገቡ።
ወተአፅወ ኆኅት
ደጅ ተዘጋ።
******
፲፩፡ ወድኅረ መጽኣ እልኩሂ ደናግል ወይቤላ እግዚኦ እግዚኦ አርኅወነ።
******
፲፩፡ እነዚያ ከገቡ ደጅ ከተዘጋ በኋላ ሰነፎች መጥተው ክፈትልን ማለት እንድንገባ አድርገን አሉት።
******
፲፪፡ ወአውሥኦን።
******
፲፪፡ መለሰላቸው
ወይቤሎን አማን እብለክን ከመ ኢየአምረክን።
አላውቃችሁም ብዬ እንዳላውቃችሁ በእውነት እነግራችኋለሁ፡፡
እስመ ስእንክን ተጊሃ ወአምስዮ አሐተ ሰዓተ ምስሌየ።
ተግታችሁ ሥራ አልሠራችሁም ከእኔ ጋራ አንዲት ሰዓት መቆም መቆየት አልተቻላችሁምና፡፡
******
፲፫፡ ትግሁኬ እስመ ኢተአምሩ ዕለታ ወሰዓታ እንተ ባቲ ይመጽእ ወልደ እጓለ አመሕያው፡፡ ማር ፲፫፥፴፫፡፡
******
፲፫፡ ወልደ እጓለእመሕያው ክርስቶስ የሚመጣበትን ዕለት ሰዓት አታውቁምና ለትሩፋት ተግታችሁ ኑሩ።
አንድም ወጐንድዮ መርዓዊ ብለህ መልስ ምጽአት በዘገየ ጊዜ ምእመናን ሁሉ መሞታቸውን መናገር ነው።
ወከዊኖ መንፈቀ ሌሊት
በማዕከለ ዘመን መርዓዊ ክርስቶስ መጥቷልና ለተዋሕዶ የሚያበቃ ሥራ ሥሩ ተብሎ ተነገረ።
(ሐተታ) ያልተካከለ መንፈቅ ነው ወንፍቃ ለሌሊት ወመንፈቆሙ ናፈቁ እንዲል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ያለውን አንድ ወገን፤ ከምጽአት በኋላ ያለውን አንድ ወገን አድርጎ መንፈቅ አለ።
አንድም የተካከለ መንፈቅ ነው ዓለም ሳይፈጠር ያለውንና ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለውን አንድ ወገን ከምጽአት በኋላ ያለውን አንድ ወገን አድርጎ ተናገረ። የዚያ ጥንቱ እንዳይታወቅ የዚህም ፍጻሜው አይታወቅምና። የቊጥር መጽሐፍ ክፍለ ዳግም መንፈቅ ይላል ተአምረ ኢየሱስ ወበ፮ ሰዓተ ሌሊት ተንሥአ እግዚእ ኢየሱስ ይላልሳ ቢሉ ሦስት ሰዓት አሳልፎ ነው መከራ መቀበል የጀመረ። ከዚያ ተነሥቶ ቊጥሮ ፮ አለ እንጂ፡፡ ልደቱም፣ ጥምቀቱም፣ ትንሣኤውም፣ ምጽአቱም በዐሥረኛው ሰዓት ነው።
ወእምዝ ተንሥአ
ለተዋሕዶ የሚያበቃ ሠርተው
ሀባነ ቅብዓ
ከሥራችሁ አትርፉልን፤
እስመ መኃትዊነ ጠፍአነ፡
ለተዋሕዶ የሚያበቃ ሥራ አልሠራንምና ማለት በአንዱ ሥራ አንዱ የሚጠቀም እንደመሰላቸው መናገር ነው
ወአውሥኣሆን እንዘ ይብላ አልቦ ዘየአክል ለነ ወለክን፤
ለእኛና ለእናንተ የሚበቃ ሥራ የለንም አሏቸው ማለት በአንዱ ሥራ አንዱ እንዳይጠቀም ማወቃቸውን መናገር ነው፤
አላ ሑራ
ምሕረትን ከሚያድሉ ከሥላሴ ምሕረትን ከሚያሰጡ ከነዳያን ለምኑ እንጂ አሏቸው፤
ወሐዊርሮን ይሣየጣ፤
ነግህ ሠልስት ሥራ እንሠራለን ሲሉ ምጽአት ደረሰ።
ወቦአ ምሰሌሁ፤
ሥራ ሠርተው የተገኙት ተዋሐዱት ተዋሐዳቸው።
ወተአጽወ ኆኅት
ምሕረት ተከለከለ፤
ወድኅረ መጽኣ ወይቤላ አርኅወነ፤
የሚገቡ እንደመሰላቸው መናገር ነው፤
ወአውሥኦን
አላውቃችሁም ብዬ እንዳላውቃችሁ በእውነት አነግራችኋለሁ፤ ፈጥሮስ አላውቃችሁም ማለት አይመችም ብሎ ወለድኳችሁ ካድኳችሁ እላቸዋለሁ።
እስመ ስእንክን ተጊሃ
ለተዋሕዶ የሚያበቃ ሥራ አልሠራችሁምና ትግሁኬ እንዳለፈው።
(ሐተታ) አብዳት የሚላቸው ሃይማኖት እንበለ ምግባር ንጽሐ ሥጋ እንበለ ንጽሐ ነፍስ ፍቅር እንበለ ተስፋ ምሕረት እንበለ ትዕግሥት ጸሎት ዘምስለ ትምክህት የያዙ ናቸው። ጠባባት የሚላቸው ሃይማኖት ዘምስለ ምግባር ንጽሐ ሥጋ ዘምስለ ንጽሐ ነፍስ። ምሕረት ዘምስለ ትዕግሥት ፍቅር ዘምስለ ተስፋ ጸሎት እንበለ ትምክህት የያዙ ናቸው፡፡ ይህን ይዛችሁ ይህን ካልያዛችሁ አይሆንም ይሏቸዋል። ከነግህ ከሠለስት እንይዛለን ሲሉ ሞት ይመጣባቸዋል እኒህ መጠቀማቸውን እኒያ አለመጠቀማቸውን መናገር ነው።
አንድም አብዳት የሚላቸው አእምሮ ለብዎ ሰሚዕ ምሕረት ትዕግሥት እኒህን አምስቱን ይዘው አሚን ተስፋ ፍሥሐ ሰላም ፍቅርን ያልያዙ ናቸው፡፡ ጠባባት የሚላቸው ዓሥሩንም የያዙ ናቸው፡፡ ይኸን ይዛችሁ ይኸን ካልያዛችሁ አይሆንም ይሏቸዋል። ከነግህ ከሠለስት እንይዛለን ሲሉ ሞት ይመጣባቸዋል እኒህ መጠቀማቸውን እኒያ አለመጠቀማቸውን መናገር ነው፡፡
አንድም አብዳት የሚላቸው አይሁድ ተንባላት ናቸው፤ ጠባባት የሚላቸው ክርስቲያን ናቸው ካላመናችሁ ከልተጠመቃችሁ አይሆንም ይሏቸዋል ከነግህ ከሠለስት እንጠመቃለን ሲሉ ሞት ይመጣባቸዋል እኒህ መጠቀማቸውን እኒያ አለመጠቀማቸውን መናገር ነው።
አንድም አብዳት የሚላቸው አምነው ተጠምቀው የክርስቲያን ሥራ የማይሠሩ ናቸው፡፡ ጠባባት የሚላቸው አምነው ተጠምቀው ሥራ የሚሠሩ ናቸው፡፡ አምናችሁ ተጠምቃችሁ ሥራ ከአልሠራችሁ አይሆንም ይሏቸዋል፡፡ ከነግህ ከሠለስት እንሠራለን ሲሉ ሞት ይመጣባቸዋል እኒህ መጠቀማቸውን እኒያ አለመጠቀማቸውን መናገር ነው።
******
በእንተ ምሳሌ ዘመካልይ።
፲፬፡ እስመ ከመ ብእሲ ዘይነግድ ወጸውአ አግብርቲሁ ወወሀቦሙ ንዋዮ ይትገበሩ ቦቱ። ሉቃ ፲፱፥፲፪፡፡
፲፬፡ መንግሥተ ሰማይ ሕገ ወንጌል፣ ሕገ ወንጌል ተስፋ ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ብላቴኖችን ጠርቶ ወጥተው ወርደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን የሰጣቸውን ነጋዴን ትመስላለችና ትግሁ። አንድም ትመስላለችኮን።
******
ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
14/10/2011 ዓ.ም
Friday, June 21, 2019
ወንጌል ቅዱስ ክፍል 122
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment