Saturday, June 8, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 114

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ምሳሌ ንጉሥ ዘገብረ ከብካበ ለወልዱ ።
ምዕራፍ ፳፪።
                    ******     
፳፩፡ ወይቤሎሙ ዘቄሣር ሀቡ ለቄሣር፡፡ ሮሜ ፲፫፥፮።
                    ******     
፳፩፡ የቄሣርን ለቄሣር ስጡ።
ወዘእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር።
የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ አላቸው ምልዓተ ንባብ ነው።
አንድም የንጉሥ የሆነ እንደሆነ ስመ ንጉሥ ይጻፍበታል ሥዕለ አንበሳ ይቀርጹበታልና የቄሣርን ለቄሣር ስጡ አለ። የእግዚአብሔር የሆነ እንደሆነ ስመ አምላክ ይጻፍበታል ሥዕለ ኪሩብ ይቀረጽበታልና የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ አለ፡፡
አንድም በተንኮል መጥተዋል መጠነ እራኃ እድ ይላታል ብር የምታህል ናት በአንድ ወገን ስመ ንጉሥ ጽፈው ሥዕለ አንበሳ ቀርጸው በአንድ ወገን ስመ እግዚአብሔር ጽፈው ሥዕለ ኪሩብ ቀርፀው ይዘው መጡ፤ ዘቄሣር ያለን እንደሆነ ዘእግዚአብሔር ይላልሳ፤ ዘእግዚአብሔር ያለን እንደሆነ ዘቄሣር ይላልሳ ብለን ምላሽ እናሳጣዋለን ብለው ነው። እሱም በመጡበት ይጨነቁበት ብሎ የግራ የቀኙን አንድ ጊዜ ተናገረው፤ እንዳይለዩት የማይለይ ነው ከእሳትም ቢያገቡት ሁሉም ይጠፋል።
አንድም አርአያ ቄሣር ሰውነታችሁን ለቄሣር አስገዙ አርአያ እግዚአብሔር ስውነታችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፡፡
አንድም አፍአዊ ሰውነታችሁን ለቄሣር አስገዙ ውሳጣዊ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ።
                    ******     
፳፪፡ ወሰሚዖሙ አንከሩ ወኃደግዎ ወኃለፉ።
                    ******     
፳፪፡ ምላሹን ሰምተው አድንቀው ትተውት ሄዱ።
                    ******     
በእንተ ሰዱቃውያን ወትንሣኤ ምውታን፡፡
፳፫፡ ወበይእቲ ዕለት መጽኡ ኀቤሁ ሰዱቃውያን እለ ይብሉ አልቦ ትንሣኤ ሙታን። ግብ ፳፫፥፰፡፡
                    ******     
፳፫፡ በዚያች ቀን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን መጡ።
                    ******     
፳፬፡  ወተስእልዎ እንዘ ይብሉ። ዘዳግ ፳፭፥፭፡፡ ማር ፲፪፥፲፱፡፡ ሉቃስ ፳፥፳፰፡፡
                    ******     
፳፬፡  እንዲህ ብለው ጠየቁት፡፡
ኦ ሊቅ ሙሴ ጸሐፈ ለነ ለእመ ሞተ እኁሁ እንዘ አልቦ ውሉድ ያውስብ ብእሲተ እኁሁ ወያቅም ዘርዓ ለእኁሁ።
መምህር ሆይ ወንድሙ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ታናሽ ወንድሙ አግብቶ ስሙን የሚያስጠራ ልጅ ይውለድለት ብሎ ሙሴ ጽፎልናል።
                    ******     
፳፭፡ ወኃለዉ ኀቤነ ፯ቱ አኃው።
                    ******     
፳፭፡ ሰባት ወንድማማች ከኛ ዘንድ ነበሩ።
ወዘይልሕቅ አውሰበ ወሞተ እንዘ አልቦ ውሉድ።
ታላቁ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፣
ወኀደገ ብእሲቶ ለእኁሁ።
ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፡፡
(ሐተታ) የምትገባው ስለሆነ እንዲህ አለ።
                    ******     
፳፮፡ ወከማሁ ካዕበ ካልዑኒ ወሣልሱኒ እስከ ፯ቲሆሙ አውሰብዋ፡፡
                    ******     
፳፮፡ እንደዚህም ሁሉ አንዱ እየሞተ አንዱ እየተተካ ሰባቱ ሁሉ አገቧት።
ወኢኃደጉ ውሉደ፣
ሁሉም ልጅ ሳይወልዱ ሞቱ፡፡
                    ******     
ወድኅረ ኵሎሙ ሞተት ይእቲ ብእሲት
                    ******     
፳፯፡ ከእሳቸው በኋላ እሱዋም ሞተች፡፡
                    ******     
፳፰፡ ወአመ ይትነሥኡ እንከ ምውታን ለመኑ እም፯ቲሆሙ ትከውን ብእሲተ፣
                    ******     
፳፰፡ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ከሰባቱ ለማን ትሆናለች።
ወበይእቲ ዕለት መጽኡ ኀቤሁ እስመ ኩሎሙ አውሰብዋ
መላው አግብተዋታልና፣
(ሐተታ) ሰዱቃውያን ትንሣኤ ሙታን የለም ይላሉ፣ ፈሪሳውያን ግን ትንሣኤ ሙታን አለ እንደ ገና ከሚስቶቻችን ከልጆቻችን ጋራ እንኖራለን ይላሉ፣ ትንሣኤ ሙታን ካለ ለማናቸው ትገባለች ይሏቸዋል ለመላው ያሏቸው እንደሆነ ዓለመ ዝሙት ናታ ይሏቸዋል፡፡ ለአንዱ ያሏቸው እንደሆነ ዓለመ ግፍዕ ናታ በወዴሁ ሥርዓት ይሠራባቸው በወዲያው ይከለከልባቸው እያሉ ምላሽ ያሳጧቸዋል እንደነዚያ መስሏቸው ጌታን ይጠይቁታል እሱም ይመልስላቸዋል።
አንድም ብእሲት ይህቺ ዓለም ሰባት እስከ ምጽአት የሚነሡት ነገሥታት ናቸው፤ በፍጹም ተናገራቸው። እስመ ኁልቁ ሳብእ በኀበ እብራያውን ፍጹም ውእቱ እንዲል።
ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ፡፡
ጌታ መለሰ።
ወይቤሎሙ ስሕትክሙ በኢያእምሮ መጻሕፍት።
የስነ ፍጥረትን ነገር የሚናገር መጽሐፍን ባለማወቅ።
ወኢኃይለ እግዚአብሔር።
አምጻኤ ዓለማትነቱን ባለማወቅ በደላችሁ።
(ሐተታ) አያስነሳም ይሉታል እንጂ አልፈጠረም ይሉታል ቢሉ ጥንቱን አካል ያለውን አካል ሰጥቶ አያስነሣም ካሉት ይህን ዓለም እምኀበ አልቦ አምጥቶ አልፈጠረም ያሰኝባቸዋልና።
አንድም ስሕትክሙ ብለሀ መልስ። የትንሣኤ ሙታንን ነገር የሚናገሩ መጻሕፍትን ባለማወቅ።
ወኢኃይለ እግዚአብሔር።
የጌታችንን ትንሣኤ ባለማወቅ በደላችሁ።
(ሐተታ) ሙታን አይነሡም ብለዋል እንጂ ጌታን አልተነሣም ብለዋልን ቢሉ ሙታን አይነሡም ካሉ ጌታ አልተነሣም ማለት ነውና።
                    ******     
፴፡ እመሰ የሐይዉ ምውታን ኢያወስቡ ወኢይትዋሰቡ።
                    ******     
፴፡  ሙታን በሚነሱበት ጊዜ አያገቡም አይጋቡም።
አላ ከመ መላእክተ እግዚአብሔር ይከውኑ እሙንቱ በሰማያት፡፡
እንደ መላእክት አንድ ወገን ሆነው በመንግሥተ ሰማይ ይኖራሉ እንጂ፣
                    ******     
፴፩፡ ወበእንተ ትንሣኤ ሙታንሰ ኢያንበብክሙኑ ዘተብህለ ለክሙ እምኀበ እግዚአብሔር ዘይቤ አነ እግዚአብሔር አምላከ አብርሃም ወአምላከ ይስሐቅ ወአምላከ ያዕቆብ።
                    ******     
፴፩፡ ትንሣኤ ሙታንማ እንዳለ ለማጠየቅ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ እኔ ነኝ ብሎ እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን አልተመለከታችሁምን አላወቃችሁምን።
ወእግዚአብሔርሰ ኢኮነ አምላከ ምውታን አላ ኣምላከ ሕያዋን።
እግዚአብሔር ግን የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ ነበሩኝ ሞቱብኝ ለማለት የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ነኝ አላለም። በነፍስ ሕያዋን ናቸውና። ይቀድሱታልና እንዲያስነሣቸው ያውቃልና እንዲህ አለ።
(ሐተታ) ይህች ዓለም ዛሬ በሰባቱ ዕለታት ትመገባለች ኋላ እንደምን ናት ቢሉት ኋላስ መዓልትና ሌሊት ክረምትና በጋ ብርሃንና ጨለማ የለም እንደ መላእክት አንድ ወገን ሁነው ይኖራሉ ብሏቸዋል። ዛሬ ሥጋና ነፍስ ይሳሳባሉ ኋላ እንደምን ይሆናሉ አሉት ኋላስ መሳሳብ የለም ዓለሙም ዓለመ ነፍስ ነው ሥጋም ነፍስን መስላ እንደ መላእክት ሁነው ይኖራሉ አላቸው። ዛሬ ሥጋዌውን ከንጉሥ እስከ ኳደሬ እስከ  አቅራሪ፡ መንፈሳዊውን ከሊቀ ጳጳስ እስከ ዓፃዌ ኖኅት ባለው አድሮ ይመግባል። ኋላ አንደምነው ቢሉት ኋላስ ገዥ ና ተገዥ የለም።
ወአስክብዎ ለውእቱ ሰይፍ ውስተ መካኑ አንዲል። ገዥው አንድ እሱ ነው። እንደ መላእክት አንድ ወገን ሁነው ይኖራሉ አላቸው።
                    ******     
፴፫፡ ወሰሚዖሙ ሕዝብ አንከሩ ምሕሮቶ
                    ******     
፴፫፡ ሕዝቡ ሰምተው ትምህርቱን አደነቁ።
                    ******     
በእንተ ዓቢይ ትእዛዘ እግዚአብሔር።
፴፬፡ ወሰሚዖሙ ፈሪሳውያን ከመ ፈጸሞሙ አፉሆሙ  ለሰዱቃውያን ተጋብኡ ኀቤሁ ኵሎሙ ኅቡረ፡፡
                    ******     
፴፬፡ ሰዱቃውያንን ምላሽ እንዳሳጣቸው ፈሪሳውያን ሰምተው ደስ ብሏቸው በአንድነት ወደሱ ተሰበሰቡ።
(ሐተታ) ቢስ የቢስ ቀን ክፉ የክፉ ቀን ብለው።
                    ******     
፴፭፡ ወተስእሎ ፩ ጸሐፊ እምኔሆሙ
                    ******     
፴፭፡ ከሳቸው ወገን አንድ ጸሐፊ ማለት አዋቂ ነኝ የሚል ጠየቀው።
እንዘ ያሜክሮ።
ሲፈትነው።
                    ******     
፴፮፡ ኦ ሊቅ አይኑ ትእዛዝ ዓባይ በውስተ ኦሪት
                    ******     
፴፮፡ መምህር ደገኛው ትእዛዝ ማናቸው ነው።
አንድም በኦሪት ማናችው ትእዛዝ ይበልጣል አለው።
                    ******     
፴፯፡ ወይቤሎ አፍቅሮ ለእግዚአብሔር አምላክከ በኵሉ ልብከ፡፡
                    ******     
፴፯፡ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡናህ ውደደው ያለው ነው።
ወበኵሉ ነፍስከ።
በፍጹም ሰውነትህ።
ወበኵሉ ኃይልከ።
በፍጹም ዕውቀትህ።
ወበኵሉ ሕሊናከ።
በፍጹም ሕሊናህ።
                    ******     
፴፰፡ ዛቲ ትእዛዝ ዓባይ ወቀዳሚት
                    ******     
፴፰፡ ደገኛዪቱ መጀመሪያዪቱ ትእዛዝ ይህች ናት።
አንድም ቀዳሚሆሙ ለአሕዛብ አማሌቅ አንዲል። ፈጽሞ ደገኛዪቱ ትእዛዝ ይህች ናት።
                    ******     
፴፱፡ ወካልዕታሂ እንተ ትመስላ አፍቅር ቢጸከ ከመ ነፍስከ።
                    ******     
፴፱፡ ሁለተኛዪቱም አፍቅር በማለት ዋጋ በማሰጠት የምትመስላት ፍቅረ ቢጽ ናት።
                    ******     
፵፡ ወበእላ ፪ቲ ትእዛዝ ተሰቅሉ ኦሪት ወነቢያት።
                    ******     
፵፡ በኒህ በሁለቱ በፍቅረ ቢጽና በፍቅረ እግዚአብሔር ኦሪት ነቢያት ተጠብቀው ይኖራሉ።
(ሐተታ) ሁለቱ እንደ ሁለቱ ፍንጅ ስምንቱ እንደ ስምንቱ ጠገግ ሁነው።
                    ******     
በእንተ መሢሕ ወልደ ዳዊት
፵፩፡ ወእንዘ ጉቡዓን ፈሪሳውያን ተስእሎሙ እግዚእ ኢየሱስ።
                    ******     
፵፩፡ ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ ጌታ ጠየቃቸው፡፡
                    ******     
፵፪፡ እንዘ ይብል ምንተ ትብሉ በእንተ ክርስቶስ።
                    ******     
፵፪፡ የክርስቶስን ነገር ምን ትናገራላችሁ ብሎ።
ወልደ መኑ ውእቱ፤
የማን ልጅ ነው፡፡
                    ******     
፵፫፡ ወይቤልዎ ወልደ ዳዊት።
                    ******     
፵፫፡ የዳዊት ልጅ ነው አሉት።
                    ******     
፵፬፡ ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ በእፎ እንከ ለሊሁ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ይቤ ይቤሎ እግዚእ ለአግዚእየ ንበር በየማንየ።
                    ******     
፵፬፡  ልጅማ ከሆነ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ እግዚእየ አብ እግዚእየ ወልድን በቀኜ ማለት በዕሪናዬ ኑር አለው እንደምን አለ።
እስከ አገብዖሙ ለጸላእትከ ታሕተ መከየደ እገሪከ።
ጠላቶችህን በእጅህ ጭብጥ በእግርህ እርግጥ አድርጌ እስካስገዛልህ ድረስ። ጸላእት አይሁድ አጋንንት መናፍቃን ናቸው። መከየደ እግር ያለው ሐዋርያት ሥልጣነ መለኮት መስቀል ረድኤት ነው።
                    ******     
፵፭፡ ዘለሊሁ ዳዊት እግዚእየ ይቤሎ እፎ እንከ ይከውኖ ወልዶ።
                    ******     
፵፭፡ ዳዊት ጌታዬ ያለው እንደምን ልጁ ይሆነዋል። ይህንንም ሊቁ በዝኒ ኢክህደ ልደተ ሥጋሁ ዘእምዘርዓ ዳዊት ብሎታል። የአምላክነቱን ነገር ሲናገር ነው እንጂ በሥጋ ከዳዊት መወለዱን አሉ ብሎት አይደለም ብሏል።
                    ******     
፵፮፡ ወአልቦ ዘክህለ አውሥኦተ ቃሉ ወአልቦ ዘተሀበለ ተስእሎቶ ምንተኒ እምይእቲ ዕለት።
                    ******     
፵፮፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ከዚያች ቀን ወዴህ ማንም ማን ሊጠይቀው ሊመልስለት የወደደ የደፈረ የለም።
                    ******     
በእንተ መደልዋን ፈረሳውያን
ምዕራፍ ፳፫።
፩፡ ወእምዝ ይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ለሕዝብ  ወለአርዳኢሁ።
፩፡ ከዚህ በኋላ ጌታ ነገራቸው።
                    ******     
  ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
02/10/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment