Saturday, June 29, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 126

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፳፮።
                    ******        
ዘከመ ከሠተ ሎሙ ለዘያገብዖ።
፳፡ ወምሴተ ከዊኖ ረፈቀ ምስለ ፲ ወ፪ቱ አርዳኢሁ። ማር ፲፪፥፲፯። ሉቃ ፳፪፥፲፱። ሉቃ ፲፫፥፳፩።
                    ******
፳፡ ሲመሽ በመሸ ጊዜ ከአሥራሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተቀመጠ።
                    ******
፳፩፡ ወእንዘ ይበልዑ ይቤሎሙ አማን እብለክሙ ከመ ፩ዱ እምኔክሙ ያገብአኒ።
                    ******
፳፩፡ ሲበሉ ከእናንተ አንዱ ያስይዘኛል ብሎ አንዲያሲዘኝ በእውነት እነግራችኋለሁ አላቸው።
                    ******
፳፪፡ ወተከዙ ጥቀ፡፡
                    ******
፳፪፡ ፈጽመው አዘኑ፡፡
ወአኃዙ ይበልዎ በበ፩ዱ አነኑ እንጋ እግዚኦ።
እያንድ አንዳቸው አቤቱ የሚያሲዝህ እኔ ነኝ እኔ ነኝ ይባባሉ ጀመር።
                    ******
፳፫፡ ወአውሥአ ወይቤሎሙ ዘያወርድ እዴሁ ምስሌየ ውስተ መጸብሕየ ውእቱ ያገብዓኒ፡፡
                    ******
፳፫፡ ከእኔ ጋራ ወጥ የሚያወጣው እሱ ያስይዘኛል አላቸው።
(ሐተታ) ለልማዱ ጌታ ስድስቱን አቁሞ ስድስቱን አስቀምጦ ይዞ ይበላሉ ይመገባሉ። ዛሬ የተቀመጡ ነገ ይቆማሉ ወጥ የሚያወጣው በተራ ነው ጌታ አያወጣ ይበላል አውጡልኝ አይልም ስድስተኛው ለአምስቱ ለራሱም እያወጣ ይበላል በዚያ ቀን ከተቀመጡት አንዱ ይሁዳ ነበር ወጥ ማውጣትም ተራው የይሁዳ ነበርና እንዲህ አለ።
                    ******
፳፬፡ ወልደ እጓለ እመሕያውሰ የሐውር በከመ ተሠርዓ በእንቲአሁ። መዝ ፵፥፲።
                    ******
፳፬፡ ተጽሕፈ ሲል ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስም ስለእሱ እንደተጻፈ ይሄዳል ማለት ይሞታል።
ወባሕቱ አሌ ሎቱ ለውእቱ ብእሲ ዘያገብዖ ለወልደ እጓለ እመሕያው።
ነገር ግን ምክንያት ሁኖ ለሚያሲዘው ለዚያ ሰው ወዮለት
እምኃየሶ ሶበ ኢተወልደ ለውእቱ ብእሲ።
ባልተወለደ በተሻለው ነበር።
(ሐተታ) እናቱን ይዳፋት ማለት ነው ቢሉ ኢተፈጥረ ሲል ነው ባልተፈጠረ በተሻለው ነበር ኦሪት ዘልደት እንዲል ዘፍጥረት ሲል። ይህስ ፍጠረኝ ብሎ ፈጥሮታልን ቢሉ ቢፈጥረውስ ግዕዛኑን ነሥቶ ፈጥሮታልን።
                    ******
፳፭፡ ወአውሥአ ይሁዳ ዘያገብዖ ወይቤ አነኑ እንጋ ውእቱ ረቢ፡፡
                    ******
፳፭፡ የሚያሲዘው ይሁዳም የሚያሲዝህ እኔ ነኝ አለው ተለይቼ ብቀር ይታወቅብኛል ብሎ
ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ አንተ ትቤ።
አንተ ትላለህ አለው። መሰወር።
አንድም በፈቃዴ የምሞተውን ሞት በግድ አስገድለዋለሁ ትላለህ።
(ታሪክ) ጌታ ሙሴን በግብፃውያን ሞተ በኵር አምጥቼ አወጣችኋለሁ አለው እንዲህማ ከሆነ የእስራኤልስ በኵር ሊሞት አይደለምን አለው፡፡ እንዲህስ እንዳይሆን የሚያዝያ ጨረቃ ሠርቅ ባደረገች በአሥር ቀን ቀንዱ ያልከረከረ ጥፍሩ ያልዘረዘረ ጠጕሩ ያላረረ ዓመት የሆነው ጠቦት ያለው ከመንጋው። የሌለው ገዝታችሁ እስከ ፲፬ት ቀን አስራችሁ በ፲፬ተኛው ቀን ፩ዱን ሰዓት ከ፫ት ከፍላችሁ ፩ዱን እጅ ትታችሁ በ፪ት እጅ ብርሃን ከሌሊቱም ፩ዱን ሰዓት ከ፫ት ከፍላችሁ በአንዱ እጅ ጨለማ ሠዉት። ስትሠዉትም ፯ት አሥር ፲፪ት ሁናችሁ። ያለው ቤተሰቡን ይዞ የሌለው ጎረቤቱን ጠርቶ ፩ድ በግ እንድትጨርሱ ሁናችሁ ደሙን መቃን መድረኩን እርጩት ያን እያየ ሞተ በኵር ይከለከልላችኋል፡፡ ዝግኑን ቅቅሉን ብርንዶውን አትብሉ ጥብሱን ብሉ ኢታትርፉ እስከ ደግደግ እንዲል። አትርፋችሁ አታሳድሩ ከአንዱ ወደ አንዱ አትውሰዱት የበላችሁትን በልታችሁ የተረፋችሁን ከእሳት ጨምሩት ሐምለ ብኂፅ ረብርቡበት ብሎታል በሀገራቸው አራት ነገር ያመጣሉ፡፡ የወይን ቅጥራን የበለስ ቅጥራን የስንዴ ቅጥራን አዞ ከል። በዚያ ወራት የሚበሉት ቂጣ ነውና እንደ አረቄ እንዲበትንላቸው። ስትበሉትም ጫማችሁን አዝባችሁ ዝናራችሁን ታጥቃችሁ ኩፌታችሁን ደፍታችሁ ቦሎታችሁን ይዛችሁ እየቸኮላችሁ ብሉት አጥንቱን አትስበሩት ብሏቸዋል ይህ ሁሉ ምሳሌ ነው። በግዕ የጌታ ምሳሌ ዓመት የሆነው ጠቦት ወርድ እንጂ ቁመት አያክልም። ጌታም ፍጹም የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ ሲሆን ነውና የተሰቀለ ዓመት የሆነው ጠቦት ቀንዱ ያልከረከረ ጥፍሩ ያልዘረዘረ ጠጕሩ ያላረረ ማለቱ ምክንያተ ኃጢአት የለበትምና። የሚያዝያ ጨረቃ ሠርቅ ባደረገች በአሥር ዋጅታችሁ እስከ አሥራ አራት አስራችሁ በአሥራ አራት ቀን ሠዉት ማለቱ የጌታም ምክረ ሞቱ በአሥር ተጀምሮ በአሥራ አራተኛው ቀን ተፈጽሟል። በሁለት እጅ ብርሃን በአንድ እጅ ጨለማ ሠዉ ማለቱ ከነግህ እስከ ቀትር ብርሃን ሁኑዋል። ከቀትር እስከ ሰዓት ጨለማ ሁኑዋል። ወጸልመ ኵሉ ዓለም እንዲል። በሠርክ ብርሃን ሁኑዋል። ወፍና ሠርክ ይብርህ እንዲል። ስትሠዉትም ሰባት አሥር አሥራ ሁለት ሁናችሁ ሠዉት ማለቱ ሰባት በእሳቸው ፍጹም ነው አሥርም በእኛ ፍጹም ነው ፍጹማን ሁናችሁ ተቀበሉ ሲል ፲፪ት ማለቱ ለጊዜው የሚቀበሉት አሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ናቸው ፍጻሜው ግን አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ናቸውና፡፡ ደሙን መቃን መድረኩን እርጩት ማለቱ ለጊዜው ያን እያየ ቸነፈር ይከለከልላቸዋል። ዛሬም ሥጋውን ደሙን ከሚቀበሉ ምዕመናን አጋንንት ላለመቅረባቸው ምሳሌ። ዝግኑን ቅቅሉን አትብሉ ማለት ሙስና መቃብር አገኘው አትበሉ ሲል ነው። ብርንዶውን አትብሉ ማለቱ ደም ካለ ነፍስ አትለይም። እስመ ነፍስ ተኃድር በደም እንዲል። ነፍስ ያልተለየውን ሥጋውን እንበላለን አትበሉ ሲል። ጥብሱን ብሉ ማለቱ መለኮት የተዋሐደውን ነፍስ የተለየችውን ሥጋውን እንበላለን በሉ ሲል ነው። አታሳድሩ አለ ካሣ ሳይፈጸም አላደረምና ከአንዱ ወደ አንዱ አትውሰዱት አለ ለጊዜው መካነ መስቀሉ ለመካነ መቃብሩ ቅርብ ነው። ፍጻሜው ግን ዛሬም መሥዋዕት ከአንዱ ሠርቶ ወደአንዱ ወስዶ መሠዋት አይገባምና የበላችሁትን በልታችሁ የተረፋችሁን ከእሳት ጨምሩት ማለቱ የተቻላችሁን ያህል ምሥጢር መርምራችሁ የቀረውን መንፈስ ቅዱስ ያውቃል በሉ አትጋፉ ሲል ነው፡፡ እሳት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ። ሐምለ ብኂዕ ረብርቡበት ማለቱ ለጊዜው በዚያ ወራት የሚበሉት ቂጣ ነበርና እንደ አረቄ አንዲበትንላቸው ነው። ዛሬም ሥጋውን ደሙን መቀበል የሚገባ የበሉት የጠጡት ከሆድ ሲጠፋ ለአፍ ምረት ሲሰማ ነውና። ጫማችሁን አዝባችሁ አለ ምግባረ ወንጌልን ሠርታችሁ፤ ዝናራችሁን ታጥቃችሁ አለ ንጽሕና ይዛችሁ ኩፌታችሁን ደፍታችሁ አለ አክሊለ ሦክን እያሰባችሁ በሎታችሁን ይዛችሁ አለ ነገረ መስቀሉን እያሰባችሁ ሲል ነው፡፡ እየቸኮላችሁ ብሉት ማለቱ ለጊዜው መንገደኞች ናቸው ፍጻሜው ግን ሞት አለብን እያላችሁ ኑሩ ሲል ነው። አረጋዊ መንፈሳዊ። ድርሳን። ዓብድ ውእቱ ዘይሄሊ  ዘእንበለ መቃብሩ እንዲል። አጥንቱን አትስበሩት ማለቱ ለጊዜው ግብፃውያን ሲጐዱ እስራኤል አለመጐዳታቸውን መናገር ነው። ፍጻሜው ግን ኃጥአን ሲጐዱ ጻድቃን ላለመጐዳታቸው ምሳሌ ነው በቁሙም የሁለቱን ወንበዶች ጭንና ጭናቸውን እየሰበሩ ሲያወርዷቸው የእሱን አልሰበሩትምና አጽሞ ኢትስብሩ እንዲል። እንደ አርዮስ ፍጡር በመለኮቱ አትበሉ ሲል ነው። ከዚህም ኦሪትን ሠርቶ አሳልፏታል። ንጉሥ ቀድሞ ሹሞት የነበረውንና ኋላ የሚሾመውን አቅርቦ ያን ወቅሶ ሽሮ ይህን አንዲሾም እሱም ወንጌልን የሚሰራ ነውና፡፡
                    ******
ዘከመ ሠርዓ ኢየሱስ አኩቴተ ቊርባን ።
፳፮፡ ወእንዘ ይበልዑ ነሥአ ኅብስተ እግዚአ ኢየሱስ ባረከ። ፩፡ቆሮ ፲፩፥፳፬፡፡
                    ******
፳፮፡ ሲባሉ ጌታ ዳቦውን አንሥቶ ይዞ ባረከ አከበረ ለወጠ።
ወፈተተ።
ገመሰ ቈረሰ።
አንድም ባረከ ገመሰ ቆረሰ ፈተተ አጠቃቀነ አሥራ ሦስት አደረገ፡፡ ጌዴዎን አሥራ ሦስት ሁኖ ሠውቷልና፤
አንድም በአሥራ ሦስቱ ዕፀወ ዕጣን ምሳሌ፤
አንድም አሥራ ሦስቱን ፀዋትወ መከራ እቀበልላችኋለሁ ሲል
አክሊለ ሦክ፡ ተኰርዖ ርእስ፤ ተጸፍዖ መልታሕት፡ ተወክፎ ምራቅ፡ ሰትየ ሐሞት፣ ተዓሥሮ ድኅሪት፤ ተቀሥፎ ዘባን፤ ርግዘተ ገቦ። ርግዘተ ገቦ ከሞተ በኋላ ነው አይሰማውም ብሎ ፀዊረ መስቀል ኃምስቱ ቅንዋት እግሩን እየራሱ ቸንክረውታል ያሉ እንደሆነ የተመቸ ነው። ደርበው ቸንክረውታል ያሉ እንደሆነ ብሱን ያያል። አንዱን እሱ ተቀብሎታል። ፲፪ን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል ዝ ሥጋየ ዝ ደምየ ብሏቸዋልና ለማስደፈር ጥዒሞ አጥአሞሙ እንዲል።
አንድም ሳይቀበል አቀብሏቸው ቢሆን ቄሱ አቀብሏቸው ሳይቀበል በወጣ ነበርና። ተቀብሎ ያቀብል ለማለት አብነት ለመሆን
ወወሀቦሙ ለአርዳኢሁ። ወይቤሎሙ ንሥኡ ብልኡ ዝ ውእቱ ሥጋየ።
ነገ በመልዕልተ መስቀል የሚሠዋው ሥጋየ ይህ ነው ብሉ፡፡
                    ******
፳፯፡ ወነሥአ ጽዋዓኒ ወአእኰተ።
                    ******
፳፯፡ ጽዋውንም ይዞ አክብሮ ለውጦ ትኩስ ደም አድርጎ
                    ******
፳፰፡ ወወሀቦሙ እንዘ ይብል ስትዩ እምኔሁ ኵልክሙ ዝ ውእቱ ደምየ ዘሐዲስ ሥርዓት ዘይትከዓው በእንተ ብዙኃን ለኅድገተ ኃጢአት።
                    ******
፳፰፡ እንግዳ ሥርዓት የሚሆን የሐዲስ ርስት የመንግሥተ ሰማያት መጽኛ የሚሆን በተሐድሶ ጸንቶ የሚኖር ስለ ብዙ ሰዎች የሚፈስ ደሜ ይህ ነው ከእሱ ጠጡ ብሎ ሰጣቸው።
(ሐተታ) በከፊል ተናገረው አንድ ሰው ተቀብሎ አይፈጽመውምና። እስከ ዕለተ ምጽአት ሲሰጥ ይኖራልና። ለኅድገተ ኃጢአት
ኃጢአት ሊሠርይ፡፡
                    ******
፳፱፡ ወናሁ እብለክሙ ኢይሰቲ እንከ እምይእዜ እምዝንቱ አፂረ ፍሬ ወይን እስከ እንታክቲ ዕለት አመ እሰትዮ ሐዲሰ ምስሌክሙ በመንግሥተ አቡየ።
                    ******
፳፱፡ በአባቴ መንግሥት ማለት በአባቴ ሥልጣን ታድሼ ተነስቼ ከእናንተ ጋራ በጥብርያዶስ እስከምመጣባት ቀን ድረስ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ አልጠጣም ብየ እነግራችኋለሁ።
                    ******
፴፡ አንቢቦሙ። ማር ፲፬፥፳፮፡፡ ዮሐ ፲፮፥፴፪፡፡ ዘካር ፲፫፥፮።
                    ******
፴፡ በኦሪት የሚደገም አለ ያን ደግመው።
ሰቢሆሙ።
ሥጋውን ደሙን ተቀብለው።
አንድም አንቢቦሙ አቡነ ዘበሰማያት ደግመው ወሰቢሆሙ ነገረ ጰራቅሊጦስን ተጫውተው።
                    ******
፴፩፡ ወፅኡ ውስተ ደብረ ዘይት።
                    ******
፴፩፡ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።
(ሐተታ) ሥጋውን ደሙን በመብል በመጠጥ ያደረገውን በሌላ ያላደረገው ስለምን ቢሉ የቀረው ከብት በአፍአ ይቀራል መብል መጠጥ ከሰውነት ይዋሐዳልና በእውነት እንደ ተዋሐደን ለማጠየቅ።
አንድም  መብል መጠጥ ያፋቅራል እንዳፈቀረን ለማጠየቅ ያውስ ቢሆን በስንዴ በወይን ያደረገው በሌላ ያላደረገው ስለምን ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም፡፡
ትንቢት እምፍሬ ሥርናይ ወወይን ወቅብዕ በዝኃ። ቀዳሜ ሕይወቱ ለሰብእ እክል ወማይ ወይን ወሥርናይ ለዘኢይሰቲ ወይነ ምንትኑ ሕይወቱ ተብሎ ተነግሯል። ምሳሌም መልከጼዴቅ በስንዴ በወይን ይሠዋ ነበር ትንቢቱን አውቆ አናግሯል ምሳሌውንም እንጂ ባወቀ አስመስሏል። ምሥጢሩ ምንድነው ቢሉ ጌታችን እመቤታችን ሲበሉ የኖሩ ስንዴ ወይን ነበረ ፍጹም ሥጋውን ፍጹም ደሙን እንደሰጠን ለማጠየቅ፡፡
አንድም በመሰለ ነገር ለመስጠት ስንዴ ስብ ሥጋ ይመስላል ወይንም ትኩስ ደም ይመስላልና።
አንድም ስንዴ ልባም ሴት የያዘችው እንደሆነ ነውር የለበትም። ነውር የሌለበት ሕግ ሠራሁላችሁ ሲል። ወይንም አንድ ጊዜ የጣሉት እንደሆነ ኃይል እየጨመረ ይሄዳል። ኃይል የምትሆን ሕግ ሠራሁላችሁ ሲል።
ወእምዝ ይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ኵልክሙ ትክህዱኒ በዛቲ ሌሊት።
ከዚህ በኋላ ጌታ በዚች ሌሊት ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ አላቸው።
እስመ ይብል መጽሐፍ እቀትሎ ለኖላዊ። ወይዘረዉ አባግዓ መርዔቱ።
መጽሐፍ። ጠባቂ ክርስቶስ ይሞታል የመንጋው በጎች ሐዋርያት ይበተናሉ ብሏልና።
                    ******
፴፪፡ ወእምድኅረ ተንሣእኩ አቀድመክሙ ገሊላ።
                    ******
ወደገሊላ እቀድማችኋለሁ ማለት ከተነሣሁም በኋላ መታየትን በገሊላ እጀምርላችኋለሁ
                    ******
፴፫፡ ወአውሥአ ጴጥሮስ።
                    ******
፴፫፡ ጴጥሮስም መለሰ።
ወይቤሎ ለእመሂ ኵሎሙ ክህዱከ አንሰ ኢይክህደክ ግሙራ።
ሁሉም ቢክዱህ እኔ አልክድህም አለው።
                    ******
፴፬፡ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ አማን እብለከ ከመ በዛቲ ሌሊት ሥልሰ ትክህደኒ ዘእንበለ ይንቁ ዶርሆ፡፡ ማር ፲፬፥፳፡፡
                    ******
፴፬፡ ጌታም በዚች ሌሊት ይሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ብዬ እንድትክደኝ በእውነት እነግርሀለሁ አለው።
                    ******
፴፭፡ ወይቤሎ ጴጥሮስ እመውትሂ ምስሌከ ወኢይክህደከ። ዮሐ ፲፫፥፴፰። ማር ፲፬፥፴፩፡፡ ሉቃ ፳፪፥፴፫ ።
                    ******
፴፭፡ ጴጥሮስም ከአንተ ጋራ እሞታለሁ ሞትክን ሞት አደርጋለሁ እንጅ አልክድሀም አለው፡፡
ወከማሁ ይቤሉ ኵሎሙ አርዳኢሁ።
ተመክቶ ያስመካቸዋል ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ እንደሱ ከእሱ ጋራ ሞትክን ሞት እናደርጋለን አንክድህም አሉ።
                    ******
ዘከመ ጸለየ ኢየሱስ በጌቴሴማን።
፴፮፡ ወእምዝ ሖረ እግዚእ ኢየሱስ ምስሌሆሙ ውስተ ዓፀደ ወይን ዘስሙ ጌቴሴማን።
፴፮፡ ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ ጌቴሴማን ከሚባለው ወይን ቦታ ሄደ።
                    ******
  ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
23/10/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment