Friday, June 28, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 125

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፳፮።
                    ******        
፩፡ ወሶበ ፈጸመ እግዚእ ኢየሱስ ዘንተ ኵሎ ነገረ ይቤሎሙ ለአርዳኢሁ። ተአምሩ ከመ እምድኅረ ሠኑይ መዋዕል ይከውን
ፋሲካ፡፡ ማር ፲፬፥፩፡፡ ሉቃ ፳፪፥፩።
                    ******            
፩፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አስተምሮ ከፈጸመ በኋላ እስከ ሁለት ቀን ድረስ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁን አላቸው፡፡
(ሐተታ) የሚያስተምረው ረቡዕ ነው ብሎ እስከ የወደቀበት ሐሙስ ነው።
አንድም ድኅረ ክልኤ ይላል ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ የሚያስተምርበት ማክሰኞ ነው ብሎ ድኅሩ ሐሙስ ነው ፋሲካ ከሐሙስ አይወጣም።
ወይእኅዝዎ ለወልደ እጓለ እመሕያው።
ወልደ እጓለ እመሕያውን ይይዙታል ማለት እያዛለሁ።
ወይሰቅልዎ
እሰቀላለሁ።
                    ******     
፫፡ ወእምዝ ተጋብዑ ሊቃነ ካህናት ወሊቃናተ ሕዝብ ውስተ ዓፀደ ሊቀ ካህናት ዘስሙ ቀያፋ።
                    ******     
፫፡ ከዚህ በኋላ የሕዝቡ አለቆችና የካህናቱ አለቆች ቀያፋ ከሚባለው ከካህናቱ አለቃ ቦታ ተሰበሰበቡ።
                    ******     
፬፡ ወተማከሩ ከመ በህብል የአኃዝዎ ለእግዚእ ኢየሱስ ወይቅትልዎ።
                    ******     
፬፡ በሐስት አንድ። በህብል ብለህ አጥብቀህ በድፍረት ይዘው ጌታን ይገሉት ዘንድ መከሩ።
                    ******     
፭፡ ወይቤሉ አኮኬ በበዓል ከመ ኢይትሀወኩ ሕዝብ።
                    ******     
፭፡ ነገር ግን ሕዝቡ እንዳይታወኩ በበዓል አይሁን አሉ።
                    ******     
ዘከመ ረፈቀ ኢየሱስ ለድራር በቢታንያ ወበእንተ ተካይዶቱ ለይሁዳ።
፯፡ ወበጺሖ እግዚእ ኢየሱስ ቢታንያ ቦአ ቤተ ስምዖን ዘለምጽ። ዮሐ ፲፩፥፪፡፡ ፲፪፥፫፡፡ ማር ፲፬፥፫።
                    ******     
፯፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢታንያ በደረሰ ጊዜ ከስምዖን ዘለምጽ ቤት ገባ።
ወመጽአት ኀቤሁ ብእሲት እንተ ባቲ ቢረሌ ዘምሉዕ ዕፍረተ ዘአልባስጥሮስ ዘብዙኅ ሤጡ።
ዋጋው ብዙ የሚሆን የደቀቀ የጣፈጠ ሽቱ ይዛ።
አንድም ዘአልባሰ ጢሮስ ይላል በጢሮሳዊ ግምጃ ዋጋ ልክ በሦስት መቶ ወቄት የተገዛ ሽቱ የያዘች ሴት መጣች።
ወሦጠት ዲበ ርእሱ ለእግዚእ ኢየሱስ እንዘ ይረፍቅ።
ጌታችን ከስምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችበት።
                    ******     
፰፡ ወርእዮሙ አርዳኢሁ አንጐርጐሩ በእንተ ዝንቱ ነገር።
                    ******
፰፡ ደቀ መዛሙርቱ ይህን አይተው አዘኑ።
ወይቤሉ ለምንትኑ ዘመጠነዝ ዕፍረተ አኅጐለት ዛቲ ብእሲት
ይህች ሴት ይህን ያህል ሽቱ ለምን አበላሸች።
እምኢተሠይጠኑ በብዙኅ ንዋይ ይትወሀብ ለነዳያን
ለነዳያን ይመጸወት ዘንድ የሀብዎ ይላል ለነዳያን ይመጸውቱት ዘንድ ለብዙ ዋጋ ባልተሸጠም ነበር አሉ።
                    ******
፲፡ ወአእመሮሙ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎሙ ለምንት ታስርኅዋ ለዛቲ ብአሲት።
                    ******
፲፡ ጌታችን እንዲህ ማለታቸውን አውቆባቸው ይህችን ሴት ለምን ታዳክሟታላችሁ አላቸው፡፡ ሠናየ ግብረ ገብረት ላዕሌየ ሊተ ሲል ለእኔ በጎ ሥራ ሠርታልኛለችና።
                    ******
፲፩፡ ወለነዳያንሰ ዘልፈ ትረክብዎሙ
                    ******
፲፩፡ ነዳያንንስ ዘወትር ታገኝዋቸዋላችሁ
ወጊዜ ፈቀድክሙ ታሤንዩ ሎሙ።
በወደዳችሁ ጊዜ ታደርጉላቸዋላችሁ።
ወኪያየሰ አኮ ዘልፈ ዘትረክቡኒ።
እኔን ግን ዘወትር አታገኙኝም
                    ******
፲፪፡ ወዘንተሰ ዕፍረተ ዘሦጠት ዲበ ርእስየ ለቀበርየ ገብረት።
                    ******
፲፪፡ ይህንም ራሴን የቀባችኝ ሽቱ ለምቀበርበት ቀን አስጠብቃዋለች።
(ሐተታ) ዕለቱን እንዳትቀበው አይሁድ አያስደርሷትም እንደ ሕጋቸው። በሦስተኛው እንዳትቀባው ፈጥኖ ይነሣባታልና። ዛሬም እጸድቅበታለሁ ብሎ ከሠራው በኋላ ማዳከም አይገባም አስቀድሞ ግን ቤተ እግዚአብሔር ልነጽበትን ለነዳያን ልስጣቸውን ብሎ ያማከረ እንደሆነ ሕንጻ እግዚአብሔር ሰው በረኀብ ሲፈርስ ሲበሰብስ ለነዳያን ስጥ እንጂ ማለት ይገባል። ከሠራ በኋላ ግን እንዲህ ማለት አይገባም። ያኑ ከመተው ያደርሰዋልና፡፡
(ታሪክ) አባ ኢዮብ አባ ጴሜን የሚባሉ ፍጹማን መነኮሳት ነበሩ ገባረ ሪፍ የሚባል በዓለም የሚኖር ደግ ሰው ነበረ እየመጣ ይጠይቃቸዋል ሊጠይቃቸው መጥቶ ሳለ አባ ጴሜን አንደምን ሁነህ ትኖራለህ አለው ተክል ተክዬ ራሴን ረድቼ እንግዳ ተቀብዬ በ.ቻለኝ ለነዳያን ተርፌ እኖራለሁ አለው። መልካም ይዘሀል ብሎ አሰናበተው። ከዚህ በኋላ አባ ኢዮብ መጣ ገባረ ሪፍ መጥቶ ነበር አለው ምን ብለህ አሰናበትከው አለው፡፡ እንዲህ ቢለኝ መልካም ይዘኀል አልሁት አለው። መልካም አላደረግህም እኛን መስለሀ ኑር እንዳትለው አለው፡፡ አጥፍቻለሁ ጠርቼ ላምጣው ብሎ ጠርቶ አመጣው፤ እኛን መስለህ ኑር አለው። ከነሁሉም አይቻለኝም ብሏል አባ ኢዮብ አላበጀሁም ማረኝ ብሏል። ይህች ሴት ከራስ ጸጐሯ እስከ እግር ጽፍሯ ይህ ቀራት የማትባል መልከ መልካም ናት፡፡ መላ አካሏን የሚያሳይ መስታወት አላት ልብሷን አኑራ መልኳን አይታ መፍረስ መበስበስ ላይቀር እንዲህ ማማር ምን ይረባል የዚያስ የዚያስ ኃጢአት የሚያስተሠርይ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቷል አሉ ለሱ የምቀባው ሽቱ ገዝቼ እሄዳለሁ ብላ በዝሙት የሰበሰበችው ሦስት መቶ ወቄት ወርቅ አላት ይዛ ሄደች። ዲያብሎስ ታመልጠኛለች ይህን ጊዜ ላስታት ብሎ ቀድሞ ከምታውቀው አንዱን መስሎ በአምሳለ ወሬዛ ሠናየ ላህይ ከመንገድ ቆያት። ወዴት ትሄጃለሽ አላት ዝም አለችው አንች ባትነግሪኝ እኔ እነግርሽ የለም እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ ለእሱ ልትቀቢው ሽቱ ልትገዥ ትሄሻለሽ አላት አዎን አለችው። ይህም አይደለም ፍቅሩ ያላለቀለት ወንድ መጥቶብሽ ለዚያ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዥ ትሄጃለሽ አላት አዎን አለችው ይህም አይደለም በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሸጥ ነጋዴ መጥቶብሽ ለእሱ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዥ ትሄጃለሽ አላት፤ አዎን አለችው ሁሉንም አዎን አዎን ትያለሽ ማናቸው ነው አላት። እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ አልክኝ ከዚህ ዓለም ልዩ የሚሆን ጌታ መጥቷል። ፍቅር ያላለቀለት ወንድ መጥቶብሻል ላልክኝ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት እንዲል። የሰው ፍቅር አገብሮት ሊሞት መጥቷል፡፡ በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሸጥ ባለጸጋ ነጋዴ መጥቶብሻል ላልከኝ አዎን በጥቂት ትሩፋት ብዙ ክብር የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥተልና ለእሱ የምቀባው ሽቱ ልገዛ እሄዳለሁ ብላ ስሙን ብትጠራበት እንደ ትቢያ በኖ እንደ ጢስ ተኖ ጠፍቶላታል። ከዚህ በኋላ ሃድኖክ የሚባል ባለ ጸጋ ነጋዴ አለ ሄዳ ለነገሥታት የሚገባ ሽቱ አምጣ ብላ ሦስት መቶ ወርቅ ሰጠችው በሀገራቸው ሐሰት የለምና ይህን ያህልስ የሚያወጣ የለኝም አላት እሱ የማያውቀው እናቱ የምታውቀው ዳዊት ሰሎሞን ተቀብተውለት የተረፈ ነበር ከእንዲህ ያለ ቦታ አለ ሽጥላት ብላው ሽጦላት አምጥታ ቀብታዋለች። ይህ ብቻም አይደል ጌታ ግብፅ ሲወርድ ሰሎሜም ፈያታይ ዘየማን ይዘውት ሳለ ከልብሱ ላይ ወዛ ቢያጽቡት ሰፈፈ ይህን በዕቃ አኑረውታል ይህም ተጨምሮበታል።
                    ******
፲፫፡ አማን እብለክሙ በኀበ ሰበክዋ ለዛቲ ወንጌል ይንግሩ ውስተ ኵሉ ዓለም ዘገብረት ዛቲ ብእሲት ተዝካረ ላቲ ወይዝክርዋ።
                    ******
፲፫፡ ወንጌል በተነገረችበት ቦታ ሁሉ ይህች ሴት የሠራችውን ሊነግሩላት ይገባል ብዬ እንዲገባ በእውነት እነግራችኋለሁ። ይኸንም ይዘው አራቱ ሁሉ ጽፈዋታል።
                    ******
፲፬፡ ወእምዝ ሖረ ፩ዱ እም፲ቱ ወ፪ቱ አርዳኢሁ ዘስሙ ይሁዳ አስቆሮታዊ ኀበ ሊቃነ ካህናት፡፡ ማር ፲፬፥፲፡፡ ሉቃ ፳፪፥፫፡፡
                    ******
፲፬፡ ከዚህ በኋላ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮት ሰው የሚሆን ይሁዳ ወደ ሊቃነ ካህናት ሄደ።
(ሐተታ) እንዲያው አይደለም በደብረ ዘይት ሲበሉ። አማን እብለክሙ ከመ ፩ዱ እምኔክሙ ያገብዓኒ አላቸው። ወአነኑ እንጋ እግዚኦ አነኑ እንጋ። የማስይዝህ እኔ ነኝ እኔ ነኝ ይባባሉ ጀመሩ።
(ታሪክ) በደብረ ዘይት ከነበሩ አዕባን አንዱን መጥተህ መስክርበት አለው መጥቶ በይሁዳ ራስ ላይ ሦስት ጊዜ ዙሮ ንጹሕ ደም የምታስፈስስ ይሁዳ ወዮልህ ብሎ መስክሮበታል ዛሬስ አለ አለና ይህ መሠርይ ደንጊያ ያናግርብኝ ጀመር እንኪያስ በማኝ ያግኘኝ ብሎ ወጥቶ ሂዷል።
                    ******
፲፭፡ ወይቤሎሙ ሚመጠነ ትሁቡኒ እመ አገብዖ ለክሙ፡፡
                    ******
፲፭፡ በአስይዛችሁ ምን ያህል ትሰጡኛላችሁ አላቸው።
ወተናገርዎ ምስሌሁ ወተሰነአው ከመ የሃብዎ ፴ ብሩረ።
ሠላሳ ብር እንሰጥሃለን አሉት። ወአስተሐለቁ ነገረ ይላል በሉቃስ፤ ነገር ቆረጡ ነገር አቆሙ ነገር ወሰኑ።
                    ******
፲፮፡ ወእምይእቲ ዕለት አኀዘ ይኅሥሥ ሳሕተ ከመ ያግብዖ ሎሙ፡፡
                    ******
፲፮፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ ከዚያ ቀን ወዲህ ሊያስይዘው ምግላል ቦታ ይሻ ነበር።
                    ******
በእንተ ደኀሪት ድራር።
፲፯፡ ወበቀዳሚት ዕለተ ፍሥሕ መጽኡ አርዳኢሁ ለእግዚእ ኢየሱስ ወይቤልዎ በአይቴ ትፈቅድ ናስተዳሉ ለከ ትብላዕ ፍሥሐ። ማር ፲፬፥፳፪። ሉቃ ፳፥፪-፮።
                    ******
፲፯፡ ፋሲካ ከሚውልባቸው ከ፯ቱ ዕለታት በመጀመሪያዪቱ ቀን።
አንድም ወአመ ቀዳሚት ዕለተ ፍሥሕ ይላል በመጀመሪያዪቱ ፋሲካ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጌታ ቀርበው በጉን ትበላ ዘንድ በወዴት ልናዘጋጅልህ ትወዳለህ አሉት። ሑሩ ወአስተዳልዉ ዘንበልዕ ፍሥሐ ብሏቸዋል በሉቃስ።
                    ******
፲፰፡ ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ሑሩ ውስተ ሀገር ኀበ እገሌ
                    ******
፲፰፡ ጌታም ወደእገሌ ሀገር ሂዱ አላቸው። እንደ ማርቆስ ምልክት ነግሮ ይሰዳቸዋል።
ወበልዎ ይቤለከ ሊቅ ጊዜየ በጽሐ በኀቤከ እገብር ፋሲካ ምስለ አርዳእየ።
መምህር ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ በአንተ ዘንድ በዓል የማከብርበት ቀን ደርሷል አለህ በሉት አላቸው።
                    ******
፲፱፡ ወገብሩ አርዳኢሁ በከመ አዘዞሙ እግዚእ ኢየሱስ።
                    ******
ደቀ መዛሙርቱ ጌታ እንዳዘዛቸው አደረጉ፡፡
አስተዳለው ሎቱ ፍሥሐ።
በጉን የሚያርዱበት ወቅለምት ደሙን የሚቀበሉበት ብርት ሥጋውን የሚቀቅሉበት ድስት አዘጋጅተዋል።
                    ******
ዘከመ ከሠተ ሎሙ ለዘያገብዖ።
፳፡ ወምሴተ ከዊኖ ረፈቀ ምስለ ፲ ወ፪ቱ አርዳኢሁ። ማር ፲፪፥፲፯። ሉቃ ፳፪፥፲፱። ሉቃ ፲፫፥፳፩።
፳፡ ሲመሽ በመሸ ጊዜ ከአሥራሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተቀመጠ።
                    ******
  ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
21/10/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment