Friday, June 14, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 118

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ዘአቅደመ ነጊረ ሙስናሃ ለቤተ መቅደስ።
ምዕራፍ ፳፬።
                    ******     
፩፡  ወወፂኦ እግዚእ ኢየሱስ እምቤተ መቅደስ ሖረ፡፡
                    ******     
፩፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ
ወቀርቡ አርዳኢሁ ወአርአይዎ ንድቀ ሕንፃሁ ለቤተ መቅደስ
ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው የቤተ መቅደስን ሥራ አሳዩት ማለት እንዲህ ሲያምር ይፈርሳል ትላለህ አሉት፤ የጧት ፀሐይ ወድቆበት ሲያሸበርቅ አይተው፡፡
ወአውሥአ እግዚአ ኢየሱስ
መለሰ፤
                    ******     
፪፡ ወይቤሎሙ ትሬእዩኑ ዘንተ ኵሎ፤
                    ******     
፪፡ ይህን ሁሉ ታያላችሁን ማለት ይህን ይደንቃችኋልን።
አማን እብለክሙ ኢይትኃደግ ዝየ ዕብን ዲበ ዕብን ዘኢይነሠት  የማይፈርስ ሁኖ ደንጊያ በደንጊያ ላይ አይቀርም ብዬ እንዳይቀር በእውነት እነግራችኋለሁ
(ሐተታ) ከጥጦስ ሠራዋት አንዱ ደንጊያ ቢፈነቅል ድስት ሙሉ ወርቅ አገኘ እንደዚያ እናገኛለን እያሉ ቤተ መቅደስን ሲያፈርሷት ፩ ፩ድ ደንጊያ አልደረሳቸውም፡፡
አንድም ትሬእዩኑ ብለህ መልስ ይህን ይደንቃችኋልን ይህስ የሰው ሕንፃ ነው
አማን እብለክሙ
ሕንፃ እግዚአብሔር ሰው ይፈርሳል ይበሰብሳል ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ።
                    ******     
፫፡ ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ።
                    ******     
፫፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ወደሱ ቀረቡ
ወይቤልዎ እንተ ባሕቲቶሙ
ለብቻቸው ጠየቁት ሦስቱ ባለሟሎቹ እንድርያስን ጨምረው ይጠይቁታል፡፡ ንግረነ ማእዜ ይከውን ዝንቱ ወናሁ ይትኃደግ ለክሙ ቤትክሙ በድወ ብሎ ነበርና ቤተ መቅደስ የሚፈርስበት ምን ጊዜ ይሆናል።
ወምንትኑ ተአምሪሁ ለምጽአትከ።
አማን እብለክሙ ኢትሬእዩኒ ብሎ ነበርና የምጻትህስ
ወለኅልፈተ ዓለም።
የኅልፈተ ዓለምስ ምልክቱ ምንድነው አሉት
                    ******     
፬፡ ወአውሥአ ወይቤሎሙ ዑቁ ኢያስሕቱክሙ፡፡ ኤፌ ፭፥፮፡፡
                    ******     
፬፡ እንዳያስቷችሁ አስተውሉ አላቸው።
                    ******     
፭፡ እስመ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ፣
                    ******     
፭፡ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙዎች በእኔ ስም ይነሣሉና፤
(ታሪክ) በአማራ መንግሥት ጊዜ ዘክርስቶስ ይሉኛል ብሎ ተነሥቶ እንደነበረ ሰቅለው ገለውታል፡፡ ከሱ ጋራ ፯ መቶ ሰዎች ሙተዋል ሰማዕታተ ዘክርስቶስ ተብለዋል፤
ወያስሕትዎሙ ለብዙኃን፤
ብዙ ሰዎችን ያስታሉ፤
                    ******     
፮፡ ወሶበ ሰማዕክሙ
                    ******     
፮፡ ፆር ሲሰበሰብ፣
ወአጽባዕተ፣
ጋሻ ለጋሻ ሲሳጐድ፤
ወድምፀ ጸባዒት፤
ገድሎ ሰልቦ ሲያገር ብትሰሙ
ዑቁ ኢትደንግፁ፤
እንዳትደነግፁ አስተውሉ
እስመ ግብተ ሀለዎ ይኩን ዝንቱ ኵሉ፤
ይሀ ሁሉ ፈጥኖ ይደረግ ዘንድ አለውና።
ወባሕቱ አኮ በጊዜሃ ዘየኃልቅ
ነገር ግን ያን ጊዜ የሚፈጸም አይደለም።
                    ******     
፯፡ ወይትነሥኡ ሕዝብ ዲበ ሕዝብ
                    ******     
፯፡ ሕዝበ ሮም በሕዝበ እስራኤል ላይ በጸላትነት ይነሱባቸዋል።
አንድም ወይትነሥኡ ሕዝብ ብለህ መልስ ሕዝበ እስራኤል በሕዝበ እስራኤል ላይ፤ ነገሥትተ እስራኤል በነገሥተ እስራኤል ላይ በጸላትነት ይነሡባቸዋል፣
(ሐተታ) ቀን ከጥጦስ ሠራዊት ጋራ ሲዋጉ ይውላሉ። ማታ ከእኔ ወገን አነግሥ ከእኔ ወገን አነግሥ እያሉ ስንዝር ስንዝር ሙሉ ሾተል አልፎ ሲሄድ አበጅተው አንዱ በአንዱ እየሸጐጠበት ይሄዳል ገዳዩ ስላልታወቀ ሞተ ዕውር ተብሏል፡፡
አንድም ሕዝበ ሮም በሕዝበ እስራኤ ላይ በጸላትነት ይነሡባቸዋል ሕዝበ ሮም ያላቸው ቅሉ ከአርዳሚስ ጋራ የሄዱ የአርዳሚስ ወገን ናቸው።
ወነገሥት ላዕለ ነገሥት።
ነገሥተ ሮም በነገሥተ እስራኤል ላይ በጸላትነት ይነሣሉ፡፡ ነገሥተ ሮም ያላቸው ቅሉ የአርዳሚስ ልጆች ናቸው።
ወይመጽአ ረኃብ ወብድብድ ወድልቅልቅ ውስተ ኵሉ በሐውርት።
በየሀገሩ ረኃብ ቸነፈር ሽብር ይደረጋል።
                    ******     
፰፡ ወዝንቱ ኵሉ ቀዳሚሁ ለሕማም ውእቱ።
                    ******     
፰፡ ይህ ሁሉ የመከራው መጀመሪያ ነው ማለት በጥጦስ ለሚደረገው መከራ ፊት አውራሪ ነው ቀዳሚሁ የጥጦስ ሕማም የሐሳዊ መሲሕ ቀዳሚሁ የሐሳዊ መሲሕ፤ ሕማም የምጽአት።
                    ******     
፱፡ አሜሃ ይትባጽሑክሙ ወይሜጥዉክሙ ለምንዳቤ። ማቴ ፲፥፲፯። ሉቃ ፳፩፥፲፪። ዮሐ ፲፭፥፳፡፡ ፲፮፥፪።
                    ******     
፱፡ ያን ጊዜ ለጸዋትወ መከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል።
ወይቀሥፉክሙ።
ከምኵራባቸው አግብተው ይገርፏችኋል፡፡
ወይቀትሉክሙ።
ይጻሏችኋል።
ወትከውኑ ጽሉዓነ በኀበ ኵሉ ሰብእ በእንተ ስምየ።
ስለ ስሜ ማለት በእኔ ስም ስላመናችሁ በእኔ ስም ስላስተማራችሁ በእኔ ስም ስለተጸራችሁ ሁሉ ይጸላችኋል።
                    ******     
፲፡ ወይእተ አሚረ የዓልዉ ብዙኃን ሃይማኖቶሙ
                    ******     
፲፡ በዚያን ጊዜ ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ
ወይጻልዑ በበይናቲሆሙ
እርስ በእርሳቸው ይጻላሉ።
ወያገብዑ ቢጾሙ ለሞት ይትቃተሉ።
አንዱ አንዱን ይጻላዋል።
                    ******     
፲፩፡ ወብዙኃን ሐሳውያን ነቢያት ይመጽኡ።
                    ******     
፲፩፡ በመምሕራን የሚያብሉ መምሕራንን የሚያሳብሉ ሐሰተኞች መምሕራን ይነሣሉ።
ወያስሕትዎሙ ለብዙኃን።
ብዙ ሰዎችን ያስቷቸዋል።
                    ******     
፲፪፡ ወእምብዝኃ ዓመፃ ወእከይ ተሐፅፅ ፍቅር እምብዙኃን።
                    ******     
፲፪፡ ከሐሰትና ከኃጢአት ብዛት የተነሳ ፍቅር ከብዙ ሰዎች ታንሳለች። ትሴኵስ ፍቅር ይላል አብነት የሐፅፅ ሲል ነው። ወይሴኵሱ ከመ ይቅብዑ መልአከ ወንጉሠ እንዲል። ዮአክስን ባነገሠ ጊዜ በዕልፍ በዕልፍ ይፋጠሩ የነበሩ እስራኤል አሥር ሠረገላ አምሳ ፈረሰኛ ሽህ እግረኛ ሁነው ተገኝተዋል።
ወብዙኃን የዓልዉ ሃይማኖቶሙ ወፍቅሮሙ።
ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ምግባራቸውን ይለውጣሉ።
                    ******     
፲፫፡ ወዘሰ አዝለፈ ትእግሥቶ ውእቱ ይድኅን።
                    ******     
፲፫፡ ፈጽሞ መከራውን የታገሠ ከፍዳ የሚድን እሱ ነው። እስከ
ፍጻሜ ይላል አብነት እስከ ዕለተ ሞቱ ታግሶ መከራ የተቀበለ ከፍዳ የሚድን እሱ ነው።
                    ******     
፲፬፡ ወይሰበክ ዝ ወንጌለ መንግሥት ውስተ ኵሉ ዓለም።
                    ******     
፲፬፡ የመንግሥት ወንጌል ማለት ጌትነቱን የምትናገር ወንጌል በ፬ቱ ማዕዘን ትነገራለች በእስላም ቤት ስንኳ ሳይቀር ትገኛለች።
(ታሪክ) በሀገራችን ቴዎድሮስ በሀገራቸው ዮሐንስ የሚባል ይነግሣል የእኛም ሂዶ ያም መጥቶ በእስክንድርያ ሦስት ቀን ይዋጋሉ አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት የክርስቲያን ደም ለምን ይፈሳል መሥዋዕት ሰውተን በመሥዋዕቱ ምልክት በታየለት ሃይማኖት ይጽና ይሏቸዋል ሁሉም በያሉበት መሥዋዕት ያቀርባሉ። የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በሰዋው አነ ውእቱ ክርስቶስ ብሎ በርግብ አምሳል ወርዶ ይመሰክራል ከዚህ በኋላ በሃይማኖት አንድ ይሆናሉ በግቢ ይገናኛሉ እንደዚህ የሚል ከምን አለ ቢሉ ከገድለ ፊቅጦር ከራእየ ሲኖዳ።
ከመ ይኩን ስምዓ በላዕለ አሕዛብ።
በአላመኑ በአሕዛብ መፈራረጃ ይሆንባቸው ዘንድ።
ወይእተ አሚረ ይበጽሕ ሕልቀት።
ያልተያያዘ ይአተ አሚረ ነው የሐሳዊ መሢሕን ሲናገር መጥቶ የጥጦስን ይእተ አሚረ አለ ነቢይ ኢሳይያስ የጼዋዌን ነገር ሲናገር መጥቶ የሚጠትን ይእተ አሚረ እንዳለ።
                    ******     
፲፭፡ ወእምከመ ርኢክሙ ትእምርተ ርኵስ ዘምዝባሬ ዘተብህለ በዳንኤል ነቢይ ዘይቀውም ውስተ መካን ቅዱስ ወዘያነብብ ለይለቡ። ዳን ፱፥፳፯፡፡ ማር ፲፫፥፲፬፡፡ ሉቃ ፳፩፥፳።
፲፭፡ በቅዱስ ቦታ የሚቆም ማለት ለቤተ መቅደስ አንባቢነት የሚሾም ያስተውል ተብሎ የተነገረውን ቤተመቅደስ በሚፈርስበት ጊዜ የሚሆን የጥጦስን ጣዖቱን ያያችሁ እንደሆነ ያን ጊዜ ፍጻሜው ይመጣል ማለት የአይሁድ ጥፋት ይሆናል ትእምርተ በላዖር እንዲል።
                    ******     
  ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
06/10/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment