====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ምሳሌ ዘዓቀብተ ወይን፡፡
ምዕራፍ ፳።
******
በእንተ ደቂቀ ዘብዴዎስ።
፳፡ ወእምዝ መጽአት ኀቤሁ እሞሙ ለደቂቀ ዘብዴዎስ ምስለ ደቂቃ፡፡ ማር ፲፥፴፭።
******
፳፡ ከዚህ በኋላ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ማርያም ባውፍልያ ልጆችዋን አስከትላ መጣች።
******
ወሰገደት ሎቱ እንዘ ትስአል
እየማለደተ ሰገደችለት።
(ሐተታ) እንዲያው አይደለም ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሆነ የሹመት ነገር አንድ ጊዜ ከተደላደለ በኋላ ያስቸግራልና ሂደሽ ተናገሪልን ለዘመድሽ ብለዋታል፡፡
ወይቤላ ምንተ ትፈቅዲ እግበር ለኪ።
ምን ላደርግልሽ ትወጃለሽ አላት።
******
፳፩፡ ወትቤሎ ረሷ ሊተ ከመ ይንበሩ እሉ ደቂቅየ ፩ዱ በየማንከ ወ፩ዱ በፀጋምከ በመንግሥትከ።
******
፳፩፡ በነገሥህ ጊዜ እኒህ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ ማለት አንዱን ቀኛዝማች አንዱን ግራዝማች በልልኝ አለችው።
******
፳፪፡ ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤላ ኢተአምሩ ዘትስእሉ
******
፳፪፡ የምትለምኑትን አታውቁም ማለት የባለጸጋ ልጅ ኃዘን ቢነግሩት አደን እንዲሉ እሞታለሁ እሰቀላለሁ ብላችሁ ሹመት ሽልማት ትለምናላችሁ አለ፡፡
ትክልኑ ሰትየ ጽዋዕ ዘአነ እሰቲ ወጥምቀተኒ ዘአነ እጠመቅ ትጠመቁኑ።
በዚያውስ ላይ የኔን ጽዋ ትጠጣላችሁ የኔን ጥምቀት ትጠመቃላችሁ ማለት እኔ የምሞተውን ሞት ትሞታላችሁ አላቸው።
(ሐተታ) ጽዋዕ ጥምቀት አለው ሞቱን። ጽዋ በተራ እንደሆነ ሞትም በተራ ነውና፡፡ ጽዋ እንዲያፋቅር ሞቱም ያፋቅራልና ጽዋ ፈጥኖ እንዲጨለጥ ፈጥኖ ተነሥቷልና ወአሕፀረ ዕድሜ ለርእሱ እንዲል። ጥምቀት እንዲያነፃ ሞቱም መንጽሒ ነውና።
ወይቤልዎ እወ ንክል
አዎን ይቻለናል አሉት፡፡
(ሐተታ) ለጌታ የሚያድር ሰው ሞትህን ሞት ሕይወትህን ሕይወት አደርጋለሁ ማለት ልማድ ነውና።
አንድም ለፍቅሩ ይሳሳሉ በፍቅሩ ይናደዳሉና።
******
፳፫፡ ወይቤሎሙ ጽዋዕየሰ ትሰትዩ ወጥምቀትየኒ ትጠመቁ።
******
፳፫፡ ጽዋዬን ትጠጣላችሁ ጥምቀቴን ትጠመቃላችሁ ማለት ሞቴንስ ትሞታላችሁ።
ወነቢረሰ በየማንየ ወበፀጋምየ አኮ አነ ዘእሁብ።
በግራና በቀኝ መቀመጥ ግን የምሰጥ እኔ አይደለሁም ማለት ቀኛዝማችነት ግራዝማችነት የምሾም እኔ አይደለሁም፡፡
ዘአንበለ ዘአስተዳለወ ሎሙ አቡየ ዘበሰማያት።
ሰማያዊ አባቴ ላዘጋጀላቸው ለነገሥታት ነው እንጂ።
አእምር ከመ ልዑል ይኴንን መንግሥተ ደቂቀ እጓለ እመሕያው ወዘፈቀደ ይሁብ እስመ ኢይሠየም መኰንን ዘእንበለ እምኀበ እግዚአብሔር ይል የለም ቢሉ አልመጣሁበትም ሲል እንዲህ አለ።
አንድም በቀኝ በግራ ሁነን እንሰቀል ትላላችሁን በቀኝ በግራ መሰቀል ለእናንተ አይደለም ሰማያዊ አባቴ በትንቢት ላዘጋጀላቸው ለፈያታዊ ዘየማን ለፈያታይ ዘፀጋም ነው እንጂ።
አንድም ትክልኑ ብለሀ መልስ። በክብር እንኑር ትላላችሁን እንግዲህስ ወዲህ በክብር መኖር ለእናንተ ብቻ አይደለም ለምዕመናን ሁሉ ነው እንጂ፡፡ ወለዲያቆናትኒ በፀጋሙ እንዲል።
******
፳፬፡ ወሰሚዖሙ ፲ቱ አንጐርጐሩ ላዕለ ፪ቱ አኃው።
******
፳፬፡ አሥሩ ይኽን ሰምተው በሁለቱ ወንድማማቾች አዘኑ ዛሬስ ከዚህ አኑረውን ሹመት ይካሰሱብን ጀመር ብለው።
******
፳፭፡ ወጸውዖሙ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎሙ ኢተአምሩኑ ከመ መኳንንቶሙ ለአሕዛብ ይኴንንዎሙ ወዓበይቶሙ ይቀንይዎሙ።
******
፳፭፡ ጌታ ጠርቶ አሕዛብን ነገሥታቱ እንዲገዟቸው ሹማምቱ እንዲያዟቸው አታውቁምን አላቸው።
******
፳፮፡ ወለክሙሰ አኮ ከማሁ።
******
፳፮፡ ለእናንተ ግን እንዲህ አይደለም።
******
፳፯፡ ወባሕቱ ዘይፈቅድ እምኔክሙ ይኩን ዓቢየ ይኩንክሙ ገብረ ወዘሂ ይፈቅድ እምኔክሙ ይኩን ሊቀ ይኩንክሙ ላዕከ።
******
፳፯፡ ከናንተ ወገን ገዢ ሊሆን የወደደ ሰው ተገዢ ይሁናችሁ በላይ ሊሆን የወደደም አገልጋይ ይሁናችሁ እንጂ።
******
፳፰፡ እስመ ኢመጽአ ወልደ እጓለ እመሕያው ከመ ይትለዓክዎ ዘእንበለ ዳእሙ ከመ ይትለዓክ ወየሀብ ነፍሶ ቤዛ ብዙኃን፡፡
******
፳፰፡ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ ሊያገለግል እንጂ ሊያገለግሉት ቤዛ ሊሆን እንጂ ቤዛ ሊሆኑት አልመጣምና። እንዲህም ባለ ጊዜ ፍቅረ ሢመትን አጥፍቶላቸዋል ሁለቱ እኛ የምንገዛቸው መስሎን ነው እንጂ የማንገዛቸው ከሆነ ሹመት ለምናችን ብለዋል፡፡ አሥሩም የሚገዙን መስሎን ነው እንጂ የማይገዙንማ ከሆነ ቢሾሙ ምንዳችን ብለዋል፡፡
******
፳፱፡ ወእንዘ ይወጽእ እምኢያሪኮ ተለውዎ ሰብእ ብዙኃን።
******
፳፱፡ ከኢያረኮ ወጥቶ ሲሄድ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።
******
በእንተ ዕውራን ዘኢያሪሆ።
፴፡ ወናሁ ፪ቱ ዕውራን ይነብሩ ጥቃ ፍኖት።
******
፴፡ ሁለት ዕውራን እነሆ ከመንገድ በአጠገብ ተቀምጠው ነበር፡፡
ወሰሚዖሙ ከመ እግዚእ ኢየሱስ የኃልፍ ጸርሑ።
ጌታ ሲያልፍ ሰምተው አሰምተው ተናገሩ።
ወይቤልዎ ተሣነሃለነ እግዚኦ ወልደ ዳዊት።
የዳዊት ልጅ አቤቱ እዘንልን አሉት።
******
፴፩፡ ወሰብእሰ ይጌሥፅዎሙ ከመ ያርምሙ።
******
፴፩፡ ሰዎች ግን ዝም በሉ ይሏቸው ነበር። ተአምራት ይደረጋል ሰው ይሳባል ወንጌል ትሰፋለች ኦሪት ትጠፋለች ብለው።
ወአዕበዩ ጸሪኃ እንዘ ይብሉ ተሣሃለነ እግዚኦ ወልደ ዳዊት
በዓይን ዋዛ ብለው የዳዊት ልጅ አቤቱ እዘንልን ብለው አሰምተው ተናገሩ።
******
፴፪፡ ወቆመ እግዚእ ኢየሱስ ወጸውዖሙ
******
፴፪፡ ለዕውር ርቆ መሄድ አይሆንለትምና ቁሞ ጸራቸው።
ወይቤሎሙ ምንተ ትፈቅዱ እግበር ለክሙ።
ምን ላደርግላላችሁ ትወዳላችሁ አላቸው።
******
፴፫፡ ወይቤልዎ ከመ ይትከሠታ አዕይንቲነ
******
፴፫፡ ዕውር ምን ይሻሃል ቢሉት ብርሃን እንዲሉ አቤቱ ዓይናችን ይበራልን ዘንድ እንወዳለን አሉት።
******
፴፬፡ ወአምሀርዎ ለእግዚእ ኢየሱስ
******
፴፬፡ ጌታችንን አሳዘኑት።
ወገሠሦሙ አዕይንቲሆሙ።
ዓይናቸውን ዳሰሳቸው።
ወበጊዜሃ ነጸሩ።
በዳሰሳቸውም ጊዜ አዩ።
ወተለውዎ።
ለጊዜው በእግር ተከተሉት ፍጻሜው በግብር መሰሉት ከ፸ አርድዕት ገብተው ተቆጠሩ።
አንድም ወእንዘ ይወፅእ እምኢያሪኮ ብለህ መልስ ከልዕልና ወደ ትሕትና በመጣ ጊዜ ነቢያት በግብር መሰሉት
ወናሁ ፪ቱ ዕውራን ይነብሩ ጥቃ ፍኖት።
ባሕታውያን ከዚህ ዓለም አፍኣ በምትሆን በበረሃ አሉ። ፍኖት ሐተታ አንዳለፈው ምዕ ፭ ቊ ፳፭። ባሕታውያንን ዕውራን አላቸው ከማየት ተከልክለዋልና። ምሥጢር ገና አልተገለጸላቸውምና
ወሰሚዖሙ
ጌታ በጸጋ እንዲገለጥ ምሥጢር እንዲገለጥ አውቀው።
ወይቤልዎ ተሣሃለነ
ምሥጢር ግለጥልን አሉት።
ወሰብእሰ።
አጋንንት ግን ገድላቸውን ያስተዋቸው ዘንድ መከራ ያጸኑባቸው ነበር በማደሪያቸው ሰብእ አላቸው።
ወአዕበዩ ጸሪኃ
የአጋንንትን ፆር ታግሠው አመለከቱ።
ወቆመ
በጸጋ ተገለጠሳቸው።
ወይቤሎሙ
ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ አላቸው።
ከመ ይትከሠታ
ምሥጢር ሊገለጥልን እንወዳለን አሉት።
ወገሠሦሙ
ምሥጢር ገለጠላቸው።
ወበጊዜሃ
ያን ጊዜ አወቁ።
ወተለውዎ
ባሕታውያን በግብር መሰሉት።
******
ዘከመ ቦአ እግዚእ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም።
ምዕራፍ ፳፩።
፩፡ ወቀሪቦ ኢየሩሳሌም በጽሐ ቤተ ፋጌ እንተ ገቦ ደብረ ዘይት። ማር ፲፩፥፩። ሉቃ ፲፱፥፩-፱፡፡
፩፡ ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ የደብረ ዘይት አጠገብ ከምትሆን ቤተ ፋጌ ደረሰ።
******
ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
23/09/2011 ዓ.ም
Friday, May 31, 2019
ወንጌል ቅዱስ ክፍል 107
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment