© መልካሙ በየነ
መጋቢት 22/
2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ስለጌታ ልደቶች
ወልደ አብ ገጽ 216-217 “የጌታችን ልደቱ ስንት ነው ቢሉ ኹለት
ነው። እንዴት ኹለት ነው እምቅድመዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን ዳግም ከእመቤታችን
በስጋ በጎል ተወለደ እንላለን ይህማ ሦስት አይደለምን እንደምን ኹለት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደትና ዛሬ
በማኅጸን በሥጋ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም። ኹለት ጊዜ ቆጥረነው አንድ
ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ
አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ
ኹለት ልደት አይባልም። ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ ያነን በከረጢት ከቶ
ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ ኹለት ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም። ዳግመኛ በአንድ ዘውድ
ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት ዘውድ አይባልም” እንደሚል
እና ሦስተ መሠረታዊ ስህተት እንዳሉበት ገልጠናል፡፡ ከሦስቱ መሠረታዊ ስህተቶች መካከል ሁለቱን ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች ተመልክተናል፡፡
ዛሬ በዚህ ክፍል የምንመለከተው ሦስተኛውን መሠረታዊ ስህተት ይሆናል እርሱም ምሳሌ ያስረዳል ተብሎ የተመሰለውን ከንቱ ምሳሌ ነው፡፡
“እምቅድመዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ
ተወለደ እንላለን ዳግም ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ እንላለን ይህማ ሦስት አይደለምን እንደምን ኹለት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም
በመለኮቱ የተወለደው ልደትና ዛሬ በማኅጸን በሥጋ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም።
ኹለት ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው
አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ
ልደት ይባላል እንጅ ኹለት ልደት አይባልም” ይላሉ፡፡ እውነት ይኼ ለማንም ለሚያይ ሁሉ እንደግንባር ግልጥ የሆነ የተሸሸገ ነገር የሌለው አይደለምን? እዚህ ላይ በግልጥ የምንመለከተው ሦስት
ልደትን ማመናቸውን ነው፡፡ መጻሕፍት “ሁለት ልደታትን እናምናለን” ብለው ስላጠሩባቸው ለመንፈራገጥ አልመች ቢላቸው ሦስት ጊዜ ቆጥሮ
ሁለት ማለት ይገባል ብለው ተናገሩ፡፡ እነርሱ የሚጠቅሷቸው በግልጥ የተቀመጡት የጌታ ልደቶች እነዚህ ናቸው፡፡
1. እምቅድመ ዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደት
2. በማኅጸን በሥጋ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት
3. ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ በማለት ሦስት ልደታትን አስቀምጠውልናል፡፡
ከእነዚህ ልደታት መካከል 2ኛው ልደት በየትኛውም መጽሐፍ ተጽፎ እንደማይገኝ
ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች በማስረጃ በማስደገፍ ጽፈናል፡፡ እነርሱ እንደሚሉት 1ኛ እና 2ኛ ላይ የተገለጡት ልደቶች አንድ ተብለው
ይቆጠራሉ እንጅ ሁለት አይባሉም ይላሉ፡፡ ለምን ለሚለው መልስ ሲመልሱ “ኹለት ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም
በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት
መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት ልደት አይባልም” ይላሉ፡፡ በእውነት ምንም
የማይመስል የማይገናኝ ከንቱ ነገር ነው፡፡ “እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ
ነው እንጅ ሌላ አይደለም” ማለት ምን ማለት ነው? እዚች ላይ ያዝ አድርጓት እስኪ፡፡ የቀደመ ልደቱ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ
ሳይቀድም ሳይከተል ያለእናት በመለኮት በረቂቅ ምሥጢር የተደረገ ነው፡፡ የዛሬው ልደቱ ደግሞ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ
በመለኮት አይደለም ምክንያቱም አብ የወለደው በሥጋ ነው ብለውናላ፡፡ በመለኮት ነው ካሉ ወልድ በመለኮቱ ስንት ጊዜ ተወለደ ብለን
እንጠይቃቸዋለን፡፡ በሥጋ ነው የወለደው ካሉን ደግሞ መለኮታዊ አካል ሥጋዊ አካልን መለኮታዊ ባሕርይም ሥጋዊ ባሕርይን ይወልድ ዘንድ
ይቻላልን ብለን እንጠይቃቸዋለን፡፡ አዎን ሊወልድ ይቻለዋል ካሉን የቀደመው ልደቱ ከአብ በመለኮት ነው የዛሬው ልደቱ ደግሞ ከአብ
በሥጋ ነውና ሁለት ብለን እንቆጥረዋለን እንጅ አንድ ልደት አንለውም ብለን በዚህ እንረታቸዋለን፡፡ ነገር ግን እነርሱ መረታትን
ስለማይሹ “ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስ ቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ
ኹለት ልደት አይባልም” ብለው መከራከራቸው አይቀርም፡፡ ነገር ግን ወላዲው አብ ይሁን ተወላዲውም ወልድ ይሁን አይቀየር አይለወጥ
እንጅ ልደቱ ግን ለየቅል ነው እንላቸዋለን፡፡ ምክንያቱም “የቀደመው ልደት በመለኮት የዛሬው ልደት በሥጋ” ነውና ልደቱ በጣም ይለያያል
እንላቸዋለን፡፡ አብ በመለኮት ቅድመ ዓለም የወለደው ልደት እና ዛሬ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የወለደው ልደት እጅግ
የተለያየ እንደሆነ ልብ ማለት ተስኗቸዋል፡፡ ለዚህም እኮ ነው ይች “ዛሬ አብ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ወለደው”
የምትለዋ ተጨማሪ የፍልስፍና ልደት ትቅር መጽሐፍ አይደግፋትም የምንለው፡፡ የጻፉትን ነገር ስትመለከቱት ፈራሽ ነገር ነው፡፡ ቀጥለው
ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ይሉናል፡፡ ልብ በሉ! ሦስት ልደት ቆጥረው ሁለት ልደት ነው ብለው ሙልጭ ብለው ለጠፉበት ክህደት የተሰጠ
ምሳሌ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ይላል ምሳሌው “ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ
ያነን በከረጢት ከቶ ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ ኹለት ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም።
ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት
ዘውድ አይባልም”፡፡ እነዚህን ምሳሌዎች ዘርዘር አድርገን ፍትፍት ብትንትን አድርገን እንመልከታቸውማ!
1. የአዲሱ ሸማ ጉዳይ ከልደቱ ጋር እስኪ ይዛመድ፡፡
ምሳሌነቱ፡- ሸማው ወልድ ነው፡፡ ለባሹ አብ ነው፡፡ ስለዚህ ለበሰ ለሚለው
ቃል አቻው ወለደ የሚለው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከረጢቱ የድንግል ማርያም ማኅጸን ምሳሌ መሆኑ ነው፡፡ ልብ በሉ አስተውሉ ወገኖቼ!!!
የጌታ ልደት እንደዚህ በከረጢት ገብቶ እንደመውጣት ያለ ተራ ነገር አድርገው ማሰባቸው ኅሊና ቢስ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ያም ሆነ
ይህ ግን ሸማው ወልድ መጀመሪያ በለባሹ (አብ) ተለበሰ (ተወለደ) ቀጥሎ በከረጢት በተመሰለው የድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ
(ተዋሐደ) ከዚያ ከዚህ ከረጢት ለባሹ (አብ) አውጥቶ ለበሰው (ወለደው) ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ለባሹም ልብሱም አልተቀየረም
አልተለወጠም ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ስንት ጊዜ ለበሰው ብለን ብንጠይቅ ለባሹ እና ልብሱ ስላልተለወጡ ስላልተቀየሩ አንድ ጊዜ
ለበሰው ሊባል ይችላል እንዴ? በእውነት ግን አንድ ልብስ የሚያረጀው ብዙ ጊዜ ስለተለበሰ አይደለምን ታዲያ በከረጢት አስገብተው
እያወጡ ሲለብሱት ያው አንድ ጊዜ ብቻ እንደተለበሰ ይቆጠራል ከተባለማ በጣም ጥሩ የኑሮ በዘዴ መምህር ሆነዋል ማለት ነው፡፡ ይች
ግን ጥሩ ፍልስፍና ሳትሆን አትቀርም፡፡ በእውነት ልብስ በከረጢት እያስገቡ ከዚያ እያወጡ ሲለብሱት ለባሹም ልብሱም ስላልተቀየረ
አንድ ተለበሰ ነው የሚባል ብለው አረፉት፡፡ ሁለት ጊዜ ስለተለበሰ ሁለት ሸማ ሳይሆን አንድ ሸማ ይባላል የሚለው ትክክል ነው፡፡
ነገር ግን በሸማው የተመሰለው ወልድ አይለወጥ አይቀየር እንጅ ሁለት ጊዜ ተወልዷል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ይህ ምሳሌ “እምቅድመዓለም
ከአብ የተወለደውንና በማኅጸነ ማርያም ከአብ የተወለደውን ሁለት ልደት ሁለት ብለን እንድንቆጥር እንጅ አንድ ብለን እንድንቆጥር
አያደርግም እና የወልድ ልደቶች ሦስት ናቸው እንደሚሉ ጥሩ ምሳሌ ነው” የምንለው፡፡
2. የዘውዱ ጉዳይ ከልደቱ ጋር ያለው ምሳሌነት ሲዛመድ፡፡
“ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት
ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት ዘውድ አይባልም”
ምሳሌነቱ፡- ዘውዱ አብ ነው፡፡ ነጋሹ ወልድ ነው፡፡ ንግሥናው የልደት
ምሳሌ ነው፡፡ እዚህ ላይ በአንዱ ዘውድ (በአብ) ብዙ ነገሥታት (ልጆች) ይነግሡበታል (ይወለዱበታል) ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይኼ
ምኑ ነው ሦስት ልደት ብለው የቆጠሩትን ሁለት እንድንል የሚያሳምነን? ምናልባት እዚህ ላይ “ዘውዱ” እንደ ልደት ተቆጥሮ ከሆነ
ነጋሹ ወልድ አንጋሹ አብ ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአንዱ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት እንደሚነግሡበት ሁሉ በአንዱ ልደትም
ሁለት ሦስት ልጆችን ወለደ ያሰኝባቸዋልና ይህም የተዋረደ ከንቱ ምሳሌ እንደሆነ በዚህ እንረዳለን፡፡
ስለዚህ በመጽሐፍ ያልተጻፈ በሊቃውንት በመምህራን ያልተነገረ እንግዳ
የሆነ ትምህርትን ዝም ብላችሁ መቀበል እንደማይገባችሁ ለሁሉም የቅብዓት እምነት ተከታዮች ሁሉ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ መሰዳደቡን
መጨቃጨቁን ትተን እውነትን ወደ መመርመር እንግባ፡፡ እኛ ከተሳሳትን መጽሐፍ ጠቅሳችሁ ሊቃውንቱን አብነት አድርጋችሁ እውነቱን አሳዩን
እናንተ ከተሳሳታችሁ ግን እኛን ምሰሉን!!!
የጌታን ሁለት ልደታት ሊቃውንቱ እንዴት ይገልጹታል የሚለውን በቀጣይ
ክፍል እንመለከታለን፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡