Wednesday, March 15, 2017

ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት---ክፍል ፭


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 6/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

የጉባኤ ቁስጥንጥንያ መጀመር
ከላይ የተመለከትናቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች ለመመልከት የተሰበሰቡ ሊቃውንት በግንቦት ወር በ381 ዓ.ም ይህንን ጉባኤ አስቀድመን እንደገለጽነው የተለያዩ ሊቃውንት በሊቀመንበርነት መርተውታል፡፡ የጉባኤው ምክንያት የሆነው መቅዶንዮስ ቀረበ እና ስለሚያስተምረው ኑፋቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አቅርብ ተባለ፡፡ ሆኖም ግን መቅዶንዮስ “መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ነው” ከማለት ውጭ ለተጠየቀው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም፡፡  ከዚያም ሊቀውንቱ ትን.ኢሳ 6÷3 ላይ “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር …” ማለቱ አንድነቱን እና ሦስትነቱን ሲገልጽ መሆኑን አትረዳምን? አንዱ ቅዱስ ለአብ አንዱ ቅዱስ ለወልድ አንዱ ቅዱስ ለመንፈስ ቅዱስ እንደተነገረ አታውቅምን? ቃሉ አለመለወጡ አንድነቱን ቃሉ ሦስት ጊዜ መነገሩ ሦስትነትን ሲያስረዳ መሆኑን አታውቅምን? ታዲያ አንተ መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ነው የሚለውን ክህደት ከወዴት አገኘኸው? ብለው በዚህ አስረዱት መቅዶንዮስ ግን በልቡ ያደረውን ሰይጣን ማዳመጥ ጀመረ፡፡ በፍጹም መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ አይደለም ፍጡር ነው እንጅ በሚል ክህደቱ ጸና፡፡ አሁንም ሊቃውንቱ ማቴ 28÷19 ላይ “… አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኳችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው” ይላልና መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ቢሆን ኖሮ በዚህ ወንጌል በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ አጥምቁ ባላለም ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ ጋር የተካከለ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ ነውና ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ይህንን ነገራቸው፡፡ ታዲያ መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ከሆነ ለምን ይህንን ትእዛዝ ለሐዋርያት ሰጣቸው ብለው መቅዶንዮስን ጠየቁት እርሱ ግን በፍጹም አላምንም አልመለስም አለ፡፡
የጉባኤ ቁስጥንጥንያ ውሳኔዎች
ቅዶንዮስ ሊቃውንቱ ያቀረቡለትን ማስረጃ አልቀበልም በማለቱ የተነሣ 150ው ሊቃውንት መቅዶንዮስን አውግዘው ለይተውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጉባኤው ቃለ እግዚአብሔር በተዋሕዶ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ከድንግል ማርያም የነሣው ሥጋን ብቻ ነው እንጅ ነፍስን አልነሳም በማለት ያስተምር የነበረውን መናፍቅ አቡሊናርዮስን እና ይህን ክህደቱን አውግዘው ለይተውታል፡፡ የዚህ የአቡሊናርዮስ ክህደት ከሥጋዊው ፈላስፋ ከፕላቶን የመነጨ ነው፡፡ ይህ ፈላስፋ ሰው በሰውነቱ ሰው ሆኖ የሚታወቀው ከመለኮት ተከፍላ በተሰጠችው ነባቢት፣ ለባዊት እና ሕያዊት ነፍሱ ነው ይል ነበር፡፡ ይህ አቡሊናርዮስም የዚህን ፍልስፍና ወስዶ ቃል ሥጋ ሲሆን የተዋሐደው ሥጋን ብቻ ነው ነፍስን አልተዋሐደም በዚህም ምክንያት መለኮት ለሥጋ ነፍስ ሆኖታል የሚል ክህደቱን ጀምሯል፡፡ ሊቃውንቱም የዚህን ክህደት “ቃል ሥጋ ሆነ” የሚለውን የዮሐንስ ወንጌል ቃል በሚገባ አብራርተው አመስጥረው አስረዱ፡፡ ከሊቃውንት መካከል አንዱ የሆነው ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ ለዚህ ክህደት ተገቢውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ይህ ነባቤ መለኮት በመባል የሚጠራው ጎርጎርዮስ “ሰው ማለት ነፍስና ሥጋ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን ብቻ ነሣ እንጅ ነፍስን አልነሣም ከተባለ ያዳነውም ሥጋን ብቻ ነው እንጅ ነፍስን አዳነ አይባልም ማለት ነው በማለት የአቡሊናርዮስን ክህደት ተናግሯል፡፡ ይህ የአቡሊናርዮስ ክህደት በዚህ ጉባኤ የተወገዘው ከሁለት ሌሎች ውግዘቶች በኋላ ነው፡፡ በእስክንድርያ ሲኖዶስ በ362 ዓ.ም እና በአንጾኪያ ሲኖዶስ በ379 ዓ.ም ከተወገዘ በኋላ በዚህ ጉባኤ በ381 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተወግዞ ተለይቷል፡፡ ሌላው በዚህ ጉባኤ ላይ የኒቅያ ጉባኤ አባቶች ባረቀቁት የሃይማኖት ጸሎት ላይ አምስት አንቀጾችን ጨምረዋል፡፡ የተጨመሩት አንቀጾችም ስለመንፈስ ቅዱስ አምላክነት ስለ ቤተክርስቲያን አንዲት መሆን ስለጥምቀት እና ስለ ትንሣኤ ሙታን የሚናገሩ ናቸው፡፡  የተጨመረው የሚከተለው ነው፡፡
v  “በጌታ በአዳኝ ከአብ በሰረፀ ከአብና ከወልድ ጋር በነባቢት በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እንስገድለት እናመስግነው” በማለት መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው ላለው ለመቅዶንዮስ ክህደት ተናግረውታል፡፡
v  “በሁሉ ባለች በሐዋርያት ጉባኤ በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን” በማለት የቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊትና አንዲት መሆን ተናግረዋል፡፡
v  “ለኃጢአት ማስተሠርያ በምትሆን በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት ለሐዋርያት አህዛብን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛሙርቴ አድርጓቸው ብሏቸው ስለነበር ይህችን አንዲት ጥምቀት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንድናደርጋት ተናገሩ፡፡
v  “የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ እናደርጋለን” በማለት የትንሣኤ ሙታንን ምሥጢር ተናግረዋል፡፡
v  “የሚመጣውንም ሕይወት እንጠባበቃለን ለዘለዓለሙ አሜን” በማለት ጸሎተ ሃይማኖትን ፈጽመዋል፡፡
በኒቅያ የተሰበሰቡ አባቶች በወሠኑት ቀኖና ላይ የቁስጥንጥንያ ጉባኤ አባቶች የጨመሩትን የጸሎተ ሃይማኖት አንቀጾች ዛሬም ድረስ ቤተክርስቲያናችን እየተጠቀመችበት ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያናችን የዚህ አንቀጸ ሃይማኖት ምንጭ ናትና፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment