Tuesday, March 28, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፱


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 19/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ከተዋሕዶ በኋላ ቅብዓት ለምን አስፈለገ?
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ገጽ 780 ላይ የቅብዓት ባህል 3 ክፍል አለው ይላሉ፡፡ መጀመሪያ በፋሲል ዘመን የተነሡት እነዘኢየሱስ መጽሐፍ “አንደየ ርእሶ” ይላልና “ቃል በተዋሕዶ ዜገ ከሥጋ ሲዋሐድ የባሕርይ ክብሩን አጣ ለቀቀ ሲቀባ ወደ ጥንተ ክብሩ ተመልሶ በሰውነቱም በአምላክነቱም አንድ ወገን በቅብዓት የባሕርይ ልጅ ሆነ ብለዋል” ይላሉ፡፡ በፋሲል ዘመን የነበሩት የመጀመሪያዎቹ የዚህ የክህደት አስተምህሮ ጠንሳሾች ቃል ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ የባሕርይ ክብሩን ከዐይን ጥቅሻ በምታንስ ጊዜ ስለዜገ ማለትም ስለደሐየ፣ ስለ አጣ፣ ስለተቸገረ ወደ ቀደመ ባሕርይ ክብሩ ለመመለስ ቅብዓት ያስፈልገዋል ባዮች ናቸው፡፡ ይህ አስተምህሮ ደግሞ አስቀድመን እንዳየነው ሚጠትና ውላጤ የተባበሩበት ክህደት ነው፡፡ ዛሬም በተወሰኑ ሰዎች ይህ ምንፍቅና ሲነገር እንሰማዋለን፡፡ በመጽሐፋቸው ላይም ወልደ አብ ገጽ 219 አጣ፣ ደሐየ፣ ተቸገረ (ዜገ) ሲሉ “…ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ብለዋል፡፡ ቀጥለውም ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱን ሲገልጹ ወልደ አብ ገጽ 166 ላይ  “… መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ ቢወለድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ልጅ ሆነ” በማለት ጽፈዋል፡፡ በተጨማሪም ወልደ አብ ገጽ 219 ላይ “ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር” በማለት አብን ሰጭ ወልድን ደግሞ ተቀባይ መንፈስ ቅዱስን ስጦታ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ ስለዚህ ነው እንግዲህ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስን ጠቀመው ረባው ማለታቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ባይወለድ ኖሮ ወልድ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ መግዛት ማዘዝ አይችልም ነበር ማለታቸው ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ያስፈልገዋል ለማለት እንደሆነ እንረዳቸዋለን፡፡ ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ገዥ ሆነ ማለት ያስነቅፋል፡፡ ይህንንም ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ብሏል “ዳግመኛ በዚህ ድርሳን እግዚአብሔር ሕያው አምላክ የሆነ ሥጋን በመንፈስ ቅዱስ ፈጠረ ዓለምንም በእርሱ አዳነ ብንል ዐላዋቆች ይነቅፉናል” ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ ም 68 ክ 28 ቁ 43፡፡
ወልደ አብ ገጽ 230 ላይ ደግሞ ለመለኮት የማይቀፀል ቃል እንዲህ ብለው ቀፀሉ “በዚህም በባሕርይ ልጅነቱ እኛ ብቻ ተጠቅመንበት አልቀረንም እርሱም ተጠቀመበት እንጅ” ይላሉ፡፡ ወልድ ምን ተጎድቶ ምን ጎድሎበት ነው በመወለዱ ተጠቀመ የሚባለው፡፡ ይባስ ብለው ገጽ 233 ላይ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ እንደአስተካከለው...” ብለው ወልድን ከባሕርይ ክብሩ ዝቅ ሲያደርጉት ይስተዋላሉ፡፡ በመወለዱ ተጠቀመ የሚባለው በእውነት ምን ጎድሎበት ይሆን? ሃይማኖተ አበው ዘኤፍሬም ም 47 ቁ 5 ግን እንዲህ ይላል “የድንግልን ሥጋ መረጠ ሰው መሆኑን ሊያስረዳ ፍጹም አካሉን በማኅጸኗ ፈጠረ ከእርሷ ሥጋን የተዋሐደ እጠቀምበታለሁ ብሎ አይደለም” ይላል፡፡
ሁለተኛው ባህላቸው በአንደኛው ዮሐንስ ዘመን የተነሡት እነ አካለ ክርስቶስ “ዜገ” የሚለውን የእነ ዘኢየሱስን ትምህርት ነቅፈው አጸይፈው መጽሐፍ “እስመ ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ ይላልና ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል ሆነ እንጅ የአምላክነት ክብር አላገኘም፡፡ ሲቀባ ግን ክብር ተላልፎለት ተፈጥሮ ተገብሮ ጠፍቶለት በቅብዓት የባሕርይ ልጅ የባሕርይ አምላክ ሆነ ብለዋል” ከመጀመሪያዎች የሚለያቸው መቀባትንና መለወጥን ለሥጋ ብቻ መስጠታቸው ነው፡፡ በዚህ ዘመንም የተነሡት ይዘውት የመጡት ክህደት ከመጀመሪያዎቹ ተመሳሳይነት ያለው ክህደት ነው፡፡ የዛሬዎቹ የቅብዓት አማኞችም ይህንን ባህል ደግፈው ይታያሉ፡፡ ወልደ አብ ገጽ 232 ላይ  “ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋሕዶ ከበረ ቅብአት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል፡፡ ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ሁለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም” ይላሉ፡፡ እነርሱ ተዋሕዶን የሚረዱበት አረዳድ እኛ የተዋሕዶ አማኞች ከምንረዳበት አረዳድ እጅጉን የተለየ እንደሆነ በዚህ እንገነዘባለን፡፡ ተዋሕዶ ለእነርሱ ሁለትነትን አጥፍቶ አንድነትን ብቻ ያጸና ነው እንጅ የሥጋ ንድየት በቃል ብዕልነት እንዳልተወገደ ያምናሉ፡፡ እኛ ደግሞ ሁለትነት ጠፍቶ አንድነት ሲጸና የሥጋ ንድየት በቃል ብእልነት ተወግዶ ቅድምና የሌለው ሥጋ ቀዳማዊ ሆነ አምላክም ሆነ እንላለን፡፡ ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ ማለት ስለዚህ ነው፡፡ የሥጋ ገንዘብ (ከኃጢአት በቀር) ለመለኮት ፤ የመለኮትም ገንዘብ ለሥጋ ገንዘቡ ሆነ የምንለው በተዋሕዶተ መለኮት ነው እንጅ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፡፡
ሦስተኛው ባህላቸው በዐጼ ቴዎድሮስ ዘመን የተነሡት እነአለቃ ጎሹ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ በቅብዓት ብቻ ማለትን ነቅፈው “መጽሐፍ በሁለቱም ሁሉ በተዋሕዶ ከበረ በቅብዓት ከበረ ይላልና ቅብዓት ያለተዋሕዶ ተዋሕዶም ያለቅብዓት ብቻ ብቻውን አያከብርም በተዋሕዶና በቅብዓት በአንድነት የአምላክነት ክብር ከብሮ የባሕርይ ልጅ ሆነ ብለዋል” ይላሉ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፡፡ በዚህ ዘመን ያሉት የቅብዓት እምነት አራማጆችም ይህንን ደግፈው ይታያሉ፡፡ ወልደ አብ በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ 126 ላይ “… ተዋሕዶ ተፈጠረ ሳይዋሐድ አልተፈጠረም፡፡ ተዋሕዶ ሳይፈጠር አልቆየም፡፡ ሲዋሐድ ሲፈጠር አንድ ጊዜ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ተዋሕዶ ቀደመ ባሉ ጊዜ ከቅብዓትም ተዋሕዶ ቀደመ ማለት ይሆናል” በማለት በተዋሕዶ እና በቅብዓት እንደከበረ ይናገራሉ፡፡
ሌላው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ራሳቸው ከቅብዓት ሦስቱ ባሕሎች ካሏቸው ውጭ ሌላ ባህል አላቸው፡፡ እርሳቸው እነዚህን ሦስቱን የቅብዓት ባህሎች ከገለጹ በኋላ ማብራሪያ ብለው የገለጹት ሌላ ባህል ውስጥ የሚያስገባ ክህደት ነው፡፡ እርሳቸው “ተቀብዐ” የሚለው አንቀጽ ለቃል በመሆኑ “ቃል መንፈስ ቅዱስን በመቀባቱ መሢህ፣ ንጉሥ፣ ዳግማይ፣ በኩረ ምእመናን ሆነ” ይላሉ፡፡ ይህ የአለቃ ኪዳነ ወልድ አስተምህሮ ወልድን ፍጡር ነው ካለው ከአርዮስ የሚደምር ክህደት ነው፡፡ አርዮስ ወልድን በመለኮቱ ፍጡር እንዳለው ሁሉ አለቃ ኪዳነ ወልድም የጻፉት ወልድ በክብር በሥልጣን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ እንደሚያንስ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ባህል ከአርዮስ ባህል ያስገባል፡፡ ምክንያቱም “ቃል መንፈስ ቅዱስን በመቀባቱ ከበረ” የሚል ሌላ ባሕል ነው፡፡ “ቃል ክቡር አምላክ የሆነው በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ነው” ማለታቸው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ከላይ ባየናቸው የቅብዓት ባሕሎች ውስጥ የመለኮት ወደ ሰውነት መለወጥን (ውላጤን) ደግፈው የሚገኙ ክህደቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ውላጤ በኋላ ደግሞ በቅብዓት ከከበረ በኋላ አምላክ ሆነ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ገዛ ይላሉና ወደ አምላክነት ክብር መመለስን (ሚጠትን) ያሳያል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ በሦስቱም ውላጤና ሚጠት ይታያል፡፡ እናውቃለን ምሥጢር እንጠነቅቃለን የሚሉ የዘመናችን የቅብዓት እምነት ተከታዮች በእነዚህ ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ባሕሎች ውስጥ የተወሸቁ ናቸው፡፡ ሦስቱንም ዓይነት ባሕል ደግፈው የሚገኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ነው እንግዲህ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ማለት ክህደት ነው ምንፍቅና ነው የምንለው፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment