Wednesday, March 22, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፮


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 14/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ቅብዓት ከበረ የሚለው ምንፍቅና                            

በምሥጢረ ሥላሴ እና ሥጋዌ ላይ እንደተማርነው የአብ ግብሩ መውለድ ማስረጽ የወልድ ግብሩ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መስረጽ ነው፡፡ ከዚህ ወጥቶ አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ የሚል የሥላሴ የሦስትነት ግብር በመጻሕፍት አይገኝም፡፡ ስለዚህ ነው “ወልድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለው አገላለጽ ኑፋቄ ነው የምንለው፡፡ “ወልድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለው አገላለጽ ሚጠትን፣ ውላጤን እና ትድምርትን የሚደግፍ ነውና “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ከሚለው እምነታችን የተለየ ነው፡፡ በዚህ እምነት ውስጥ ያሉ ሰዎች “ተዋሕዶ” የሚሉት እኛ የተዋሕዶ አማኞች “ተዋሕዶ” ከምንለው የተለየ ነው፡፡ እነርሱ “ተዋሕዶ” የሚሉት የኅድረት ተዋሕዶን ነው፡፡ ይህ የኅድረት ተዋሕዶ እግዚአብሔር በቅዱሳን ላይ በጸጋ የሚያድርባቸው ተዋሕዶ ነው፡፡ እነርሱ ተዋህዶ የሚሉት ይህንን ዓይነት ተዋሕዶ ነው፡፡ እኛ ግን “ተዋሕዶ” ስንል የከዊን ተዋሕዶን ነው፡፡
የከዊን ተዋሕዶ ማለት ቃል እና ሥጋ የተዋሐዱት በአካልም በባሕርይም ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ከተዋሕዶ በፊት ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያት የነበሩት ከተዋሕዶ በኋላ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ማለት ከሁለት ባሕርያት አንድ ባሕርይ ከሁለት አካላት አንድ አካል የሆነ ሰው የሆነ አምላክ ማለት ነው፡፡ ቃል በባሕርዩም ከሥጋ ጋር ተዋሕዷል ከተባለማ እግዚአብሔር በባህርይ አንድ ነውና ሦስቱም ሥጋ ለበሱ ያሰኝባችኋልሳ ቢሉ አያሰኝም፡፡ ለዚህም ሊቃውንቱ ያብራሩበት በቂ ማስረጃዎች አሉን፡፡
1ኛ. ማስረጃ፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ “ቃል ሥጋ ኮነ” በማለት ተናግሯል፡፡ አካል ብቻ ተዋሕዶ ቢሆን ኖሮ የአካል መጠሪያ ሥም በሆነው በተናገረ ነበር፡፡ “ወልድ ሥጋ ኮነ” ቢል ኖሮ “ወልድ” የሚለው የአካላዊ ቃል መጠሪያ ሥም ስለሆነ አካል ብቻ ተዋሕዷል ባሰኘ ነበር፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው አካልም ባሕርይም እንደተዋሐዱ ሲያጠይቅ በባሕርይ የከዊን ስም “ቃል” ብሎ “ቃል ሥጋ ኮነ” አለ፡፡ በሥላሴ ዘንድ የአካል ሦስትነት እንጅ የአካላት አንድነት የለምና ሦስቱም ሥጋ ለበሱ ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ነው ባሕርይም ሥጋም ተዋሕደዋል ማለት፡፡ ሥላሴ በከዊን ሦሰት ሲሆኑ በህልውና አንድ ናቸው (በህልውና ይገናዘባሉ)፡፡ ሥላሴ ግን በአካላት ሦስት ናቸው እንጅ አንድ የሚሆኑበት የሚገናዘቡበት ነገር የለም፡፡ ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል፡፡ 1ኛ. ምሳሌ ፀሐይ አንድ ስትሆን ሦስት ከዊን አላት ይኸውም ክበቧ፣ ብርሃኗ እና ሙቀቷ ነው፡፡ ክበቧ በአብ ብርሃኗ በወልድ ሙቀቷ በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ የፀሐይ ብርሃን ከሙቀቱ እና ከክበቡ ሳይቀድም ሳይከተል ሳይለይ ሳይከፈል ከዓይናችን ብርሃን ጋር ተዋሕዶ እንድንመለከት ይረዳናል፡፡ ዓይናችን ለማየት ከፀሐይ የሚፈልገው ክበቡን እና ሙቀቱን አይደለም ብርሃኑን ነው እንጅ፡፡ ምንም እንኳ ዓይናችን ለማየት የፀሐይን ብርሃኗን ይፈልግ እንጅ ብርሃኗ ግን ከሙቀቷ እና ከክበቧ አይለይም፡፡ የሰው ዓይን ለማየት ከብርሃን ጋር ይዋሐዳል እንጅ ከሙቀት እና ከክበቡ ጋር አይዋሐድም፡፡ ወልድም ሥጋን ሲለብስ ልክ እንደዚህ ነው፡፡ ሦስቱም ሥጋን ለበሱ አያሠኝም፡፡
2ኛ. ምሳሌ ነፍስ ሦስት ከዊን አላት ልብ ቃል እና እስትንፋስ ማለት ነው፡፡ የነፍስ ልብ ከሥጋ ልብ ጋር ተዋሕዶ እውቀት ይሆናል፡፡ የነፍስ ቃል ከሥጋ ምላስ ጋር ተዋሕዶ ንባብ ይሆናል፡፡ የቃል እስትንፋስ ከሥጋ እስትንፋስ ጋር ተዋሕዶ ሕይወት ይሆናል፡፡ ሰው ልናገር ባለ ጊዜ ከልቡ እውቀት መንጭቶ በእስትንፋሱ ሰረገላ ተጭኖ ከሩቅ ደርሶ ይሰማል፡፡ ይህ ቃል ከልብ እና ከእስትንፋስ ሳይለይ ከሩቅ ይሰማል፡፡ እዚህ ላይ ነፍስ በቃልነቷ ከዊን ከሥጋ ምላስ ጋራ ተዋሕዳ ንባብን ስትሰጥ በልብነቷ ከዊንና በእስትንፋስነቷ ከዊን ከምላስ ጋራ እንደማትዋሐድ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ቃል ከሥጋ ጋራ በአካልም በባሕርይም ሥጋን ተዋሐደ ስንል ሦስቱ አካላት ተዋሕደዋል አያሠኝም፡፡
2ኛ. ማስረጃ፡ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከህግም በታች በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ገላ 4÷4 ይላል፡፡ ስለዚህ ለለቢሰ ሥጋ የመጣው ወልድ እንጅ አብ እና መንፈስ ቅዱስ አይደሉም፡፡ ልጁ የተባለው ወልድ ነውና፡፡ ስለዚህ ሦስቱም አካላት ሥጋን ተዋሕደዋል አያሰኝም፡፡
3ኛ. ማስረጃ፡ “አሐዱ ዘእምቅድስት ሥላሴ ርእዮ ትሕትናነ አጽነነ ሰማየ ሰማያት መጽአ ወኃደረ ውስተ ከርሰ ድንግል፤ ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ መዋረዳችንን አይቶ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ባሕርዩን ዝቅ አደረገና መጥቶ በድንግል ማኅጸን አደረ” ይላል ሊቁ አባ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም፡፡ ስለዚህ በተለየ አካሉ ለለቢሰ ሥጋ የመጣው አንዱ አካል ወልድ እንጅ አብ እና መንፈስ ቅዱስ አይደሉም እና ሦስቱ አካላት ሥጋን ለበሱ አያሰኝም፡፡
4ኛ. ማስረጃ፡ ሃይማኖተ አበው ዘኪራኮስ ም 91 ቁ 17 ላይ “ወኢንብል ከመ ሠለስቱ አካላት ተሠገው በሥጋ ወኢሥላሴ በአሐዱ አካል ከመ ይሠገው አላ አሐዱ አካል እም ሠለስቱ አካላት ዘውእቱ እግዚአብሔር ቃል ጥበቡ ለአብ ወኃይሉ ብርሃነ ጽድቅ ዘያበርህ እምብርሃነ አብ ብሩህ አምላክ ዘኢይትዌለጥ እምአምላክ ዘበአማን ዘተወልደ እመለኮተ አብ፤ ሦስቱ አካላት ሥጋን እንደ ተዋሐዱ አንናገርም ወይም ሰው ይሆኑ ዘንድ ሥላሴ አንድ አካል ሆኑ አንልም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሰው ሆነ እንላለን እንጅ ይኸውም የአብ ጥበቡ ኃይሉ የሚሆን ከብሩህ አብ ብርሃን የተገኘ የሚያበራ የእውነት ብርሃን ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የማይለወጥ አምላክ ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ እግዚአብሔር ቃል ነው” ይላል፡፡ ስለዚህ ሦስቱ አካላት ተዋሕደዋል አያሰኝም፡፡
ተዋሕዶ የሚለው ስም የሚያመለክተው ከተዋሕዶ በፊት ሁለት አካላት ሁለት ባሕርያት ይባል የነበረውን ሁለትነት አጥፍቶ የባሕርይ አንድነትን እና የአካልን አንድነት አጽንቶ ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ የሚለውን ነው፡፡ በተዋሕዶተ ቃል ሥጋ ክቡር አምላክ ሆኗልና በተዋሕዶ ከበረ እንላለን፡፡ ይህንንም ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ድርሳን 2 ቁጥር 155 ላይ እንዲህ ይላል “…አብን በልብነት መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስነት ገንዘብ ለማድረግ ሥጋ ቃልን ተዋሐደ” ስለዚህ ሥጋ የአብን ልብነት የመንፈስ ቅዱስን እስትንፋስነት ገንዘቡ ያደረገው ቃል ስለተዋሐደው እንጅ መንፈስ ቅዱስ በቅብአትነት ስላከበረው አይደለም ማለት ስለዚህ ነው፡፡
ቅብዓቶች ተዋሕዶን የሚረዱት በዚህ ቀጥሎ በምናየው መልኩ ነው፡፡ “ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋሕዶ ከበረ ቅብዓት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል፡፡ ለሊህ ምን ይመልሷል ቢሉ ተዋሕዶማ ሁለትነትን አጠፋ አንድነትን አጸና እንጅ ንዴትን አላጠፋም ክብርን አላሳለፈም” ይላሉ ወልደ አብ ገጽ 232 ላይ። ስለዚህ እነርሱ “ተዋሕዶ” የሚለውን የሚረዱበት አረዳድ እኛ “ተዋሕዶ” ብለን ከምንረዳበት አረዳድ ጋር በጣም ይለያያል ማለት ነው፡፡ እነርሱ ተዋሕዶ የሚሉት የሁለት አካላትን እና ባሕርያትን አንድነት እንጅ፤ ሥጋ ከፍ ማለቱን አምላክ መሆኑን መክበሩን ግን በተዋሕዶተ መለኮት አላገኘውም የሚሉ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የአካል ይሁን የኩነት ይሁን የምን ይሁን የምን የማይታወቅ ስም “አብ ቀባዒ ወልድ ተቀባዒ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ” የሚሉት፡፡ እዚህ ላይ ምን ለማለት መሰላችሁ “አብ አክባሪ ወልድ ተከባሪ መንፈስ ቅዱስ ክብር” ማለታቸው ነው፡፡ በእውነት ወልድ ራሱ “ቀባዒ” ወይም “አክባሪ” አይደለምን? ሌላ “ቀባዒ፤ አክባሪ” የሚሻው? ብለን ስንጠይቃቸው መልስ የላቸውም ወልድ ግን ራሱ “ቀባዒ፤ አክባሪ” ነው፡፡ ይህንንም ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ላይ እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ስምዐት 124÷34 “ወካዕበ ይቤ እስመ ክርስቶስ ኢተቀብዐ በእንተ መፍቅድ ዘቦቱ አላ ለሊሁ ቀባዒ ውእቱ ወዐርገ ኀበ ሥልጣነ መለኮቱ እንዘ ሰብእ ውእቱ ወለሊሁ እግዚአብሔር አምላክ ተብህለ በእንቲአሁ ከመ ውእቱ ተለዐለ ፈድፋደ በእንተ ትህትና ወሕጸጽ እንተ ዘትስብእት ወንዴት ወለሊሁ ጸገዎ ስመ ዘላዕለ ኩሉ ዝንቱ ዘኮነ በህላዌ ከመ አምላክ ከመ ያልዕለነ ለነሂ ዓዲ ኀበ ሀሎ ዝኩ፤ ዳግመኛ ክርስቶስስ ክብር መሻት ኖሮበት አልከበረም እርሱ ራሱ አክባሪ ነው እንጅ ሰው ቢኾንም በባህርይ ክብሩ ከበረ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው ሥጋ ትሁት ሕጹጽ ነዳይ ስለሆነ ተለዐለ ተብሎ ተነገረለት ከሁሉ በላይ የሆነ ስምንም እሱ ራሱ ሰጠው ተባለ ይህም የሆነ በባህርይ ተዋሕዶ ነው አምላክ እንደሆነ እኛንም እሱ ወደ አለበት ያቀርበን ዘንድ” ብሎ ቄርሎስ ለቅብዓት ምንፍቅና ተከታዮች እሾህ ተከለባቸው። ስለዚህ ራሱ አክባሪ ነው ይህም ማለት ሥጋ በተዋሕዶተ መለኮት አምላክ ሆነ ለሥጋ አምላክ ከመሆን የበለጠ ምን ክብር ይመጣለታል ታዲያ!!!
ተዋህዶ ሁለትነትን ብቻ ያጠፋ ክብርን ያላሳለፈ ነው የሚሉት ቅብአቶች ክብርን ያገኘ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ወልድም በባሕርይ ክብሩ ሥጋን አልተዋሐደም ያሰኝባቸዋልና ክብርን ለማግኘት የጸጋ አምላክ ሆነ ያሰኛል፡፡ የከዊን ተዋሕዶ አያምኑም ያልኩትም ለዚሁ ነው በከዊን ተዋሕዶ ቢያምኑ ኖሮ ባሕርይም ተዋሕዷል ባሉ ነበር፡፡ ባሕርይ ተዋሕዷል ካሉ ደግሞ በባሕርይ ክብሩ አከበረው ባሉ ነበር፡፡ ነገር ግን በተዋሕዶ ሁለትነት ጠፋ አንድነት ጸና እንጅ ክብር አላሳለፈም ይላሉ፡፡ ከዚህ ክህደት ራሳችንን እናወጣ ዘንድ ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment