Thursday, March 16, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፩


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 8/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤያትን በስድስት ክፍሎች የቋጨሁት በጉባዔያት የተወገዙ ትምህርቶች እንዴት ወደ አገራችን እንደገቡ ከሥር ከመሠረቱ አንድ ብለን እንድንመለከት ፈልጌ ነው፡፡ በዚያው ክፍል ሰባት ብየ ልቀጥል ነበር ሆኖም ግን ክፍሎችን ከማብዛት በአዲስ ብንጀምር መልካም ነው በሚል እሳቤ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ተከታታይ ክፍሎች በዋናነት የምንመለከተው የቅብዓትን ትርጉም፣ አስፈላጊነት፣ በመጻሕፍት ቅብዓት የሚለው ቃል እንዴት ይተረጎማል የሚለውን እና ከዚህ ጋር በተያያዘ የቅብዓት እምነትን አጭር ታሪካዊ አመጣጥ እና ምንጭ እንጠቁማለን፡፡
****************************************************************************
 የቅብዓት ትርጉም
ይህን ቃል በተለያዩ መዝገበ ቃላት እንዲሁም በሰዋስውና በግስ መጻሕፍት ላይ ምን ተብሎ እንደተተረጎመ እንመልከት፡፡ በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 94 ላይ ያለውን እንመልከት፡፡ ቅብዓት (ቅባት) ከልዩ ልዩ እንጨቶች ተቀምሞና ተነጥሮ የሚወጣ ፈሳሽ ዓይነት ዘጸ 30÷22-32፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡ 1ኛ ዮሐ2÷20፡27 ብሎ ‹‹ቀባ›› ይመልከቱ ይላል፡፡ በመጀመሪያ በዚህ የተጠቀሱትን ጥቅሶች እንመልከት፡፡ ዘጸ 30÷ 22-32 ላይ “ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፡፡ አንተም ክቡሩን ሽቱ ውሰድ የተመረጠ ከርቤ ዐምስት መቶ ሰቅል ግማሽም ጣፋጭ ቀረፋ ሁለት መቶ ዐምሳ ሰቅል የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ ዐምሳ ሰቅል ብርጉድም ዐምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መሥፈሪያ ትወስዳለህ፡፡ በቀማሚም ብልኀት እንደተሠራ ቅመም የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ታደርገዋለህ፡፡ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሆናል፡፡ የመገናኛውንም ድንኳን የምስክሩንም ታቦት ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ መቅረዙንም ዕቃውንም የዕጣን መሠዊያውንም ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋእት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ፡፡ ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፡፡ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው ቀድሳቸውም፡፡ አንተም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር ይህ ለልጅ ልጃችሁ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሁንልኝ፡፡ በሰው ሥጋ ላይ አይፍሰስ እንደ እርሱም የተሠራ ሌላ ቅብዐት አታድርጉ ቅዱስ ነው ለእናንተም ቅዱስ ይሁን” ይላል፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እግዚአብሔር ለሙሴ ቅብዐት እንዴት እንደሚዘጋጅ እና ለምን አገልግሎት ሊውል እንደሚገባ ነግሮታል፡፡ ሙሴም በዚሁ መልኩ እያዘጋጀ ለተባለው አገልግሎት ያውል ነበር፡፡ ከዚህ ቀጥለን ደግሞ ቅብዐት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ እንደሆነ የሚያስረዳውን ጥቅስ እንመለከታለን፡፡ 1ኛ ዮሐ2÷20 ላይ “እናንተም ከቅዱሱ ቅብዐት ተቀብታችኋል ሁሉንም ታውቃላችሁ” ይላል ዳግመኛም 1ኛ ዮሐ2÷27 ላይ “እናንተስ ከርሱ የተቀበላችሁት ቅብዓት በእናንተ ይኖራል፡፡ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም ነገር ግን የእርሱ ቅብዓት ስለሁሉ እንደሚያስተምራችሁ እውነተኛም እንደሆነ ውሸትም እንዳልሆነ እናንተም እንዳስተማራችሁ በርሱ ኑሩ” ይላል፡፡ እነዚህ ሁለት ጥቅሶች ላይ ቅባት ተብሎ የተገለጸው ምሳሌነቱ ለመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ ቀጥለን ቀባ ወደሚለው ቃል ትርጉም እንመለስ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 90 ላይ እናገኘዋለን፡፡


ቀባ መቀባት በመጽሐፍ ቅዱስ ለ3 ዓይነት ነገር ያገለግላል፡፡ ይልና ይዘረዝራቸዋል ማስረጃ ጥቅሶችንም ይሰጣል፡፡ እኛ ግን ማስረጃ ጥቅሶችን ሁሉንም እንጽፋቸዋለን፡፡
1.  ለአገልግሎት፡- ሰዎችና ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ሥራ ሲለዩ ይቀቡ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን የመገናኛው ድንኳንና ዕቃው ተቀብቷል፡፡ ዘጸ 30÷ 22-29 ከላይ የተጻፈውን ተመለከት፡፡ ካህናት፣ ነቢያትና ነገሥታት ተቀብተዋል፡፡ ይህን ለተጠሩበት ሥራ በእግዚአብሔር መለየታቸውንና ለሥራቸው የሚያበቃቸው በዘይቱ የተመሰለው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያሳያል፡፡ ዘጸ 30÷30 ላይ “በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው ቀድሳቸውም” ብሎ ሙሴን አዝዞታልና፡፡ 1ኛ ሳሙ 9÷16 ላይ “ነገ በዚች ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እሰድልሃለሁ ልቅሷቸው ወደእኔ የደረሰ ህዝቤን ተመልክቻለሁና ለህዝቤ ለእስራኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ህዝቤን ያድናል” ብሎ እግዚአብሔር ለሳሙኤል ነገረው፡፡ 1ኛ ሳሙ 10÷1 ላይ “ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው ሳመውም እንዲህም አለው በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል የእግዚአብሔርንም ህዝብ ትገዛለህ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ” ይላል፡፡ ከዚያም ይቀጥልና ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል (በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ ሐዋ 10÷38) ይላል፡፡ ጥቅሱን እንመልከተው ሐዋ 10÷38 ላይ “እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና” ይላል፡፡ የዚህን ጥቅስ ትርጉም በስፋት የምንመለከትበት ክፍል ስለሚኖረን እዚህ ላይ ማብራሪያ አንሰጥም፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ምእመናን በመንፈስ ቅዱስ ይቀባሉ ይላል፡፡ 2ኛ ቆሮ1÷21-22 ላይ “በክርስቶስም ከእናንተ ጋራ የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፡፡ ደግሞም ያተመን የመንፈሱም መያዣ በልባችን የሰጠን ርሱ ነው” ይላል፡፡ ከላይ የተመለከትነው ጥቅስ 1ኛ ዮሐ2÷20፡27 ላይም ተገልጿል፡፡ 1ኛ ዮሐ2÷20 ላይ “እናንተም ከቅዱሱ ቅብዐት ተቀብታችኋል ሁሉንም ታውቃላችሁ” ይላል ዳግመኛም 1ኛ ዮሐ2÷27 ላይ “እናንተስ ከርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፡፡ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለሁሉ እንደሚያስተምራችሁ እውነተኛም እንደሆነ ውሸትም እንዳልሆነ እናንተም እንዳስተማራችሁ በርሱ ኑሩ” ይላል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ‹‹መሢሕ›› በዕብራይስጥ ‹‹ክርስቶስ›› በግሪክ ቋንቋዎች የተቀባ ማለት ነው ብሎ መቀባት ለአገልግሎት አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
2.  ለአክብሮት፡- ተጋባዦች ለአክብሮት ይቀቡ ነበር፡፡ ሉቃ 7÷46 ላይ “አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም ርሷ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች” በማለት ክርስቶስ ለማርያም እንተ እፍረት ሲመሰክርላት እንመለከታለን፡፡ የሰዎች ሬሳ ሳይቀበር ሽቱ ይቀባ ነበር፡፡ ማር14÷8 ላይ “የተቻላትን አደረገች አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋየን ቀባችው” ይላል ማር16÷1 ላይም እንዲሁ “ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ” ይላል፡፡ ስለዚህ ለአክብሮት ሽቱ ይቀቡ እንደነበርና ሬሳንም እንዲሁ ይቀቡ እንደነበር ያስረዳል፡፡
3.  ለሕክምና፡- ቁስለኞችና ሌላም በሽታ ያለባቸው በዘይት ይቀቡ ነበር፡፡ ማር 6÷13 ላይ “ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሷቸው” ይላል፡፡ ሉቃ 10÷34 ላይም “ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍሶ አሰራቸው …” ይላል፡፡ ያዕ 5÷14 ላይም “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችን ወደርሱ ይጥራ በጌታም ሥም ርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት” ይላል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ‹‹ዘይት›› ይመልከቱ ብሎ ይጨርሳል እኛ ግን የዘይትን ትርጉምም እንመለከተው ዘንድ መጽሐፋችንን (መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ) ገጽ 213 ላይ ገለጥን እና ዘይት የሚለውን ቃል ትርጉም እንዲህ ወሰድነው፡፡                                       ዘይት ከወይራ ፍሬ ይጨመቃል፡፡ ሰዎች ይህን ዓይነት ዘይት ለምግብ፣ ለልዩ ልዩ ቅባት፣ ለጠጉር ለመድኃኒት፣ ለመብራት፣ ሰዎችንና ዕቃዎችን ለእግዚአብሔር አገልግሎት ለመለየት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ 1ኛ ሳሙ 10÷1፣ 1ኛ ነገ17÷2-16፣ ሉቃ 10÷34፣ ያዕ 5÷14 ‹‹ቀባ›› ይመልከቱ ብሎ ይደመድማል፡፡ እኛ ግን ‹‹ቀባ›› የሚለውን ቃል አስቀድመን ስለተመለከትነው ድጋሜ አንመለስበትም፡፡ ከእነዚህ ከተቀመጡት ጥቅሶች መካከል ያልተመለከትነው 1ኛ ነገ17÷2-16 ያለውን ታሪክ ነው፡፡ ሌሎችን ጥቅሶች አስቀድመን ተመልክተናቸዋልና አንደግማቸውም፡፡ ይህንን ጥቅስ ሙሉውን አንብቡት ዋናው መልእክት ዘይትን ሰዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚጠቀሙበት ለማሳየት ነውና ያንን እንጽፋለን ቁጥር14-16“…ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም፡፡ እርሷም ሄዳ እንደ ኤልያስ ቃል አደረገች እርሷና እርሱ ቤቷም ብዙ ቀን በሉ፡፡ በኤልያስም እጅ እንደተናገረው እንደእግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም” ይላል፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment