© መልካሙ በየነ
መጋቢት 12/
2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
የቅብዓት ምንፍቅና ምንጩ
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው “ቅብዓት” የሚለውን
ቃል ሲተረጉሙ መቅባት፣ መቀባት፣ አቀባብ፣ ቅብነት፣ ቅባት፣ የሃይማኖት ሥም ብለው ይተረጉሙታል፡፡ በዚህ ርእስ የምንመለከተው ቅብዓት
ስለሚባለው ሃይማኖት ምንጭ ይሆናል፡፡ ይህ እምነት በሀገራችንም የሚገኝ ሲሆን “ኢየሱስ ክርስቶስ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ
አምላክ ገዥ ሆነ” የሚል መሠረታዊ የኑፋቄ አስተምህሮ ያነገበ ነው፡፡ ይህ እምነት በሀገራችን ጥንታዊነት ያለው እና አገር በቀል
ሳይሆን መጤ እምነት እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዱናል፡፡ ከታሪክ መዛግብት በተጨማሪም ይህ እምነት ጥንታዊና አገር በቀል ቢሆን
ኖሮ ቢያንስ በሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች ላይ መገኘት ነበረበት ነገር ግን እንደ ዕቃ እና እንደ ልብስ ከውጭ አገር ሰርጎ የገባ
ስለሆነ በሁሉም አካባቢዎች አናገኘውም፡፡ እንዲያውም የዚህ እምነት ስሙ የማይታወቅበት የሀገራችን ክፍል ይበዛል፡፡ የዚህ እምነት
አስተምህሮ ቀድሞ በሊቃውንት በታላላቅ ጉባኤዎች የተወገዘ ቢሆንም ወደ ሀገራችን የገባበት ዘመን ግን ቅርብ ጊዜ እንደሆነ ታሪክ
ይነግረናል፡፡
የዚህ እምነት ምንጮች በብልጽግናቸው አፍሪካን የመቀራመት ራእይ የነበራቸው
የአውሮፓ ሀገራት ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት በእርዳታ ሰበብ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን፣ ሃይማኖታቸውን ወዘተ በአፍሪካ ሀገራት ላይ
መጫን ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም የተነሣ የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠሩ በዋናነት እምነታቸውን በአፍሪካ ላይ ይጭኑ ነበር፡፡ እዚህ ኃያላን
የአውሮፓ ሀገራት የካቶሊክ እምነት አራማጆች እንደሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሀገራት በሀገራችን ላይም ይህንኑ የእምነት
ማስፋፋት ዘመቻ ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ ወደ ሀገራችን ለመግባት ምክንያታቸው ዘመናዊ ትምህርትን ለማስተማር ወይም የጦር መሣሪያዎችን
በእርዳታ መልኩ በማስገባት መሣሪያዎችን እንዴት እንደምንጠቀምባቸው ለማሳየት ቢሆንም ዋናው ዓላማቸው ግን በድብቅ እምነታቸውን ማስፋፋት
ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ነው እንግዲህ ምንጩ ካቶሊክ የሆነ እምነት ወደ ሀገራችን ገብቶ በሀገራችን ቋንቋ በሀገራችን ልጆች ትምህርቱ
መሰጠት የጀመረው፡፡ ምንም እንኳ ይህ እምነት ምንጩ ካቶሊክ ቢሆንም ወደ ሀገራችን ሲገባ ግን በሀገራችን ወግ፣ ባህል እና የጥንት
እምነት የተወሰነ ማሻሻያ የተደረገበት ነው፡፡ ምክንያቱም በጥንታዊቷ እምነት ስም በተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንዳሉ ነውና
እምነታቸውን የለወጡት፡፡
የቅብዓት ምንፍቅና ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ገባ?
ለዚህ እምነት ወደ ሀገራችን መግባት ምክንያቱ ግራኝ መሐመድ የተባለው
አረመኔ እስላም ነው፡፡ በ1453 ዓ.ም የቱርክ እስላሞች ቁስጥንጥንያን እና ሞንጎልያን ከያዙ በኋላ ከዐረብ እስላሞች ጋር ኃይላቸውን
አስተባብረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ኃይላቸው እየጨመረ ስለሄደ የክርስትና ሀገራትን በመውረር እስልምናን በግድ በሌሎች ላይ መጫናቸውን
ተያያዙት፡፡ ወደ አፍሪካም በመግባት ሰሜን አፍሪካን የራሳቸው ግዛት በማድረግ ዓላማቸውን አስፈጸሙ፡፡ ሆኖም ግን ወደ ኢትዮጵያ
መግባትና እምነታቸውን ማስፋፋት አልቻሉም ነበር፡፡ ሆኖም ግን በሀገራችን ተወልዶ የሀገራችንን ውኃ ጠጥቶ የሀገራችንን እህል ተመግቦ
ያደገው ግራኝ መሐመድ ክርስቲያኖችን በመደምሰስ አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል ክርስትናን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት ከቱርክ እስላም
ባለሥልጣናት ጋር ወዳጅነቱን ጀመረ፡፡ የዚህ የግራኝ መሐመድ ድብቅ ሴራ ከቤተመንግሥት እንደደረሰ ባለሥልጣናቱ ከክርስቲያን ሀገሮች
እርዳታ መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ነገር እነዚህ ለእርዳታ ጥያቄ የቀረበላቸው ሀገራት ካቶሊካውያን ስለሆኑ እርዳታውን አዘግይተውታል፡፡ የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበሯ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ለይታ የራሷ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡ ነገር ግን ይህ ሊሳካላት ስላልቻለ
አሁን የቀረበውን የእርዳታ ጥሪ ለመስማት ዘግይታለች፡፡ ግራኝ መሐመድም በኅቡእ ያደራጀውን የጥፋት ወታደር አሰልፎ በድብቅ ከቱርክ
እየተላላከ ያስመጣውን መሣሪያ አስታጥቆ በሀገራችን ላይ በጠላትነት ተነሣ፡፡ በዚህ የሃይማኖት ወረራ ላይ የቤተክርስቲያናችን ውድ
ቅርሶች፣ መጻሕፍት፣ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ ምእመናን አንገታቸው ለስለት ደረታቸው ለጥይት ሆነ፡፡ ብዙዎች በሰማእትነት አለፉ
የክርስቲያኖች እልቂት ሆነ ደማቸው ፈሰሰ፡፡ የእስልምናን እምነት በግድ ተቀበሉ እየተባሉ ሳይወዱ ከሞት ለማምለጥ ብቻም እምነታቸውን
ለውጠው እስላም የሆኑም አልጠፉም፡፡ በዚህ የጥፋት እና የእልቂት ዘመን ሁሉ ክርስትና አልጠፋችም፡፡ ይህን የግራኝ ወረራ ለማስቆም
ሀገራችን የፖርቹጋሎችን ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ይህን ውለታ ነው እንግዲህ ለሃይማኖታቸው ማስፋፊያነት እንደ ምክንያት የተጠቀሙበት፡፡
የፖርቹጋሎችን ድጋፍ የጠየቁት አጼ ልብነ ድንግል ሲሆኑ ድጋፋቸው የደረሰው እና ግራኝን ድል ለማድረግ የተቻለው ግን በልጃቸው በአጼ
ገላውዴዎስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 1542 ዓ.ም ነበር፡፡ ከዚህ የግራኝ መሸነፍ (መገደል) በኋላ የፖርቹጋሎችን ትብብር ምክንያት
በማድረግ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ባለሥልጣኖች በተላላኪያቸው ቤርሙዴዝ አማካኝነት አንድ ጥያቄ ለገላውዴዎስ አቀረቡ፡፡ ቤርሙዴዝ
ገላውዴዎስን እንዲህ አለው ‹‹ገላውዴዎስ ሆይ አባትዎ እርዳታ እንድናደርግላቸው ሲጠይቁን ከሀገራችሁ መሬት ቆርሰው ሊሰጡን እና
የሀገራችሁ ብሔራዊ ሃይማኖት የሮማ ክቶሊክ እንዲሆን ቃል ገብተውልን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከግብጽ የሚመጡት ጳጳሳት ቀርተው
ጳጳሳቱ ከሮማ እንዲመጡ ቃል ገብተውልን ነበር፡፡ ስለዚህ ይህን አባትዎ የገቡልንን ቃል ኪዳን ይፈጽሙልን እኔም የመጀመሪያው ጳጳስ
ልሁን›› አላቸው፡፡ ገላውዴዎስ ግን ‹‹ሀገራችንን ቆርሰን አንሰጥም፣ ሃይማኖታችንንም አንለውጥም፣ ጳጳሳትንም ከግብጽ ማስመጣታችንን
አቁመን ከሮማ አናስመጣም ላደረጋችሁልን ትብብር ግን ገንዘብ እንከፍላችኋለን›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ቤርሙዴዝ በጣም ተናደደ ከንጉሡ
ከገላውዴዎስ ጋርም ተጣላ፡፡ በዚህ ጠብና ክርክርም የተነሣ የተናደደው ቤርሙዴዝ በ1559 ዓ.ም ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለፖርቹጋል ቤተ
መንግሥትና ለቫቲካን ቤተ ክህነት የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡
(ንጉሡ የኢትዮጵያን ሊቃውንት አማክሮ ሊቃውንቱ ጉባዔ እናድርግ እና
ካሸነፉን የወደዱትን ያድርጉ ካሸነፍን ግን እኛ የወደድነውን እናድርግ ብለው በንጉሡ ትእዛዝ በአባ ዝክሪ እና በአባ ጳውሊ መሪነት
ጉባኤ ተደርጓል፡፡ ይህንን ከዚህ በፊት በሦስት ክፍሎች ተመልክተነዋል ያላችሁት ግን ይህንን ሊንክ ተጭናችሁ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment