Tuesday, March 28, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፲


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 20/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
ጠቅለል ባለ መልኩ የዛሬዎቹ የቅብዓት እምነት ተከታዮች ክፍል ፱ በተጠቀሱት አራቱም ባህሎች ውስጥ የሚዋኙ ናቸው፡፡ ተዋሕዶ ያለ ቅብዓት ክብርን አያሳልፍም በማለታቸው ለጥምቀት፣ ለተክሊል፣ ለንሥሐ መደምደሚያው ቁርባን እንደሆነ ሁሉ ለተዋሕዶም መደምደሚያው ቅብዓት ነው ያሰኝባቸዋል፡፡ ይህንንም መጽሐፋቸውን እየጠቀስን እንመልከተው፡፡ ወልደ አብ ገጽ 219 ላይ “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ፡፡ እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ እን ጳውሎስ ፪ኛ ቆሮ ም፰ ቁ፱ ስለዚህ ከእምቅድመ ዓለም ልደቱ ፩ድ ለማድረግ በሰውነቱ የባሕርይ ህይወቱን በመላ ተቀብሎ ከአብ ተወለደ እንጅ የቀደመ ልጅነቱስ አልተነሣውም፡፡ ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር ኢይሁብ ክብርየ ለባዕድ ለተሳትፎ ወስብሐትየ ለግልፎ እን ኢሳ ም፵፪ ቁ፰ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ቢወለድ ግን እንደአብ ገዛ አዘዘ፡፡ አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን ሰጠው አኮ ዘይሁብ እግዚአብሔር አብ መንፈሶ በመስፈርት አላ አብሰ ያፈቅር ወልዶ ወኲሎ ኲነኔሁ አወፈዮ ለወልዱ ውስተ እዴሁ እን ወን ዮ ም፫ ቁ፴፬፡፡ ወረሰዮ ወራሴ ለኲሉ እን ጳው ዕብ ም፩ ቁ፪” ይላል። ይህ የመጽሐፋቸው ክፍል እርስ በርሱ የሚጋጭ ሃሳብ ይዟል ነገር ግን የቅብአት እምነት ተከታዮች አይጋጭም ይላሉ። ስለዚህ የማይጋጭ ሃሳብ ከሆነ ሊስማማ የሚችለው እንደሚከተለው ይሆናል። መጀመሪያ ሁለት የተዋሕዶ ሂደቶች ይከወናሉ። የመጀመሪው “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ” የሚለው መለኮት ከሥጋ ጋር ያደረገው ተዋሕዶ ነው። በዚህ ተዋሕዶ ላይ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሐደ እንጅ ሥጋ ከመለኮት ጋር አልተዋሐደም። በዚህ ተዋሕዶ ሥጋ የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጎ በቃል መጠሪያ ተጠራ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ተባለ ማለት ነው። የሚገርማችሁ እስከዚህ ድረስ መለኮት የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አላደረገም በሥጋ ስምም አልተጠራም። ስለዚህ ሙሉ ተዋሕዶ ይደረግ ዘንድ ሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ አለበት ይኸኛው ቀጣዩ ተዋሕዶ ነው። ሁለት ነጥላ ተዋሕዶዎች ናቸው እንግዲህ አንድ ሙሉ ተዋሕዶን የሚፈጥሩት። በእርግጥ ይህንን የምንላችሁ እነርሱ “ተዋሐደ” እያሉ ስለጻፉት እንጅ እንደ እኛ ትምህርት ግን ይኼ ተዋሕዶ አይባልም። ተዋሕዶ ከተባለም እንኳ የኅድረት ተዋሕዶ ሊሆን እንደሚችል ብቻ ነው የምናስበው። ቀጣዩ ተዋሕዶ ደግሞ የሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ ነው። “ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ይላሉ ሥጋ ከመለኮት ጋር እንደተዋሐደ ለማጠየቅ። ቅድም ልጅነት አገኘ ቃለአብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ያሉት ሥጋ አሁን ከመለኮት ጋራ ሲዋሐድ መለኮት በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ፡፡ ምክንያቱም መለኮት ሥጋን ቢዋሐደው ሥጋ በመለኮት ርስት ልጅነትን አገኘ እንጅ ሥጋ ከመለኮት ጋር ስላልተዋሐደ መለኮት በሥጋ ርስት ልጅነት አላገነም ነበርና ይህንን ልጅነት ለማግኘት ሥጋ ከመለኮት ጋር ተዋሐደ ይላሉ። ስለዚህ ቃል በሥጋ ርስት ልጅነት ያገኝ ዘንድ ሥጋ ከመለኮት ጋር መዋሐድ ያስፈልገዋል ማለት ነው። ከዚህ ቀጥሎ እነዚህ ሁለት የተዋሕዶ ሂደቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ይፈጠራል ይላሉ ይቅር ይበለንና። አርዮስ ወልድ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት ታዲያ እነዚህስ ወልድ ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ ተፈጠረ ሲሉ ክህደት የማይሆነው  እንዴት ነው? ከተዋሐደ በኋላ እንደተፈጠረ ወልደ አብ ገጽ 131 “ ሥጋ ሲፈጠር መለኮት ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ አብሮ ተፈጠረ ካላሉ እንደ ንስጥሮስ ፪ አካል ማድረግ ኃደረ በብእሲ ማለት ነውና ክህደት ነው” ይላሉ፡፡ ወልደ አብ ገጽ 127 ላይም እንዲሁ “… በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና” ይላሉ፡፡ ወልደ አብ ገጽ 126 ላይ ደግሞ ሲፈጠር እና ሲዋሐድ አንድ ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ  “… ተዋሕዶ ተፈጠረ ሳይዋሐድ አልተፈጠረም፡፡ ተዋሕዶ ሳይፈጠር አልቆየም፡፡ ሲዋሐድ ሲፈጠር አንድ ጊዜ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ተዋሕዶ ቀደመ ባሉ ጊዜ ከቅብዓትም ተዋሕዶ ቀደመ ማለት ይሆናል” ብለው ጽፈዋል፡፡ እስካሁን ባየናቸው የመጽሐፍ ክፍሎቻቸው የቃል ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ መፈጠርን የሚያስረዱ ናቸው ሎቱ ስብሐት፡፡  አሁን መለኮት ከሥጋ ጋር ሥጋም ከመለኮት ጋር ተዋሕዶ ተፈጥሯል ማን ፈጠረው? የሚለውን ጥያቄ ግን ማንም ሊመልሰው አይችልም ምክንያቱም አምላክ ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጥሯል ብለውናልና ከአምላክ ውጭ ማን ሊፈጥር ይችላል? ደግሞ በጣም የሚገርመው ጉዳይ “መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ ካላሉ ክህደት ነው” ማለታቸው ነው። እንግዲህ ይህ ተዋሕዶ ከተከናወነ በኋላ የተፈጠረው አካል እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ያዝዝ ይገዛ ዘንድ በቅብአት መክበር ያስፈልገዋል፡፡ ይህንንም ወልደ አብ ገጽ 166 ላይ “… መንፈስ ቅዱስን በመላ ተቀብሎ ከአብ ቢወለድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ልጅ ሆነ” ይላሉ፡፡ ከዚህእንደምንረዳው ለቅብዓት እምነት ተከታዮች ከተዋሕዶ በኋላ ቅብዓት መክበሪያ፣ መደምደሚያ እንደሆነ ነው፡፡ ሆኖም ግን እግዚአብሔር በመለኮት፣ በህልውና፣ በአገዛዝ፣ በመፍጠር፣ በማሳለፍ አንድ እንደሆነ ዘንግተውታል፡፡ ይህን የሥላሴ በመፍጠር አንድ መሆን ምሥጢር ባይዘነጉት ኖሮ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ ማለት ክህደት እንደሆነ በተረዱት ነበር፡፡ በእርግጥ የሥላሴን በህልውና መገናዘብንም አልተረዱትም፡፡ ወልደ አብ ገጽ 232 ላይ “ተዋሕዶ ክብር የሚያሳልፍ ንዴትን የሚያጠፋ መስሏቸው የቃልን ክብር ለሥጋ ካሳለፍን ብለው ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት በተዋሕዶ ከበረ ቅብአት አልረባውም ብለው ተነሥተዋል” ብለው መጻፋቸው የሥላሴን በህልውና መገናዘብ ባለማሰብ ነው፡፡ በህልውና እንደሚገናዘቡ ቢያውቁ ኖሮማ ወልድ ባለበት አብና መንፈስ ቅዱስም እንደሚገኙ ማወቅ ይገባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ስላልተረዱ ለሦስቱም አካላት ማለትም ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ በዚህ የተዋሕዶ ምሥጢር ላይ አንተን ይህን ሥራ እኔ ይህን ልሥራ ተባብለው ሥራ እንደሚከፋፈሉ ሠዎች ለየብቻቸው የግብር ክፍፍል ሲያደርጉላቸው እንመለከታለን፡፡ ለዚህም ነው እኛን ሲወቅሱ የአምላክን ምሉዕ በኩለሄነት ዘንግተው በአንድ ቦታ ወስነው “ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ ቢያጡለት” ማለታቸው፡፡ እነርሱ ለእያንዳንዳቸው ቦታ ሰጥተዋቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ወልድ በመለኮቱ ከሥጋ ጋር ተዋሐደ፡፡ ቀጥሎም አብ መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ ፈጠረው፡፡ በመጨረሻም መንፈስ ቅዱስ ከመለኮት ጋር ተዋሕዶ በአብ የተፈጠረውን ሥጋ በቅብዓትነቱ አከበረው፡፡ ለዚህ ነው እኛ “በተዋሕዶ ከበረ” ስንል ለመንፈስ ቅዱስ ቦታ አጡለት ብለው የወቀሱን፡፡ ጭራሽ ለአብ ለወልድ እና ለመንፈስ ቅዱስ ለየግላቸው የሆነ ሥራ ፍለጋ ነው የገቡት!!!
በአጠቃላይ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለው ኑፋቄ ከተዋሕዶ በኋላ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ መክበር አለበት የሚል አስተምህሮ የያዘ ነውና ቅብዓትን ለተዋሕዶ መደምደሚያ ሲያደርግ ይታያል፡፡ መጽሐፍ ግን ሊደግፋቸው አይችልም፡፡ ሃይማኖተ አበው አመ ዘሐዋርያት ምእራፍ 6 ክፍል 2 ቁጥር 28 ላይ “ዘገብረ ሎቱ ሥጋ እምድንግል ንጽሕት እግዝእትነ ማርያም ወውእቱ ገባሬ ኩሉ ሰብእ ወዘተንሥአ ባሕቲቱ እምነ ሙታን ውእቱ ዘያነሥእ ኩሎ ሙታነ፤ ከንጽሕት ድንግል እመቤታችን ሥጋን ፈጥሮ የተዋሐደ እርሱ ነው ሰውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ ነው ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ሙታንንም ሁሉ የሚያስነሣ እርሱ ብቻ ነው” ይላል፡፡ ስለዚህ ወልድ የተዋሐደውን ሥጋ ራሱ ፈጠረው እንጅ ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ አልተፈጠረም፡፡

No comments:

Post a Comment