© መልካሙ በየነ
የካቲት
23/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም
facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT,
LIKE ያድርጉ፡-
==============================================
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋእለ ሥጋዌው እነሆ ከሰማይ የወረድሁ የእግዚአብሔር ልጅ የሕይወት
ምግብ እኔ ነኝ እያለ ያስተምር ይመክር ይገስጽ ነበረ፡፡ ነገር ግን
ትምህርቱን የሚንቁ ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት፡፡ እርሱም እንዲህ አላቸው
በመሸ ጊዜ ሰማዩ ቀልቷልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ ማለዳም ሰማዩ ደምኖ ቀልቷልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ የሰማዩን ፊትማ መለየት
ታውቃላችሁ የዘመኑንስ ምልክት አትችሉምን፡፡ ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም
ብሎ ትቷቸው ሄደ፡፡ እነዚህ ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን በክርስቶስ ትምህርት አያምኑም ለዚህም ነው ሁልጊዜ ትምህርቱን ለመስማት
ሳይሆን ሊፈትኑት የሚቀርቡ፡፡ እነዚህ ሰማይን ቀልቷል ብራ ይሆናል ደምኖ ቀልቷል ዝናብ ይጥላል እያሉ ለራሳቸው ምልክትን የሚሹ
ናቸው፡፡ የሰማዩን ምልክት በዚህ ይተረጉሙታል የዘመኑን ምልክት ግን አላወቁምና ምልክትን ፈለጉ፡፡
እግዚአብሔር ዝናብን ሊሰጠን ሲፈልግ ሰማይ ላይ ምልክት ማሳየት አይጠበቅበትም፡፡ አይተናል እኮ ከጭንጫ
ዓለት ላይ ውኃ ሲያፈልቅ ከሰማይ መና ሲያወርድ፡፡ አይተናል እኮ ሰማይ ሲለጎም ዝናብ መስጠት ሲያቆም፡፡ እርሱ ሁን ያለው ይሆናል
እርሱ አትሁን ያለው አይሆንም ሁሉ ነገር ከእርሱ ነው፡፡ የሰማይ እና የምድር ጌታ ፊት ቆመው እንድናምንህ ከሰማይ የወረድህ የእግዚአብሔር
ልጅ ነህ እንድንልህ ምልክት አሳየን አሉት፡፡ በእውነት እግዚአብሔርን እግዚአብሔር ነው ብለን ለመቀበል ምልክት መፈለግ አለብንን
የለብንም፡፡ ምክንያቱም ድንቅ ምልክቶችን የሚያደርጉ የዲያብሎስ ወገኖችም አሉና፡፡ ለመሆኑ እንዲያዩት የሚሹት ምን ዓይነት ምልክትን
ነው፡፡ እነርሱ ተአምራትን ማየት ይፈልጋሉ ምልክት ሲያደርግ መመልከትን ይሻሉ፡፡ እርሱም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ይሠራ ነበር፡፡
የዐራት ቀን ሬሳ ዓልአዛርን ሲያስነሣ በባዶ ግንባር ላይ ዓይን ሲፈጥር የ38 ዓመት በሽተኛን አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ሲል ማየ
ቃናን ወይን ሲያደርግ ዓይተናል ተመልክተናልም፡፡ ነገር ግን እነዚህን ተአምራት ሲያደርግ የተደረገላችሁን ድንቅ ተአምር ለማንም
አትናገሩ እያለ ነበር የሚያሰናብታቸው፡፡ ሆኖም አንዳንዶች ለፈሪሳውያን እና ለሰዱቃውያን እየሄዱ የናዝሬቱ ኢየሱስ እንዲህ ያለ
ድንቅ ተአምር አደረገልኝ እያሉ ይናገሩ ነበር፡፡ እነዚህ ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያንም ጌታችንን ይህን ተአምር የሚያደርገው እኮ
በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል ነው ብለው ተራ ወሬ ማራገብ ጀመሩ፡፡ እዚህ ላይ ምልክት አድርግልን ይላሉ እዚያ ላይ ደግሞ በአጋንንት
አለቃ ምልክትን ያደርጋል ይሉታል፡፡ ከክፉ የልብ መዝገብ ክፉ ወሬ ከፉ አሳብ ብቻ ነው የሚመነጨው ለዚህም ነው ክፉ እና አመንዝራ
ትውልድ ምልክትን ይሻል ያለው፡፡
እኔ እግዚአብሔርን አምላኬ ነው ብየ ለማመን ምልክትን የምሻ ተአምራትን እንዲያደርግልኝ የምማጸን ከሆነ
እኔ ክፉ ወይም አመንዝራ ትውልድ ነኝ ማለት ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ ትውልዱ ምልክትን የሚሻ ተአምራትን የሚናፍቅ ክፉ እና አመንዝራ ሆኗል፡፡ እግዚአብሔር ሁልጊዜ
ድንቅ ተአምር ይሠራልናል እኮ አላስተውል ብለን እንጅ፡፡ ሰማይን ያለምሰሶ የዘረጋ ምድርን ያለመሠረት በውኃ ላይ ያጸና አምላክ
በእውነት ሌላ ምልክትን እንዲሰጠን እንዴት እንለምነዋለን፡፡ ፀሐይን በቀን ከዋክብት ጨረቃን በሌሊት ያሰለጠናቸውን አምላክ ሌላ
ምልክት እንዴት ስጠን እንለዋለን፡፡ ፀሐይን በምሥራቅ አውጥቶ በምዕራብ የሚያስገባ አምላክን እንዴት ካንተ ሌላ ምልክትን እንሻለን
እንለዋለን፡፡ ጨለማውን አስወግዶ ብርሃንን የሚያመጣልንን አምላክ እንዴት ሌላ ምልክት አሳየን እንለዋለን፡፡ ተኝተን በዚያው እንዳንቀር
ቀስቅሶ የሚያስነሣንን አባት እንዴት ሌላ የተለየ ምልክትን እንሻበታለን፡፡ ይህ የምንሻው ምልክት ተአምር ነው፡፡ በእርግጥ ተአምራትንም
የምንሻ ሲደረጉ እንድናይ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተደረጉ ተአምራትን አንፈልጋቸው ተአምረ ማርያም፣ ተአምረ ኢየሱስ ፣ተአምረ
መላእክት፣ ተአምረ ቅዱሳን፣ ተአምረ ጻድቃን፣ ተአምረ ሰማእታት ሲነበቡልን እንቅልፋችን ይመጣል ነገር ግን ምልክትን እንሻለን፡፡
የምንሻው ምልክት፡- ወይ እኛ ላይ እንዲደረግ ወይ እኛ እንድናደርገው አልያም ዓይናችን እያየ ሌላ ሰው ላይ እንዲደረግ ነው፡፡
በእርግጥ ፊልም እና የእግር ኳስ ሲመለከት የሚውል ዓይን ከዚህ የተለየ ማየት አይፈልግም፡፡ በቃ ሁሉ ነገር በቀጥታ ስርጭት ሲሆን
ብቻ ነው ደስ የሚለው፡፡ እውነትም ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፡፡
ይቀጥላል
ይቆየን፡፡
No comments:
Post a Comment