Wednesday, March 1, 2017

ዝክሪ እና ጳውሊ እነማን ናቸው?---ክፍል ፫




© መልካሙ በየነ
የካቲት 22/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
==============================================

 ዐራተኛ ጥያቄ፡፡
ሮማዊ አምላክ ከኾነ አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት ብሎ ለምን ጠየቀ የተቀበረበትን ባላወቀውም ነበረን፡፡ ኹለቱ ዕውራንስ የዳዊት ልጅ ይቅር በለን ባሉት ጊዜ ምን ትሻላችሁ ብሎ ለምን ጠየቃቸው የሚሹትን ባላወቀውም ነበረን አለ፡፡


አባ ጳውሊ ሲመልስ እግዚአብሔር አዳምን አይቴ ሀሎከ  ብሎ ጠየቀው ይላል ዘፍ ፫÷፱፡፡ ሙሴንም ምንት ውስተ እዴከ ብሎ ጠየቀው ይላል፡፡ ዘፀ ፬÷፪፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መጠየቁ አዳም ያለበትን ቦታ አጥቶት፤ ሙሴም በእጁ ምን እንደያዘ አላውቀው ብሎ ይኾን አይደለም፡፡ ይህም ይህን የመሰለ ጥያቄ ነው፡፡ በዚያውስ ላይ ፍጡር ከኾነ አልዓዛር አልዓዛር ነዓ ፃዕ አፍአ እመቃብር ብሎ ሊያስነሣው እንደምን ቻለ፡፡ በደረቅ ግንባርስ ላይ ዐይን ሊፈጥር እንደምን ቻለ አለው፡፡

ሮማዊ ይህን የመሳሰለስ ቅዱሳንም ልዩ ልዩ የኾኑ ብዙ ተአምራት ያደርጋሉ አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱሳን ልዩ ልዩ ተአምራት ቢያደርጉ የርሱን ስም ጠርተው በስሙ ለኢየሱስ ናዝራዊ ተንሥእ ወሑር እያሉ ነው፡፡ ግብ ሐዋ ፫÷፮ ፤፱÷፴፬፤ ፲፮÷፲፰ እርሱ ግን እኤዝዘከ ፃዕ እምኔሁ እያለ በገዛ ሥልጣኑ ነውና ቅዱሳን ከሚያደርጉት ተአምራት ጋራ ሊነጻጸር አይገባውም አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
ዐምስተኛ ጥያቄ፡፡
ስሙን ልዮን የሚሉት አንድ ሮማዊ ተነሥቶ ወልደ አብ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሥጋ ማርያምን በለበሰ ጊዜ ሰይፍ በሰገባው እንዲከተትና እንዲቀመጥ አደረበት እንጅ አልተዋሐደውም በሰላሳ ዘመኑ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በራሱ ላይ ሲቀመጥ መለኮቱ ከትስብእቱ ተዋሐዶ የጸጋ አምላክ ኾነ መዋቲ ትስብእትም የማይሞት ኾነ ከሰላሳ ዘመን በፊት የጸጋ አምላክ ስላልኾነ አምላካዊ ሥራ አልሠራም ከተጠመቀ በኋላ ግን የጸጋ አምላክ ስለኾነ ውኃውን ወይን አደረገ ብዙ የአምላክነት ሥራ ሠራ አለ፡፡

እንደዚኸውም በንግድ ምልክት መጥቶ እስክንድርያዊ መስሎ በኢትዮጵያ የሚኖር አንድ ሰው ተነሥቶ እንዲህ ሲል ተናገረ እናንተ ኢትዮጵያውያን ቃል ሥጋ በለበሰ ጊዜ በማኅጸነ ማርያም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ የባሕርይ አምላክ ኾነ ትላላችሁ በማኅጸን መንፈስ ቅዱስን ሲቀበል ያየው የለም፡፡ ሮማውያን ግን እስከ ሰላሳ ዘመን በሰብአዊ ግብር ኖሮ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ሰው ሁሉ እያየው በራሱ ላይ ስለተቀመጠበት የጸጋ አምላክ ኾኖ የአምላክነት ሥራ ሠራ ይላሉና ከእስክንድርያ ሃይማኖት የሮማ ሃይማኖት ትሻላለች አለ፡፡

አባ ጳውሊ ሲመልስ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ሲያበሥራት መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የአብም ኃይሉ ይጋርድሻል ካንች የሚወለደውም ቅዱስ ነው የልዑል የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ብሎ ሦስቱም አካላት በማኅጸነ ማርያም እንደ አደሩ ተናግሯል፡፡ ማደራቸውም አብ ለአጽንዖ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ነው እንጅ ሦስቱ ኹሉ ለለቢሰ ሥጋ ያደሩ አይምሰልህ፡፡
በዚህ ጊዜ መለኮት ርቀቱን ለቆ ሳይገዝፍ ሳይለወጥ ትስብእትም ግዘፍነቱን ለቆ ሳይረቅ ሳይለወጥ እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ኾነ፡፡ ወልድ ለለቢሰ ሥጋ ማለት ይህ ነው አብ ለአጽንዖ ማለትም ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ምሉዕ ስፉሕ ረቂቅ መለኮትን እመቤታችን በጠባብ ማኅጸን እንድትችለው አጸናት ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ማለትም ትስብእትን ከአዳም መርገም አንጽቶ ቀድሶ ለተዋሕዶተ መለኮት የበቃ አደረገው ማለት ነው፡፡ ይህን በማኅጸን በረቂቅ ምሥጢር የሠሩትን አምላካዊ ሥራ በዮርዳኖስ ወልድ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲጠመቅ በመታየት አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ የሚል ድምጽ በማሰማት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጦ አብ ልጀ ይህ ነው ብሎ የመሰከረለት ወልድ ይህ ነው ብሎ በጣት ጠቅሶ እንደ ማሳየት በመመስከሩ ገልጸውለታል እንጅ እስከዚያ ድረስ ሰላሳ ዘመን መንፈስ ቅዱስ ተለይቶት ኖሮ በዮርዳኖስ አደረበት ማለት አይደለም አለ፡፡ ያ ሮማዊ መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ገላውዴዎስ አባ ዝክሪንና አባ ጳውሊን እኔ የክርስቶስ ባሪያ ሃይማኖቴ እንደ ሃይማኖታችሁ ኦርቶዶክስ እስክንድርያዊ ነው ይህነንም እናንተ ታውቁልኛላችሁ ነገር ግን እኛ የሕክምናና የተግባረ እድ ትምህርት የለንም ሮማውያን ብዙ ጥበብ ያውቃሉና ይህን ጥበባቸውን እስኪያስተምሩን ድረስ በሀገራችን እንዲቆዩ ፈቃዳችሁ ይኹን ሲል ለመናቸው፡፡
አባ ዝክሪ የተባለው መነኲሴ ተነሥቶ እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች እሊህ ሮማውያን በሀገራችን ይቀመጡ ካላችሁ ወደፊት በኢትዮጵያ ላይ የሚደርስባትን ነገር ልንገራችሁ እኒህ ሰዎች ከእህቶቻችን ከልጆቻችን ይወልዳሉ እኒያ ልጆች በድብቅ ያባቶቻቸውን የካቶሊካውያንን ትምህርት ይማራሉ እኛ ወገኖቻችን መስለውን ቅስና ዲቁና ስንሾማቸው የመምህርነት ማዕርግ ስንሰጣቸው ውስጥ ውስጡን የኹለት ባሕርይን ባህል እያስተማሩ ሃይማኖታችንን ይለውጧታል ይህም የተናገርኩት ነገር አይቀርም አምስት ነገሥታት ካለፉ በኋላ ስድስተኛ ንጉሥ ከወደ ዐረማውያን ሀገር መጥቶ ይነግሣል በርሱ ጊዜ ይፈጸማል ሲል ትንቢት ተናገረ፡፡ ከዚህ በኋላ ከዐፄ ገላውዴዎስ ዐፄ ፋሲል፤ ከዐፄ ፋሲል ዐፄ ሚናስ፤ ከዐፄ ሚናስ ዐፄ ሠርጸ ድንግል፤ ከዐፄ ሠርጸ ድንግል ዐፄ ያዕቆብ፤ ከዐፄ ያዕቆብ ዐፄ ሱስንዮስ  ዐፄ ሱስንዮስ ከዐረማውያን ሀገር መጥተው ነገሡ፡፡ በስድስተኛው ንጉሥ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ የአባ ዝክሪ ትንቢት ተፈጸመ፡፡
===========================================================
አባ ዝክሪ እና አባ ጳውሊ ማለት ለኢትዮጵያ ሊቃውንት አፈጉባዔ የሆኑ ለተዋሕዶ እምነት ጠበቃ የኾኑ የደብረ ጽሙና መነኮሳት ናቸው፡፡ ዛሬ የቅብአት ምንፍቅና አራማጆች ግን በእነዚህ አባቶች ስም የራሳቸውን ክህደት እያስፋፉ ነው፡፡ እነዚህ አባቶች ካቶሊካውያኑን ያሳፈሩ የተዋሕዶ አርበኞች ናቸው፡፡ ነገር ግን የቅብአት መናፍቃን የእነዚህ አባቶች ትንቢት እና ትምህርት በብራና ተጽፎ በእጃችን ይገኛል ይህንንም በወረቀት እናሳትመዋለን ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ትክክለኛው የአባ ዝክሪ እና የአባ ጳውሊ ትንቢት ወይም ትምህርት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡   
ፈጸምኩ፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

No comments:

Post a Comment