Monday, March 20, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፫

© መልካሙ በየነ

መጋቢት 11/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

የቅብዓት አስፈላጊነት
ቅብአት ለተለያዩ ነገሮች እንደሚያስፈልግ ከላይ ባሉት ክፍሎች ተመልክተናል፡፡ በዋናነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለአገልግሎት፣ ለአክብሮት እና ለህክምና እንደሚያስፈልግ በዝርዝር ተመልክተናል፡፡ እኛም በ40 እና በ80 ልጅነትን ያገኘንበት ሀብተ ወልድን የተቀበልንበት በጥምቀት ከብረን በቅብዓ ሜሮን ታትመን ክርስቲያን የተባልንበት ምሥጢር ለእግዚአብሔር መመረጣችንን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ መወለዳችንን ያመለክታል፡፡ ይህ ምሥጢር ልጅነትን የምንጎናጸፍበት እንዲሆን ያደረገው በቅብዓቱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ስለሚያድርበት ነው፡፡ ረቂቅ የሆኑ ሥራዎችን መጻሕፍት ለመንፈስ ቅዱስ ሰጥተው መናገር ልማዳቸው ነው እንጅ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ባደረበት አብና ወልድም ያድሩበታል፤ መንፈስ ቅዱስ ባለበትም አብና ወልድ አሉ፡፡ ቅብዓቱ የሚረባን የሚጠቅመን ለእኛ ነው ምክንያቱም ዳግም የምንወለድበት ምሥጢር የሚፈጸመው በጥምቀት ብቻ ሳይሆን በዚህ ቅዱስ ቅብዓት ጭምር ነውና፡፡ በዚህ በሜሮን ጸጋ መንፈስ ቅዱስን እንቀበላለን ለዚህም ነው በ40 በ80 ቀናችን ከተጠመቅን በኋላ ወይም ካለማመን ወደ ማመን የተመለሰ ሰው በማንኛውም የዕድሜ ዘመኑ ከተጠመቀ በኋላ ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በቅብዐ ሜሮን የሚታተመው፡፡ ይህ ቅብዓት ለእግዚአብሔር ወልድ ይረባዋል ይጠቅመዋልን? ቢባል መልሳችን እርሱስ አምላክ ነውና አይረባውም አይጠቅመውም እንላለን፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ላይ ለአገልግሎት በሚለው ሥር ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል (በመንፈስ ቅዱስ ተሞላ ሐዋ 10÷38) ይላል፡፡ የጥቅሱም ሙሉ ቃል “እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና” ሐዋ 10÷38 ይላል፡፡ ይህንን ወደፊት ሙሉ አንድምታ ትርጉሙን የምንጽፍ ይሆናል፡፡ ሆኖም ለዚህ ላነሣነው ጉዳይ ግን ለአገልግሎት እንደመጣ ራሱ እግዚአብሔር ነውና ራሱን እግዚአብሔር አድርጎ ለአገልግሎት ለይቷልና መርጧልና ይህንን ተናገሩ፡፡ ይህንን ይዘው እግዚአብሔር አብ ወልድን በመንፈስ ቅዱስ ቅብአትነት አከበረው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ነገር ግን አክብሮት ላይ ሳይሆን አገልግሎት ላይ የተጻፈ ስለሆነ የእነርሱን ኑፋቄ አይደግፍም፡፡ ቅብአቱ ይረባዋል ይጠቅመዋል ብለው የሚያስተምሩትም ለዚሁ ነው፡፡ “ቅብአቱስ እንደረባው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንዳስተካከለው…” ብለው ክህደታቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል ወልደ አብ ገጽ 233 ላይ፡፡ ይህንን በሌላ ርእስ የምንመለስበት ቢሆንም ለጊዜው ግን ቅብዓት ለወልድ እንደረባው እንደጠቀመው መናገራቸው ኑፋቄ መሆኑን ጠቁመን እናልፋለን፡፡ ይህ ቅብዓት የረባን የጠቀመን እኛን በጸጋ የአምላክ ልጆች ለሆንነው እንጅ የባሕርይ ልጅ ለሆነው ለወልድ አይደለም፡፡ ወልድንማ በሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ ም 54÷34 ላይ እንዲህ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ “እኛም አስቀድመን እንደተናገርን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዘለዓለም አንድ የባሕርይ ገዢ እንደሆነ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ በባሕርየ መለኮቱ ሳለ በእውነት ሰው እንደሆነ እግዚአብሔር በአጻፋቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ሁላችን ህጋችንን አስቀድሞ ልናስረዳ ይገባል” ይላል፡፡
ቅብዓት መንፈስ ቅዱስ ነውን?
ቅብዓት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ እንደሆነ በብዙ መጻሕፍት ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ምሳሌ ነው ማለት ግን ነው ማለት አይደለም፡፡ ቅብዓት ማለት መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው በማለት የሚከራከሩት የቅብዓት እምነት ተከታዮች ራሳቸው ወልደ አብ በሚባል መጽሐፋቸው ገጽ 184 ላይ “መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ነው ማለት እንዴት ነው ቅቤ ነውን ቢሉ ቅቤስ አይደለም በምሳሌ ጠርቶ ቅብዕ አለው” ይላሉ፡፡ እነርሱ ራሳቸው ቅብዓት የሚለውን ለመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ አድርገው ይጠቀሙበታል እንጅ ቅብዓት ማለት መንፈስ ቅዱስ ማለት እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን ቅብዓት ማለት መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው በማለት የሚከራከሩ ራሳቸው መሆናቸው ያስገርማል፡፡ ምሳሌ ነው ማለት ግን ነው ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ ያህል ኃጥአን በፍየል ጻድቃን በበግ ተመስለው እናገኛለን ይህ ማለት ግን ኃጥአን ፍየሎች ናቸው ጻድቃንም በጎች ናቸው ማለት አይደለም፡፡  ሙሴ ያያት ዕጸ ጳጦስ የእመቤታችን ምሳሌ ናት ያ ማለት ግን እመቤታችን ዕጸ ጳጦስ ናት ማለት አይደለም ምክንያቱም ድንግል ማርያም ክብርት ንጽሕት አምላክን ለመውለድ በቅታ የተገኘች ድንግል ሴት የሃና የኢያቄም ልጅ እንጅ ዕጽ አይደለችምና፡፡ ለምሳሌ ያህል እነዚህን ከተመለከትን መንፈስ ቅዱስም በቅብዓት ይመሰላል እንጅ ራሱ ቅብዓት እንዳልሆነ ግን እንረዳለን ማለት ነው፡፡ ረቂቅ የሆነውን ግብር መጻሕፍት ለመንፈስ ቅዱስ ሰጥተው ስለሚናገሩ በቅብአቱ ላይ አድሮ የሚገኘውን መንፈስ ቅዱስ በዚያ መስለውታል፡፡ ቅብዓት መንፈስ ቅዱስ ነው ከተባለ ግን “ቅብአቱ ላይ መንፈስ ቅዱስ አደረበት” ብለን ስንናገር መንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ላይ አደረበት ያሰኛልና አያስሄድም፡፡ ታዲያ መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘኤጲፋንዮስ ላይ ገጽ 96 አክሲማሮስ ዘሠሉስ ቁጥር 18 ላይ “ወእምዝ ተቀብዓ ቅብዓ ትስብእት ዘክርስቶስ ዘቦቱ ይነሥዑ ቅብዓ መንፈስ ቅዱስ ኩሎሙ አሕዛብ” ያለውን ሲተረጉም “ይህስ ቅብዓት ምንድነው ቢሉ ቀድሞ ጌታችን ከባሕርይ አባቱ በባሕርይ ልጅነት ተወልዶ የባሕርይ ልጅነት ያገኘበት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ዛሬም ሕዝቡ አሕዛቡ ከሥላሴ የፀጋ ልጅነት የሚወለዱበት ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ይህ ነው፡፡ የሚለው ለምንድን ነው? ቢባል ቅብዓት ያለው ወልድ ከባሕርይ አባቱ ከአብ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የተወለደበትን ረቂቅ ምሥጢር ሲገልጽ ነው፡፡ አንድም መንፈስ ቅዱስ ለወልድ የባሕርይ ሕይወቱ ነውና በህልውና እንደሚገናዘቡ ሲያመለክት ነው፡፡ ምሥጢረ ሥላሴ ላይ ስንማር አብ ወላዲ አስራጺ ነው ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ ነው፡፡  ይህ ከሰው ልጆች አእምሮ በላይ የሆነ በሥላሴ ዘንድ ጥበብ ነው፡፡ ይህን ጥበብ ልንመረምረው አንችልም ድንቅ ድንቅ ድንቅ እንለው ዘንድ ብቻ የተገባ ነው እንጅ፡፡ ይህንንም ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ላይ እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ምእራፍ 53 ክፍል 1 ቁጥር 2 ላይ  “እግዚአብሔር በሰው ኅሊና እንደማይመረመር ስለ መለኮት ባሕርይ እንናገራለን፡፡ የሰው ሕሊና መለኮትን መርምሮ አያውቀውምና የመለኮት ባሕርይም በሰው ሕሊና ከመመርመር የራቀ ነውና ከሕሊናትም ሁሉ ፈጽሞ የራቀ ነውና” ይላል፡፡ ዳግመኛም ይኸው ቅዱስ አባት በዚሁ ምእራፍ ቁጥር 5 ላይ እንዲህ ይላል “ተመርምሮ የማይታወቅ ከሆነስ አለመመርመሩን ማወቅ ይገባናል ድንቅ ምንድን ነው? የባሕርዩ ሥራ ነው እንጅ ድንቅ እርሱ ከሆነ ድንቅ የሆነ እርሱም ሁል ጊዜ  ድንቅ በመባል የሚኖር ከሆነ ዕውቀትን ድንቅ ድንቅ ሥራ ለሚሠራ ለፍጥረቱ ሁሉ ገዢ ለእርሱ ተው” ይላል፡፡ ስለዚህ ወልድ የተወለደውን ልደት በሰው ሕሊና መመርመር አይቻልምና ድንቅ ብሎ ነገሩን ለእርሱ መተው የተሸለ ነው፡፡  ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት ተወልዶ የባሕርይ ልጅነትን አገኘ ማለት ግን ክህደት ነው ምክንያቱም አብ ወልድን በመለኮቱ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ቀብቶታል አይባልምና፡፡ መጽሐፈ አክሲማሮስ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት ተቀቡ የሚላቸው በርካታ ነገሮች አሉ አክሲማሮስ ዘእሁድን ይመልከቱ ፡፡ እነዚያ ተቀቡ እየተባሉ የተገለጹት ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓነት ተቀብተው አምላክ ሆኑ ልንላቸው እንደማንችል ሁሉ ወልድም በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት በመለኮቱ  ተቀብቶ አምላክ ሆነ አንልም፡፡ ስለዚህ ወልድ ከባሕርይ አባቱ ከአብ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የተወለደበትን ረቂቅ ምሥጢር ሲገልጽ ተቀባ አለ፡፡
ቅብዓት (ቅባት) ከልዩ ልዩ እንጨቶች ተቀምሞና ተነጥሮ የሚወጣ ፈሳሽ ዓይነት ነው ብለን አስቀድመን ተመልክተናል፡፡ ቅብዓት ማለት በቀጥተኛ ትርጉሙም ክብር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነው “ይህስ ቅብዓት ምንድነው ቢሉ ቀድሞ ጌታችን ከባሕርይ አባቱ በባሕርይ ልጅነት ተወልዶ የባሕርይ ልጅነት ያገኘበት መንፈስ ቅዱስ ነው” የሚለውን ወልድ ከባሕርይ አባቱ ከአብ አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ የተወለደበትን ረቂቅ ምሥጢር ሲገልጽ እንጅ ቅብዓት ማለት መንፈስ ቅዱስ ነው ሲለን እዳልሆነ የተናገርነው፡፡ በቅብዓት የባሕርይ ልጅነት አገኘ ከተባለማ ወልድ በክብር ልጅነትን አገኘ ያሰኛልና ቅብዓት የሚለን ረቂቅ ምሥጢሩን ሲገልጽ ነው፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment