Tuesday, March 21, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፭



© መልካሙ በየነ

መጋቢት 13/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በወቅቱ የነበሩት የሮማው ጳጳስና የፖርቹጋሉ ንጉሥ በዚህ የቤርሙዴዝ መግለጫ ላይ በጥልቀት ከተወያዩበት በኋላ ሌሎች ሚሲዮኖችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የካቶሊክ እምነት ወደ ሀገራችን እንዲገባ ሰፊ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያን ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ ወዘተ አሰልጥነው ዐሥር የሚሆኑ ሚሲዮኖችን ወደ ሀገራችን ላኩ፡፡ በዚህ ጊዜ የሀገራችን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደ አባ ዝክሪ እና እንደ አባ ጳውሊ ያሉት ከጳጳሳቸው ከአቡነ ዮሴፍ ጋር ሆነው ሚሲዮናውያኑን ተከራከሯቸው፡፡ (ክርክራቸውን እዚህ ላይ ተጭነው ማንበብ ይችላሉ፡፡)
ለጊዜው የተሸነፉ መስለው ከክርክሩ ራሳቸውን አሸሹ፡፡ ከዐጼ ገላውዴዎስ ሞት በኋላ በተሾሙት በወንድማቸው በዐጼ ሚናስ ዘመነ መንገሥትም እንዲሁ ክርክር አድርገዋል፡፡ በእነዚህ ዘመናት ሁሉ እምነታቸውን በድብቅ ያስተምሩ ነበርና ንጉሡ የሚሲዮኖችን ፓትርያርክ ኦቢያዶን አስጠርተው ድጋሜ የካቶሊክን እምነት እንዳያስተምር አስጠነቀቁት፡፡ “እጸድቅ ብየ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች” እንደሚባለው ሆኖ ኦብያዶ በዚህ የተነሣ የንጉሡን ሥም ማጥፋት እና ከእስላሞች ጋር በምሥጢር እየተገናኘ ንጉሡን ለማስገደል እንዲሁም የኢትዮጵያን ክርስቲያኖች ለማስያዝ ወጥመዱን ያጠምድ ጀመረ፡፡ ይህ ክፉ ሥራው ስለታወቀ ከጓደኞቹ ጋር ተይዞ በግዞት ተቀመጡ ሆኖም ግን ከዚህ አምልጠው በኢትዮጵያ ዙሪያ ከሰፈሩት ጠላቶቻችን ከቱርኮች ጋራ ተቀላቀሉ፡፡
ሚሲዮኖቹ ግን የካቶሊክ እምነትን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ቆርጠው ተነሥተዋልና ብዙ አማራጮችን ተጠቅመዋል፡፡ ከዐጼ ሚናስ ሞት በኋላ በዐጼ ዘድንግል ዘመነ መንግሥት በ1603 ዓ.ም በአባ ጴጥሮስ ፖኤዝ የሚመሩ ላቲኖች ወደ ሀገራችን ገቡ፡፡ የፖርቹጋል መንግሥት ባደረገው ውለታ ምክንያት በሀገራችን እንዲቀመጡ ስለተፈቀደላቸው በሀገራችን ተቀምጠው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሁሉ እምነታቸውን በድብቅ ማስፋፋት ጀመሩ፡፡ በዚህ መልኩ ከቀጠሉ በኋላ በይፋ ደረታቸውን ነፍተው ልባቸውን ሞልተው በኩራት እምነታቸውን ማስፋፋት የጀመሩት ግን በዐጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ ፈሊጥ አዋቂው ጴጥሮስ ፖኤዝ የሀገራችንን ቋንቋ ግእዝን ተምሮ ይሰብክ እና ይቀድስ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከንጉሡ ዘንድም እየሄደ የካቶሊክ እምነትን ቢቀበሉ የፖርቹጋል መንግሥት የጦር መሣሪያን ያስታጥቅዎታል እያለ ይሰብካቸው ነበር፡፡ ንጉሡም በዚህ ተታልለው ለካቶሊኮች የቤተክርስቲያን መሥሪያ ቦታ ሰጧቸው በኋላም በ1622 ዓ.ም በጴጥሮስ ፓኤዝ እጅ ከነቤተሰቦቻቸው በሮማ ካቶሊክ ሥርዓት ተጠምቀው ካቶሊክነታቸውን በይፋ አረጋገጡ፡፡
የጴጥሮስ ፓኤዝን ሞት ተከትሎ በሮማው ጳጳስ እጅ ጵጵስና የተሾመው የእስፔኑ ተወላጅ አልፎንሱ ሜንዴዝ በየካቲት 1623 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ተብሎ ተሰይሞ ወደ ሀገራችን ሰኔ 21 ቀን 1625 ዓ.ም ገባ፡፡ ከዚህ የካቶሊክ ፓትርያርክ ጋር አንድ ረዳት ኤጲስ ቆጶስ እና 18 ቀሳውስት አብረውት ተልከው ወደ ሀገራችን ገብተዋል፡፡
ንጉሥ ሱስንዮስ የካቲት 11 ቀን 1626 ዓ.ም የሀገሪቱ ብሔራዊ ሃይማኖት ካቶሊክ እንዲሆን እና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሮም ሥር እንድትተዳደር ዐዋጅ ዐወጁ፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሡ ከአልፎንሱ ሜንዴዝ ጋር ተባብረው የሚከተሉትን ህጎች አወጡ፡-
v  ኢትዮጵያ ክርስቲያኖች እንደገና እንዲጠመቁ፣
v  ካህናቱም እንደገና እንዲካኑ፣
v  አብያተ ክርስቲያናትም እንደገና በሮማውያን እንዲባረኩ፣
v  በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉት ቅዱሳት ሥዕላት ቀርተው በሮማውያን ሥርዓት የተቀረጹ ምስሎች እንዲቆሙ፣
v  የሮማውያን የቀን መቁጠሪያ በኢትዮጵያ እንዲሠራበት፣
v  የአርብና የረቡዕ መጾም ቀርቶ ቅዳሜ እንዲጾምና የቅዳሜ ሰንበትነት እንዲሻር፣
ይህንን ህግ የማይጠብቅ ሁሉ የአካል ቅጣት እንደሚወሰድበት ንጉሡ ዐዋጅ እንዲያውጁ አልፎንሱ ሜንዴዝ ስለነገራቸው ንጉሡም በዚሁ ተስማምተው ዐዋጁን ዐውጀዋል፡፡
በዚህም የተነሣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጳጳስ የሆኑት አቡነ ስምኦን ለሃይማኖታቸው ተቆርቋሪ የሆኑትን ካህናት፣ መኳንንት እና ምእመናን ሰብስበው ከንጉሡ ጋር ጦርነት ከፈቱ፡፡ የንጉሡን ተከታዮች ለመቀነስም አቡነ ስምኦን ‹‹ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ለውጠዋልና እርሳቸውን የሚከተል እንደ አርዮስ የተወገዘ ይሁን›› ብለው የንጉሡን ተከታዮች በማውገዝ ድጋፋቸውን አጠናከሩ፡፡ ሆኖም ግን ድሉ ለንጉሡ ሆነና ጳጳሱም በዚሁ ጦርነት ተገደሉ፡፡ በዚህም የተነሣ በካቶሊካውያኑ ዘንድ ንዴትን ፈጠረ እና የተዋሕዶ እምነትን በሚከተሉ ክርስቲያኖች ዘንድ ስቃይ አጸኑባቸው፡፡ ይህንን በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ እና መከራ የሰሙ የጎጃም፣ ቤጌ ምድር፣ የትግራይና የላስታ ሰዎች ሰማእትነት እንዳያመልጠን እያሉ ወደ ሱስንዮስ ዐደባባይ ስለመጡ ብዙ ክርስቲያኖች ተገድለዋል፡፡ ይህ ጦርነትም ለሰባት ዓመታት ያህል ከተካሄደ በኋላ ንጉሡ ታመሙና አንደበታቸው ተዘጋ፡፡ ልጃቸው ፋሲልም ወደ ገዳማትና አድባራት በመሄድ አባቴ የክርስቲያኖችን ደም በማፍሰሱ እግዚአብሔር ተቆጥቶበት አንደበቱ ተዘግቷልና ጸልዩለት የምትፈልጉትን ሁሉ አደርጋለሁ አለ፡፡ በዚህ የፋሲል ልመና የማኅበረ ሥላሴው አምደ ሥላሴ የተባሉ ባሕታዊ የገዳማቸውን መነኮሳት አስከትለው በመሄድ ለሦስት ሱባኤ ያህል በጸሎት በምህላ ቆይተው ጸበል አጠመቋቸው፡፡ ንጉሡም አንደበታቸው ተከፈተ መናገር ቻሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ለልጃቸው ‹‹የእስክንድርያ ሃይማኖት ትመለስ፣ የሮም ሃይማኖት ትርከስ፣ ፋሲል ይንገሥ ብለህ ዐዋጅ ተናገር›› ብለው ነገሩት እርሱም ዐዋጁን ዐወጀ፡፡ ህዝቡም ተደሰተ አድባራትና ገዳማትም የደስታ ደወላቸውን ደወሉ በአልፎንሱ ምክንያት የተሰደዱት በየዋሻው በየበረሃው የገቡ መምህራን፣ መነኮሳት ሁሉ መጽሐፎቻቸውን እና ጽላቶችን እየያዙ ወደየቦታቸው ተመለሱ፡፡ በካቶሊካውያኑ ተታልለው ሃይማኖታቸውን የለወጡትንም ንስሐ እንዲገቡ እያደረጉ ወደ ቤተክርስቲያን መለሷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሡ ሞቱና ልጃቸው ፋሲል ነገሠ ህዝቡ ይበልጥ ደስ አለው አልፎንሱ ግን እስካሁን ድረስ ከሀገራችን አልወጣም ነበር፡፡
ዐጼ ፋሲል መንግሥቱን ካደላደለ በኋላ የተዋሕዶ ሊቃውንት ከአልፎንሱ ሜንዴዝ ጋር በጎንደር ጉባኤ ተደርጎ ተከራከሩ፡፡ በዚህም ጉባኤ በዕጨጌ በትረ ጊዮርጊስ መሪነት የተከራከሩት የተዋሕዶ ሊቃውንት አሸነፉ፡፡ ዐጼ ፈሲልም አልፎንሱን ለማስወጣት ስለፈለጉ በሀገራችን የፈጸማቸውን ግፎች ዘርዝረው ለፖርቱጋል የካቶሊኮች ፓትርያርክ ደብዳቤ ላኩላቸው፡፡ ከዚያም አልፎንሱን እንዲወጣ ትእዛዝ ሰጡት በዚህም ትእዛዝ መሠረት ከጎንደር ወጥቶ በትግራይ ፍሬሞና ከምትባል ቦታ ተደበቀ፡፡ ንጉሡም በዚች ቦታ መደበቁን ሰምተው በምጽዋ በኩል እንዲወጣ ወታደሮችን ላከ፡፡ ከዚያም በኋላ አልፎንሱ አሞኛል ብሎ በሐማሴን ተቀመጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ከጎንደር ተከትለውት ለነበሩት ሁለት ኢትዮጵያውያን ማለትም ለኤዎስጣቴዎስ ዘጎጃም እና ለቆረንጭ መናፍቅ ተክለ ሃይማኖት ዘሸዋ ሁለት እምነቶችን አስተምሯቸዋል፡፡ ለጎጃሙ ኤዎስጣቴዎስ ዘሳንኳ ጊዮርጊስ የቅብዐትን እምነት ባህል ሲያስተምረው ለቆረንጭ መናፍቅ ተክለ ሃይማኖት ዘሸዋ ደግሞ የጸጋ እምነትን ባህል አስተምሮታል፡፡ አልፎንሱም እነዚህን እምነቶች በኢትዮጵያ ከተከለ በኋላ ወደ ህንድ ሄዷል፡፡
ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው የቅብዓት እምነት ምንጩ ባህሉ የካቶሊክ እምነት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የቅብዓት እምነት በሀገራችን ብቅ ማለት የጀመረው፡፡ ከዚህ በኋላ ይህን የቅብዓት እምነት በማስፋፋት ብዙ ተከታዮችን ማፍራት እንደቻለ እናውቃለን፡፡ የዚህ ርእስ ዓላማ የነበረው የቅብዓት እምነት ወደ ሀገራችን እንዴት እንደገባ ማሳየት ብቻ ስለነበር በዚህ እንቋጫለን፡፡ አጠቃላይ ታሪኩን ግን በተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ላይ ተመዝግቦ ስለምናገኘው ከዚያ በማንበብ እንድንረዳ እንመክራለን፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment