Saturday, March 18, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፪



© መልካሙ በየነ


መጋቢት 9/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

በክፍል አንድ ቅብዐት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዴት እንደተተረጎመ ተመልክተናል፡፡ ቀጥለን በዚህ ክፍል ደግሞ ሌሎችን መዝገበ ቃላት፣ ሰዋስውና ግስ መጻሕፍትንም በማገላበጥ የቃሉን ግስ አገባብ አፈታት አተረጓጎም እንመለከታለን፡፡
1ኛ. ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው መጽሐፈ ግስ ወሰዋስው መርኆ መጻሕፍት በተሰኘ መጽሐፋቸው ገጽ 199 ላይ ቀብዐ ቀባ የሁሉ ካሉ በኋላ ግሱን ማርባት ይጀምራሉ፡፡ ቅቡዕ ውስጠዘ ቅቡዓን (በብዙ) ቅብዕት (ለሴት) አብ መቅብዕ (ባዕድ ቅጽል) ቀባዕት (መድበል) ቆብዕ ቅብዕ (ዘመድ ዘር) ቀዋብዕ ቅብዓት(በብዙ) ቅብዐት (ሳቢ ዘር) ---ማስረጃ በዘተሰብአ ተቀብዐተዋሐደ (ቆብዕ ቆብ ማለት ነው) ምቅባዕ ባዕድ ዘር ከመዝ ይትቀብዑ እምቅዱስ ቅብዕ በኀበ ምቅባዕ እን ቆስጠ 39 ወፈነወ ኢየሱስሀ ወአቅደመ ቀቢዖቶ አዘጋጀ ብለው ቀብዐ ያለውን ግስ ይፈጽማሉ፡፡ በዚህ ግስ እርባታ ላይ ቀብዐ የሚለው ግስ ቀባ ከሚለው የአማርኛ ትርጉም በተጨማሪ አዘጋጀ አዋሐደ ተብሎ እንደሚተረጎም ማስረጃዎችን አስቀምጠዋል፡፡ በዘተሰብአ ተቀብዐ ባለው ላይ ተቀብዐ ያለውን ቃል ተዋሐደ ተብሎ ተተርጉሞ እናገኛለን፡፡ ወፈነወ ኢየሱስሀ ወአቅደመ ቀቢዖቶ ሲል ደግሞ ቀብዐ የሚለው ቃል አዘጋጀ በሚለው አማርኛ ተተርጉሞ እናገኘዋለን፡፡
2ኛ. አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 779 እና ገጽ 780 ላይ በዝርዝር ያስቀመጡትን እንመልከት፡፡ ቀቢዕ፤ ዖት፤ (ቀብዐ፡ ይቀብዕ፡ ይቅባዕ፡፡ ዕብ፡ ቃባዕ፡ ሐገገ፡ ዐደመ ፡ መልአ ፡ ሤመ) ይልና፤ ሲተረጉም መቅባት፣ መቀባት፣ መላላክ፣ መለቅለቅ፣ ለመሾም፣ ለማክበር፣ ለማሳመር ለመፈወስ ይላል፡፡ ቀብዖ በሕጉሬ፡፡ ቀብዖ ወርቀ ንጹሐ፡፡ ኢትቅብዖ ዕፍረተ፡፡ ገብረ ጽቡረ በምራቁ በቀብዖ አዕይንቲሁ (ሢራ 45÷15 ጥበ 13÷14 3ኛ ነገ 10÷18 ፍት ነገ 51፡፡ ዮሐ 9÷20)፡፡ ልብስና ቀለም ሽቱና ተቀቢው ልዩ ልዮች ስለሆኑ መጋጠማቸው ለተዋሕዶ ምሳሌ እየሆነ ይነገራል፡፡ ከመ ፀምር ውስተ ሠርዮ ከማሁ ተቀቢዖ ትስብእተ በመለኮተ፡፡ ዕፍረትሰ ሥጋ ዚአኪ ወተቀባዒሁ ቃል ውእቱ (ኤጲ አክሲ፡፡ አርጋ)፡፡ እንዲህ ያለው ንባብ ግስ ሠም ለበስ ይባላል ካሮች ግን ሠሙን ወርቅ ምሣሌውን ጽድቅ አድርገው ቀብዐን አዋሐደ  ተቀብዐን ተዋሐደ እያሉ አለቋንቋው አለንባቡ አለስልቱ አላገባቡ አላንጻሩ አለምሥጢሩ ይፈቱታል፡፡ የተቀባዐ ፍች ተዋሐደ ማለት ከሆነ ቄርሎስ አፈወርቅ ኢይጽሕቅ ቅብዐተ በህላዌሁ፡፡ ወመለኮቱሰ ኢይትቀባዕ ይላሉና ይህ ንባብ ሳይወዱ በግድ በባሕርዩ ተዋሕዶ አይሻም፡፡ መለኮቱ አይዋሐድም ያሰኝባቸዋል፡፡ ተማሪ ሳይሆኑ መምህር መሆን እውነቱን ሐሰት ሐሰቱንም እውነት እያሰኘ እንዲህ ፈራሽ ነገር ያናግራል፡፡ የተሰብአንና የተቀብዐን ምሥጢር ስንኳን ልቡን ዠርባውን አላገኙትም ቅባቶችም እንዲሁ ናቸው ይላሉ፡፡
እኪዳነ ወልድ ክፍሌ “ካሮች” እና “ቅብአቶች” የተሰብአንና የተቀብዐን ትርጉም (ምሥጢር) እንኳን ልቡን ዠርባውንም አላገኙትም ብለዋል፡፡ እኛ ስለካሮች እና ስለ ቅብአቶች ባይመለከትንም እኛ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” የምንል ኦርቶዶክሳውያን ግን የምንለው ነገር ይኖረናል፡፡ ይህን መዝገበ ቃላት ወጥተው ወርደው ደክመው በማዘጋጀታቸው የግእዝ ችሎታቸውን እንዳሳዩበት እንረዳለን፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከዚህ ቃል ጋር በተያያዘ ግን ጉድለት እንዳለባቸው እንገነዘባለን፡፡ እሳቸው ያዩበት ዓይናቸው እንዴት እንደሆነ ባናውቅም እኛ ግን ሊቅነታቸው መራቀቃቸው እንደጎዳቸው እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም አንድ ቃል በተለያዩ አገባቦች የተለያየ ትርጉም እንደሚኖረው አልተገነዘቡትም፡፡ በእርግጥ ይህን ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም ምክንያቱም እርሳቸው የሚያምኑት ምንታዌነት ተጋፍቷቸው እንደሚሆን እንረዳለንና፡፡ አንድ ቃል በተለያዩ አገባቦች ላይ የተለያዩ ትርጉሞችን እንደሚይዝ መጽሐፍ ቅዱስን አብነት አድርገን አንድ ቀላል የሆነ ምሳሌ እንመልከት እስኪ፡፡
“አዳምም ሚስቱን ሔዋንን ዐወቀ ጸነሰችም ቃየንንም ወለደች” ይላል ዘፍ 4÷1 ላይ፡፡ ይህንን “ዐወቀ” የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ምን ብለው ይተረጉሙት ነበር፡፡ “ዐወቀ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ ተረዳ፣ ተገነዘበ፣ ልብ አለ፣ አስታወሰ፣ እውቀትን አገኘ ወዘተ ማለት ነው፡፡ በዚህ ትርጉም ብንሄድ ይህ የመጽሐፍ ክፍል ትርጉም አይኖረውም ምክንያቱም አዳም ሚስቱን ተረዳ፣ ተገነዘበ፣ ልብ አለ፣ አስታወሰ፣ እውቀትን አገኘ ወዘተ ተብሎ ሊነገር አይችልምና፡፡ ምክንያቱም አዳም ከግራ ጎኑ የተፈጠረችለትን አጋዡን አስታወሳት ቢባል አያስማማም ምክንያቱም ሚስቱ እንዴት ትጠፋዋለች በዚያ ላይ በዓለም ያሉ ሰዎች እኮ ሁለት ብቻ ናቸው አዳም እና ሔዋን ታዲያ አዳም የትናዋ ሴት በመልክ ከሔዋን ጋር ተመሳስላበት ሊረሳት ይችላል፡፡ እሽ ይሁን ብለን እንኳ ብንቀበለው ቀጥሎ ከሚመጣው ቃል ጋር መስማማት አንችልም፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ቃል መጽነስና መውለድን የሚገልጽ ነው፡፡ አዳም የረሳት ሚስቱን በማስታወሱና በማወቁ ብቻ ሔዋን ልትጸንስና ልትወልድ አትችልም፡፡ ስለዚህ “ዐወቀ” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ ቀድሞ የምናውቀውን ትርጉም ይዞ ሊገኝ አይችልም፡፡ በመሆኑም “ዐወቀ” የሚለው ቃል በዚህ አገባብ “በግብረ ሥጋ ተገናኘ” ተብሎ የሚተረጎም እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሆኖም ግን ዐወቀ የሚለው ቃል ሁልጊዜ ይህንን ትርጉም ይዞ ይገኛል ማለት ደግሞ አይቻልም፡፡ በሌላ አገባብ በሌላ ቦታ ላይ ድሮ ከምናውቀው ትርጉም ጋር አንድ ሆኖ ገጥሞ የምናገኝበት ጊዜ አለ፡፡ ዮሀ 20÷13 ላይ “…ጌታየን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው” የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ አላውቅም የሚለውን ቃል ከላይ በተረጎምንበት አገባብ ብንተረጉመው ምን መልእክት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህን ቃል ግን ከላይ በተረጎምንበት አገባብ ተርጉመን “በግብረ ሥጋ አልተገናኘሁም” ብንለው ትርጉሙ ምን እንደሚሆን ለመረዳት ይከብዳል፡፡ ስለዚህ በዚህ አገባብ ላይ ይህ ቃል ድሮ በምናውቀው ትርጉም ልንተረጉመው ይገባል ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት አላውቅም ስትል አልተረዳሁም አልተገነዘብኩም ልብ አላልኩም አላስታወስኩም ወዘተ ብለን ብንፈታው ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ “ቀብዐ” የሚለው ቃል ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ትርጉም ብቻ ነው ያለው የሚለው የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ አባባል ችግር እንዳለበት እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም አገባቡንም ልንመለከተው ያስፈልጋልና፡፡ “ተማሪ ሳይሆኑ መምህር መሆን እውነቱን ሐሰት ሐሰቱንም እውነት እያሰኘ እንዲህ ፈራሽ ነገር ያናግራል፡፡ የተሰብአንና የተቀብዐን ምሥጢር ስንኳን ልቡን ዠርባውን አላገኙትም” በማለት መተርጉማኑን የነቀፉበት አገላለጻቸው ደግሞ ከቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት የሚጠበቅ ንግግር እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም እኔ ትል ነኝ፣ እኔ አፈር ትቢያ ነኝ፣ እኔ ጭንጋፍ ነኝ፣ እኔ አላዋቂ ነኝ ወዘተ የሚሉ የትህትና አባቶች በህይወት ኖረው ያስተማሩባት ቤተክርስቲያን ናትና እኔ ሊቅ ነኝ ሌላው የሚለው ሁሉ ድንቁርና ነው አይባልም፡፡
ስለዚህ “ቀብዐ” የሚለው ቃል ቀባ ከሚለው አማርኛም በተጨማሪ እንደአገባቡ ሌሎች ትርጉሞችን እንደሚይዝ እንገነዘባለን፡፡ ኢሳ 61÷1 “መንፈሰ እግዚአብሔር ዘላእሌየዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ…” የሚለውን ሊቃውንቱ ሲተረጉሙ “በህልውናየ ያለ መንፈስ ቅዱስ ስለከዊነ ትስብእት ያዋሐደኝ…” ብለው ብለው ነው የተረጎሙት፡፡ ከዚህ የምንረዳው “ቀብዐ” የሚለው ቃል ቀባ ከሚለው አማርኛ በተጨማሪም አዋሐደ ተብሎ እንደሚተረጎም እንደሚፈታ ነው፡፡ ሌላው “ዘተቀባእከ ሥጋሃ ለማርያም” የሚለውን “የማርያምን ሥጋ የተዋሐድህ” በማለት ተርጉመውታል መጽሐፈ አርጋኖን ዘአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፡፡ “ወከመዝ ነአምሮ ለሊሁ ተቀብዐ ከመ ሥርዓተ ትስብእት ወዳእሙ ውእቱ ዘይቀብዕ ርእሶ በመንፈሱ ባሕቲቱ” የሚለውንም “በተዋሕዶ እንደከበረ እናውቃለን ግን በገዛ ሥልጣኑ ራሱን የሚያከብር እሱ ነው” በማለት ተርጉመውታል ሃይማኖተ አበው ስምዓት ምእራፍ 124 ክፍል 2 ቁጥር 14 ላይ፡፡ ስለዚህ ቀብዐ የሚለው ቃል አዋሐደ በሚለው ቃል ተተርጉሞ እንደምናገኘው መገንዘብ ያሻል፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment