Sunday, March 12, 2017

ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት---ክፍል ፫ (የጉባኤ ኒቅያ መጀመር እና የተሰጡውሳኔዎች)




© መልካሙ በየነ
መጋቢት 4/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
=============================================
በመጀመሪያ ( facebook.com/beyenemlkm እና/ወይም facebook.com/melkamtiwulid ) ላይክ ያድርጉ ከዚያ ጽሑፉን ያንብቡ ቀጥለውም ጽሑፉን SHARE, COMMENT, LIKE ያድርጉ፡-
=============================================
የአርዮስን እና የእለእስክንድሮስን ነገር ደግ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ሰምቶ ከምንጩ ለማድረቅ የሚረዳውን መፍትሔ ማሰብ ጀመረ፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አርዮስና እለእስክንድሮስ የሚታረቁበትን ነገር ያሰላስል ነበር፡፡ ለዚህ እርቅ ደግሞ አስተዋይና በእምነቱ ምስጉን የሆነውን የኮርዶቫውን (ስፓኝ) ጳጳስ (ኦ)ሆስዮስን ወደ እስክንድርያ ደብዳቤ አስይዞ በመላክ አርዮስና እለ እስክንድሮስ እንዲታረቁና ልዩነታቸውን እንዲያስወግዱ ጥረት አድርጓል፡፡ ሆኖም ግን አርዮስ ክህደቱን በአገኘው ሁሉ አጋጣሚ እየነዛ በክህደቱ ስለጸና ኦስዮስ ተመልሶ ለንጉሡ የአርዮስን አልመለስም ባይነት ገልጾለታል፡፡ ቆስጠንጢኖስም የእለእስክንድሮስ  ትምህርት እውነት እንደሆነ አውቆ ጉባኤ ላቁምልህ በጉባኤ ተከራከሩ ብሎ እለእስክንድሮስን ጠየቀው፡፡ እለእስክንድሮስም አባቱ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ በጉባኤ እንደሚረታውና ክህደቱን ለሁሉ እንደሚገልጠው ነግሮት ነበርና እጅግ በጣም ደስ አለው፡፡ በዚህም መሠረት ከሚያዝያ 21 እስከ መስከረም 21 ድረስ በኒቅያ እንዲሰበሰቡ ንጉሡ ዐዋጅ አስነገረ፡፡ ከዚያም በኋላ በዐዋጁ መሠረት 2340 ሊቃውንት ተሰበሰቡ ንጉሡም የመጡበትን ሀገርና ሃይማኖታቸውን ጽፈው እንዲሰጡት አዘዘ፡፡ በዚህም መረጃ መሠረት እለእስክንድሮስን መስለው የተገኙት 317 ሊቃውንት ብቻ ነበሩ፡፡ እነዚህም በገድል የተቀጠቀጡ በትሩፋት የታነጹ ሃይማኖታቸው የቀና ሊቃውንት ናቸው፡፡ በዚህም ጉባዔ ላይ ዐራቱ ታዋቂ ሊቃነ ጳጳሳትና የመርዐሱ ኤጲስ ቆጶስ ቶማስ፣ እጆቹ በእሳት የተቃጠሉት የሜሶፖታሚያው ጳጳስ ጳውሎስ፣ ብብህትውናና በትህርምት የሚታወቀው እና በዲዮቅልጥያኖስም ዘመን ቀኝ ዓይኑን ያወጡትና የግራ እግሩን ጅማት የቆረጡት በፍኑትዮስ፣ በዓባይ በረሐዎች በብህትውና ይኖር የነበረው ቅዱስ እንጦንዮስ፣ በዘመነ ሰማዕታት አንድ ዐይኑን ያወጡት የሄራቅሊያው ጳጳስ ፓታሞን፣ ያዕቆብ ዘንጽቢን፣ የቆጵሮሱ ጳጳስ ሲፒሪዲዮን፣ የኢየሩሳሌሙ ጰጳስ መቃርዮስ እና ሌሎችም በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን መከራን የተቀበሉ አባቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚህ ሃይማኖታቸው የቀና 318ቱ ሊቃውንት በአንድነት ተሰብስበው ምሥጢራትን መመርመር ጀመሩ፡፡ በዚህ ጉባኤ መካከልም ጌታ አንዱን ተሰብሳቢ መስሎ የጠመመውን እያቀና የጎደለውን እየመላ አብሯቸው ይውል እና ያድር ነበር፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ይህንን እየተመለከተ ግሩም ድንቅ ኤጲስ ቆጶስ ይለው ነበር፡፡ ንጉሡ ጌታ መሆኑን የተረዳው ምግባቸውን ሲልክላቸው 318ቱ ተቀብለው አንድ ይተርፍ ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ዘጠኝ ሱባኤ ከቆዩ በኋላ ህዳር 9 ቀን 325 ዓ.ም በእለእስክንድሮስ መሪነት ጉባኤው በኒቅያ ተጀመረ፡፡ በዚህ ጉባኤ ዐራት መንበሮች ተዘረጉ፡፡ እነዚህ መንበሮችም፡-
1.  ለሮም ሊቀ ጳጳሳት ለአውሳንዮስ ወይም ዮናክንዲኖስ
2.  ለእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ለእለ እስክንድሮስ ለጉባኤው ሊቀመንበር
3.  ለኤፌሶን ሊቀ ጳጳሳት ለሶል ጴጥሮስ እና
4.  ለአንጾኪያ ሊቀጳጳሳት ለኤውስጣቴዎስ እንደሆኑ ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት ምእራፍ 18 ቁጥር 12 ላይ ይናገራል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም ከሊቀ ጳጳሳቱ ዝቅ ያለ መንበር አዘጋጅቶ በዚያ ተቀምጦ ነበር፡፡ ከዚያም የአንጾኪያው ጳጳስ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ የመግቢያ ንግግር አደረገ፡፡  ከዚያም አርዮስ ቀርቦ “ምን ይዘህ ወልድ ፍጡር ነው አልክ” ተብሎ ተጠየቀ እርሱም “ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ አብ መቅድመ ኩሉ ተግባሩ፤ጥበብ እግዚአብሔር ፈጠረኝ ለፍጥረቱም ተቀዳሚ አደረገኝ” የሚል ንባብ አግኝቼ ምሳ 8÷22 ላይ አለ፡፡ እለእስክንድሮስም ከአፉ ነጥቆ “እምቅድመ አድባር ወአውግር ወለደኒ፤ ተራሮች እና ኮረብቶች ሳይፈጠሩ ወለደኝ” ይልብሃልሳ አለው፡፡ አርዮስም አወ ይወልደዋል ይፈጥረዋልም ብሎ ሲመልስ እለእስክንድሮስ መውለድ መፍጠር የሚሆን ከሆነማ እስኪ የወለድኸውን ፈጥረህ አሳየኝ አለው፡፡ አርዮስም የወለደውን መፍጠር ስለማይችል በዚህ ተሸንፎ ተረትቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሡ በዐዋጅ ኤጲስ ቆጶሳቱ በውግዘት ከቤተክርስቲያን አንድነት ከለዩት በኋላ ብዙ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል በርካታ ድርሰቶችንም ደርሰዋል፡፡ ከዚህ አትለፍ ከዚህም አትትረፍ ብለው የወሰኗትንም ሃይማኖት ለሁሉ ገልጠዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ የተደረሱ ድርሰቶችም የሚከተሉት ናቸው፡፡
v  ለምእመናን ድኅነት የሚሆነውን ጸሎተ ሃይማኖትን “ሁሉን በሚገዛ የሚታየውን የማይታየውን ፍጥረትን ሁሉ በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡ ከአብ በተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በእግዚአብሔር ልጅ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡ ይኸውም ከአብ ባሕርይ የተገኘ ነው ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን የተወለደ እንጅ ፍጡር ያይደለ ከአብ ጋር በጌትነቱ የተካከለ ሁሉ በእርሱ ቃልነት የተፈጠረ ያለእርሱ ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ በሰማይና በምድር ያለውም ቢሆን፡፡ ሰው ሆነ ስለእኛም ተሰቀለ ታመመ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በምሥጋና ወደሰማይ ዐረገ በሕያዋን እና በሙታን ይፈርድ ዘንድ በጌትነት ዳግመኛ ይመጣል” እስከሚለው ድረስ ያለውን የሃይማኖት ጸሎት አዘጋጅተዋል፡፡
v  ለካህናት ደግሞ ግሩም የሚባለውን ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምእትን ጽፈዋል፡፡
v  ለመነኮሳትም ህንጻ መነኮሳት የሚባለውን መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment