Sunday, March 19, 2017

“አዳራሽ ውስጥ ምሕላ የሚያደርስ...መናፍቅ ነው”..አቡነ ማርቆስ

© መልካሙ በየነ

መጋቢት 9/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ


ዛሬ መጋቢት 9/2009 ዓ.ም የምሥራቅ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስ ደብረ ዘይትን ምክንያት በማድረግ ትልቅ ጉባኤ በደብረ ማርቆስ ከተማ በጽርሐ ጽዮን አብማ ማርያም አደረጉ። በዚህ ጉባኤ ከ አዲስ አበባ ይዘዋቸው የመጡ ተጋባዥ መምህራን አሉበት። አቡነ ማርቆስ ስለዘገዩ የማይክ ፍቅር የተጠናወተው ሁሉ ማይኩን እያነሣ የራሱን ነገር ይናገር ጀመር። እኔ የደረስኩት ግን የዋሻው ቅዱስ ሚካኤል ገዳም “አስተዳዳሪ” አባ ፍቅረ ማርያም ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡ ብለው ሲያስተምሩ ነበር። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡ አሉ ከዚያም ህዝቡን ይህን ቃል ድገሙት ተባለ ህዝቡም ቃሉን ደገመው። ከዚያ ትንሽ እንዳስተማሩ ህዝቡ  ከመቀመጫው እየተነሣ መቆም ጀመረ ምንድን ነው ብለን ስንመለከት “አባ ማርቆስ” እየመጡ ነው ለካ። ሰባኪው ትምህርቱን አቋረጡና “ማርቆስ ሐመልማለ ወርቅ” እያሉ መዘመር ጀመሩ። ህዝቡም እያጨበጨበ በእልልታ እያቀለጠ አቡኑን ተቀበሏቸው። ከዚያ በጸሎት ተከፈተ እና የመርሐግብር መሪ የሆነው የአብማው የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊው የትእቢት ወንድም የሆነው “ዮናስ” ማይኩን ያዘ። ብዙ መምህራን አሉን “እግዚአብሔርን አመስግኑ” አለ አጨብጭቡ ማለት ነው፡፡ ስሟን ቀይራ የመጣች ቋንቋ መሆኗ ነው። ህዝቡም በእልልታ እና በጭብጨባ የጽሙና እና የአርምሞውን ጾም ዐቢይ ጾምን እንዲህ ሻረው። ከዚያም ለቀሲስ ማይኩን ሰጣቸው እና “ሃሌ ሃሌ ሉያ” የሚለውን የሊቀ መዘምራን ኪነ ጥበብን መዝሙር ዘምረው ከአ.አ ለመጡት መምህር ማይኩን ሰጧቸው። ከዚያም ዮሐንስ ወንጌልን ጠቅሰው ማስተማር ጀመሩ። አልፎ አልፎ ጭብጨባውና እልልታው ግን አሁንም አልቀረም እነደቀጠለ ነው እንጅ፡፡

እስካሁን አንድ ውስጤን ያሳረረው ነገር “ጭብጨባ እና እልልታው” ነው። ከበሮ እና ጸናጽል ይህን ዐቢይ ጾም በአርምሞና በጽሙና ሊጾሙ ከቅኔ ማኅሌቱ ከጠፉ ብዙ ቀን ሆኗቸዋል። አባቶቻችንም ይህ ጾም የአርምሞ የጽሙና የሐዘን የለቅሶ ሰለሆነ በመጋቢት ወር የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላትን ወደፊት እየወሰዱ በዚያ ቀን እንዲከበር አዘዙን። በዐቢይ ጾም እልልታ ሳቅ ጨዋታ ጭብጨባ የለምና። ለምሳሌ መጋቢት 5ን ጥቅምት 5 መጋቢት 27ን ጥቅምት 27 መጋቢት 29ን ታህሳስ 22 እንዲከበሩ አባቶቻችን አዝዘውናል። ለምን ቢባል በዐቢይ ጾም በደስታ በዓላትን በማክበር የጌታችንን ሕማም እንዳንዘነጋ ነው። እነ ዮናስ ግን እልል በሉ አጨብጭቡ እያሉ በግድ ያስጨበጭቡታል። አንዳንድ አላዋቂዎች ለምን ይጨበጨባል ይሉ ይሆናል እያሉ ሥርዓት ይከበር ያሉትንም ያሸማቅቃሉ።
 
በርግጥ በእነርሱም አይፈረድም እልል ካልተባለ ካልተጨበጨበ ህዝቡ የሰማቸው አይመስላቸውማ። በዚያውስ ላይ ዐቢይ ጾም ጾማችን እንጅ ጾማቸው ይመስል ምን ገዷቸው። የተሐድሶ መናፍቃን ግርፎች አይደሉም እንዴ? አረ ናቸው!!!

አሁን ለአቡኑ ማይክ ተሰጠ መምህሩ ያስተማሩትን ደግመው አንዳንድ ነገሮችን እያነሱ ህዝቡን ማሳቅ እና ማሳቀቅ ጀመሩ። ዛሬ የዘገየሁ ደጀን ሄጀ ነው አሉ። ደጀን የሄድኩም አጉል ባህልን ላስተምር ተጋብዠ ነው አሉ። አጉል ባህል ያለእድሜ ጋብቻ ነው ብለው ሴት ልጅ እድሜዋ ሳትደርስ ለምን እንድራታለን አሉ። ሴት ልጅ ስትደርስ ትታወቃለች አሉ ከዚያም ከዚህ በፊት ይመስሉት የነበረውን ድንች እና በቆሎ ወደ ጎን ተውትና አዲስ ምሳሌ መሰሉ፡፡ የዛሬው ምሳሌ ዳቦ ነው፡፡  ዳቦ እንዴት ይጋገራል ብለው ጠየቁ። አንዷን ነይ ብለው መድረክ ላይ አመጧት እና ተናገሪ ተባለች። ዳቦ ጋግሬ አላውቅም አለች። ማን የጋገረውን ልትበይ ነው። አሁን እኮ ይሄ ዘመናዊ ትምህርት አበላሸን ሽሮ እንዴት ይሰራል ብየ ብጠይቅ እኮ ውኃ አፍልቶ ሽንኩርት የሚከትፍ ሰው ይኖራል አሉ። ደግሞ ሌላኛይቱን ነይ አሏት፡፡ ወደ መድረክ መጣች ፍርሐት የወረራት ናት፡፡ ማይኩ ላይ አብዝታ ስትተነፍስ “እፍፍፍፍ” የሚል ድምጽ ያስተጋባል፡፡ መልሽ እንጅ ብለው አሁንም ጮኹባት፡፡ እርሷ ግን ፈርታለች “እፍፍፍፈ” አለች፡፡ “ዋን ቱ ስሪ በይ” አሏት፡፡ “ዋን ቱ ስሪ” አለች፡፡ በይበዚሁ ተናገሪ አሏት የሆነ ነገር ላለማሳፈር ተናግራ ወደ መቀመጫዋ ሮጠች፡፡ ደግሞ ሌላኛይቱን ነይ አሏት። መድረክ ላይ ወጣች እና የተወሰነ ነገር ተናግራ ስትሄድ "ኮሳሳ" አሏት። ሁሉም እኮ ኮሳሳ ነው አሉ። ከዚያም ዳቦ ሲጋገር ያለውን ሂደት ተናገሩ ለመጋገር ሲደርስ ማለት ሲቦካ ምልክት ያሳያል ሽታው አካባቢን ያውዳል አሉ ሴትም ስትደርስ እንዲያ ናት ማለት ነው። ከዚያም ስላገዱት ጸሎተ ምህላ መናገር ጀመሩ። በየአዳራሹ ጸሎት የለም ስግደት የለም። ያ የመናፍቃን ነው አሉ። እኔ ወደተቀመጥኩበት አካባቢ ሕጻናት ድምጽ አሰሙ፡፡ ድምጻቸውን ሲሰሙ የተቀመጠው ሰው ያጉረመረመባቸው ስለመሰላቸው  “ጀመራችሁ እንግዲህ አናንተ ትሆናላችሁ እንግዲህ በየአዳራሹ የምትሰግዱ” አሉ ፊታቸውን ወደ እኛ ሳይዞሩ፡፡ ሌላው መድረክ ላይ ያለው ሰው ግን ወደ እኛ ፊቱን አዞረ፡፡ ይህን ሲሰሙ አንዳንድ እህቶች እና ወንድሞች እየተነሡ ወደቤታቸው ሲሄዱ ተመለከቱ እና እንዲህ አሉ “እየውላችሁ ደህና ቆይታችሁ ነበር በተኑን ስጫነው መሮጥ ጀመራችሁ” አሉ፡፡
እኔ ይህን ስሰማ ውስጤ ተሰበረ። በእውነት መላእክት እንደ ሻሽ ተነጽፈው እንደ ግንድ ተረብርበው ሌሊት ከቀን የሚጠብቋትን ቤተክርስቲያን የመናፍቃን ናት ማለት ምን ማለት ይሆን? ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግበትን አዳራሽ የመናፍቃን ነው ማለት ምን ማለት ነው? በእውነት በዚያ አዳራሽ መስገድ የተጀመረው ዛሬ ነውን? እርስዎ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለ እኮ ነው ወይስ ደግሞ ዘንድሮ ነው ዓይንዎ የተገለጠ? በእውነት ይህን ያህል ዘመን መናፍቃን ሆነን ስንቆይ እንዴት ዝም ብለውን ቆዩ? በራስዎ ሀገረ ስብከት ስንት አዳራሾች ናቸው ለበዓላት ሥርዓተ ማኅሌት የሚደረስባቸው? እነ አቡነ ጴጥሮስ (ከአቡነ ማርቆስ በፊት የነበሩት ጳጳስ) ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን እና የመለኮት እና የትስብእት ነገር ከሚነገርበት አዳራሽ በጫማ መግባት አይቻልም ጫማችሁን አውልቃችሁ ግቡ ብለው ያስከበሩትን አዳራሽ እርስዎ የመናፍቅ ነው ሲሉ ምን ማለትዎ ይሆን? ሰውን እንዳይጸልይ እንዳይሰግድ ማድረግ የመንፈስ ቅዱስ ወይስ የሰይጣን ምክር ነው ብለው ይገምታሉ? ወይስ ደግሞ እስካሁን በመስገዳችሁ እና በመጸለያችሁ መናፍቃን ነበራችሁ አሁን ግን መለስኳችሁ ብለው ይህን ያህል መናፍቅ አጠመቅሁ ብለው ሊሸለሙበት ፈልገው ይሆን? አንድ ሰው ቤቱስ ውስጥ ቢሆን መስገድ መጸለይ አይችልምን ይችላል። ታዲያ እርስዎ የመናፍቅ ነው ያሉት ምኑን ነው?  ምናልባት የመናፍቃኑን ምህላ ስላልሰማነው ልዩነቱ ላይገባን ይችላል እርስዎ ግን የሚያውቁት ይመስላሉ እና ቢያብራሩት ደስ ይለናል። በእውነት በአብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ከሚሠሩት ቤቶች መካከል አንዱ ይህ የማናፍቅ ነው ያሉት አዳራሽ አይደለምን?

ከዚህ ስድብ በኋላ “የእኔን መዝሙር የሚዘምራት፤ አሁን በቅርቡ ካሴት አውጥቻለሁ ካሴቴን የሰማው የለም” ብለው ቀለዱ፡፡ አንድ ወጣት “ነአምን በአብ” ነው አላቸው፡፡ በል ና ዘምረው ብለው ወደ መድረክ ጠሩት። ማይኩን ሊቀበላቸው ሲል  የተሐድሶው ግርፍ ዮናስ መጥቶ “መሐረነ አብ ስለምንል ጊዜ ዳርሷል” አላቸውና ልጁን አሰናበቱት። ጠዋት ባገዱት ስግደት ምትክ የመጣ ጸሎተ ምህላ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ከዚያም የቅዳሴ መምህሩ መሐረነ አብን በዚያ በሚያምር ድምጻቸው በዜማ ማለት ጀመሩ። እኛም በእውነት እስካሁን ድረስ የነበረውን ስድብ ረስተን በዜማ መቀበል ጀመርን፡፡ ጥቂት እንደተደረሰ ዮናስ እየተመላለሰ ቶሎ ጨርሱ እየዘለላችሁ ሂዱ አላቸው ግራ ተጋብተው ሳይጨርሱት ጨረሱ። እኛም ተመልሰን ወደ ቀደመ ብስጭታችን እና ቁጭታችን ገባን፡፡ አስቡት እንግዲህ ዳቦ እንዴት ይጋገራል? እያሉ የቀለዱበት ጊዜ ለጸሎተ ምህላው አልሆን አለ። ጉባኤው ነገ መጋቢት 10ም ይቀጥላል። ውስጤ ስለተጎዳ እነሆ መጋቢት 9/2009ዓ.ም ከምሽቱ 4:10 ላይ ለጠፍኩት።

No comments:

Post a Comment