Wednesday, March 29, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፲፩


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 21/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

የጌታ ልደቶች
በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚሉ ወገኖች  “አብ ልጁ ወልድን ከድንግል ማርያም ማኅጸን በሥጋ ወለደው” ብለው እኛ ከምናምናቸው ልደቶች በተጨማሪ ይጠቅሳሉ። እዚህ ላይ ግን አንዳንድ ምሥጢር ያልገባቸው የቅብዓት እምነት ተከታዮች በጣም የሚገርም ነገር ይናገራሉ፡፡ “በተዋሕዶ ከበረ የምትሉ ሰዎች ገናን በ28 እና በ29 እያከበራችሁ ሦስት ልደት ታምናላችሁ” ይላሉ፡፡ እነዚህ በጣም የሚያስቁ ምሥጢር ያልጠነቀቁ ጨቅላ ቅባቶች ናቸው፡፡ ታህሳስ 28 እና 29 የልደት በዓል የሚከበርባቸው ቀናት ናቸው፡፡ እንደእነርሱ አስተሳሰብ ከሆነማ ጌታችን በየዓመቱ  ይወለዳል ማለት እኮ ነው፡፡ በዓል ማክበሪያ ቀንና እና የበዓሉ መከበሪያ ምክንያትንማ ጠንቅቀን ማዎቅ አለብን፡፡ ለምን ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ ታህሳስ 28 ቀን ልደትን ታከብራላችሁ የሚል ጥያቄ ከመጣ እሱን ሥርዓት ስለተሠራልን ዶግማ ስላልሆነ ነው ብለን  እንመልሳለን፡፡ ስቅለት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገት፣ ጰራቅሊጦስ፣ በየዓመቱ መቸ መቸ ነው የሚከበሩ ለምን ይቀያየራሉ ለምንስ በጥንተ ቀናቸው አይከበሩም ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ልደትማ ከዐራት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እኮ ነው ያውም በአንድ ቀን ልዩነት ብቻ፡፡  እነዚህ የጠቀስኩላችሁ በዓላት ግን በየዓመቱ ከጥንተ ቀናቸው እጅግ በራቀ ሁኔታ ነው የሚከበሩ ለምን ሥርዓት ቀኖና ስለሆነ ዶግማ መሠረተ እምነት ስላልሆነ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ምሥጢር የለውም፡፡

ወልደአብ የተሰኘው የክህደት መጽሐፋቸው ገጽ 216-217 ስናነብ እንዲህ ይላል። “የጌታችን ልደቱ ስንት ነው ቢሉ ኹለት ነው። እንዴት ኹለት ነው እምቅድመዓለም በመለኮቱ ተወለደ ብለናል ኋላም በማኅጸን በሰውነቱ ከአብ ተወለደ እንላለን ዳግም ከእመቤታችን በስጋ በጎል ተወለደ እንላለን ይህማ ሦስት አይደለምን እንደምን ኹለት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የተወለደው ልደትና ዛሬ በማኅጸን በሥጋ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ የተወለደው ልደት አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም። ኹለት ጊዜ ቆጥረነው አንድ ማለታችን እንዴት ነው ቢሉ እምቅድመዓለም በመለኮቱ የወለደው አብ ነው። ዛሬም በሰውነቱ በማኅጸን የወለደው አብ ነው እንጅ ሌላ አይደለም። ወላዲው ተወላዲው ዛሬም የተወለደበት መንፈስቅዱስ ያ የጥንት የባሕርይ ሕይወቱ ስለአልተለወጠ አንድ ልደት ይባላል እንጅ ኹለት ልደት አይባልም። ለዚህም ምሳሌ ያስረዳል ምሳሌ እንዴት ያስረዳል ቢሉ እነሆ ዛሬ ሰው አዲስ ሸማ ለብሶ ያነን በከረጢት ከቶ ዳግመኛ አውጥቶ ቢለብሰው አንዱን ሸማ ኹለት ጊዜ ለበሰው ተብሎ አንድ ሸማ ይባላል እንጅ ኹለት አይባልም። ዳግመኛ በአንድ ዘውድ ሁለት ሦስት ነገሥታት ቢነግሡበት ኹለት ሦስት ነገሥታት ነገሡበት ተብሎ አንድ ዘውድ ይባላል እንጅ ኹለት ዘውድ አይባልም” ይላል። እዚህ ጽሑፍ ላይ በዋናነት ሦስት መሠረታዊ ስህተቶችን እንመለከታለን፡፡
1.   በመጻሕፍት ተጽፎ የማናገኘው “አብ ወልድን በማኅጸነ ማርያም በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ወለደው” የሚል ስህተት አለበት፡፡
2.   መጻሕፍት “ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱም አባት አትሹለት” እያሉ እዚህ ላይ ግን “ለምድራዊ ልደቱ አባት ሽተውለታል” ስለዚህም ሁለተኛ ስህተት ብለን ቆጠርነው፡፡
3.   የተቀመጠው ምሳሌ “ሦስት ጊዜ የተቆጠረውን ልደት ሁለት” ብለን እንድንቀበለው የሚያደርግ ማስረጃ አለመሆኑ፡፡
በእነዚህ ቅደም ተከተሎች በማስረጃ እያስደገፍን የዚህን ስህተት እናጋልጣለን፡፡ “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” የምንል ክርስቲያኖች የምናምናቸው ልደታት ሁለት ናቸው፡፡ እነዚህም፡-
1.  ቅድመዓለም ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል ሳይቀድም ሳይከተል በዚህን ጊዜ ተወለደ በማይባል ረቂቅ ጥበብ ወልድ ከአብ ያለ እናት የተወለደው ቀዳማዊው ልደት ነው፡፡
2.  የአዳምን በደል ለማጥፋት ከሴት የሚወለድበት ዘመን በደረሰ ጊዜ በኅቱም ድንግልና በግብረ መንፈስ ቅዱስ በተዋሕዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለአባት የተወለደው ደኃራዊው ልደት ነው፡፡
ሊቃውንቱ “ቀዳማዊ ልደቱ በደኃራዊ ልደቱ ታወቀ” ይላሉ፡፡ ሁለቱም ልደታት ከሰው ኅሊና በላይ ከመመርመርም እጅግ የራቁ ናቸው፡፡ ማንም እነዚህን ልደታት መርምሮ አይደርስባቸውም በረቂቅ ምሥጢር የተከናወኑ ናቸውና፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን የምትቀበላቸው የምታምናቸው የምታስተምራቸው በመጻሕፍት የጻፈቻቸው የጌታ ልደቶች ቅድመ ዓለም ያለእናት ከአብ በመለኮት የተወለደው ልደት እና ድኅረ ዓለም ያለአባት ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በቅብዓት መናፍቃን ዘንድ “ወልድ በማኅጸነ ማርያም በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ተወልዷል” የሚለው ሦስተኛው ልደት በየትኛውም የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት ዘንድ ተመዝግቦ አናገኘውም፡፡ ለዚህም በርካታ ማስረጃዎችን እንጠቅሳለን፡፡ በእውነት “ወልድ ከአብ ሁለት ጊዜ ተወለደ” የሚል መጽሐፍ ከወዴት ይገኛል? የትም አይገኝም፡፡ ታዲያ ይህ “ሦስተኛው ልደት” ከየት መጣ ስንል አንድ የሚጠቅሱት ጥቅስ አለ እርሱም መጽሐፈ ምሥጢር ምእራፍ 3 ቁጥር 46 ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በዚህ መጽሐፉ ላይ የጻፈው እንዲህ የሚል ነው፡፡ “ነገርነኬ በእንተ ህላዌ መለኮቱ ወትስብእቱ እምድኅረ ስጋዌሁ ኢንቤሎ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወወልደ እጓለእመሕያው በትስብእቱ፤ ድንግልኒ ወለደት ዘኢዚአሃ መለኮተ በዘዚአሃ ሥጋ ምስለ ዘዚአሃ ሥጋዌ ፤ አብኒ ወለደ ዘኢዚአሁ ሥጋ በዘዚአሁ መለኮት ምስለ ዘዚአሁ ኃይል ዘህሉና አምላክ ፤ ስለመለኮቱ እና ስለ ትስብእት ህልውና እነሆ ተናገርን፡፡ ሰው ከመሆኑ በኋላ በመለኮቱ የእግዚአብሔር ልጅ በሰውነቱም የሰው ልጅ አንለውም፡፡ ድንግልም ለእርሷ በተገባ ሥጋዌ የእርሷ በሆነ ሥጋ የእርሷ ያልሆነውን መለኮት ወለደችው ፤ አብም የባሕርይው ያልሆነውን ሥጋ የባሕርዩ ከሆነ የህሉና አምላክ ኃይል ጋር የእርሱ በሆነ መለኮት ወለደ” የሚል ነው፡፡ ከዚህ ትምህርት መካከል ቅብዓቶች አብ በማኅጸነ ማርያም ወልዶታል ለሚለው ክህደታቸው ቆርጠው የወሰዱት “አብም የባሕርይው ያልሆነውን ሥጋ የባሕርዩ ከሆነ የህሉና አምላክ ኃይል ጋር የእርሱ በሆነ መለኮት ወለደ” የሚለውን ነው፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ መለኮታዊ አካል ሥጋዊ አካልን፤ ሥጋዊ አካልም መለኮታዊ አካልን፤ መለኮታዊ ባሕርይ  ሥጋዊ ባሕርይን፤ ሥጋዊ ባሕርይም መለኮታዊ ባሕርይን  ሊወልድ ይቻላልን? ሊቁ ይህን የተናገረው በእውነት እነርሱ እንደሚሉት ነውን? አይደለም፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የእውቀት ጽዋእን የጠጣ አባቶች ያላስተማሩትን እንግዳ ትምህርት ለመናገር ነውን? አይደለም፡፡ ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ም 60 ቁ 20 ላይ “ዛሬ ግን ከድንግል ብቻ ተወለደ ድንግልናዋንም ባለመለወጥ አጸና ድንቅ የሚሆን መጽነስዋ የታመነ ይሆን ዘንድ ቅድመዓለም ከአብ እንደተወለደም ለማመን መሪ ይሆን ዘንድ” የሚለውን ትምህርተ ሊቃውንት ዘንግቶት ይሆን ለምድራዊ ልደቱ አባት የሻለት? አይደለም፡፡ ሊቁስ ወደ ምሥጢር ሄዶ “አብም የባሕርይው ያልሆነውን ሥጋ የባሕርዩ ከሆነ የህሉና አምላክ ኃይል ጋር የእርሱ በሆነ መለኮት ወለደ” ብሎ ተናገረ፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብም ለቃል ገንዘቡ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ታዲያ ይህንን ካወቅን ቃል ከሥጋ ጋራ በተዋሐደ ጊዜ ሥጋ “ወልደ አብ ቃለ አብ” መባልን ገንዘቡ አደረገ ብንል እውነት ነገር ነው፡፡ ስለዚህም ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ሆነ ቀዳማዊ አምላክ በመሆኑም ወልደ አብ ተባለ በሥጋ ወለደውም ተባለ፡፡ ለወልድ አባቱ የሆነ አብ ለክርስቶስም (ለሥግው ቃል) አባቱ ተባለ ማለት እኮ ነው፡፡ ስለዚህ ሥጋ ወልደአብነትን (የአብ ልጅ መባልን) ገንዘቡ አደረገ አለ ሊቁ፡፡ ይህን ምሥጢር አርቀቆ የተናገረበት ግሩም ትምህርት እንደሆነ በዚህ እንረዳለን፡፡ አብ በማኅጸነ ማርያም ወልድን ዳግም ወልዶት ቢሆን ኖሮ በግልጽ በጎላ በተረዳ ነገር በተናገረልን ነበር፡፡ ነገር ግን ሊቁ ይህንን አልተናገረውም፡፡ የመጽሐፈ ምሥጢር 3÷46ን ትርጓሜ በሰፊው ማብራሪያ ለማየት ከፈለጉ ይህንን ሊንክ ተጭነው ያንብቡ፡፡ ወንድማችን ዲያቆን ሰሎሞን በብሎጉ ላይ በጥሩ ማብራሪያ አስቀምጦታል እና ይህንን መድገም አያስፈልግም በሚል ነው፡፡

እነርሱ በተረዱት አረዳድ ከሆነማ “እመቤታንም በመለኮት ወልዳዋለች ያሰኝባቸዋል” እኛ ግን አባቶቻችን እንዳስተማሩን “ወልደ አብ በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትስብእቱ” እንላለን፡፡ ይህም ማለት በመለኮቱ ከአብ ተወለደ በሰውነቱም ከድንግል ማርያም ተወለደ ማለት ነው፡፡ ድንቅነቱም እኮ ይህ ነው “መለኮትን በሰውነት መውለድ”፡፡ መለኮትን በመለኮት መውለድ፤ ሰውን በሰውነት መውለድማ ምን ይደንቃል? ይህ አያስደንቅም አያስገርምም ማለት አይደለም ነገር ግን በጣም የሚደንቀው በጣምም የሚገርመው “መለኮትን በሰውነት መውለድ” ነው ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ መለኮትን በሥጋ መውለድ ማለት “ስፉህ፣ ረቂቅ፣ ምሉዕ የሆነን መለኮት ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በጸባብ ማኅጸን ተሸክሞ ጊዜው ሲደርስ ድንግልናዋን ሳይጥስ ሳይለውጥ ከአምላክነቱ ሳይለወጥ ሰው በሚወለድበት ሥርዓት መውለድ ነው” ይህ ድንቅ ጥበብ ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ ሥጋ ከመለኮት ጋራ ሲዋሐድ በመጠባበቅ ነው፡፡ ተዋሕዶ ስንል ተዓቅቦ ያለበት ተዋሕዶ ማለታችን ነውና!!!
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment