Thursday, March 23, 2017

የቅብዓት ምንፍቅና ምንጭ---ክፍል ፯


© መልካሙ በየነ
መጋቢት 15/ 2009 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ

“ወልድ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለው አገላለጽ ሚጠትን፣ ውላጤን እና ትድምርትን የሚደግፍ ነውና “ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ” ከሚለው እምነታችን የተለየ ነው፡፡ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” በሚለው ኑፋቄ ውስጥ ወዳሉ ሦስት ነገሮች እንሂድ፡፡ “እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነው ወልድ ነው ማለት እንዴት ነው ቢሉ፡፡ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ተዋሕዶ እንዲፈጠር ወልድም ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋራ ተዋሕዶ ተፈጥሯልና፡፡ እንደ ዘርአ ብእሲ የሆነ ወልድ ነው ማለት ስለዚህ ነው” ወልደ አብ ገጽ 127፡፡ በዚህ ኑፋቄያቸው ውስጥ ወልድ ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ እንደተፈጠረ ይናገራሉ ሎቱ ስብሐት፡፡ ከዚህ ላይ በግልጽ እንደምንመለከተው አምላክ ከሥጋ ጋራ ተዋሕዶ በድንግል ማርያም ማኅጸን እንደተፈጠረ ነው፡፡ ይህም ማለት ወልድ ከአምላክነት ዝቅ ብሎ ፍጡር እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይህንንም በድፍረት በድጋሜ በሌላ ቦታ ላይ ጽፈውት እናገኛለን፡፡ “ወልድ በሰውነቱ ፍጡር ይባላል፡፡ ወልድንማ ፍጡር ብንለው እንደአርዮስ ክህደት አይሆንብንም ቢሉ አርዮስ በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት እንጅ በሰውነቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ባልሆነበትም ነበር፡፡ ነገር ግን በመለኮቱ ፍጡር ቢለው ክህደት ሆነበት” ወልደ አብ ገጽ 130-131 ይላሉ፡፡ የቀደሙ አባቶቻችን ይህንን የክህደት ትምህርት አውግዘውታል፡፡ ቃለ ግዘት ምእራፍ 120 ክፍል 3 ቁጥር 1 ላይ “እሱ ሰውን ፈጠረ ከዚህም በኋላ በእሱ በፍጡሩ እግዚአብሔር ቃል አደረበት የሚል ቢኖር ውጉዝ ይኹን” ይላል ሃይማኖተ አበው፡፡ እነርሱ የሚያምኑት ተዋሕዶ የኅድረት ተዋሕዶ ነው ማለታችን ስለዚህ ነው፡፡ የከዊን ተዋሕዶን አምነው ቢሆን ኖሮ የአካል እና የባሕርይ ተዋሕዶ ነውና ከተዋሕዶ በኋላ በሥጋና በመለኮት መለያየት፣ መከፋፈል የሌለበት ስለሆነ ከተዋሕዶ በኋላ በሥጋ ርስት በመለኮት ርስት በማለት መግለጽ እንዲያስነቅፍ ባወቁ ነበር፡፡ ነገር ግን እነርሱ የሚያምኑት ተዋሕዶ “የኅድረት ተዋሕዶ” ነውና በሰውነቱ እና በመለኮቱ እያሉ ከተዋሕዶ በኋላ ሲከፋፍሉት እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ቅብዓቶች እንደጻፉት እስካሁን ድረስ ወልድ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ አምላክነቱን እንዳጣ የሚመሰክሩ ማስረጃዎችን ተመለከትን፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች በዋናነት ውላጤን ይጠቁማሉ ምክንያቱም መለኮት ሰው ሆነ የሚለውን ወደ ሰውነት ተለወጠ ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉና፡፡ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ ማለት ወደ ፍጡርነት ተለወጠ ያሰኛልና ውላጤ መለወጥ ማለት ይህ ነው፡፡ ይህ ውላጤ እንደ ማየ ቃና እንደ ብእሲተ ሎጥ ያለ ነው፡፡
ሌላው “በመንፈስ ቅዱስ ቅብዓትነት ከበረ” የሚለው ክህደት ሚጠትን ያሳያል፡፡ ይህንንም ወልደ አብ ገጽ 219 ላይ እንዲህ ይገልጹልታል “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ፡፡ ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ይላል አሁን ወልድ ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ተዋሕዶ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ ማለታቸው ነው፡፡ “ይህ የጸጋ ልጅነት የሌለው ባእድ ሥጋ እምቅድመ ዓለም የባሕርይ ልጅነት ካለው መለኮት ጋራ ቢዋሐድ የቃልን ገንዘብ ተቀብሎ ወልደአብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ ልጅነት አገኘ” የሚለው አገላለጽ በጣም ጥሩ እና የሚደገፍ ነው፡፡ ምክንያቱም “ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆነ” ብለውታልና ትክክል ነው፡፡ አሁን ሥጋ ወልደ አብ ቃለ አብ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህን ካሉ በኋላ ወልደ አብ መባሉን በአንዴ ዘነጉትና “ይህ ልጅነት ያለው ቃል ልጅነት ከሌለው ሥጋ ጋራ ቢዋሐድ በሥጋ ርስት ልጅነትን የሚሻ ሆነ” ብለው ተቃራኒ ነገር አሰፈሩ፡፡ ምናልባት የጸሐፊ ስህተት እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ ይኸኛው ቀድሞ ያኛው ተከትሎ የሚጻፍ ሊሆን ይችላል፡፡ እነርሱን ሊደግፋቸው የሚችልም እንደዛ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ ወልድ ከአምላክነት ወደሰውነት እንደተለወጠ የሚገልጽ አስተምህሮ ነው፡፡ አሁን ወደቀደመ አምላክነቱ ለመመለስ በሥጋ ርስት ልጅነት የሚሻ ሆነ ብለዋል፡፡ ይህ በሥጋ ርስት ልጅነት የሚሻ ወልድ ልጅነትን ለማግኘት ቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ያስፈልገዋል የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ይህንንም እዚሁ ገጽ ላይ ሲገልጹ  “ወልድስ በሰውነቱ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ተቀብሎ ባይወለድ ወልድ በሰውነቱ እንደ አብ ባልገዛም አብም ለወልድ በሰውነቱ አገዛዙን ክብሩን በመላ በሰፋ ባልሰጠውም ነበር” ይላሉ፡፡ ስለዚህ ነው “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ማለት ሚጠትን ይደግፋል ማለታችን፡፡ አሁን እነርሱ እንደሚሉት በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ አምላክ እንደሆነ ወደ ቀደመ አምላክነቱ እንደተመለሰ ያስረዳሉ፡፡ ሚጠት ማለት መመለስ ማለት ነው እንደ እስራኤላውያን ያለ ነው፡፡
ሌላው “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ማለት ትድምርትን የሚደግፍ ነው፡፡ “ወልድ በባሕርይ ክብሩ ከበረ” የሚለውን ይነቅፋሉ ስለዚህ ነው “መንፈስ ቅዱስ አከበረው” የሚሉት፡፡ እንደ እነርሱ አባባል ሥጋን የባሕርይ አምላክ ያደረገው እና ያከበረው የቃል ከሥጋ ጋር መዋሐድ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ “በሥግው ቃል ላይ መጨመር ነው” ማለት ነው፡፡ “መጨመር ነው” ይላሉ ያልኩት  ዝም ብየ አይደለም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ካልተቀባ እንደ አብ እንደመንፈስ ቅዱስ  ባልገዛ ባላዘዘም ነበር ብለዋልና ነው፡፡ “ወልድ” እንደአብ እንደ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ለመሆን “መንፈስ ቅዱስን እንደገና ሕይወቱ ማድረግ አለበት” ይላሉና ነው ትድምርትን (መጨመርን) ይደግፋል ማለታችን፡፡ ትድምርት የሌለበት ተዋሕዶ ቢሆንማ ወልድ በቀደመው ክብሩ ሥጋን አከበረው ባሉን ነበር፡፡
ስለዚህ ነው እንግዲህ በቅብዓተ “መንፈስ ቅዱስ ከበረ” ማለት ኑፋቄ ነው ማለታችን፡፡ እዚህ ላይ የሥላሴን በህልውና መገናዘብ በፍጹም እንደማይቀበሉ እንረዳለን፡፡ በህልውና መገናዘብን ቢያምኑ ኖሮ መንፈስ ቅዱስ በወልድ ህልው ሆኖ ስለሚኖር ያ በወልድ ህልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ወልድ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ሥጋ የአብን ልብነት የመንፈስ ቅዱስን ሕይወትነት  ገንዘቡ አደረገ ወልድ ራሱ ሥጋን አከበረው ባሉ ነበር፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ከወልድ የተለየበት ቅጽበት እንኳ የለምና፡፡ አባቶቻችን ያስተማሩን እንደዚህ አነርሱ እንደሚሉት ያለ ትምህርትን አይደለም፡፡ ሳዊሮስ ም 87 ክ 9 ቁ 18 እንዲህ ይላል “…መንፈስ ቅዱስ ገንዘቡ ሆነ መባሉ ቃል ሰው ስለሆነ ነው ሰውማ ባይሆን ኖሮ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ህልው እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ በባሕርየ መለኮት ገንዘቡ ነውና እንደምን ገንዘቡ ሆነ ይባላል አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ  ህልው መሆኑን እንደተናገረ” ይላል፡፡ ስለዚህ ሳዊሮስ በግልጽ እንዳስቀመጠልን መንፈስ ቅዱስ በወልድ ህልው ሆኖ ይኖራል ያ ህልው ሆኖ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ወልድ ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ለሥጋ ገንዘቡ ሆነ ማለት ነው እንጅ ዳግመኛ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚል ትምህርት አላስተማረም እንዲያውም እዚሁ ክፍል ቁጥር 19 ላይ ሳዊሮስ እንዲህ ይላል “በዚህም ግብር ተዋሕዶ ጠፍቶ ከነቢያት እንደአንዱ አልሆነም መንፈስ ቅዱስ ያደረበት አይደለም” ይላል፡፡ ስለዚህ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለው ኑፋቄ በአባቶቻችንም የተወገዘ ትምህርት እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ በየትኛውም መጻሕፍት ላይ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚል ትምህርት ተጽፎ አናገኝም፡፡ እነርሱ የሚጠቃቅሷቸው መጻሕፍት አሉ እነዚያ መጻሕፍት ግን የቤተክርስቲያናችን እንዳልሆኑ ምናልባትም የአንድ ግለሰብ ፍልስፍናዎች እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ እነርሱ ግን መጽሐፍ ላይ የሌለውን ትምህርት ወልደ አብ ገጽ 182 ላይ “መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ሆነ ማለት ምሥጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ተሠጠ ማለት ነው፡፡ መሠጠቱ ወርቅ ተመዝኖ ከብት ተቆጥሮ እህል ተሰፍሮ እንዲሰጥ እንደዚያ ተሰጠ ማለት  ነውን ቢሉ እንዲህስ አይደለም፡፡ እንዴት ነው ቢሉ ጥንተ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ለወልድ በሰውነቱ የባሕርይ ሕይወት ሆነው ማለት ነው” ብለው የራሳቸውን የፍልስፍና ትምህርት ጽፈዋል፡፡ በእውነት ይህ ትምህርት የቤተክርስቲያናችን ቢሆን ኖሮ አንድ ሊቅ እንኳ እንዴት ሳይጽፈው ይቀር ነበር? ግን የእኛ ትምህርት አይደለምና አወገዙት እንጅ ትምህርቱን አላስተማሩትም፡፡ እንዲያውም ይህንን ትምህርት እንዲህ ሲሉ አውግዘውታል “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው፤ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል፤ በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል የሚለው፤ መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው፤ የአምላክነትንም ሥራ እርሱ ራሱ ይሠራል የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን” ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ 73÷49 ይላል፡፡ እዚህ ላይ እነዚህን 4 ነጥቦች ማንሣት እንችላለን፡፡
1.  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡
2.  ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል የሚለው ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡
3.   በሰውም የአምላክነትን ሥራ ይሠራል  የሚለው ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡
4.  መንፈስ ቅዱስ የባሕርዩ ነው  የማይል ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡ የሚሉ ናቸው፡፡
ተአምራት የሚላቸው እነማንን ነው ካሉ ደግሞ ሃይማኖተ አበው ዘቴዎዶጦስ ም 53 ቁ 4 ላይ እንዲህ እናነባለን፡፡ “በውኑ ቃል ሰው ይሆን ዘንድ ይቻላልን? ብለህ ለምን ትጠይቀኛለህ? የእግዚአብሔርን የተአምራቱን ነገር መርምር እንጅ አለ” ይላል፡፡ የቃል ሰው መሆን የሰው አምላክ መሆን ድንቅ ተአምር ነው፡፡ ቅብዓቶች የተወገዘ ይሁን ያለው እኮ ተአምራትን ሲያደርግ ማለትም ሙት ሲያነሣ፣ ሽባ ሲተረትር፣ ውኃውን ወይን ሲያደርግ፣ ርኩሳን አጋንንጥን ሲያወጣ መንፈስ ቅዱስ አደረበት የሚሉትን ሰዎች ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ በ2ኛው ነጥብ ላነሣነው እንጅ በመጀመሪያው ነጥብ ላነሣነው ማስረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእርሱ አጋዥነት ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ከበረ የሚለው ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡ ማለት ምን ማለት ነው? ሽባ መተርተር እውር ማብራት ለምጻሙን ማንጻት ነውን አይደለም፡፡ ይህ ሰው ስለመሆኑ ሥጋን ስለመዋሐዱ በድንግልና ስለመወለዱ ወዘተ የሚነገር ድንቅ ተአምር ነው፡፡ ሽባ ስለመተርተር ሙት ስለማንሣት ወዘተ ሁለተኛው ነጥብ ላይ የሚገኘው ግዘት ነው የሚገልጸው ፡፡ ርኩሳን አጋንንትን በማውጣት ጊዜም ኃይልን ተአምራትን ከመንፈስ ቅዱስ ይቀበላል የሚለው ቢኖር ውጉዝ ይሁን፡፡ ተአምር ማለት እኮ ሙት ማንሣት ሽባ መተርተር ብቻ አይደለም፡፡ አምላክ ሰው መሆኑ በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና መወለዱን ሥጋን የባሕርይ አምላክ ማድረጉን ሁሉ ነው ተአምር የሚለው፡፡ ለዚህም ነው ቴዎዶጦስ ከላይ የጻፍኩላችሁን ቃል የጻፈልን፡፡

ስለዚህ ይህ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለው ትምህርት በአባቶቻችን የተወገዘ የተለየ ነው፡፡ በቅብዓት መክበር ለቅዱሳን የተሰጣቸው የጸጋ ክብር ነው፡፡ ሊቁ በመልክአ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ላይ “ለመልክእከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ደም ግባቱ ለሚያንጸባርቀው ሥነ መልክእህ ሰላም እላለሁ፡፡ ቅብዐ መንፈስ ቅዱስን ተቀብቷልና” ይላል፡፡ ይህን ቅብዐ መንፈስ ቅዱስ መቀባት አምላክ የሚያደርግ ከሆነማ ገብረ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ናቸው ማለት ይሆንብናል፡፡ “በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ” የሚለውን ኑፋቄ ለማሳየት  ይህንን ያህል ከተመለከትን ወደ ቀጣዩ ርእስ እንግባ፡፡
ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment