ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው ይኖሩ ዘንድ የተፈጠሩ ፍጥረታት የፈጠራቸውን ፈጣሪ በገለጠላቸው መጠን በሰጣቸው ልዩ ልዩ ቋንቋና ጸጋ ያመሰግናሉ፡፡ እነዚህ ፍጡራን የሰው ልጅና መላእክት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ፈጣሪውን ማመስገን የሚችልበት ቋንቋ የተሰጠው ከመሆኑም በላይ የምስጋና ጊዜያትንም የሚያውቅበት አእምሮ የተሰጠው የከበረ ፍጡር ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ መዝ118፥164 ላይ “በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ” ባለው መሠረት ክርስቲያን የተባልን ሁላችን በቀን ሰባት ጊዜ ልናመሰግን ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ የምስጋና ጊዜያት 12 እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ፣ 12 በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ፣ 12 ኦ አምላክ፣ 12 ኦ ክርስቶስ፣ 12 ኪርያላይሶን፣ 12 ኤሎሄ፣ 12 ያድኅነነ እመዓቱ ወይሰውረነ በምሕረቱ በእንተ ማርያም ወላዲቱ፣ 12 በከመ ምሕረትከ አምላክነ ወአኮ በከመ አበሳነ፣ 12 ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ፣ 12 ስምዐነ አምላክነ ወመድኃኒነ ን ማድረስና ከሰንበትና ከታላላቅ በዓላት እንዲሁም ሥጋና ደሙን ከተቀበልንባቸው ቀናት ውጭ ሰባት ሰባት ጊዜ ልንሰግድ ያስፈልጋል፡፡ ሰባቱ የምስጋና ጊዜያት የራሳቸው የሆነ ሐተታ አላቸው ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡
v ጸሎተ ነግህ ፡-ከፀሐይ መውጣት አስቀድሞ እጅንና ፊትን ታጥቦ ከምንሠራው ሥራ ሁሉ በፊት የሚቀርብ ነው፡፡ ጨለማን አስወግዶ ብርሃን ስላበራልን፣ ቀኑን እንዲባርክልን፣ አዳም የተፈጠረበት ስለሆነ፣ ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት ለፍርድ የቆመበት ስለሆነ፣ ጠባቂ መላእክት ለተልዕኮ የሚገናኙበት ወዘተ… ስለሆነ የነግህ ጸሎት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ሊደረግ ይገባዋል፡፡መዝ5፥3፣ መዝ62፥1
v ጸሎተ ሠለስት ፡-ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት የሚጸለይ ነው፡፡ ሔዋን የተፈጠረችበት፣ እመቤታን የመልአኩን ብሥራት የሰማችበት ፣ ክርስቶስ ስለእኛ በጲላጦስ ፊት የተገረፈበት፣ ዳንኤል በመስኮት የጸለየበት፣ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበት ሰዓት ስለሆነ ወዘተ… ይህን እያሰብን እንጸልያለን፡፡
v ጸሎተ ቀትር ፡-ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ የሚደረግ ነው፡፡ የሰው ኃይል የሚደክምበት የአጋንንት ኃይል የሚበረታበት በመሆኑ፣ ሰይጣን አዳምን ያሳተበት፣ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት፣ ሄኖክ ገነትን ያጠነበት ወዘተ… በመሆኑ ይህን እያሰብን እንጸልያለን፡፡
v ጸሎተ ተሰዓት ፡-ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ክርስቶስ ነፍስና ሥጋውን የለየበት፣ መላእክት የሰውን ሥራ ወደ ፈጣሪ የሚያሳርጉበት፣ መቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ በጸሎቱ ምላሽ ያገኘበት ወዘተ… በመሆኑ ይህን እያሰብን እንጸልያለን፡፡
v ጸሎተ ሰርክ ፡-ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ የሚደረግ ነው፡፡ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ነፃ ያወጣበት ነው፡፡ በኦሪት መስሥዋዕት ይቀርብበት ነበር፡፡ ዘጸ9፥39-41፣ 1ኛነገ18፥29፣ መዝ140፥2 እንደ ነግህ ጸሎት ሁሉ ይህም በቤተ ክርስቲያን መደረግ አለበት፡፡
v ጸሎተ ንዋም ፡-የቀኑን የድካም ሥራ አስፈጽሞ የዕረፍት ሰዓት ስላመጣልን ለማመስገን፣ ሌሊቱ የሰላምና የዕረፍት እንዲሆንልን ለመለመን፣ እንቅልፍ የሞት ምሳሌ ነውና ፈጣሪ እንዲጠብቀን አደራ ለመስጠት፣ ጌታችን ለሐዋርያት የጸሎት ሥርዓት ያስተማረበት፣ በአይሁድ ጭፍሮች የተያዘበት ወዘተ… በመሆኑ ይህን እያሰብን እንጸልያለን፡፡
v መንፈቀ ሌሊት ፡- መዝ118፥62 እኩለ ሌሊት ማለትም ከሌሊቱ በስድስት ሰዓት የሚደረግ ነው፡፡ ጌታችን የተወለደበት፣ የተነሣበት፣ ዳግም የሚመጣበት የፍጻሜ ዘመን ማሰቢያ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እና ሲላስ በእስር ቤት ሳሉ የጸለዩበት /የሐዋ16፥25 / ወዘተ… በመሆኑ ይህን እያሰብን እንጸልያለን፡፡
ከላይ ለማየት እንደተሞከረው የሰው ልጅ በግልም ይሁን በማኅበር በሰባቱ ጊዜያት ለምን እንደሚያመሰግን በመጠኑ መረዳት ችለናል፡፡ ነገር ግን አሁን በብዙዎች ዘንድ የምናየው ነገር የሰው ልጅ የራሱ ቀመር በማውጣት የምስጋና ጊዜያትን ራሱ ሲወስን ነው፡፡ ለምስጋና የሚቆመውም የከፋ ችግር ሲገጥመው ወይም ከከፋ ችግር ስላወጣው ብቻ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው ችግር የሚሆነው ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ችግሩ ሲፈታለት ያንን መርሳቱ ጋር ነው፡፡ በሉቃ17፥17 እንደተጻፈ አሥር ለምጻሞች ኢየሱስ ክርስቶስን ተገናኙት፡፡ እነርሱም ኢየሱስ ሆይ ማረን ይሉ ነበር፡፡ እርሱም ራሳችሁን ለካህን አሳዩ አላቸው፡፡ ሲሄዱም ከለምጻቸው ነጹ፡፡ ከነጹትም መካከል አንዱ ብቻ ስላደረገለት ውለታ ሊያመሰግን ተመለሰ ዘጠኙ ግን ያዳናቸውን ዘንግተው በየግል ሥራቸው ሄዱ፡፡ አያችሁ ትልቁን ችግር፡፡ የእኛንም ጉዳይ ተመልከቱት፡፡ በዚህ ጊዜ ያልተመሰገነ መቼ ሊመሰገን ነው እንዳትሉኝ እንጅ መኪና ተገልብጦ ሌሎች ሞተው እርሱ ስለተረፈ፣ ጥይት ተተኩሶበት ወይሙ ቦንብ ተጥሎበት ከዚያ ስለተረፈ ፈጣሪውን ያመሰግናል፡፡ በዚህ ምስጋናው እስከ ሞቱ ከጸና ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሰው በዓይኑ ስላየ ብቻ ነው ምስጋና የሚያበዛው፡፡ ይህ ሰው መኪና ባይገለበጥ፣ ጥይት ባይተኮስ፣ ቦንብ ባይጣል ለምስጋና ይቆም ነበርን? ታዲያ እግዚአብሔርን እንድናመሰግነው የግድ መኪና መገልበጥ፣ ጥይት መተኮስ፣ ቦንብ መጣል አለበት እንዴ? ከጉዳቱ ነጻ ብንወጣ ፍርሐትና መንቀጥቀጥ መቼ ይቀርልናል፡፡ መኪና ተገልብጦ ሳይጎዱ ከመውጣት የሚበልጠው መኪና ሳይገለበጥብን ከፈለገነው ቦታ በሰላም ስንደርስ አይደለም እንዴ? ጥይት ተተኩሶብን ቦንብ ተጥሎብን ከመትረፍ ይልቅ ጥይት ሳይተኮስብን ቦንብ ሳይጣልብን መቅረቱ አይበልጥም? እኛ ሳናይ እግዚአብሔር በቸርነቱ የመለሰልን መቅሰፍት ተቆጥሮ የማያልቅ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አደጋዎች የሰዎችን ሞት እንሰማለን ነገር ግን ከዚያ አደጋ ከጊዜው ጊዜ ከቦታው ቦታ አገጣጥሞ ከሞት የጠበቀን እግዚአብሔር ያልተመሰገነ ማን ይመስገን ወገኖቼ? በዚያ ጊዜና ቦታ ተገኝተን ቢሆን የችግሩ ተጋሪዎች መሆናችን ይቀርልን ይመስላችኋል? እኛ ግን ልምድ ሆኖብን እግዚአብሔርን የምናመሰግን ከአደጋ ነጻ ስለወጣን ብቻ ነው፡፡ ጆሯችንም መስማት የሚፈልገው ብዙ ሰዎች ያለቁበትን አደጋ ነው፡፡ የሚገርመው “መኪና ተገልብጦ አንድ ሰው ሞተ” የሚል ዜና ቢነገር ከዜና ቆጥሮ ጆሮ ሰጥቶ የሚሰማው አለመኖሩ ነው፡፡ ክርስቶስ የጠፋውን አንዱን አዳም ሊፈልግ እንደመጣ ማስተዋል አለብን፡፡ የሰው ልጅ ጉዳቱ በራሱ ላይ ካልደረሰ በቀር አያዝንም፡፡ አንድ ሰውስ ቢሆን ለምን ይሞታል? በዚያ አደጋስ ከስንት ሰዎች መካከል የሞት ዕጣ ለዚያ ሰው ብቻ መውጣቱ አያሳዝንም? በዚያ ሰው ቦታ እኛ ብንሆን ኖሮስ? እግዚአብሔርን የምናመሰግን እኔ ብሆን ኖሮስ ማለት ከቻልን ነው፡፡ በጠዋት ተነሥተን ቤተክርስቲያን ሄደን ውዳሴ ማርያም ደግመን በሰላም እንዲጠብቀን ብንለምነው የሚፈጀው ጊዜ በደቂቃዎች የሚቆጠር ነው ነገር ግን በዓመታት የሚቆጠር ጊዜን ይለግሰናል፡፡ በምስጋና ወቅት ክብር የሚያገኘው አመስጋኙ እንጅ ተመስጋኙ አይደለም፡፡ ተመስጋኙ ፈጣሪማ እከብር አይል ክቡር፣ እነግሥ አይል ንጉሥ፣ እበለጽግ አይል ባዕለጸጋ፣ እጸድቅ አይል ጻድቅ፣ እቀደስ አይል ቅዱስ ነው፡፡ በቸርነቱ ከማናየው አደጋ ሁሉ ጠብቆ ጊዜያትን ስለሰጠን ካላመሰገንን ሰው መሆናችን ያጠራጥራል፡፡ ሁልጊዜ መኪና ተገልብጦብን፣ ጥይት ተተኩሶብን፣ ቦንብ ተጥሎብን ለምስጋና የምንነቃ ከሆነ ፈጣሪን መፈታተን ነው፡፡ ይልቅስ መኪና ስላልተገለበጠብን፣ ጥይት ስላልተተኮሰብን፣ ቦንብ ስላልተጣለብን ፈጣሪን ልናመሰግን ይገባል፡፡ በዓይናቸን ካየነው አደጋ ይልቅ ሳናይ ስላተረፈን ተመስገን ልንለው ያስፈልጋል፡፡ ትልቁ ውለታ ይህ ነውና፡፡ መኪና ከተገለበጠ በኋላማ ሰውስ፣ የመድኅን ድርጅቶችስ፣ ህክምና መስጫ ቦታዎችስ ይተባበሩ የለም እንዴ እንኳን እግዚአብሔር? መኪና እንዳይገለበጥ ማድረግ የሚችል ሰው፣ የመድኅን ድርጅት፣ ህክምና መስጫ ቦታ አለ እንዴ? እግዚአብሔር ይጠብቅ እንጅ፡፡ ስለዚህ አምላካችንን ስላሳየን ብቻ ሳይሆን ስላላሳየን ተመስገን ልንለው ያስፈልጋል፡፡ በሰላም ጠብቆ ያኖረንን ሁል ጊዜ ካላመሰገንን ማንን ልናመሰግን ነው?
No comments:
Post a Comment