enatie ethiopia |
እኔ እና ድቃቅ አፈር አብረን እንጫወታለን፡፡ “አፈር ከምንም አትቆጠሪም እኮ” አልኳት፡፡ ቀና አለችና “ምነው ጋሼ እኔ ለእይታ ታናሽ ብሆንም እኮ ብዙ ሥራዎችን እሰራለሁ አይናቁኝ እንጅ ጋሽዬ” አለችኝ፡፡ እንኳን አፈርን ቀርቶ ሰው እውቀት ከሌለው አልያም ገንዘብ ከጎደለው ከምንም አልቆጥረወምና ናቅ አደረግኋት፡፡ ሳቅ አልኩና “አንች ደግሞ ምን ሥራ ነው የምትሰሪው? ሥራውን ለእኛ ለሰዎች ለትልልቆቹ ተይው” አልኳት፡፡ እርሷም እንደመሳቅ አለችና “ጋሽዬ ኧረ ይተው! እኔም እኮ ብዙ ሥራዎችን እንደ አቅሜ እሠራለሁ፡፡ ትልቆች እኮ ትልቅ የሚባሉት እኛ ድቃቆች ስለኖርንላቸው ነው፡፡ ሰደበችኝ እንዳይሉኝ እንጅ የእኔ መኖር እኮ ለእርስዎም ትልቅ ዋስትና አለው፡፡ እስኪ አሰብ ያድርጉት ጋሼ! ባለፈው ቤት ሲሰሩ እኔን አይደል እንዴ የቀዳዳ መድፈኛ ያደረጉኝ፡፡ ትልቆች እኮ እኛ ትንንሾች የምንውልላቸውን ውለታ ከምንም ስለማይቆጥሩት ነው ዞረው የማያዩን፡፡ ትልቆች ለመኖራቸው እኛም ትንሾች ትልቅ አስተዋጽኦ አለን፡፡ ጋሼ ዛሬ እኔን ቢንቁኝም እንኳ ጊዜው ሲደርስ እኩል እንሆን ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል ታሪክ ሲለወጥ ነገር ሲገለበጥ እርስዎም እንደእኔ ይሆናሉ መቼም እኔስ እንደእርስዎ መሆን አይቻለኝ ይሆናል” አለች፡፡ በጣም ከመጠን ያለፈ ሳቅ እየሳቅሁ “ምን አልሽ አንች ደቃቃ? ምን ያህል እየተደፋፈርሽኝ እንደሆነ ይገባሻል ግን?” አልኳት፡፡ “ጋሽዬ ኧረ ድፍረት አይደለም፡፡ እኔ ታናሽ እንደሆንኩ አውቃለሁ እርስዎም ትልቅ እንደሆኑ እረዳለሁ፡፡ እኔ ማለት የፈለግሁት ነገ እርስዎ ምን እንደሚገጥምዎ አያውቁትምና እንደእኔ ሊሆኑ ስለሚችሉ በታናሽነቴ አይናቁኝ እርስዎም በታላቅነትዎ አይመኩ ለማለት ነው፡፡ ትልቆቹ ትልቅ የሚሆኑት እንደእኔ ዓይነት ድቃቆች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ የእኔ መኖር ለእርስዎ ክብር እንጅ ውርደት አይደለም ምክንያቱም ትልቅ የተባሉ እኔ ትንሽ ተብዬ ነዋ!” አለች፡፡ “እባክሽ አንች ደቃቃ ማንነትሽን እወቂ” አልኳት ቆጣ ባለ አነጋገር፡፡ ድቃቋ አፈርም “ጋሼ እኔ እኮ ማንነቴን አውቃለሁ፡፡ በጣም ትንሽ ተራ ከሚባሉት ተርታ ነኝ፡፡ ነገር ግን ድሮ እኔም እንደ እርስዎ ትልቅ ነበርሁ ዛሬ ጊዜ ሲለወጥ እኔም ተለወጥሁ፡፡ ኦ አዳም መሬት አንተ ወትገብእ ውስተ መሬት የሚለውን አልሰሙም እንዴ? አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ የሚለው አምላካዊ ቃል እኔን ዛሬ ትንሽ አድርጎኝ እንጅ እንደ እርስዎ የከበርኩ ነበርሁ” አለች፡፡ “ኧረ እባክሽ አንች ደቃቃ! ብለሽ ብለሽ ደግሞ ከእኔ ጋር እኩል ማውራትሽ አንሶሽ መካሪየ ልትሆኝ ደፈርሽ?” አልኳት፡፡ እርሷም “ጋሼ የሚሰሙ መስለውኝ እኮ ነው፡፡ እኔ ትንሽ ብባልም ትልቆቹን ሳይቀሩ አስለቅሳለሁ እኮ፡፡ ይህን ያህልማ አይናቁኝ፡፡ ራሴን ዝቅ ማድረጌ ምንም ስራ እንደማልሰራ አስቆጠረኝ መሰል አሁንስ” አለች፡፡ “ምን ማለትሽ ነው አንች ነሽ እንዴ እኔን የምታስለቅሽ ካ ካ ካ ካ” በጣም ሳቅሁባት፡፡ ድቃቋ አፈር በጣም ተበሳጨች “ጋሼ እኔ የማስለቅሰው ንስሃ እንደሚገባ ሰው አይምሰልዎ፡፡ እንደ አዞ ለቅሶም አይደለም፡፡ ሰው ንስሃ ሲገባ የሚያለቅሰው ኃጢአቱን እያሰበ ከአምላኩ መራቁን እያስታወሰና ወደ ቀደመ መልካም ሥራውም አምላኩ እንዲመልሰው ነው፡፡ ጴጥሮስ እንባውን ያፈሰሰ አምላኩን ሦስት ጊዜ ስለካደ ነበር፡፡ አምላክም እንባውን ተቀብሎ የሐዋርያት አለቃ አደረገው፡፡ አዞ ግን የምታነባው ስትበላ ነው፡፡ የሚበላ ያገኘ ሰው ይደሰታል ፈጣሪውን ያመሰግናል እንጄ ያለቅሳል እንዴ? እኔ ግን ሰውን የማስለቅሰው በትልቅነቱ ሲመካብኝ ማንነቱን እንዲረዳ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ትንሽ የሚባሉትም የራሳቸው ዋጋ እንዳላቸው ለማሳየትና ለማስረዳት ያህል ነው፡፡ ሽንኩርት ከእኔ ብትበልጥም ከእርስዎ አንጻር ግን በጣም ትንሽ ናት ነገር ግን ምን ያህል እንደምታስለቅሳችሁ አውቃለሁ፡፡ እኔም እንደእርሷ አስለቅሳለሁ” አለችኝ፡፡ እኔም “አፈር ነሽ እኮ ያውም ደቃቃ በምን አቅምሽ ነው ይህን ያህል ሥራ የምታደርጊው፡፡ ለመሆኑ ምን ያህል ጉልበት ቢኖርሽ ነው እኔን መሰሎችን የምታስለቅሻቸው?” አልኳት፡፡ “ጋሼ እኔ በጉልበቴ አልመካም፡፡ ዛሬ እዚህ በአጋጣሚ ተገናኘን እንጂ ቦታየ አንድ ቦታ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከቦታ ቦታ የምዞረው ግን ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእንደእኛ አይነት ትናንሾች ቦታ የሚሰጠን የለማ!” አለችኝ፡፡ በጣም ገረመችኝና “አንዴ አስለቅሳለሁ አንዴ ከቦታ ቦታ ያንከራትቱኛል ትያለሽ ምን መቀባጠር ነው?” አልኳት፡፡ “ጋሼ ያንንማ ነገርኩዎት እኮ እኛን ከጉዳይ የሚለን የለም፡፡ ለዚህም ነው የመጣው ሁሉ ከቦታ ቦታ የሚያንከራትተኝ፡፡ እናንተን መሰል ትልቆች ሲፈልጉ በልብሳቸው፣ ሲፈልጉም በጫማቸው ከዚያዚያ ያመላልሱኛል እንጅ ወድጄ መሰልዎት? ይልቅስ አሁንም ሊወስደኝ የመጣ ኃይል አለ በቃ ደህና ይሁኑ” አለችኝ፡፡ ወዲያውም የሚስገመገም ድምጽ መጣ፡፡ ዛፎች ከዚያዚያ ይንገላታሉ ወረቀት ላስቲኩ ወደ ሰማይ እየወጣ ይሽከረከራል፡፡ ያ ኃይል ወደ እኔም ተጠጋና ስራወራኝ የነበረችውን ደቃቃ አፈር ዓይኔ ውስ አሸጋት፡፡ እጅግ አለቀስኩ እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ ሸሚዜን እያጠፍኩ አፈሯን ለማውጣት ብሞክርም ዓይኔን ከመጉዳት ውጭ ምንም ማድረግ አልቻልሁም፡፡ አፈሯም ዓይኔ ውስጥ እየተሸከረከረች “ጋሼ አሁን ገባዎት?” አለችኝ አብዝታ እየሳቀች፡፡ እንባዬን እየጠረግሁ “እባክሽ ውጭልኝ በጣም ተረድቼሻለሁ፡፡ እባክሽን ተባበሪኝ” አልኳት በልማና ቃል፡፡ አብዝታ ሳቀችና “እኔን መሰል ለሰው ዓይን የማንሞላ ትናንሽ ነገሮች ሁሉ የራሳችን ሥራ አለን፡፡ አሁን ገባዎት?” አለችኝ ደግማ፡፡ “እባክሽን ተለመኝኝ ሁሉም ገብቶኛል” አልኳት፡፡ እርሷም “ጋሼ እንኳን ገባዎት እንጅ እሄድልዎታለሁ” አለችና ወደ ዓይኔ ዳር መጣች፡፡ እኔም በሸሚዜ ኮሌታ አውጥቼ ጣልኳት፡፡ በትንሽነቷ ስንቃት እኔን ትልቁን ስለአስለቀሰችኝ ማንነቴን እንድረዳ ትልቅ ትምህርት ሆነችኝ፡፡
No comments:
Post a Comment