Sunday, August 24, 2014

ቁልፉ የት ነው?

“በሔዋን ምክንያት የተዘጋ የገነት ደጅ በድንግል ማርያም ተከፈተልን፡፡” ውዳሴ ዘሐሙስ በሔዋን ምክንያት ለ5500 ዘመን ያህል ተዘግታ የነበረችው ገነት በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ቤዛነት በፈሰሰ ደሙ ተከፍታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህች ገነት ክፍት ብትሆንም መግባት የሚችሉት ጻድቃን እንጅ ኃጥአን አይደሉም፡፡ ኃጢአት ገነት ስለማያስገባ ለኃጥአን አሁንም ቢሆን ዝግ ናት፡፡ ታዲያ በኃጢአታችን የተዘጋችብንን ገነት እንዴት ልንከፍታት እንችላለን? መክፈቻ ቁልፉ የት ይገኛል? የሚሉትን ለማየት እንሞክር፡፡ በክርስቶስ ደም መፍሰስ ነጻነት የታወጀልን ክርስቲያኖች በኃጢአታችን ዳግም በባርነት ቀንበር ውስጥ የተያዝን ከሆነ ገነት ተዘግታብናለችና መክፈቻ ቁልፍ ያስፈልጋል፡፡ መክፈቻ ሳንይዝ ምድራዊ ቤታችንን እንኳ መክፈት አይቻልም፡፡ የምድራዊ ቤታችንንስ ቁልፉን ሰብረን ልንገባ አልያም መክፈቻ ቁልፉን ተመልሰን ልንፈልግ እንችል ይሆናል፤ የሰማያዊ ቤታችን ግን እንዲህ አድርገን ልንከፍት ወይም ተመልሰን ቁልፉን ልንፈልግ ጥቂት እንኳ ሥልጣን የለንም፡፡ ከሞት በፊት የሰማይ ቤት መክፈቻ ቁልፎችን መፈለግ ብልህነት ነው፡፡ እነዚህ መክፈቻ ቁልፎችን በካህናት እጅ ሁል ጊዜ እናያቸዋለን ነገር ግን እንዲሠጡን ጠይቀናቸው አናውቅ  ይሆናል፡፡ ታዲያ ቁልፉን ሳንይዝ ወዴት ልንገባ ነው? እስከ ሞት ድረስ ንስሓ አባት ሳንይዝ በኃጢአት ላይ ኃጢአት በበደል ላይ በደል ስንሠራ የምንገኝ፡፡ ወደድንም ጠላንም የገነት መክፈቻ ቁልፍ ማግኘት የምንችለው በንስሓ የምንመለስ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ኑሯችን በምክረ ካህን የተመሠረተ ከሆነ ገነት የተቆለፈችባቸውን ቁልፎች ሰብረን ሳይሆን ከፍተን የምገባባቸውን መክፈቻዎች ተረክበን ለመሄድ ሥልጣን ይሰጠናል፡፡ ገነት የተዘጋችባቸው ታላላቅ ቁልፎች ሁለት ሲሆኑ እነዚህም አሥር እና ስድስት መክፈቻዎች ያሏቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ገነትን ከፍቶ ለመግባት በጠቅላላ አሥራ ስድስት መክፈቻዎችን ከአባቶቻችን መረከባችንን ማረጋገጥ ግዴታችን ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ቁልፎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ቁልፍ 1፡- ፲ቱ ትዕዛዛተ ኦሪት
ይህ የገነት ቁልፍ የሚከፈተው የሚከተሉትን አሥር መክፈቻዎች መያዝ ስንችል ብቻ ነው፡፡
፩. እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፡፡ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፡፡
፪. የአምላክህን ሥም በከንቱ አትጥራ፡፡
፫. የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፡፡
፬. አባትህንና እናትህን አክብር፡፡
፭. አትግደል፡፡
፮. አታመንዝር፡፡
፯. አትስረቅ፡፡
፰. በሐሰት አትመስክር፡፡
፱. ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፡፡
፲. የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፡፡
በእነዚህ አሥር መክፈቻዎች  የመጀመሪያውን ቁልፍ ስንከፍት ስድስት መክፈቻ ያለውን ሁለተኛ ቁልፍ ተቆልፎ እናገኛዋለን፡፡
ቁልፍ 2፡- ፮ቱ ሕግጋተ ወንጌል
ይህን ቁልፍ ለመክፈት ስድስት መክፈቻዎችን መያዝ ይኖርብናል፡፡ እነዚህም፡-
  . በወንድምህ ላይ በከንቱ አትቆጣ፡፡
  . ወደ ሴት አትመልት በልብህም አታመዝር፡፡
  . ሚስትህን ያለ ዝሙት ምክንያት በሌላ ነውር አትፍታ፡፡
  . ፈጽመህ አትማል፡፡
  . ክፉን በክፉ አትመልስ፡፡
  . ጠላትህን ውደድ፡፡
ይህን ሁለተኛ ቁልፍ መክፈት ከቻልን ጻድቃን የሚኖሩባትን ገነት መግባት የምችልበት ፈቃድ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ አሥራ ስድስት መክፈቻዎች መካከል አንዲቷ እንኳ ብትጠፋን የገነት መግቢያ ፈቃድ ስለማናገኝ የጠፋብንን ቁልፍ በቀጥታ ወደ ካህናት በመሄድ ንስሓ በመግባት መረከብ የምንችልበት መብት ስላለን ተረክበን ጉዟችንን መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ቁልፎች ደግሞ በትክክል መክፈት እንዲችሉ ለማድረግ ተርቤ አብልታችሁኛል? ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል? እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል? ታርዤ አልብሳችሁኛል? ታምሜ ጠይቃችሁኛል? ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋል? የሚሉትን ጥያቄዎች አሁን እየመለስናቸው መሆኑን ቆም ብለን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ጉዞው ሩቅ ስለሆነ ለመመለስ የሚቻል ባለመሆኑ ከመጓዛችን በፊት የመክፈቻ ቁልፎችን መዘንጋት የለብንም፡፡ ካህናት አባቶቻችን ያላቸው ሥልጣን ቀላል የሚመስለው ካለ ያ ሰው መክፈቻ በማያስፈልገው ሲኦል መቃጠሉ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ገነት በዋዛና በፈዛዛ ኖረን የምንገባባት ተራ ቦታ አይደለችምና፡፡ ማንም በኃጢአት የኖረ ሁሉ ያለምንም መክፈቻ ሲኦል ሊገባ ይችላል ገነትን ግን ያለ መክፈቻ ከፍቶ የሚገባ ማንም የለም፡፡ ስለዚህ ገነት መግባት የምንፈልግ ሁሉ በቸርነቱ የሚሰጠንን መክፈቻ ከካህናት አባቶቻን ልንረከብ ግድ ነው፡፡   

No comments:

Post a Comment