በአንድ ዘመን ሁለት ውሾች ይኖሩ ነበር አሉ፡፡ አንዱ “ከተሜው” ሌላኛው ደግሞ “ገጠሬው”
በመባል ይጠራሉ፡፡ አንድ ቀን ያ የገጠሬው ውሻ ከጌታው ጋር ተጣልቶ ወደ ከተማ ይኮበልላል፡፡ ከተማ እንደ ደረሰ አንድ ውሻ በመኪና
ውስጥ ከጌታው ጋር ተቀምጦ ሲጫወት ያየዋል፡፡ በጣም ገረመውና “እንዴ! እንዲህም በቅንጦት መኖር አለ ለካ? ያውም በክብር ከጌታው
ጋር ቁጭ ብሎ መጫወት? የእኔ ጌታማ እንኳን አብሮ ሊያስቀምጠኝ ቀርቶ አላፊ አግዳሚ በተመላለሰ ቁጥር ካልጮኽኩለት ሲፈልግ በዱላ
ሲያሻው በድንጋይ አይደል እንዴ የሚያባክነኝ! እኔም ሆነ ይኽ በመኪና የሚዝናናው ሁላችንም ውሾች ነን እኮ ነገር ግን መኖሪያ ቦታችንን
አመራረጥ ላይ ልዩነቶች አሉ፡፡ ያ ልዩነት ብቻ ነው እኔና እርሱን እንዲህ የሰማይና የምድር ያህል ያለያየን፡፡ ዛሬ ግን እኔም
ትክክለኛ ቦታየን መርጫለሁ፡፡ ሁልጊዜ በጭቆና ቀንበር ሥር እስከመቼ ድረስ እኖራለሁ? ለማንኛውም ግን የከተማውን የኑሮ ሁኔታ እንዲያስረዳኝ
ከዚህ የከተማ ውሻ ጋር መተዋወቅ አለብኝ” አለና ወደ መኪናው ተጠጋ፡፡ ከተሜው የገጠሬውን ውሻ ሲመለከት “ኡ! ኡ! ኡ!” ብሎ
ጮኸ፡፡ ገጠሬው አሁንም ተጠጋውና “ከመኪናው ውጣና እንተዋወቅ” አለው፡፡ ከተሜው ጌታውን አስፈቅዶ ከመኪናው ወረደና ከገጠሬው ጋር
ተዋወቁ፡፡ ቀስ በቀስም ተለማመዱና ወጋቸውን መሰለቅ ጀመሩ፡፡ “የከተማ ኑሮ እንዴት ነው?” አለ ገጠሬው፡፡ “በጣም ይደላል ግን
ከየት እየመጣህ ነው?” አለ ከተሜው፡፡ “ከጌታየ ጋር ተጣልቼ ከገጠር ነው ወደዚህ የመጣሁት” ብሎ መለሰ ገጠሬው፡፡ “እንዴ ምን
ብሎህ?” አለ በመገረም አይነት፡፡ “ኧረ ተወኝ በእኔ የደረሰ አይድረስብህ! ከሁለት ቀናት በፊት ጌታዬ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ
ገስግሶ ተነሣ፡፡ ከዚያም ከበጎች ማደሪያ አጠገብ ደም ይመለከታል፡፡ እኔ ሌሊቱን በሙሉ ከቀበሮ ጋር ስታገል ስላደርኩ ትንሽ አረፍ
ብዬ ነበር፡፡ እንደተኛሁ መጣና አንተ እንቅልፋም አንተን አምኜ በጎቼን ጉድ ሆንኩ! ብሎ አንባረቀብኝ፡፡ ይህን ያህል ደም ሲፈስ
አንተ እዚህ ትተኛለህ አይደል? አለና በያዘው ዱላ ቅጥቅጥ አደረገኝ፡፡ እኔም ነፍሴን ለማትረፍ ሮጥሁ እርሱም በድንጋይ እየወረወረ
አባረረኝ፡፡ እስክደማ ድረስ እንደምታየኝ አድርጎ ቀጠቀጠኝ” አለና የተመታ ሰውነቱን አሳየው፡፡ ከተሜው በጣም ገረመው እንዲህ አይነት
ወሬ ሰምቶ ስለማያውቅም ቀልድ የሚቀልድበት መሰለው፡፡ ከዚያም “ለመሆኑ በጎችን ቀበሮ ሲበላቸው አንተ ተኝተህ ነበር እንዴ?” አለ፡፡
ገጠሬው ቀጠለ “አልሰማኸኝም እንዴ? እኔ እኮ ሌሊቱን ሙሉ የመጡትን ቀበሮዎች ሁሉ እየታገልሁ ነው በጎቹን ስጠብቅ ያደርሁት፡፡
ጌታዬ የተመለከተውም የበጎችን ሳይሆን የቀበሮዎችን ደም ነው፡፡ የበጎችን ማደሪያ ከፍቶ ሳያይ ነው እኮ ያን ያህል መዓት ያወረደብኝ፡፡
እኔ በጣም ያዘንኩም በዚሁ ነው፡፡ ቢያንስ ጉረኖውን ከፍቶ ካየ በኋላ በጎች ከተወሰዱበት ቢደበድበኝ እኮ አይቆጨኝም ነበር” አለ፡፡
“ብቻ በጣም ያሳዝናል! እንዲህ ዓይነት ጌታ እዚህ በእኛ አካባቢ አይቼ አላውቅም፡፡ ግን እንጅ! ቀበሮዎች ሲመጡብህ አልጮኽክም
እንዴ? ቢያንስ ጩኸትህን ሰምቶ ይነቃልህ ነበር እኮ” አለ ከተሜው፡፡ “ቀበሮዎችን ለመከላከል መጮኹ አላስፈለገኝም ነበር፡፡ ጌታዬም
እንቅልፉን እንዲያጣ አልፈለግሁም፡፡ ለዚያም ነው በሚመጡበት ሰዓት ሁሉ ሳልጮኽ አድብቼ በመያዝ ስገድላቸው የነበረው” አለ፡፡
“በጣም የሚገርም ታሪክ ነው፡፡ አንተ ለጌታህ ስታዝን እርሱ ያን ያህል ዱላ አወረደብህ አይደል? እኛ እኮ በዚህ ከተማ ተከብረን
የምንኖረው እንደ አንተ ከቀበሮ ጋር ታግለን ስላሸነፍን አይደለም አብዝተን ስለምንጮኽ ብቻ ነው፡፡ የእኛ ጉልበታችን አፋችን ነው፡፡
አንተም እዚህ ከተማ ለመኖር የግድ አፍ ያስፈልግሃል፡፡ ጠዋት ማታ በሆነ ባልሆነው መጮኽ ያስከብራል” አለ ከተሜው፡፡ ገጠሬው ራሱን
እየነቀነቀ “የሚበላ ነገር የት ታገኛላችሁ ግን?” አለ፡፡ “እንዴ! ጌታ የሚባለው ታዲያ ምኑ ላይ ነው፡፡ ጌታህ አይመግብህም ነበር
እንዴ?” አለ ከተሜው፡፡ ሳቅ አለና “ጌታየማ እንኳን ሊመግበኝ ቀርቶ የሚበላ ልፈልግ ስሄድ ይደበድበኝ የለም እንዴ? እኔ ሆዴን
የምሞላው የሞቱ እንስሳት ሲጣሉ እነርሱን በመመገብ ነው” አለ፡፡ “እንዴ! የሞተ የወደቀ እንስሳ ተመግበህ አትታመምም? ነው ወይስ
ሕክምና ይወስዱሃል” አለ ከተሜው፡፡ ገጠሬውም ገርሞት በረጅሙ ከሳቀ በኋላ “ እንዴ! እየቀለድክ ነው እንኳን እኔ እራሳቸው ጌታየም
ሕክምና የሚባለውን ነገር አያውቁትም፡፡ በእርግጥ ሕመም አልፎ አልፎ ይሰማኛል ግን ዋጥ አድርጌ እይዘዋለሁ እንደ ምንም እችለዋለሁ
እንጅ ሕክምና ውሰዱኝ ብዬ አፌንም አላበላሽ፡፡ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው የውሻ ሕክምና የመጣው ብለው ነዋ የሚወግረኝ” ብሎ በድጋሜ
ሳቀ፡፡ ውሻ ሕክምና መከታተሉን የሰማ ዛሬ ብቻ ነዋ፡፡ ለውሻ ጌታው ምግብ እንደሚሰጠው የሰማም ዛሬ ስለሆነ በጣም ደንቆት የከተማ
ኑሮ ሳይኖረው ናፈቀው፡፡ ከተሜው “ታዲያ ጌታህ ምግብ ካላበላህ ህክምና ካልወሰደህ ጌትነቱ ምኑ ጋር ነው? ለሥራህ የሚከፍልህ ደመወዝህስ
ምን ሊሆን ነው?” አለ፡፡ በጣም ፍርፍር ብሎ ሳቀና “የምን ምግብ የምን ሕክምና ነው? ጌታዬ እኮ ጌታዬ የሆነው የግቢውን አጥር
ስለፈቀደልኝ ብቻ ነው፡፡ የእኔ ደመወዝ በጎቹን ሊነጥቁ የሚመጡ ቀበሮዎችን ማደን ብቻ ነው፡፡ ይኽን ያህል ክብር ደግሞ ለውሻ ማን
ይሰጠዋል?” አለ ገጠሬው፡፡ “የራስህን መብት ማስከበር የአንተ ሥራ ነው፡፡ ማንም መጥቶ መብትህን አያስከብርልህም፡፡ በዚህ ከተማ
ተከብረን ለመኖራችን ትልቁ ምሥጢር መብታችንን ማስከበራችን ነው፡፡ ለሠራሁት ሥራ ሁሉ ክፍያ ካልተሰጠኝ ተኝቼ እውልለታለሁ፡፡ አጥሩን
እየጣስኩም ለሌባ መግቢያ በር አዘጋጅለታለሁ፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ሲባል ሰምተህ አታውቅም? እኔ በጣስኩት አጥር ሌባ ገብቶ
ያለ ንብረቱን ያግበሰብስለታል፡፡ ስለዚህ የግድ ደመወዜን ይከፍለኛል፡፡ እኔ አንተን ብሆን ኖሮ በጎቹን በቀበሮ አስነጥቄ ነበር
የሚያመጣውን የማየው፡፡ ታዲያ የእኔ ደመወዝ ምግብ ብቻ እንዳይመስልህ ሙሉ ሕክምና እና በሳምንት ሁለት ቀናት የመኪና ጉብኝት እንዲሁም
በሚያሰፈልገኝ ቀን ሁሉ ሻወር የምወስድበት ሁኔታዎች ሁሉ ተመቻችተውልኛል፡፡ ይህን ጥቅም ማግኘት የቻልኩት ግን ቅድም እንዳልኩህ
መብቴን አሳልፌ ባለመስጠት ነው” አለ ከተሜው፡፡ “ልክ ነህ ራሴን ቀብሬ የኖርኩ ራሴ ነኝ፡፡ መብቴንም ማስጠበቅ የራሴ ፈንታ ነው፡፡
በእርግጥ ይህን ሁሉ ነገር ማወቅ የቻልኩት ወደዚህ በመምጣቴ ነው፡፡ ስንት የእኔ ቢጤ ውሾች አሉ መሰለህ ያለምንም ክፍያ ከነብር፣
ከአንበሳ፣ ከቀበሮና ከጅብ ጋር ሲታገሉ የሚውሉና የሚያድሩ፡፡ ምንም እኮ እንቅልፍ የላቸውም” አለ ገጠሬው፡፡ “የገጠር ውሾች እኮ
ሳይማሩ እንደተሾሙ መንግሥት ሰራተኞች ናቸው ማለት ነው፡፡ ሳይማር የተሾመ ሰው ሁልጊዜ የሚያስበው መቼ ያነሡኝ ይሆን? የሚለውን
ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ያችን ሹመት ላለማጣት ሰውን የሚያስጨንቀው፡፡ ከዚያች የሹመት ወንበር ከወረደ የት ሊገባ እንደሚችል ያውቀዋላ፡፡
የተማረው ግን ከሹመቱ ቢወርድም አይደንቀውም ምክንያቱም በጣም በርካታ አማራጮች አሉት፡፡ በተማረው ትምህርት ሊቀጠር እንደሚችል
ስለሚያውቅ ለማንም አደርባይ አይሆንም፡፡ ያልተማረው ግን ኃላፊው በል ያለውን ብቻ ነው ሌት ከቀን የሚያነበንበው፡፡ እኛ እንዲህ
የምንዝናናው በርካታ አማራጮች ስላሉን ነው፡፡ በሙያችን የትም ሄደን መቀጠር ስለምንችል ቅድሚያ ለመብታችን ነው የምንታገለው፡፡
እንዳልተማረ ተሿሚ አንጨቃጨቅም” አለው ከተሜው፡፡ “ታዲያ ግን እዚህ ከተማ ለመኖር ምን ባደርግ ነው ጌታየ የሚወደኝ፡፡ ወደፊት
ያ የድሮው ነገር እንዳይገጥመኝ ያንተን ምክር እሻለሁ” አለ ገጠሬው፡፡ “እንዳልኩህ በዋናነት አፍህን መጠቀም ነው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ
ስትጮኽ ታድራለህ ከዚያም ጠዋት ጌታህ ምን ሆነህ ነው ስትጮኽ ያደርህ ብሎ ሲጠይቅህ አንድ ቀን ነብር መጥቶብኝ፣ ሌላ ቀን አንበሳ
መጥቶብኝ ደግሞ በሌላ ጊዜ ጅብ መጥቶብኝ ትለዋለህ፡፡ ሌላው ደግሞ የከተማ ሰው ሲመጣብህ ተኝተህ ታሳልፈዋለህ የገጠር ሰው ሲመጣብህ
ግን አገር ይያዝ ትላለህ፡፡ ጌታህ ሲመጣ ጅራትህን ውን ውን እያደረግህ ትቀበለዋለህ ሲሄድም እንደዚያ አድርገህ ትሸኘዋለህ፡፡ ከልጆች
ጋር ሁን እንዳሉህ ሆነህ ታጫውታለህ፡፡ ከጌታህ ሳታስፈቅድ ሰርቀህ መመገብ የለብህም በአጠቃላይ ግን ተግባቢ መሆን አለብህ፡፡ ገጠሬ
ነው ብለው እንዳይንቁህ ሲያፏጩልህ ዝም ነው ማለት፡፡ ቦቢ! ቦቢ! ቦቢ! ሲሉህ ብቻ ነው አቤት ማለት” አለው ከተሜው፡፡ “ይኽንን
ሁሉ ማድረግ አያቅተኝም ምንም ችግር የለውም በታማኝነት እንደማገለግል አውቃለሁ፡፡ ምግቤን እያሰበ ከሰጠኝ ራሱ ትልቅ ነገር ነው
እኮ! እዚያ ገጠርማ በፉጨት እጠራለሁ እያለ ጆሮየን አደንቁሮኝ አልነበር እንዴ? ታዲያ የከተማ ውሻ ሆንኩ ማለት ነው አይደል፡፡
ከዚህ በኋላ ስሜ ተለውጧል ቦቢ ቦቢ ቦቢ…” አለ ገጠሬው፡፡ የከተሜው ጌታ ከተሜውን “ቦቢ ና!” ብሎ ጠራው፡፡ ከተሜውም ገጠሬውን
ሳመውና መልካም ዕድል ተመኝቶ ተሰነባበቱ፡፡ ከተሜው በመኪና ገጠሬው በእግሩ የከተማውን አስፋልት ተያያዙት፡፡
No comments:
Post a Comment