በአንድ አካባቢ ሁለት ጎረቤታሞች ይኖሩ ነበር፡፡ አንዱ ገንዘብ የበዛለት
ይህ ቀረህ የማይባል ንብረቱ ስፍር ቁጥር የሌለው ባማረና በተዋበ ቤት በምቾትና በቅንጦት የሚኖር ተንኮለኛና ምቀኛ ባለጠጋ ሲሆን
ሌላኛው ግን ከአንዲት የጎሰቆለች ጎጆ ቤት በቀር ምንም የሌለው አዛኝና ርኅሩኅ ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘቡ ያደረገ ድሃ ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ያ ተንኮለኛና ምቀኛ ባለጠጋ ተንኮሉን ለመጀመር ከድኃው ጎጆ ጋር አያይዞ ጎጆ ቤት ሠራ፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት
በኋላ ባለጠጋው ያንን መከረኛ ድሃ ጎረቤቱን “ብርዱ በጣም ስለጨመረ
ጎጆዬን በእሳት አቃጥዬ ልሞቃት ስለሆነ ያንተ ጎጆ እንዳትቃጠል ከፈለግህ ራቅ አድርጋት” አለው ድሃው ጎጆውን አፍርሶ የሚሠራበት
ገንዘብ እንደሌለው ስለሚያውቅ አብሮ ለማቃጠል ልቡ በተንኮል ስለተነሣሣ፡፡ ድሃውም በተንኮል እንደተነሣሣበት ስለገባው ቤቱን ለማትረፍ
ገንዘብ ተበድሮ አፍርሶ ራቅ አድርጎ ለመሥራት ቢሞክርም ገንዘብ የሚያበድረው ሰው በማጣቱ ባለጠጋው የራሱን ቤት ሲያቃጥል የድሃውም
ቤት አብሮ ተቃጠለ፡፡ በቀል የእግዚአብሔር መሆኑን በሚገባ የሚያውቀው ድሃ በቀሉን ለእግዚአብሔር ትቶ ቤቱ የተቃጠለበትን ቦታ አጥሮ
ከቆፈረ በኋላ ባቄላ ዘርቶት ወደ ሩቅ አገር ተሰደደ፡፡ ባቄላው ለእሸት በደረሰ ጊዜ ያ ድሃ ሁኔታውን ለማየት ከስደት ተመልሶ ሳለ
የባለጠጋው ልጅ እሸቱን እየቀጠፈ ሲበላ ስለደረሰበት ምስክር ለሚሆኑ ሽማግሌዎች ያሳያቸዋል፡፡ ወዲያውኑ ከዳኛ ዘንድ ሄዶ የደረሰበትን
መከራና ግፍ በምሬት “በጉርብትና ሳለን ቤቴን አቃጠለብኝ እኔም ቦታዬን
ባቄላ ዘርቼ ተሰደድኩለት፡፡ የባቄላውን ሁኔታ ለማየት ከስደት ስመለስ ልጁ አጥሩን ጥሶ የባቄላውን እሸት ሲቀጥፍ ደረሰኩበት፡፡
ይህንንም የአካባቢው ሽማግሌዎች ሳይቀሩ አይተዋል፡፡ ስለዚህ ለተበደልኩ ለእኔ ፍረድልኝ ፡፡” ሲል ተናገረ ዳኛውም ይህን የተበደለ ሰው ድምጽ እንደሰማ ያን ባለጠጋ ከነልጁ አስጠርቶ
መልስ እንዲሰጥ አደረገው፡፡ የባለጠጋው መልስ ግን “የባቄለውን እሸት እተካለታለሁ፡፡ ቤቱን ግን እኔ አላቃጠልኩበትም የራሴን ቤት እንጅ” የሚል ነበር፡፡ ልቡ በግፍ ብዛት
የቆሰለው ድሃ ግን “ምትክ አልፈልግም የልጁ ሆድ ተሰንጥቆ የራሴ የሆነው
ባቄላ ወጥቶ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡” በማለት በዳኛው ፊት ተናገረ፡፡
ዳኛውም ግፍህ በዝቷልና የወደድከውና የፈቀድከው ይሁን ብሎ ፈረደለት፡፡ ያ ባለጠጋ ደንግጦ ፈዘዘ ደነገዘ፡፡ ልቡ ሲመለስለት “የልጄ ሆድ ከሚሠነጠቅ ያለኝን ሀብትና ንብረት እኩል ላካፍለው” በማለት በዳኛው ፊት ተማጸነው፡፡ ድሃውም ከብዙ ልመና በኋላ “ምን ያህል ግፍ እንደፈጸምክብኝ እንድትረዳ በመፈለጌ እንጅ የልጅህን ሞት
ፈልጌ አይደለም፡፡ አሁን ግን ሥራህን ሁሉ ስላወቅኸው እንድትማርበት ትቼዋለሁ” በማለት ገንዘቡን እኩል ለመካፈል ተስማማ፡፡
ዳኛውና ሽማግሌዎች የባለጠጋውን ሀብትና ንብረት በሙሉ ለሁለት እኩል ከፍለው ሠጡት፡፡ ያ ድሃም በግፍ ከተባረረበት ቦታው ላይ ያማረ
ቤት ሠርቶ በደስታ እግዚአብሔርን በማመስገን ኖረ፡፡ “በመከራህ ቀን
ጥራኝ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ፡፡”መዝ 49÷15 በማለት
የተናገረ አምላክ “አቤቱ ፍረድልኝ ከጽድቅ ከራቁ ሕዝብም ክርክሬን
ተከራከር ከሸንጋይና ከግፈኛ ሰው አድነኝ፡፡” መዝ 4÷21 በማለት የዳዊትን ልመና በመለመን ላይ የነበረውን ድሃ ልመና እግዚአብሔር
ሰማ፡፡ መዝ33÷6 ይህ ድሃ በበቀል ተነሣስቶ በባለጠጋው ላይ አንዲትም ጉዳት አላደረሰበትም፡፡
በቀል የእግዚአብሔር መሆኑን ያውቅ ስለነበር “አቤቱ ተነሥ በቀልህንም
ተበቀል፡፡” መዝ73÷22 የሚለውን የዳዊት መዝሙር እየዘመረ
ቦታውን ለቅቆ ተሰደደ፡፡ “እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው፡፡ የበቀል
አምላክ ተገለጠ፡፡”መዝ 93÷1 በማለት ዳዊት ያመሰገነው እግዚአብሔር ለድሃው የልመናውን ዋጋ ሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ በባለጠግነታችን
ተመክተን በድሆች ላይ አንዳች ግፍ ልንፈጽም አይገባም፡፡ ምክንያቱም በገንዘባችን ብዛት መግዛት የማንችላቸው ነገሮች በርካታ ስለሆኑ፡፡
ገንዘብ እንደ በረሐ አበባ ታይቶ የሚጠፋ ከንቱ ነገር ነው፡፡ በአግባቡ ሲጠቀሙበት የሚጠቅም በአግባቡ ካልተጠቀሙበት ደግሞ የሚጎዳ
ነው፡፡ ገንዘብ የምንገዛበት እንጅ የሚገዛን አይደለም፡፡ በገንዘባችን ከገዛንበት ጥቅም ላይ ዋለ ማለት ነው፤ ነገር ግን ገንዘቡ
ከገዛን ትልቅ ጉዳት ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ “ለችግረኛና ለምስኪን የሚራራ
ምስጉን ነው፡፡” መዝ40÷1 ይላልና ለድሆች ራርተን የምንመጸውት
ከሆነ ገንዘባችንን እንደ አብርሃም ጥቅም ላይ ማዋል ቻልን ማለት ነው፡፡ ወገኖቼ ገንዘብ በአግባቡ ካልተያዘ ጥፋቱ ይበዛልና በአግባቡ
መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ባለጠግነት ደግሞ ከአምላክ ካልተሰጠ በቀር ከየትም አይገኝም፡፡ አንዳንድ ሞኞች ስለወጡ ስለወረዱ ያገኙ ይመስላቸዋል፤
ለማግኘት መሥራት ግዴታ ነው፤ ነገር ግን አምላክም እንዲጨመርበት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ከአምላክ ፈቃድ ውጭ የትም መሄድ አይቻልምና፡፡
ስለዚህ ለድሆች ራርተን ካለን መጽውተን በእግዚአብሔር ቤት መኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
ማጣቀሻ፡- መዝ61÷10፣
ማቴ 19÷24፣ ሉቃ12÷15፣ ሉቃ21÷1-4
No comments:
Post a Comment