Tuesday, August 12, 2014

ፀረ ዲያብሎስ ማኅበር

የጋራ ችግር በማስወገድ የግል ጥቅምን ለማስከበር ማኅበራት ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡ በተለያዩ ችግሮች ዙሪያ ዓለም አቀፋዊና አገር አቀፋዊ ማኅበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
ለእነዚህ ማኅበራት መመሥረት መሠረቶቹ የፖለቲካ ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የሐይማኖት ጉዳዮች ወዘተ…ናቸው፡፡ ማኅበራቱ የራሳቸው የሆነ ዓላማና ተልዕኮ አንግበው ለዓላቸው መሳካት በትጋት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በሀገራችን ካሉት ማኅበራት ጥቂቶቹን ብንጠቃቅስ እንኳ ፀረ ሙስና፣ ፀረ ወባና ፀረ ኤድስ ፣ ፀረ ሽብር ወዘተ…ተብለው የተሰየሙ አሉ፡፡ ከተጠቀሱት ማኅበራት ውስጥ የዚህ አይነት ስያሜ የተሰጣቸው ከሌሉ ወደ ፊት መሰየማቸው አይቀርም፡፡እነዚህ ማኅበራት በአባላቸው ላይ ለሚደርስ የመብት ጥሰት ፈጥነው የሚደርሱ ናቸው፡፡ ከራሳቸው ባለፈም ሌሎችን ለመርዳት የተመሠረቱ ማኅበራት እንዳሉ አልዘነጋሁም፡፡ ያም ሆነ ይህ ችግር የሚፈጥሩት መብት የሚጥሱት ጉቦ የሚቀበሉት ሙስና የሚሠሩት በዲያብሎስ የሚመሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ጉቦ ሰጥቶ በማይገበውና በማይመጥነው ሥራ የሚቀጠር ሰው ቀጣሪውም ተቀጣሪውም ወንጀለኞች ናቸው፡፡ለዚህ ወንጀል መፈጠር  ዲያብሎስ እጁ አለበት፡፡የመንግሥት፣ የቤተ ክርስቲያን፣ የሌሎችን ሃብትና ንብረት ለራሳቸው መድለቢያ የሚጠቀሙ ሰዎችም የዲያብሎስ ባሪያዎች ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም፡ ታዲያ እነዚህንና መሰሎቻቸውን ለመቆጣጠር “ፀረ ሙስና” ማኅበር መቋቋሙ ግድ ሆነ፡፡ ነገር ግን ይህ ማኅበር በራሱ ጥቅም ፈላጊ ሆኖ ሙስና ቢሠራስ ሌላ “ፀረ-ፀረ ሙስና” ማኅበር ሊመሠረት ነውን? “ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጣ ውኃ ቢያንቅ በምን ይዋጥ” ይላል የአገሬ ሰው “ፀረ ሙስና” በሙስና ከተዘፈቀ ከፊቱ ተዝቆ የማያልቅ “ፀረ” ን በመጨመር “ፀረ- ፀረ ሙስና” አሁንም “ፀረ-ፀረ ፀረ ሙስና” ወዘተ… በማለት ስሙን መጥራት እስኪያዳግተን ድረስ ከመጓዝ መፍትሔ መፈለግ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሌሎችንም እንዲህ እንመልከትና የጋራ መፍትሔ ላይ በመድረስ ጽሑፋችንን እንቋጫለን፡፡ ወጣቱን በዝሙት አልጋ እያጋደመ ለአስከፊ በሽታ ያጋለጠው ዲያብሎስ ከጸሎት፣ ከጾም፣ ከስግደት ወዘተ… አርቆ የአልጋ ቁራኛ አድርጎታል፡፡ይህን ችግር ለመከላከልም “ፀረ ወባና ፀረ ኤድስ” ማኅበር ለምሥረታ በቃ፡፡ የፀረ ወባና ፀረ ኤድስ ማኅበር አባላት ከሚመክሩትና ከሚያስተምሩት ጥቂት ነገር ሳይሠሩ በኤድስና በወባ የሚሰቃዩ ከሆነ ሌላ የዚህ ማኅበር “ፀር” “ፀረ-ፀረ ወባና ፀረ ኤድስ”  መመሥረት አለበት ማለት ነው፡፡ አሸባሪዎችን ለመታገል “ፀረ ሽብር” ማኅበር ቢመሠረትም ራሱ ለዲያብሎስ ተገዝቶ አሸባሪ ከሆነ የማኅበሩ መመሥረት ምን ዋጋ አለው? የችግሩ መንስኤ ዲያብሎስ፤ የተመሠረቱት ማኅበራት ደግሞ የሚታገሉት ሌላ አካል በመሆኑ “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” ወይም “አህያውን ሲፈሩ ዳውላውን” ሆኗል ነገሩ፡፡ ዓለም በየትኛውም አቅጣጫ የፈለገችውን ያህል ማኅበር ብትመሠርት ችግሯን ሙሉ በሙሉ ቀርቶ በከፊል መቅረፍ አትችልም፡፡ ምክንያቱም ችግር ፈጣሪውን አካል መዋጋት የሚችል ማኅበር እስካሁን ድረስ መመሥረት ስላልቻለች፡፡ በየጥቃቅኗ ነገር ማኅበር በመመሥረት ጊዜን ከማባከን ይልቅ እነዚህ የተመሠረቱት እልፍ አእላፋት ማኅበራት ዓለምን ከችግር ነጻ በማውጣት ሰላማዊ ኑሮን ለመመሥረት “ጸረ ዱያብሎስ ማኅበር”ን በጋራ መመሥረት ያስፈላጋቸዋል፡፡ ማኅበሩ ምን አይነት ዓላማና ተልዕኮ እንዳለውና የማኅበሩ አባላት እንዴት ሊመለመሉ እንደሚችሉ የሚከተለውን ዝርዝር መግለጫ ማጤን ተገቢ ነው፡፡
v  የፀረ ዲያብሎስ ማኅበር ዝርዝር መግለጫ
§  የማኅበሩ ሥም፡ ፀረ ዲያብሎስ
§  የማኅበሩ ዓላማ፡ የዲያብሎስን ፈተና ድል በማድረግ በቅድስናና በንጽሕና በመኖር ለመንግሥተ ሰማያት የሚበቃ ትውልድ በዝቶ ማየት፡፡፡
§  የማኅበሩ ተልዕኮ፡ የዲያብሎስን ሴራዎች የሚያከሽፍ ትውልድ መፍጠር፡፡
Ø  የአባላት መመልመያ መስፈርቶች
·         ራሳቸውን መግዛት የሚችሉ፣
·         ዲያብሎስን መዋጋት የሚችሉበት መሣሪያ ያላቸው፣
·         መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ፣ መመጽወት ወዘተ…  የሚችሉ፣
·         ከዚህ በፊት በዲያብሎስ ተወግተው የአካል ጉዳት ያልደረሰባቸው ወይም የአካል ጉዳታቸውን በንስሓ የጠገኑ፣
·         ለገንዘብ የማይስገበገቡና አድልዎ የማይፈጽሙ፣
·         የሥላሴ ልጅነት ያላቸው ወይም ልጅነት ለማግኘት የፈቀዱ፣
·         የክርስቶስን ሥጋና ደም የተቀበሉ ወይም ለመቀበል የተዘጋጁ፣
·         አሥራት በኩራቱን የከፈሉ ወይም ለመክፈል የፈቀዱ፣
·         ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ችሎታ ያላቸው፣
·         የትምህርት ደረጃቸው ምዕመንና ከዚያ በላይ የሆኑ፣
·         የዘመኑን የሰበካ ጉባኤ ክፍያ የከፈሉ ለዚህም ትክክለኛ ደረሰኝ ማቅረብ የሚችሉ፣
·         ንስሓ አባት ያላቸው ወይም ንስሓ አባት ለመያዝ ፈቃደኞች የሆኑ፣
·         የነቢያትን፣ የሐዋርያትን፣ የሊቃውንትን፣ የቅዱሳን አባቶችን ቃል አምነው የተቀበሉ ወይም ለመቀበል የፈቀዱ፣
·         መጽሐፍ ቅዱስን ፣ ቅዳሴያትን፣ ድርሳናትን፣ ገድላትን፣ ውዳሴያትን፣ ተአምራትን እና ሌሎች አዋልድ መጽሐፍትን የተቀበሉ ወይም ለመቀበል የፈቀዱ፣
·         የቅዱሳንን አማላጅነት፣ የመላእክትን ተራዳኢነት፣ የድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት፣ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ወይም ተምረው ማመን የሚችሉ፣
·         የማኅበሩን ምሥጢር የሚጠብቁ፣
·         በቤተ ክርስቲያን ፊት ድንግል ማርያምን ተጠግተው ዲያብሎስን የካዱ ወይም ለመካድ የወሰኑ፡፡
Ø  የምዝገባ ቦታ፡ በአቅራቢያ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ እና በሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤቶች በአካል በመቅረብ መመዝገብ ይችላሉ፡፡
Ø  የምዝገባ ቀን፡ ዛሬ ጀምሮ፡፡
Ø  የማኅበሩ መንቀሳቀሻ በጀት፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት ወዘተ…
Ø  ለበለጠ መረጃ፡ በወንጌል፣ በድርሳን፣ በገድል የተጻፉትን ጽሑፎች መመልከት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በአቅራቢያዎ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአካል በመገኘት የሚሰጠውን ማብራሪያ መከታተል ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ማኅበር ለበሽታ የሚዳርገውን፣ ለክፉ ሥራ የሚያጋልጠውን ዲያብሎስ ማሰር የሚችል በመሆኑ ዓለም የመሠረተቻቸው ማኅበራት የዚህ ማኅበር ቅርንጫፎች በመሆን ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ እንደ አሸን ለፈሉት ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ማኅበራት መመሥረት ዲያብሎስ ዋናው ችግር ፈጣሪ ተዋናይ መሆኑን የተረዱ ጥቂቶች በጋራ የመሠረቷቸው ዲያብሎስን የሚታገሉ ማኅበራት በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ እንዳሉ ልብ ልንል ይገባል፡፡ ስለዚህ ችግር ፈጣሪ የሆነውን ዲያብሎስን ለማሰር “ፀረ ዲያብሎስ ማኅበር” መመሥረት ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ዲያብሎስን ድል ማድረግ የሚቻለው በወሬ ሳይሆን በሥራ በመሆኑ መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ፣ መመጽወት ወዘተ… የማኅበሩ አባላት መሠረታዊ ግዴታዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ዲያብሎስን ድል በማድረግ የኃጢአትን ሥራ በጽድቅ በማደስ የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ የዲያብሎስ ደጋፊዎች ከመሆን ወጥተን የዲያብሎስ ፀሮች እንሆን ዘንድ አማላካችን እግዚአብሔር ብርታቱን ጽናቱን ያድለን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment