Wednesday, August 20, 2014

አምላካችን ስንት ነው?


የሰው ልጅ በጥበብ ቢራቀቅም በፍልስፍና ቢበለጽግም እንኳ ከእርሱ የበለጠ ኃይል አለበት:: ያን አንድ ኃይል ያስገኘው አካል የለም:: ይህን የሁሉ አስገኝ ፈጣሬ ኩሉ ዓለማት አምላክ እንለዋለን:: ማንኛውም ሰው እርሱን የፈጠረ አምላክ እንዳለው ያምናል:: አምላክ መኖሩን የሚያምን ሰው አምላኬ የሚለው ነገር ከእርሱ የበለጠ መሆን አለበት:: አምላኬ ብሎ የሚያምነው ነገር የሚሸነፍ መሆን የለበትም ወይም አምላክ ከሚባለው ነገር የበለጠ ሌላ ነገር ሊኖር አይገባውም:: ለምሳሌ፡-
- ሰው ዛፍን  የማምለክ ነጻ ፈቃድ አለው:: ነገር ግን ያ አምላክ የተባለውን ዛፍ ሰው ራሱ ይቆርጠዋል:: ሰው በፈለገው ቅርጽ ያደርገዋል፡፡ ይጠርበዋል ይፈልጠዋል፡፡ ይህ ማለት አምላክ የተባለው ዛፍ አምላኬ ብለው ከሚጠሩት ሰዎች እጅግ ያነሰ ነው ማለት ነው:: በመሆኑም ዛፍ አምላክ ሊሆን አይችልም::
-
ፀሐይ ለዓለም ሁሉ ታበራለች ሙቀትም ትሰጣለች፡፡ብርሃኗም እንደፈለግን እንወጣለን እንገባለን:: ዕፅዋት ምግባቸውን የሚሰሩት በፀሐይ ብርሃን ነው፡፡ ለመኖር ፀሐይ የግድ ታስፈልገናለች፡፡ በዚህም የተነሳ ከሰው ልጅ የበለጠች አድርገን ቆጥረን አምላኬ ልንላት እንችላለን:: ነገር ግን የሚጎድላት ነገር አለ:: ጨለማ ያሸንፋታል ተራራ ይከልላታል፣ ዛፍ ይጋርዳታል:: ስለዚህ ፀሐይ አምላክ ልትሆን የማትችልበት ጉድለት አለባት ማለት ነው:: ስለዚህ  ፀሐይ አምላክ አይደለችም::
-
ውኃ ሲታጠቡበት ያጠራል ሲጠጡት ያረካል ዕጽዋትን ያለመልማል:: ለሰውም ለሌላውም ፍጡር ውኃ ለመኖር መሠረት ነው:: ውኃ ከሌለ በሕይወት መኖር ስለማይቻል ውኃ አምላክ ነው ልንል እንችላለን:: ነገር ግን ውኃ በሰው ይገደባል፣በእንስራ ይቀዳልሰው በሚፈልገው አቅጣጫ ይመረዋል:: ስለዚህ ሕፀፅ አለበት ማለት ነው:: ይህን ሕፀፅ የያዘ ደግሞ አምላክ ሊሆን የሚችልበት ነገር የለም::  በመሆኑም ውኃ አምላክ አይደለም፡፡
-
ጨረቃ በሌሊት ብርሃን ትሰጣለች ጨለማን የማሸነፍ ብቃት አላት:: በዚህም አምላክ ልናደርጋት እንችላለን ነገር ግን ከእርሷ የበለጠ ብርሃን አስገኝ አካል አለ:: ጨረቃ በጨለማ ከምትሸነፈው ፀሐይ እንኳ ታንሳለች:: የጨረቃ ብርሃን ከራሷ የሚወጣ ሳይሆን ከፀሐይ የተገኘ ነው:: ስለሆነም ጨረቃ በፀሐይ ትበለጣለች፡፡ ስለዚህ አምላክ ልትሆን አትችልም ማለት ነው::
-
ነቢያት ትንቢት ይናገራሉ፣የሚመጣውን ነገር ያውቃሉ፣ሙት ያነሣሉ፣ድውይ ይፈውሳሉፀሐይን ያቆማሉ፣ሰማይን ይለጉማሉ:: ስለዚህ ከነቢያት መካከል አንዱን አምላኬ ልንለው እንችላለን:: ነገር ግን ነቢያት በፀጋ ያገኙት እንጅ በባሕርያቸው ያለ አይደለም:: ለዚህም ነው ትንቢት የሚነፈጉበት፣ ተአምራት የሚከለከሉበት ጊዜነበረው:: ከዚህ የምንረዳው ከነቢያትም የሚበልጥ ነገር መኖሩን ነው:: ስለዚህ አምላክ አይደሉም ማለት ነው::
-ጻድቃን ሰማዕታት ብዙ ተአምራትን ያደርጋሉ፣በመከራ ይጸናሉ፣  በሕይወታቸውም ምሥክር ይሆናሉ፣ መራራ ሞትንም ይታገሳሉ:: ከእነዚህ መካከል አንዱን አምላኬ ብንል መብታችን ነው:: ነገር ግን ከእነርሱ የበለጠ በመከራ እንዲጸኑ፣ተአምራትን እንዲያደርጉ የሚያበረታቸው አካል አለ:: በመሆኑም አምላካችን ፈጣሪያችን አንላቸውም፡፡ እስከ አሁን ድረስ የጠቀስናቸው ሁሉ የራሳቸው የሆነ ከሌሎች የሚበልጡበት ነገር አላቸው:: ነገር ግን የራሳቸው የሆነ ጉድለትም ስላለባቸው አምላክ ብለን አናመልካቸውም:: ሁሉም የሚጎድላቸው ነገር አላቸው ከእነርሱ የበለጠ እነርሱን የሚያሸንፍ ኃይልም አለባቸው:: ኅልፈት ውላጤ ያገኛቸዋል:: ስለህም እነርሱን ያስገኘ ሌላ አካል ለመኖሩ እነዚህ ማረጋገጫዎቻችን ናቸው:: በመሆኑም እንደሰው ሰውኛው የምናወጣውን አምላክ የመሆንን መስፈርት አያሟሉም ማለት ነው::
እኛ አምላክ ብለን የምናመልከው:-
v  አስገኝ የሌለው፣
v  ማንም ማን ሊተካከለው የማይችል፣
v  ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፣
v  ሁሉን የሚመግብ፣
v  የሚያሸንፈው የሌለ፣
v  እርሱን የሚገድበው የሌለ፣
v  ከእርሱ የሚበልጥ የሌለበት፣
v  ሰማይን የዘረጋ ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፣
v  ጊዜ የማይለውጠው ዘመን የማይሽረው፣
v  ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘላለማዊ፣
v  የሚመጣውን የሚያውቅ፣
v  ሁሉን በፈቃዱ የሚያደርግ፣
v  ድካም የሌለበት፣
v  እንቅልፍ የማያሸንፈው፣
v  አማክሩኝ የማይል፣
v  ሌላ አጋዥ የማይሻ፣
v  ዘመናትን በዘመናት ጊዜያትን በጊዜያት የሚተካ፣
v  ሁሉን የሚገዛ፣
v  ሁሉን የሚያስተደድር፣
v  በሥራው የማይፀፀት፣
v  የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥ ረቂቅ፣
v  በሁሉ ቦታ ያለ /ምሉዕ በኩለሄ የሆነ/፣
v  ከእርሱ ውጭ አንድ ነገር እንኳ የማይደረግ፣
v  እውነተኛ ፈራጅ፣
v  ውሸት የሌለበት፣
v  ንፁሕ፣ ኃጢአት የማይስማማው፣
v  በማንም የማይመራ
v  ሁሉ በእርሱ የሆነ፣
v  ተመርምሮ ሊደረስበት የማይችል፣
v  ከአእምሮ በላይ የሆነ ነው::

እኛአምላካችን ብለን የምናመልከው ከላይ የተዘረዘሩትን በሙሉ የሚያሟላ ከሆነ ብቻ ነው:: ይህን አምላክ እግዚአብሔር እንለዋለን፡፡ አምላክ ዓለምን የሚያስተዳድር ነው:: ዓለምን ሲገዛ ደግሞ የሚያግዘው አይሻም:: መለኮት በጋርዮሽ ሥርዓት አይመራም:: አምላክ ልዩነት ያለባቸውን ተቃራኒ የሆኑ መለኮታዊ ሥራዎችን አይሠራም:: ዓለምን የሚሠራ አንድ አምላክ ዓለምን የሚያፈርስ ሌላ አምላክ የለም:: ግማሹን ዓለም አንዱ ግማሹን ሌላ አምላክ አይመራም ሁሉንም አንድ አምላክ ይገዛዋል እንጅ:: አምላክነት ዕገዛን አይሻም ሁለት ተቃራኒ ሃሳቦችም የሉበትም:: አንዱ ወደ ግራ ሌላው ወደ ቀኝ የሚሉ የተለያዩ አመለካከቶች ጥምርታም አይደለም:: የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች መነሻቸው ምሥጢረ ሥጋዌ ነው:: አምላክ በሥጋ ማርያም በተገለጠ  ጊዜ ዓለም የራሷን ሥም እየሰጠች አዳዲስ እምነቶችን መፈልፈል ጀመረች:: ከነቢያት መካከል አንዱ ነው ያሉት የራሳቸውን እምነት አንድ አሉ:: ከድንግል የተወለደው አምላክ አይደለም ዕሩቅ ብእሲ ነው ያሉት ሌላ እምነት መሠረቱ:: ይህ ከድንግል የተወለደው ከአምላክ ጋር የሚያስታርቀን አማላጅ እንጅ አምላክ አይደለም ያሉት ሌላ እምነትን ፈጠሩ:: በቅርብ ጊዜ የተመሠረቱት እምነቶች ሁሉ መነሻቸው ምሥጢረ ሥጋዌን በሚገባ ካለመረዳት የመጣ ነው:: በሰው አእምሮ መርምረው ለመድረስ ሞክረው መድረስ ያልቻሉ ሰዎች ሁሉ የራሳቸውን እምነት መሥርተዋል:: የተዋሕዶ እምነት ግን መሠረቱ ወልድ ዋሕድ እግዚአብሔር በተዋሕዶ ከበረየ ሚል ነው:: መሥራቹ ደግሞ ራሱ ባሕርይው ረቂቅ የሆነው አምላካችን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ በዚህ እምነት ውስጥ አምላካችን አንድ ብቻ ነው ብለን እናምናለን:: ሌሎች እምነቶች ግን በግልጽ አይናገሩ እንጅ ከአንድ በላይ የሆኑ አማልእክትን ያመልካሉ:: እንደ እነርሱ እየመሰላቸው ቅዱሳን ያማልዳሉ ስንል ቅዱሳንን አምላካችን ናቸው አሉ ይሉናል:: ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ የዓለም ሁሉ አማላጅ ናት ስንል አምላካቸው ድንግል ማርያም ናት ይሉናል:: እኛ የተዋሕዶ አማኞች አንድነቱ ሦስትነቱን በማይጠቀልለው ሦስትነቱም አንድነቱን በማይከፋፍለው አምላክ ብቻ እናመልካለን:: አምላካችን እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስትሦስት ሲሆንም አንድ ነው:: አንድነቱ በመለኮት፣ በአገዛዝ፣ በሥልጣን፣ በባሕርይ፣ በህልውና ወዘተ ነው:: ሦስትነቱም በሥም፣ በአካል፣ በግብር ነው:: የሥም ሦስትነት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መባል ነው:: አንዱ በሌላው ሥም አይጠራም:: የግብር ሦስትነት አብ ወላዲ፣ አስራፂ፤ ወልድ ተወላዲ፤ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ ይባላል:: አብ ቢወልድ ቢያሰርጽ እንጅ አይወለድም አይሰርጽምም፤ወልድ ቢወለድ እንጅ አይወልድም፣ አያሰርጽም፣ አይሰርጽምም፤ መንፈስ ቅዱስ ቢሰርጽ እንጅ አይወልድም፣ አይወለድም፣ አያሰርጽምም፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስቅዱስ ለየራሳቸው ፍጹም ገጽ ፍጹም  አካል አላቸው:: እግዚአብሔር እንዲህ ባለ አንድነትና ሦስትነት ጸንቶ ይኖራል:: አንዱ ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሲወለድ ከላይ ከአምላክነቱ (ከአንድነቱና ከሦስትነቱ) አልጎደለም አልጨመረምም:: በታችም በአንድነቱና በሦስትነቱ ላይ አልተጨመረም አልተቀነሰም:: እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም መወለዱ ከአምላክነት ዝቅ አላደረገውም:: አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ብለን እናምናለን:: የጠፋ በግ አዳምን ሊፈልግ የመጣው ወልድ ከራሱ ጋር አስታረቀን:: ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ በዘመነ ሥጋዌው ሰውን ከራሱ ጋር አስታረቀ:: ከዘመነ ሥጋዌው በኋላ አሁን ግን አማላጅ አንለውም ምክንያቱም ማማለድና አምላክነት የተለያዩ ናቸውና፡፡ ሁለት የማይገናኙና የማይተዋወቁ ነገሮችን ሦስተኛ አካል በመካከላቸው ገብቶ ቢያገናኛቸው ወይም ቢያስተዋውቃቸው ምልጃ ነው:: እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም የማንችል በመሆኑ ቅዱሳን ስለእኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢለምኑልን ምልጃ ነው:: ከዚህ እንደምንረዳው ምልጃ የፍጡር ሥራ ነው:: በፍጡራን መካከል ደግሞ እኩል የሆነ ቅድስና የለም:: ስለዚህ በቅድስና የሚበልጠው ለሌሎች ይማልዳል:: ሙሴ ለሕዝበ እስራኤል ይማልድ የነበረው ቅዱስ ስለነበረ ነው:: አምላካችን አንድ እንደሆነ አይተናል በሥም ሦስት መሆኑንም እንዲሁ:: ከሥስቱ አካል አንዱን አካል ወልድ አማላጅ ነው የሚሉ እምነቶች አሉ:: እነዚህ እምነቶች ኢየሱስ በሥጋ ማርያም ለምን እንደተገለጠ ያልተረዱ ናቸው:: ምልጃ የፍጡር ሥራ ነው ብለናል ስለዚህ ኢየሱስ ፍጡር ነውን? ይቅር ይበለን:: እርሱስ የባሕርይ አምላክ ነው:: አምላካችን ደግሞ አንድ ነው:: ማማለድ እና አምላክነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው:: ምልጃ የሚቀርበው እኮ ለሚበልጥ አካል ነው:: ኢየሱስ ይማልዳል ማለት ከኢየሱስ የሚበልጥ ሌላ አካል አለ ማለት ነው:: ከአምላክ የሚበልጥ ነገር ካለ ደግሞ አምላክ ሊሆን የሚችለው ያ የበለጠው ነገር ነው:: ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንዶች እንደሚሉት አማላጅ ሳይሆን የባሕርይ አምላክ ነው:: አምላክን አማላጅ ማለት ነጭን ጥቁር፣ ወፍራምን ቀጭን እንደ ማለት ነው:: ስለዚህ አምላካችን አንድ ነው እርሱም እግዚአብሔር ነው፡፡

No comments:

Post a Comment