Thursday, August 7, 2014

የሰማይ ቤት ለመሥራት


የአፈርነት ባሕርይ ያለው የሰው ልጅ “ኑሮ ኑሮ ከሞት ውሎ ውሎ ከቤት” እንዲሉ ከዚህች የስቃይና የመከራ ቦታ ለመሰናበት ይገደዳል፡፡ በዚች አሸንክታቧ በበዛ ያሸበረቀች ዓለም የሠራነው በጎ ወይም መጥፎ ሥራ ወደ ሰማይ ቤት አብሮን ስለሚሄድ የምንቀልሰው የሰማይ ቤታችን  በምድር የሠራናቸው ሥራዎች መሠረት፣ ጣሪያና ግድግዳ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ምድራዊ ቤቶችን የተዋቡና ያሸበረቁ ለማድረግ ለቁሳቁስ መግዣ የምናወጣው ገንዘብ የምናፈሰው ጉልበት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የዋጋ ውድነት እሳት ሆኖ በሚያቃጥልበት በዚህ ወቅት ለአንገት ማስገቢያ የምትሆን ቀላል ጎጆ ለመሥራት እንኳ በሽዎች የሚቆጠር ገንዘብ መከስከስ ግዴታችን ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የተሻለ ዘመናዊ ቤት ለመሥራት ደግሞ በሚሊዮንና በቢሊዮን ከዚህም በላይ የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣትን ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ግን ይህን ያህል ገንዘብ ከስክሰን በሠራነው ቤት ውስጥ ባወጣነው ገንዘብ ልክ የመኖር ዕድል የለንም፡፡ ሰባ ሰማንያ ዘመን ለምንኖርበት ምድራዊ ቤት ሰባ ሰማንያ ሚሊዮን ብር እንከሰክሳለን፡፡ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ብንደራርብ በዕንቍ ብናሽቆጠቁጠው ለዘላለም የምንኖርበት አይሆንም፡፡ በዚህ ዘመን ሰው እየተጨነቀ ያለው ለምድራዊ ቤቱ ውበት ነው፡፡ እገሌ ፎቅ ስለሠራ እኔም ፎቅ መሥራት አለብኝ በሚል ከማን አንሼ አስተሳሰብ ድሃ በቅዱሳን ሥም ለልመና እጁን ሲዘረጋ አምስት ሳንቲም ለመሥጠት እጃችን አልፈታ ያለን ንፉጋን በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ፎቅ ለመሥራት ብቻ እጃችን ይፈታል፡፡ ታዲያ በዚህ ሂደት የተሠራው ቤት ምን አይነት መሠረት ሊኖረው እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የሆነ  የሰው ፍቅር ከዙፋኑ ያወረደው ኃያል ወልድ ክርስቶስ ኢየሱስን አንድ ጻፊ ቀርቦ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ ባለው ጊዜ ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም በማለት መመለሱ ምድራዊ ቤት ሊያስጨንቀን እንደማይገባ ሲገልጽልን ነው፡፡ ማቴ8፥20  ይህ ጻፊ እንግዳ ከማይቀበልበት፣ የተራበን ከማያበላበት፣ የተጠማ ከማያጠጣበት ቤቱ ተለይቶ ክርስቶስ ከሚውልበትና ከሚያድርበት ሊውልና ሊያድር የሚችልበት ልቡና የሌለው በአፉ ብቻ ሊከተለው የሚወድ ነው፡፡ የልቡን ሃሳብ ያወቀ እግዚአብሔር ራሱን የሚያስጠጋበት ቤት እንኳ እንደሌለው ገለጸለት፡፡ መቼም ቢሆን የሰው ልጅ በራሱ ምድራዊ ቤትም ሆነ በኪራይ ቢኖር በጥገኝነትም ሆነ በበረንዳ ወድቆ ቢኖር አድልዎ የሌለበት የሥጋ ሞት ሁሉንም ይጎበኛል፡፡ ከዚህ በኋላ በሰማይ መኖር ይጀመራል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ሀገራችን በምድር ሳይሆን በሰማይ ነውና ፊል3፥20 ፡፡ ታዲያ ሀገራችን በሰማይ ከሆነ ከሞት በኋላ ባልሠራነው የሰማይ ቤት ማን ያኖረናል? እዚያ መከራየት የለ? ፎቅን ይዞ መሄድ የለ? ታዲያ የት ልንገባ ነው? በእርግጥ ቤት የሌላቸውን የሚቀበል የሲኦል ባለቤት ዲያብሎስ ወደ እሳት ባሕር ይሰበስባል፡፡ በምድራዊ ኑሮ የሠራነው በጎ ሥራ የእግዚአብሔር ቸርነት ሲጨመርበት የሰማይ ቤታችንን የተዋበ ያደርግልናል፡፡ ይህ ሰማያዊ ቤት በሽህ፣ በሚሊዮን፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያላቸው ሃብታሞች የሚሠሩት አይደለም፡፡ በዚህን ጊዜ ሊፈርስ ይችላል የሚል ሥጋት የሌለበት ዘላለማዊ መኖሪያ ሰማያዊ ቤት ድሃዎችም በፍጹም እምነት የሚሠሩት ነው፡፡ እንደ ሰው ሰውኛው 1000 ብር መብዐ የሰጠ ሰው 1 ብር ከሚሰጥ ሰው የበለጠ የገነት ባለቤት አድርገን እንስለዋለን፡፡ እግዚአብሔር ግን የልብን ንጽሕና ተመልክቶ ዝቅተኛ ገንዘብ ለሰጠው ሰው  ብዙ ገንዘብ ከሰጠው ቀድሞ የሰማይ ቤቱን ሊከፍትለት ይችላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋእለ ሥጋዌው ወቅት መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለጠጎችን አየ፡፡ አንዲትም ድሃ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና እውነት እላችኋለሁ ይህች ድሃ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና ይህች ግን ከጉድለቷ የነበራትን ትዳሯን ሁሉ ጣለች፡፡ ሉቃ21፥1-4  ይህች መበለት የጣለቸው ሁለት ሳንቲም ባለጠጎች ከጣሉት የበለጠ መጠን ያለው አይምሰለን፡፡ መጠኑ እጅግ አነስተኛ የሆነ ገንዘብ የጣለችው ይህች መበለት በፍጹም እምነት፣ በንጹሕ ልቡና የያዘቻትን ሳንቲም ለነፍሴ እጠቀምባታለሁ በማለት መጣሏ ከባለጠጎች የበለጠች እንድትሆን አደረጋት፡፡  ባለጠጎች ብዙ ገንዘብ አላቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ የጣሉም ስላላቸው ነው፡፡ መበለቲቱ ግን ሁለት ሳንቲም ብቻ ነበር ያላት ያችኑ በእግዚአብሔር መዝገብ ላይ ጣለች፡፡ ስለዚህም የሰማይ ቤቷን በሁለት ሳንቲም ሠራች ፡፡ የሰማይ ቤት ለመሥራት እንደ ምድራዊው ቤት አስቸጋሪና ውጣ ውረድ የበዛበት ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ አይደለም በጠበበው ደጅ በፍጹም እምነት፣ በንጽሕና መጓዝ ነው የሚጠበቀው፡፡ የምንንቃት ገንዘብ አምስት ሳንቲም  በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለች ዘላለማዊ ቤት የምትሠራ ታላቅ ገንዘብ ናት፡፡ የሰማይ ቤት በመጾም፣ በመጸለይ፣ በመመጽወት፣ በበጎ ሥራ በእግዚአብሔር ቸርነት የሚሠራ በመሆኑ በዓለት ላይ ልንመሠረት ያስፈልጋል፡፡ ሽህ ጊዜ ቢጎርፍና ቢነፍስ በዓለት ላይ የተመሠረተ ቤት አይወድቅም፡፡ የሰው እጅ ያልተጠበበበት፣ ግድግዳው የማይላጥ፣ መሠረቱ የማይናወጥ የዘላለም መኖሪያ ሰማያዊ ቤት መንግሥተ ሰማያት ቀለም ቀቡኝ፣ ግንብ ገንቡኝ፣ ብሎኬት ደርድሩብኝ፣ ኮርኔስ ሥሩልኝ፣ አናጢ ምረጡልኝ፣ አረጀሁ አድሱኝ ወዘተ… የሚል ያይደለ ዓለም ሳይፈጠር የተፈጠረልን የዘላለም መኖሪያ ነው፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ዘላለማዊ ቤት እንደ ታክሲ ዘለን የምንገባበት ስላልሆነ ምድራዊ ኑሯችንን በቅድስና ልንፈጽመው ያስፈልጋል፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር የእግዚአብሔር ቸርነት ረድቶ ኑ የአባቴ ቡሩካን የሚለውን የደስታ ቃል ያሰማን፡፡ አሜን፡፡
visit: melkamubeyene.blogspot.com

No comments:

Post a Comment