Thursday, August 14, 2014

ድንግል ማርያም አልተነሳችምን?

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
በምንፍቅና እድሜን የሚቆጥሩ ፕሮቴስታንቶች ስለጾም ስታነሱ መዘላበድ ልማዳቸው ሆኖ ስለጾም ማውራት ትተው ስለድንግል ትንሣኤ ይጠይቃሉ:: ቤተክርስቲያናችን ለሚጠይቋት ሁሉ መልስ መስጠት የምትችል “ስንዱ እመቤት” ናት:: እነርሱ “ድንግል ማርያም በመቃብር ቀረች” የሚል እምነት አላቸው፡፡ አያይዘውም “የሞተ አያማልድም” በሚል ድንቁርና ውስጥ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተቀምጠው “ድንግል ማርያም አታማልድም” ይላሉ:: በእርግጥ “ማማለድ” ሌላ ጥያቄ ነው “የድንግል ትንሣኤ” ደግሞ ሌላ ነው:: ድንግል ማርያም አልተነሣችም የምትሉ የጨለማ ልጆች ሆይ! ከመነሣት መሞት አይቀድምምን? “ድንግል ማርያም ሞተች፣ ተቀበረች” የሚል ጥቅስ አሳዩን እስኪ? እናንተ የምትፈልጉት ተነሣች የሚል ጥቅስ ብቻ ነው:: እኛ ደግሞ ከመነሣት የሚቀድመውን መሞትና መቀበርን የሚገልጥ ጥቅስ አሳዩን እንላለን፡፡ ድንግል ማርያም መቼና የት ተወለደች? የትስ እንዴትስ አደገች? መቼ ሞተች? የተስ ተቀበረች? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚችል ጥቅስ ካሳያችሁን በቃ በጣም እናደንቃችኋለን!!! በዚህ ቦታ ተቀበረች፣ በሥጋም አልተነሣችም የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ አቅርቡልንና እንተማመን:: ከመስቀሉ ሥር የተረከባት ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉና መልእክታቱ ላይ “ብዙ የምጽፈው ነገር ነበር ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች አሁን አልገልጣቸውም” ማለቱ መጽሐፍ ቅዱስ የተደረገውን ሁሉ አጠቃልሎ አለመያዙን ያሳያል:: ጊዜው በደረሰ ጊዜ ግን እነ አባ ሕርያቆስ፣ እነ አባ ኤፍሬም፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገለጡታ! በቃ ይህ ነው እኮ የሆነው፡፡
የድንግል ማርያም ክብር እንደ ባሕር አሸዋ እንደ ሰማይ ክዋክብት እጅግ የበዛ ሰብአ ዓለም ቢሰበሰብ ጽፎ የማይጨርሰው ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሙሉ ታሪኳ ሊቀመጥ እንዴት ይችላል? ኢየሱስ ክርስቶስ የሰራው ሥራ ያ በወንጌል ብቻ የተቀመጠው አይደለም፡፡ ብዙ የሰራው ሥራ አለ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች በአጠቃላይ አልተገለጠም፡፡ ይገለጥ ቢባልስ ማነው ጽፎ የሚጨርሰው፣ ምንስ ላይ ነው የሚጻፈው? የድንግል ማርያምም ክብሯን ዘርዝሮ የሚይዝ የሚጽፍም የለም ነገር ግን በውዳሴዋ በቅዳሴዋ መንፈስቅዱስ የገለጠላቸውን ያህል ጽፈውልናል፡፡ በዚህም መሰረት ድንግል ማርያም በእናት በአባቷ ቤት 3 ዓመት በቤተ መቅደስ 12 ዓመት በዮሴፍ ቤት ደግሞ 34 ዓመት ከዚያም ከዮሐንስ ጋር 15 ዓመት በድምሩ 64 ዓመት ኖረች፡፡ ከዚያም በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን ዐረፈች በነሐሴ ወር ሐዋርያት ሥጋዋን አግኝተው ቀበሩት፡፡ ከዚያም በነሐሴ 16 ተነሳች ዐረገች!!! የሚገርመው ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር መሆኑ ነው፡፡ እኛ የኦርቶዶክስ ልጆች መቼም ቢሆን ከዚህ እውነታ ማንም አያናውጠንም!!!
visit: http://www.melkamubeyene.blogspot.com
“ወስብሐት ለእግዚአብሔር”

3 comments:

  1. ሰው ሆኖ የማይሞት ማን አለናነው ስለቅድስት ማሪያም ሞት መፅ. ቅ. ውስጥ የሚፃፈው? የሁሉም ቅዱሳን ሞት እኮ አይደለም የተገለፀው። መፅ. ቅዱስ ደግሞ ይህ ቀረሽ ሊባል የማይችል ነው። ለትምህርታችን ይሆነን ዘንድ የተፃፈው ብቻ እንዲፃፍ መንፈስ ቅዱስ እንዳደረገ ከዮሃንስ ወንጌል እንረዳለን። ሌሎች መፅሃፎች ታልገባንን የመፅ.ቅዱስ ክፍል እንዲገባን ሊያግዙን ይችላሉ እንጂ በራሳቸው እንደብቁ ማስረጃ ልናደርጋቸው የምንችል አይመስለኝም። ምክንያቱም እግዚያብሄር መፅ. ቅዱስን ለሰው ልጅ እንዲገባው አድርጎ እንጂ ለመላዕክት አልፃፈውም።

    ReplyDelete
  2. ለመናፍቃን፡ ሰው ስለሆች መሞቷ አይቀርም ማለትማ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሔኖክና ኤልያስ ሰዎች ነበሩ ነገር ግን አልሞቱም፡፡ ስለዚህ ድንግል ማርያም አልተነሳችም እያልን ከምንከራከር መሞቷን አሳዩን፡፡

    ReplyDelete
  3. ያልተፃፈን ከመፈለግ የተፃፈውን መረዳዳቱ የሚሻል ይመስለኛል። ትንሳኤ ደግሞ በመፅ.ቅ. እይታ ትልቅ ነገር ነው። ለዚህ ነው ኤፌሶን መፅሃፍ ላይ ወደሰማይ ከወጣው በቀር ወደላይ የወጣ እንደሌለ የሚነግረን። ሞትን የሚያክል ነገር አሸንፎ ካረገ አንድ የእግዚአብሄር ቅዱስ ሰው መፅሃፍ ቅዱስ ላይ መገለፁ አይቀሬ ይመስለኛል። ምክንያቱም እግዚአብሄር ክብሩን ማሳየትና ሰዎችን ማስተማር ስለሚፈልግ። መነሳቷን የምታምን ከሆነ ደግሞ ያልሞተ ተነሳ ልንል እንገማንችል ትረዳዋለህ ብየ አስባለሁ። ላልሞተ ሰው ተነስታል ልንል አንችልምና። ስለዚህ የድንግል ማርያምን ትንሳኤ የምታምን ከሆነ መሞቷን ማመንህንም እየገለፅክ ነው።

    ReplyDelete