Thursday, August 28, 2014

የቅናቱ መቅናት

እግዚአብሔር አምላክ ሰይጣናዊ ቅንዓትን ወደ መልካም ሲቀይር የጥበቡን ስፋት ተመልከቱ፡፡ አንድ ሁሉ የሞላው ንፉግና ቅንዓተኛ ባለጠጋ  እና ከዕለት ጉርሱ ከዓመት ልብሱ የሚተርፍ ገንዘብ የሌለው እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያመሰግን ድሃ በአንድ ሰፈር  በጉርብትና ይኖሩ ነበር፡፡የድሃው የሁልጊዜ ልመናና ጸሎት እንዲሁም የልቡ ምኞት የዕለት ምግቡን እንዳይነፍገው፣ ጤናውን እንዲሰጠውና ያለውን ጥቂት ነገር እንዲባርክለት፣ በዓለም ፍጻሜም ከቅዱሳኑ ጋር በቀኙ እንዲያቆመው ነው፡፡ በአንጻሩ የባለጠጋው ምኞት ደግሞ ይህ ድሃ ሰው ከአጠገቡ ተነቅሎ እንዲሄድለትና መሬቱን የራሱ አድርጎ መኖር ነበር፡፡ ይህ ንፉግ ባለጠጋ ድሃው ለምግብ ያህል ሰርቶ በሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ እጅግ አብዝቶ ይቀና ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ድሃው የነበረችውን ትንሽ መሬት በጥሩ ሁኔታ አርሶና አለስልሶ የሚዘራው የጤፍ ዘር ስላልነበረው ከአጠገቡ ከሚገኝ ቤተክርስቲያን ሄዶ በእምነት "አምላኬ ሆይ ጉልበቱን ሰጥተህ ከእኔ የሚጠበቀውን ተግባር ሁሉ ፈጽሜያለሁ ነገር ግን የምዘራው የጤፍ ዘር የለኝምና ድካሜን ከንቱ አታስቀርብኝ የምዘራው ዘር ስጠኝ፡፡ አዳምን ከኅቱም ምድር የፈጠርህ በባዶ ግንባር ላይ ዓይንን የሠራህ አምላክ የሚሳንህ ነገር እንደሌለ አምናለሁና የባሪያህን ልመና ተቀብለህ የልቤን መሻት ፈጽምልኝ " በማለት የሚመካበትን እግዚአብሔር ለመነ፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ድሃ እግዚአብሔር ልመናውን እንደሚፈጽምለት አምኖ ወደቤቱ ተመልሶ መሬቱን አርሶ ለዘር ምቹ አደረገው፡፡ በዚህ ተግባሩ ዓይኑ ደም የለበሰው ባለጠጋ "ይህ የሚልሰው የሚቀምሰው የሌለው ድሃ ምን የሚዘራው ነገር ኖሮት ይሆን እንዲህ የሚደክም? ይህን መሬት ለእኔ ያላደረኩት እንደሆነ ሰው አይደለሁም " ሲል ዛተ፡፡ የእግዚአብሔርን ኃያልነትና ጠቢብነት የተረዳው ድሃ ጀንበሯ ስትጠልቅ ኩልል ባለችው ጨረቃ የምድጃውን አመድ በቁና እያፈሰ ለዘር ባመቻቸው መሬት ላይ በእምነት ዘራው፡፡ ይህን ሲያደርግ በቤቱ መስኮት ቀዳዳ ይመለከት የነበረው ባለጠጋ ድሃው ነጭ ጤፍ የዘራ ስለመሰለው በቅንዓት አረረ፡፡ በሌሊትም ተነሥቶ "ነጭ ጤፍ" በተዘራበት በድሃው መሬት ላይ ቀይ ጤፍ ዘራበት፡፡ ድሃውም ጤፍ እንደበቀለለት ባየ ጊዜ እጅጉን ተደስቶ እግዚአብሔርን በማመስገን ጤፉን በማረምና በመንከባከብ አጭዶ ሰብስቦ በብዙ ኩንታል የሚቆጠር ቀይ ጤፍ አምርቶ አሥራቱን ከፍሎ ለድሆች መጽውቶ የተረፈውን በጎተራ አስገብቶ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ኖረ፡፡ " ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ ታገኙማላችሁ " ማቴ7÷7  በማለት የተናገረ አምላክ የድሃውን የልመና ቃል ሰምቶ ፈጸመለት፡፡ የባሕራንን የሞት ደባዳቤ ወደ ሕይወት የለወጠ፣ ዳንኤልን ከአናብስት አፍ የጠበቀው፣ ሶስናን ከዕደ ረበናት ያተረፈ፣ ቂርቆስና ኢየሉጣን ከፈላ ውኃ ያዳነ፣ የአንጢላርዮስን ንፍገት ወደ ለጋስነት የቀየረ፣… ተዘርዝሮ የማያልቅ ተአምራትን ያደረገ አምላክ የዚህን ድሃ ልመና ሰምቶ የባለጠጋውን ቅንዓት አቀናለት አመድን ጤፍ አደረገለት፡፡ "አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም" መዘ24÷3  ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔርን ተስፋ ብናደርግ የሚያሳጣን ነገር እንደሌለ ልናምን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ከዚህም በላይ ሊያደርግልን ይቻለዋል ለሰው የማይቻል ሁሉ በእርሱ ዘንድ ይቻላልና፡፡ በመጀመሪያ ጽድቅና መንግሥቱን እንፈልግ እንጅ ሌላውን ይጨምርልናል፡፡ ምክንያቱም እርሱ እኛ ለእኛ ከምናስበው በበለጠ ያስብልናልና፡፡ ለኛ መቼ ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃልና ሁሉንም በጊዜው መጠበቅ ከኛ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን አምላክነት፣ ቸርነት፣ ፍቅርና ርኅራኄ አምነን ሥሙን በማመስገን  ለመኖር አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ አሜን፡

No comments:

Post a Comment