Monday, August 4, 2014

ድንግል ማርያምና መናፍቃን /ሦስተኛ ክፍል/

የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም/ማቴ1:25/ በዚህ ክፍል የምናየው “እስክትወልድ ድረስ” ስላለ “ከወለደች በኋላ ዮሴፍ በግብር አወቃት” ማለት ነውን? የሚለውን ነው፡፡ መናፍቃን የሚያነሡት “የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም/ማቴ1:25/” ስለዚህም የበኩር ልጇን ከወለደች በኋላ ዮሴፍ “በግብር አውቋታል” የሚል ነው፡፡ “እስክትወልድ አላወቃትም ” ማለት ከወለደች በኋላም አላወቃትም ማለት ነው፡፡ “እስከ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት አገባብ አለው፡፡ - ፍጻሜ ያለው እስከ እና - ፍጻሜ የሌለው እስከ ማለት ነው፡፡ “እስከምትወልድ ድረስ” የሚለው ላይ የምናገኘው እስከ ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው፡፡ ትርጉሙም ከወለደች በኋላም አበግብር አላወቃትም የሚል ነው፡፡መናፍቃን እዚህ ላይ ያለውን እስከ ፍጻሜ ያለው አድርገው የሚወስዱት ከሆነ የሚከተሉትን ማስረጃዎችን እንዴት ሊተረጉሟቸው እንደሚችሉ እንመልከት፡፡ - “… ቁራውም የጥፋት ውኃ እስኪጎድል ድረስ አልተመለሰም” ዘፍ8፡7 ይላል፡፡ ይህ ማለት ከጎደለ በኋላም አልተመለሰም ማለት እንጅ ከጎደለ በኋላ ተመለሰ ማለት አይደለም፡፡ - “… ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ የነገርኩህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና፣ ዘፍ 28፡15 ይላል፡፡ ይህ ማለት የነገርኩህን ሁሉ ካደረግሁልህ በኋላ ሁሉ አልለይህም ማለት እንጅ የነገርኩህን ሁሉ ካደረግሁልህ በኋላ እተውሃለሁ ማለት አይደለም፡፡ - “ ሳሙኤልም እስከሞተበት ቀን ድረስ ሳዖልን ለማየት ዳግመኛ አልሄደም” 1ኛ ሳሙ 15፡35 ይላል፡፡ ይህ ማለት ሳሙኤል ከሞተ በኋላ ሳዖልን ሊያይ አልሄደም ማለት እንጅ ከሞተበት ቀን በኋላ ሳዖልን ሊያይ ሄዷል ማለት አይደለም፡፡ - “…ሜልኮል እስከሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም” 2ኛ ሳሙ6፡23 ይላል፡፡ ይህ ማለት ከሞተች በኋላም ልጅ አልወለደችም ማለት እንጅ ከሞተች በኋላ ልጅ ወልዳለች ማለት አይደለም፡፡ ሰው ከሞተ በኋላ ይወልዳል የሚል እምነት ካላቸው ምናልባት አናውቅም፡፡ - “… በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ፡፡ እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሠረይላችሁም” ኢሳ 22፡14 ይላል፡፡ ይህ ማለት ከሞታችሁ በኋላም በደላችሁ ፈጽሞ አይሰረይላችሁም ማለት እንጅ ከሞታችሁ በኋላ በደላችሁ ይሰረይላችኋል ማለት አይደለም፡፡ - “…የባሪያዪቱም ዓይን ወደ እመቤቷ እንደሆነ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዓይናችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ነው” መዝ 122፡2 ይላል፡፡ ይህ ማለት ከማረን በኋላም ዓይናችን ወደ እግዚአብሔር ነው ማለት እንጅ ከማረን በኋላ ዓይናችንን ወደ እግዚአብሔር አናደርግም ማለት አይደለም፡፡ - “የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም/ማቴ1:25/ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስን ከወለደች በኋላም ዮሴፍ በግብር አላወቃትም ማለት እንጅ ከወለደች በኋላ ዮሴፍ በግብር አውቋታል ማለት አይደለም፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን ይቆየን

No comments:

Post a Comment