የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ አላወቃትም/ማቴ1:25/
በክፍል አንድ “ማዎቅ” የሚለውን ቃል ትርጉም ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ “በኩር” የሚለውን ቃል ትርጉም እንመለከትና ከዚሁ ጋር የተያያዘ “የጌታ ወንድሞች” የሚለውን እናብራራለን፡፡
በኩር፡- ---› ከሰው ወይም ከእንስሳት ለመጀመሪያ ጊዜ የእናቱን ማኅፀን ከፍቶ የሚወጣ ማለት ነው፡፡ ይህን ቃል መናፍቃን የሚረዱት “በኩር” ካለ ከእርሱ በኋላ ተከታዮች የግድ ሊኖሩት ይገባል በሚል ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ለእናቴም ለአባቴም የመጀመሪያ ልጅ ነኝ ተከታይ እህቶችና ወንድሞች የሉኝም አንድ ልጃቸው እኔና እኔ ብቻ ነኝ ስለዚህ እኔ የበኩር ልጅ ነኝ ማለት አይቻልም? ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የእናቴን ማኅጸን ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ከፍቼ የወጣሁ እኔ ነኝና፡፡ ይህን ስንል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ይዘን ነው፡፡
“እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳትም ማኅፀንን የሚከፍት በኩር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ የእኔ ነው” /ዘፀ13፡1-2/
መናፍቃን ሆይ!!! “በኩር” ማለት የግድ ተከታይ ያለው ማለት ከሆነ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡
እግዚአብሔር ግብጻውያንን በሞተ በኩር በቀጣበት ጊዜ ተከታይ የሌላቸውን የመጀመሪያ ልጆች አልገደለምን? /ዘፀ12፡12//ዘፀ12፡29/ እግዚአብሔር ከእንስሳትም ከሰውም የእናቱን ማኅፀን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍቶ የወጣውን ግብጻዊ በሙሉ ገድሏል እንጅ ተከታይ ያላቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህ “በኩር” ማለት ለመጀመሪያ ጊዜ የእናቱን ማኅፀን ከፍቶ የወጣ ሰው ወይም እንስሳ ማለት እ3ንጅ የግድ ተከታይ እህቶችና ወንድሞች ያሉት ማለት አይደለም፡፡ መናፍቃን ግን “… በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ የበኩር ልጇንም ወለደች” /ሉቃ2፡7/ የሚለውን ቃለ፤ ንባ ይዘው “የጌታ ወንድሞች” እያለ መጽሐፍ ብዙ ጊዜ በርካታ ቦታ ላይ ከገለጻቸው ጋር በማገናኘት ተከታይ ወንድሞችና እህቶች አሉት ይላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ማን እንደሆነ በውል ያልተረዱ አይሁዳውያን የተናገሩት የስድብ ቃል ዛሬ መከራከሪያ መሆኑ በራሱ መናፍቃን የአይሁድ ወገኖች ለመሆናቸው ማሳያ ነው፡፡ “… አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን?” /ዮሐ6፡42/ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደ አምላክ እንደሆነ ስላልተረዱ ከማርያምና ከዮሴፍ በሥጋ የተወለደ/ዕሩቅ ብእሲ/ ነው ብለው በማመናቸው ይህንን ተናገሩ፡፡ የዛሬ መናፍቃን ደግሞ እነዚህ የተሳሳቱበትን መንገድ ይዘው ክርክር ጀመሩ፡፡ አይሁድ እንዲህ ማለታቸው ኢየሱስን ፍጡር አድርገው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ታዲያ እነርሱ እንዳሉት እኛም ኢየሱስን የዮሴፍ ልጅ ነው፣ ከሰማይ አልወረደም፣ አምላክ አይደለም፣ ፍጡር ነው ማለት አለብንን? የለብንም፡፡ ዮሴፍ በሞት ከተለየችው ሚስቱ ልጆች እንደነበሩት በአይሁድ ዘንድ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አይሁድ የኢየሱስን አምላክነት ላለመቀበል የስጋ አባቱ ዮሴፍ እንደሆነ አድርገው ለማደናገር የዮሴፍን ልጆች የጌታ ወንድሞች አሏቸው፡፡ ወንድም የሚለው ቃል በራሱ በሥጋ ከአንድ አባት ወይም እናት መወለድ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ አብሮ ማደግን፣ በፍቅር መኖርን ፣ እጅግ በጣም መተዋወቅን የሚጠቁም ጭምር ነው፡፡ ሊቃውንት ወንድማማችነትን በ አራት ይከፍሉታል፡፡
- በሥጋዊ ልደት ላይ የተመሠረተ
- በዘር ሐረግ ወይም በደም ትሥሥር ላይ የጠመሠረተ
- በአንድ አይነት ቤተሰባዊ ሐረግ ላይ የጠመሠረተ
- በመንፈሳዊ ፍቅር ጓደኝነት ወይም ወዳጅነመት ላይ የተመሠረተ
“የጌታ ወንድሞች እና እህቶች” የሚለው ሦስተኛውን ወንድማማችነት የሚገልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- “አብርሃም ሎጥን አለው እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ”/ዘፍ13፡8/ ወንድምነት በሥጋ መወለድ ብቻ ከሆነ አብርሃም የሎጥ አጎት እንጅ ወንድም አይደለም፡፡ ታዲያ ለምን ወንድም አለው? /ዘፍ11፡27/፣/ዘፍ12፡4-5/
መናፍቃን የሚያነሷቸው ጥቅሶች፡
- “ገናም ለሕዝቡ ሲናገር እነሆ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር” /ማቴ12፡46/
- “ይህን ጥበብና ተአምራት ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም፣ ይሁዳም አይደሉምን? እህቶቹስ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?” /ማቴ 13፡55-58/
- ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ” /ዮሐ2፡12/
- “እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር” /የሐዋ1፡14/
- “እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች…” /1ኛ ቆሮ 9፡5/
- “ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም” /ገላ1፡19/
ለመሆኑ የእመቤታችንና የዮሴፍ ዝምድና እንዴት ነው?
አልዓዛር----› ማታን------›ያዕቆብ-----› ዮሴፍ
አልዓዛር-----› ቅስራ------› ኢያቄም-----› ድንግል ማርያም
ታዲያ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሴፍ ልጆች ወንድማቸው ነው ቢባል ምን ችግር አለው ያውም በአንድ አብረው አድገው፡፡ ዮሴፍ ልጆችን የወለደችለት ሚስቱ ሞተች፡፡ በዚህም የተነሣ የዮሴፍ ልጆች እንደ ቤተሰብ ሆነው ከእመቤታችን ጋር አደጉ፡፡ ስለዚህም የጌታ ወንድሞችና እህቶች ለመባል በቁ እንጅ እመቤታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ልጅ አልወለደችም ለዘላለም ድንግል ናት፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ግር ያለአባት የወለደችው አንድያ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ያለአባት የወለደችው የበኩር ልጇ ተባለ፡፡ ድንግል ማርያምስ እንዲህ መናፍቃን እንደሚሉት ያለውን ርኩሰት ልትሰራው ቀርቶ አታስበውም በአሳቧ፣ በኅሊናዋ፣ በሥጋዋ ንጽሕት ናትና፡፡ ስለዚህ የጌታ ወንድሞች ሲል የዝምድናን የዘር ሐረግን አብሮ ማደግን እጅግ አብዝቶ መተዋወቅን የሚያሳይ እንጅ እመቤታችን ከዮሴፍ ልጆችን ስለወለደች አይደለም፡፡ ምሳሌ ለመጨመር ያህል
- “ላባም ያዕቆብን ፡- ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? አለው” /ዘፍ29፡15/
ላባና ያዕቆብ ከአንድ አባት ወይም እናት ተወልደዋልን? በፍጹም ያዕቆብ የላባ የእህት ልጅ ነው፡፡ ይህ ማለትም ላባ የያዕቆብ አጎት ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ የአጎት ልጅ ማለት ወንድም ማለት ነው? በእብራውያን አነጋገር በአንድ ቤተሰብ ሥር ያደጉ ወገኖችን ሁሉ ወንድሞች እህቶች እያሉ መጥራት ልማድ ነው፡፡ ስለዚህ “የጌታ ወንድሞች” ያለበት ዋናው ምክንያት ከላይ በጠቀስነው መልኩ ነው፡፡ ሌላው መናፍቃን የሚያነሡት “እስክትወልድ ድረስ” ስላለ “ከወለደች በኋላ ዮሴፍ በግብር አወቃት” የሚል ነው፡፡ በሚቀጥለው ክፍል ይህንን በዝርዝር እናያለን፡፡
ይቆየን
አሜን፡፡