Wednesday, August 6, 2014

ጾም

ጾም ሥጋህን ለነፍስህ የምታስገዛ ልዩ መሳሪያ ናት፡፡ ይችን መሳሪያ መታጠቅ ነፍስ በሥጋ ላይ የበላይነትን ሥልጣን እንድትጎናጸፍ ይረዳል፡፡ የነፍስህን ቁስል የምትጠግን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የምታሰጥ ናት፡፡ ጾም ለአምላክህ መገዛትህን የምታረጋግጥባት ጸጋ ናት፡፡ የቀደመ ፍጥረት አዳምን እግዚአብሔር “አትብላ” ብሎ ዕፀ በለስን መከልከሉ ጾምን ሲያስተምረውና ለፈጣሪው መገዛት አለመገዛቱን ለማየት ነው፡፡ ለአዳም የተሰጠው ጾም ከገነት ካሉ ዛፎች ሁሉ ዕፀ በለስን አለመብላት ነበር፡፡ አንተም የተከለከልካቸውን ነገሮች ሁሉ እስከ ዘመንህ መጨረሻ ድረስ ካልፈጸምካቸው መጾምህ ያን ጊዜ ይረጋገጥልሃል፡፡ ከምግበ ሥጋ ማለትም ከእህል ከውኃ መከልከል ብቻውን ጾም ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ትእዛዛቱን ማክበር፣ አለመመኘት፣ አለመዋሸት፣ በሐሰት አለመመስከር፣ የባልንጀራን ቤት አለመመኘት ከእህል ከውኃ መከልከል ጋር ተቀባይነትን ያገኘ በረከትን የሚያስገኝ ጾም ይሆናል፡፡ ሲሚንቶ ውኃና አሸዋ ሲጨመርበት እንጅ ብቻውን ጠንካራ እንዳይደለ ሁሉ ጾምም እንዲሁ ነው፡፡ የሥጋ ፈቃድህን እየፈጸምክ ከእህል ከውኃ ብቻ ብትከለከል ጾምህ ዋጋ አላስገኝ ስለሚልህ ጾምን ለመራቅ ትወስናለህ፡፡ ከእህል ከውኃ መከልከሉ “የረኀብ አድማ” ይመስልብሃል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በዝርዝር እንደገለጸልን ማለት ነው፡፡ ጾምህ ዋጋ አላስገኝ ሲልህ ወደ አምላክህ “ስለምን ጾምኩ? አንተም አልተመለከትኸኝም፡፡ ሰውነቴን ስስለምን በጾም አዋረድኳት? አንተም አላወቅኸኝም” ብለህ ትጮኻለህ፡፡ ነገር ግን አምላክህ እንዲህ ይላል “እነሆ በጾምህ ቀን ፈቃድህን ታደርጋለህ፡፡ ሠራተኞችህን ሁሉ ታስጨንቃለህ፤ እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላህ፡፡ በግፍ ጡጫም ትማታለህ፤ እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን?” አሁን ይህን ስትሰማ አንተ አብዝተህ ትጨነቃለህ፡፡ የጽናትህና የብርታትህ ደረጃ ትልቅ ከሆነ አሁንም “አምላኬ ሆይ አንተ የመረጥከው ጾም የትኛውን ነው” ብለህ ትጠይቃለህ፡፡ ብርታትና ጽናትህ ዝቅተኛ ከሆነ ግን አንተ ያልመረጥከውን ጾም እያደረግሁ ከሆነስ ጾም በቃኝ ብለህ ከዚህ አገልግሎት ትሸሻለህ ርቀህም ትቆማለህ፡፡ እዚህ ላይ ሆነህ አምላህን ልትጠይቅ የሚገባህ “አንተ የመረጥከውን ጾም መስፈርት ንገረኝ” በማለት ነው፡፡ ዝም ብሎ ሥራህን ውድቅ አድርጎ የሚሸሽ አምላክ አይደለም፡፡ እርሱ የመረጠውን ጾም እንዲህ ያስረዳሃል፡፡ “እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነው፡፡ የበደልን እስራት ትፈታ ዘንድ፣ የተገፉትን አርነት ታወጣ ዘንድ፣ ቀንበሩን ትሰብር ዘንድ፣ የቀንበርህን ጠፍር ትለቅቅ ዘንድ፣ የተራቆተውን ታለብስ ዘንድ ነው” ይልሃል፡፡ አሁን የጾም መስፈርቱ ተብራርቶ በጉልህ ቀርቦልሃል፡፡ እነዚህን መስፈርቶች አክብረህ ብትጾም የምታገኘው ዋጋ አለ፡፡ በዚህ መልኩ ብትጾም ብርሃንህ እንደ ንጋት ኮከብ ያበራል፤ ፈውስም ፈጥኖ ይመጣልሃል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል፡፡ የዚህን ጊዜ እግዚአብሔርን ስትጠራው ይሰማሃል፤ ወደ እርሱ ስትጮኽም እነሆኝ ልጄ ይልሃል፡፡ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል፤ ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል፤ አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ፡፡ /ኢሳ 58፥1-12/ እግዚአብሔር የመረጠው ጾም ይህን ሁሉ ዋጋ የሚያድል ነው፡፡ ጠላት ግን ይህን ሁሉ በረከት ስታገኝ ማየት ስለማይፈልግ ከተመረጠው ጾም ያርቅሃል፡፡ ለመጾም ስትወስን ደግሞ በግብዝነት ፊትህን በማጠውለግ እና ጾመኛ ለመምሰል ፊትህን በማጥፋት እንዲሆን ይገፋፋሃል አንተም ታደርገዋለህ፡፡ ግብዞች የተቀበሉትን ፍዳ አንተም ትቀበላለህ፡፡ ወደ አምላክ ጮኸህ መልስ አታገኝም፤ ዕንባህን አፍስሰህ ዋጋ አትቀበልም፡፡ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ያሳጣሃል፡፡ ስለዚህ አንተ ስትጾም በሥውር ራስህን በፍቅር፣ በትሕትና፣ በምግባር ተቀብተህ ፊትህን በንስሓ ሳሙና ታጥበህ ይሁን፡፡ /ማቴ 6፥16/ አንተ ልትጠነቀቀው የሚያስፈልገው እግዚአብሔር ያልመረጠውን የግብዝነት ጾም ነው፡፡ ሰይጣን በሆድህ ውስጥ ታስሮ ሲያጉረመርም እንጀራን አትቁረስለት፤ ውኃም አትቅዳለት፡፡ እርሱ ከመኝታህ በተነሣህ መጠን ማጉረምረሙን አይተውም፤ አንተም እርሱ በጮኸ መጠን ልታጎርሰው አይገባም፡፡ ያን ያህል የሚጮኸው ጾም መሻርን ሊያለማምድህ ፊሽካ እየነፋ መሆኑን ልትረዳ ያስፈልጋል፡፡ እርሱ መብላትን ከማለማመዱ በፊት አንተ ጾምን አለማምደው፡፡ ከዚህ የሰይጣን ፈተና ማለፍ ስትችል ጾምህ በረከትን ያጎናጽፍሃል፡፡ የቅዱሳኑን የጾም ሥርዓት መለማመድ ትጀምራለህ፤ እንደ እሬት ሲመርህ የነበረው ጾም እንደ ማር ሲጥምህ ደግመህ ደጋግመህ ታጣጥመዋለህ፡፡ ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ ጾመ ፍልሠታ ነው፡፡ ይህ ጾም ጾመ ማርያምም ይባላል፡፡ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 15 ቀን ድረስ የሚጾም ነው፡፡ ይህ ጾም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገት ምሥጢር ለሐዋርያ የተገለጠበት ነው፡፡ እመቤታችን በጥር 21 ካረፈች በኋላ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና “ኑ ሥጋዋን እናቃጥል” ብለው በጠላትነት ተነሡ፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መላእክት ሥጋዋን በገነት አኖሩት፡፡ ሥጋዋ በገነት መኖሩን ያየው ሐዋርያው ዮሐንስ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ለዮሐንስ ብቻ የተገለጠ ምሥጢር ለሌሎች ሐዋርያትም ይገለጽላቸው ዘንድ ነሐሴ 1ቀን ጀምረው በጾምና በጸሎት ሱባኤ ቢቆጥሩ የለመኑትን የማይነሣ አምላክ ሥጋዋን ገልጦላቸው በጌቴሴማ ቀብረዋታል፡፡ ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ ዐረገች፡፡ ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ አግኝተው በጌቴሴማኒ ሲቀብሯት ሐዋርያው ቶማስ አላየም ነበር፡፡ ቶማስ አስተምሮ በደመና ሲመለስ ስታርግ አግኝቷት በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ የአንችን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ተበጠበጠ ከደመናም ሊወድቅ ወደደ፡፡ ነገር ግን ትንሣኤየን ዕርገቴን ያየህ አንተ ብቻ ነህ አሁንም ለሐዋርያት ሁሉ ተነሥታለች ዐርጋለች ብለህ ንገራቸው ብላ ሰበኗን ሰጠችው፡፡ በዓመቱ ሐዋርያት ቶማስ ያየውን የዕርገቷን ምሥጢር ለማየት ነሐሴ 1 ቀን ጀምረው ሁለት ሱባኤ ከጾሙ በኋላ ነሐሴ 16 ቀን ትንሣኤዋና ዕርገቷ ለሁሉም ሐዋርያት ተገልጦላቸዋል፡፡ ስለዚህ እኛም ሐዋርያትን አርአያ አብነት አድርገን እመቤታችን የተሠወረብንን ምሥጢር ሁሉ እንድትገልጥልን እንጾማለን፡፡
visit: melkamubeyene.blogspot.com

No comments:

Post a Comment