ክብርና ምስጋና ይግባውና ኢየሱስ
ክርስቶስ ነፋስና ባሕር እንዴት እንደታዘዙለት የአምላክነቱን ጥበብ በወንጌል ላይ እንዲህ እናነባለን፡፡ “በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ፡- ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው፡፡ ሕዝቡንም ትተው
በታንኳ እንዲያው ወሰዱት ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ
በታንኳይቱ ይገባ ነበር፡፡ እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፡፡ አንቅተውም መምህር ሆይ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት፡፡
ነቅቶም ነፋሱን ገሰጸው ባሕሩንም ዝም በል ፀጥ በል አለው፡፡ ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታ ሆነ፡፡ እንዲህ የምትፈሩ ስለምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው፡፡ እጅግም ፈሩና እንግዲህ ነፋስም ባሕርም
የሚታዘዙለት ይህ ማነው ተባባሉ?” ማር4፥35-41፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደካማ ሥጋ መልበሱን ፣ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ
መሆኑን ያስተማረበት ክፍል ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ሰውነቱ ተኝቶ ተቀሰቀሰ እንደ አምላክነቱ ነፋሱን ባሕሩን ገስጾ ያሳየበት በመሆኑ፡፡
ባሕር መገሰጽማ እነሙሴስ አድርገውት የለም? ትለኝ እንደሆነ አድርገውታል ነገር ግን እነርሱ በጸጋ እርሱ ግን በባሕርይው ነው፡፡
በታንኳይቱ የነበሩት ሰዎች መገሰጽ የሚችሉ ባለመሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስን አንቅተው “አቤቱ ስንጠፋ አይገድህምን?” ማለታቸው ደግሞ ከእነርሱ የሚበልጥ እንደሆነ በመረዳታቸው ነው፡፡ ባሕሩንና ነፋሱን በገሰጸውና ማዕበሉ ፀጥ ባለ
ጊዜ ፈርተው ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማነው? ብለው የአምላክነት ሥራውን አድንቀዋል፡፡ ይህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለትን
የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአማልክት አምላክ ክርስቶስ ኢየሱስ እንደሆነ እናምናለን፡፡ “ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፡፡” ሮሜ 9፥5 ተብሎ እንደተጻፈ
ክርስቶስ በተዋሕዶ በሥጋ ማርያም ቢገለጥ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም አልበለጠምም ትክክል
ነው እንጅ፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና የቀስቃሹን ተቀስቃሽ መሆን እንመልከት፡፡ ክርስቶስን አንቅተው ስንጠፋ አይገድህምን?
ያሉት በእርሱ የተፈጠሩ በክብራቸው በማዕርጋቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፍጡራን ናቸው፡፡ እነርሱ በጊዜው የተሸለ ልመና አቅርበዋል፡፡ በዚያ
ሰዓት ከእርሱ ውጭ ሌላ አካል ሊያድናቸው እንደማይችል ያውቃሉና፡፡ ይህን ወደ እኛ ሕይወት እንመልሰው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደ እኛ
አመለካከት ያልተማሩ ፣ አላዋቂ የሚመስሉን ሥልጣንና ማዕርግ የሌላቸው ሰዎች የተማሩ፣ አዋቂ ከሚባሉ ሥልጣንና ማዕርግ ካላቸው በአስተሳሰብና
በአመለካት በልጠው ወይም ተሽለው የሚገኙበት ጊዜ አለ፡፡ ምእመናን ከዲያቆናት፣ ዲያቆናት ከቀሳውስት፣ቀሳውስት ከጳጳሳት፣ ጳጳሳት
ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃነ ጳጳሳት ከፓትርያርኩ የተሻለ አስተሳሰብና አመለካከት ይዘው ስለሚገኙ በማዕርግ የሚበልጧቸውን መካሪና አስተማሪ
እንዲሁም ቀስቃሽና ተግሳፅ የሚሰጡ ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚ አለ፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ምእመናን ሥርዓት ተጣሰብን ቀኖና ፈረሰብን በማለት
በክብርና በማዕርግ የሚበልጧቸውን በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች በመቀስቀስና በማንቃት “ስንጠፋ አይገዳችሁምን?” በማለት ላይ ናቸው “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብለው ከተኙት በቀር፡፡“አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉ ሆን
ብለው ሥርዓት በመጣስ ቀኖና በማፍረስ ላይ የተሰማሩት ግን የምእመናን ጩኸት “የዝኆን ጆሮ ስጠኝ” ብለው ላይነቁ እሰከወዲኛው ያንቀላፉ
ሆነዋል፡፡ ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠውን የነባብያን በጎች እረኝነት መቀበላቸውን ዘንግተው /ዮሐ21፥16-17/ ሊጠብቋቸው አደራ በተረከቧቸው በጎች የማንቂያ ቅስቀሳ ሲደርሳቸው ዞር ብለው የሆነውን ነገር
ከማየት ይልቅ “በምድር ያሰራችሁት በሰማይም የታሰረ ነው፡፡” ማቴ
18፥18 የሚለውን ሰማያዊ ሥልጣን ብቻ በመጠቀም ለመገዘት /ለማሰር/ ይፈጥናሉ፡፡መምህራችን ክርስቶስ እንዳስተማረን የምንጓዝ
ከሆነ “ስንጠፋ አይገዳችሁምን” የሚለውን የምእመናን ጩኸት ልንሰማና ተገቢውን መልስ ልንሰጥ እንገደዳልን፡፡ከዚያ ውጭ ግን ሥልጣን
ማሰሪያ ብቻ ሳይሆን መፍቻም ጭምር መሆኑን ልንረዳው ይገባል፡፡ “መምህር
ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ፡፡” ማቴ 23፥7 ተብሎ እንደተጻፈ ስሙን ብቻ የምንፈልግ ከሆነ ግብዝነት ነው፡፡
ገንዘባቸውን ፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ዓለማዊ አውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን ለማፍሰስ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚጠጉትን የግል
ጥቅም የሚቀርብን የሚመስላቸው አንዳንዶች ሊገልጻቸው የማይችል ሥም ይለጥፉባቸዋል፡፡ መቼም እናትም ትሁን አባት የልጃቸውን ቅስቀሳ
ካልሰሙ የእናትነትና የአባትነት ክብራቸው በልጆቻቸው ዘንድ መቀነሱ አይቀርም፡፡ ተቀስቃሽ ላለመሆን አለማንቀላፋት፤ ካንቀላፋን ግን
ተቀስቃሽ መሆንን መጥላት የለብንም፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ በፍጡር ከተቀሰቀሰ እኛ ደግሞ በወንድሞቻችን፣ በእህቶቻችን፣ በልጆቻችን
ቅስቀሳ መንቃት የማንፈልግ ከክርስቶስ በልጠን ነውን? የምእመኑ ጥያቄ
“ስንጠፋ አይገዳችሁምን?” የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም በአንዳንድ የግል ጥቅም ፈላጊዎች በተፈጠረ ማዕበል የሚናወጠው ምእመን ቁጥሩ
እየጨመረ ነውና፡፡ ምእመኑ ሲጠፋ የማይገደው እረኛ ደግሞ “የቀስቃሽ ተቀስቃሽ” የሆነ በእንቅልፍ የተጠቃ ያለቦታው የተቀመጠ ግዴለሽ
ነው፡፡ መቼም ቢሆን በልጅነት ፍቅር የምንለምነው አርአያችን የሆነውን መምህር ክርስቶስን እንድንከተል ነው፡፡ መቀስቀስ ስንችል
ተቀስቃሽ ልንሆን አይገባም፤ ይልቁንም “እንዲህ የምትፈሩ ስለምን ነው? እንዲህ የምታለቅሱት ስለምን ነው? በማለት አለንላችሁ ብለን ልናጽናና የአባትነት
አደራ ሐይማኖታዊ ግዴታ አለብን፡፡ ይህን በሚገባ ለመወጣት የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment